Sunday, 28 January 2018 00:00

ማደፍረስና ማናጋት የበረከተው… አዳሜ በማን ላይ ተማምኖ ነው?

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(5 votes)

 • “አንዱ፣ አገሬውን ሲያምስ፤ አንተም አብረህ አተራምስ” የተባለ ይመስላል ነገሩ። ታምሶ ተተራምሶስ?
    • አንዱ በጀማሪነት አገሪቱን ሲያናጋት፣… ተቀናቃኞቹ፣ አብረው ለማናወጥ መንጋጋት! እድሏ ያረጋጋት?
    • ኢህአዴግ፣ “የህዝብ ጥቅም” እያለ ኢኮኖሚን ያቃውሳል። ተቃዋሚው፣ “የሕዝብ ጥያቄ” እያለ ያባብሳል።
       
    “የሰው ማንነት፣ የግል ማንነት” መሆኑን ባለማወቅ ወይም ይህንን እውነታ በመካድ፣… ሰዎችን በተወላጅነትና በዘር ሃረግ ለማቧን ሲጣጣር፣… የብሔር ብሔረሰብ ፖለቲካን ሲሰብክ፣… በብሔረሰብ ስሌት ሲቆምርና ሲያባዛ የከረመ መንግስትም ሆነ ፖለቲከኛ፣ ገዢ ፓርቲም ሆነ ተቃዋሚ፤… በእርግጥም ጥረት ያለ ውጤት፣ ስህተት ያለ ውድቀት፣ መርዝ ያለ መዘዝ አይቀርምና፣… ይሄውና በበርካታ አመታት የስህተት ዘመቻ አማካኝነት፣ አገሬው… ጤና የራቀው አገር ሆኗል።
በአንድ በኩል፣ በብሔር ብሄረሰብ ፖለቲካ አማካኝነት፣ “ተቃዋሚ ፓርቲ፣ አገር ሲያደፈርስ ይቅር የማይባል ጥፋት ነው። መንግስት ሲያደፈርስ ግን፣ ችግር የለም።” በሚል የተሳከረ ስሜት የተተበተቡ አሉ።… ለመሆኑ፣ አገሬው በብሄር ብሄረሰብ ፖለቲካ ከደፈረሰ በኋላስ? የደፈረሰውን ነገር ማስከን፣ የተቃዋሚዎች ስራ ነው? ወይስ፣ አገሬው ደፍርሶ፣ በራሱ እድል ይጠራል?
በሌላ በኩል ደግሞ፣ “መንግስት ሲያደፈርስ ይቅር የማይባል ጥፋት ነው። ተቃዋሚ ግን፣ በብሔር ብሔረሰብ ፖለቲካ አገር ምድሩን ቢያደፈርስ ችግር የለም።” የሚል የስካር ስሜት የተጠናወታቸው አሉ። በማን ተማምነው ነው? በመንግስት ተማምነው ነው ወይስ፣ የደፈረሰው ነገር፣ በእድሉ ይጠራል?  
እንግዲህ፣ የአገራችንን ጉዞ እያየነው ነው። እንደተለመደው፣ “አይተን እንዳላየን ለመሆን” መሞከር እንችላለን። አገሬው፣ በጭፍንነት ጨለማ እየተደናበረ፣ በጥፋት ቁልቁለት እየተንገጫገጨ፣ በክፋት ወደ ረከሰ እንጦሮጦስ እየወረደ ቢሆንም፣… አዳሜ፣… አንዳንዴ ድንግጥ፣ ብንን፣… ለአፍታም ቀና፣ ነቃ… ማለቱ ባይቀርም፣… ሳልስት ሳምንት ሳይሞላው፣… ወደ ተለመደው ወደ ነባሩ የብሽሽቅ ውድድርና የጥፋት እሽቅድምድም ይመለሳል። ከጥፋት ያድነናል ብለው የተማመኑበት ነገር ያለ ይመስላል። ወይም ያስመስላሉ። ራስን የማታለል ችሎታ፣… እንደመተማመኛ… መሆኑ ነው!
እንደዚያ ባይሆን ኖሮ፣ በብሔር ብሔረሰብ ሲያቧድንና ሲደራጅ፣ በጅምላ ሲያሰባስብና ሲፈርጅ የቆየ መንግስት፣ ተቃዋሚም ሆነ ምሁር፣… እንዴት ነው፣… ዛሬ አሳስቦትና አስጨንቆት፣… በማግስቱ እንደገና ወደዚያው የጥፋት መንገድ የሚመለሰው? እናም፣ ለነገ የተለየ ውጤት ይጠብቃል! እንዴት ነው፤… በጅምላ በዘር የመቧደን አመል በአንዳች ተዓምር እንዲቀንስ፣ በአንዳች አስማት ደግሞ፣ በመርህ ላይ የተመሰረተ ግንኙነት እንዲስፋፋ የሚጠብቀው? በብሔረሰብ ከመቧደን የፀዳ፣ ለህግ የበላይነት በፅናት የቆመ ህግ አስከባሪ እንዲበራከትስ፣ እንዴት እንዴት ሊጠብቅ ይችላል?
ወይስ፣… እኔ ያጣመመኩት ሌሎች ያቃኑታል ብሎ ይጠብቃል? መንግስት ሲያናጋ፣ ተቃዋሚ እንዲያረጋጋ ነው የሚጠብቀው? ወይስ፣ ተቃዋሚ እየቀወጠ፣ መንግስት እንዲያረጋጋ ነው የሚጠብቀው? በእርግጥ እንዲህ አይነት አጥፊ የስካር ምኞት፣ ወደ ጥፋት ፉክክር ነው የሚያመራው። እንደምናየው፣… አንዱ ሲያደፈርስ፣ ሌላኛውም በእልህ በፉክክር ስሜት፣ አባብሶ በማደፍረስ በልጦ ለመገኘት ይፎካከራል።
“ሲሆን ሲሆን፣ በጭፍን ቅስቀሳ፣ በብሄርብሄረሰብ ፖለቲካ አገሬውን በብቸኝነት ቀውጢ የማድረግ ፍላጎት” ይዞ፣ ሌሎች ተቀናቃኞች የተቀወጠውን አገር ከጥፋት ለማውጣት፣ ለመጠገንና ለማዳን ያለ ፋታ የሚለፉ የአደጋ መከላከያ አገልጋዮች እንዲሆኑለት ሲመኝ አስቡት። እንዳሻው እያጣመመ፣ እያደፈረሰ፣ እየናደ፣ እየቦረበረ፣ እያደፈረሰ መኖር! ሌሎች እንደሚያስተካክሉ እየተማመነ… ባይተማመንም እየተመኘ!
ብሔር ብሔረሰብ እያለ ጭፍንነትን ሲሰብክ፣… ተቀናቃኞቹ ግን፣… በስክነት የእውነትና የእውቀት ብርሃንን ለመፍጠር እንዲፍጨረጨሩ ይጠብቃል? እሱ ሲያጨልም፣ ሌሎች ብርሃን እንዲያመጡ? አገሬው ሙሉ ለሙሉ ጨለማ እንዳይሆን? አንዱ ተቃዋሚ በበኩሉ፣ “የሕዝብ ጥያቄ” ብሎ በጀመረው ቅስቀሳ፣… አገሩ ቢተራመስና መውጪያ መግቢያ ቢጠፋ እንኳ ችግር የለውም - የማረጋጋት ስራ ለመንግስት መተው ይቻላል።  
ሌላኛው የቁማር ካርድ።
ከብሔር ብሔረሰብ ፖለቲካ ጋር በሚመሳል ሌላኛው የቁማር ካርድ፣ መንግስት “የሃብት ክፍፍል” እያለ በአምራቾች ላይ ሲዘምት፣… “የአውስትራሊያ የሌሊት ወፎች በሙቀት ተጎዱ” እያለ ፋብሪካ ይዘጋል።
ይህንን የጥፋት ጉዞ የመግታትና አደጋውን የመከላከል ስራ ለተቀናቃኞቹ፣ ለተቃዋሚዎች ይተውላቸዋል፣… “ለግል ንብረት ባለቤትነት፣ ለነፃ ገበያ እና ለኢንዱስትሪ ምርታማነት ብንጥር ይሻላል” እያሉ እየተከራከሩ፣ የመፍትሄ ሃሳብ እያቀረቡ ከጥፋት እንዲመለስ እንዲወተውቱት ይጠብቃል።
መንግስትም ሆነ ተቀናቃኙ፣… በየፊናው እንዳሻው እያሳከረ፣ እያቃወሰ፣ እየበጣጠሰ፣ ያለፍሬን እየተንደረደረ ለመቀጠልና ለመኖር የሚመኘው በምን ላይ ተማምኖ ነው? በተቀናቃኙ ነው የተማመነው? መንግስት በተቃዋሚ ላይ፣ ተቃዋሚ ደግሞ በመንግስት ላይ ተማምነው፣… ለምሳሌ ተቃዋሚ ሲያቃውስ፣ መንግስት አንዳች የሚያሰክን መፍትሄ እንዲያቀርብ፣… መንግስት መረን ለቆ ገደል እንዳይገባም ተቃዋሚዎች አንዳች ፍሬን የሚሆን የተቃውሞ ሃሳብ እንዲያቀርቡ ነው የሚጠብቁት?
እንዳሻው እየበጣጠሰ ሲንቀለቀል አንዳች የተበጣጠሰው እየለቀመ ለማያያዝ የሚፍጨረጨር ተቀናቃኝ ተቃዋሚ ይኖራል በሚል ግምት ነው? ቢኖር ጥሩ ነበር። ይንንን የብሽሽቅና የመናቆር፣ የጨለማና የቁልቁለት፣ የጥፋትና የውድቀት አዙሪትን ለማስቆም፣ እንዳይደገም ለማስተካከልም አመቺ እድል ይፈጠር ነበር። ነገር ግን፣ አዙሪቱን የሚያስቆምና ወደ ትክክለኛው ጎዳና የሚያስገባ ጥረት እስካሁን አይታይም።
ይልቅስ፤ እርስበርስ እየተቀባበሉና እየተመጋገቡ፣ የተለኮሰውን በማግለብለብ፣ የተንገጫገጨውን የመከስከስ እሽቅድምድም፣ የማባባስ ፉክክር ውስጥ የሚገቡ ናቸው የበረከቱት። በየፊናው አንዱ፣… ይጀምራል፣ ይለኩሳል። አንዱ ከሌላኛው ያየውን ጭፍንነት በአርአያነት እየኮረጀ፣…  በራሱ ዜማ፣ በራሱ ዘፈን፣ በራሱ ቅኝት፣ በራሱ ሜዳ ገብተው የሚፎካከሩ ተቀናቃኞች ተራብተው ይባዛሉ።
አስገራሚው ነገር፣… የማቃወስና የማደፍረስ መድረክ ላይ በብቸኝነት መቆየት፣ ሜዳውን ሙሉ ለሙሉ መቆጣጠር የሚችሉ ይመስላቸዋል።

የቁልቁለት ምኞት፣… የውድቀት ቅብብልና እሽቅድምድም።
የኢህአዴግ አንድ ምኞት ምን ሊመስል እንደሚችል አስቡት።…
…በአንድ በኩል “ስግብግብ ባለሃብቶች” ብዬ እያወገዝኩ፣ በሌላ በኩል “የሃብት ክፍፍል” ብዬ የብዙ ሰዎችን ጭፍን ስሜት አግለበልባለሁ። በዚህም፣ ስልጣን ላይ እቆያለሁ። ተቃዋሚ ፓርቲ ግን፣ “የንብረት ባለቤትነት መብት ይከበር” እያለ ይከራከራል እንጂ፣ “የድሆች አለኝታ፤ የሃብት ከፍፍል” እያለ የጥፋትና የውድቀት ስሜቶችን አያግለበልብም፤ እናም ብዙ ድጋፍ አያገኝም። ስለዚህ፣ የስልጣን ተቀናቃኝ አይሆንብኝም። እንዲያውም፣ አረጋጊ ፍሬን ይሆንልኛል”…
እንዲህ አይነት የመንግስትና የገዢ ፓርቲ ምኞት፤… የእውነት ቢሳካና፣ “በስራ ኑሮን ማሻሻል፣… በራስ ጥረት፣ ንብረት ማፍራት፣… የንብረት ባለቤትነት ማክበር ያስፈልጋል፣… የነፃ ገበያ ስርዓት፣ ምርታማ የስኬት ስርዓት ነው” የሚል ትክክለኛና ፅኑ አቋም ይዘው የሚከራከሩ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ቢፈጠሩ፣ ቢጠናከሩ ጥሩ ነበር። በእርግጥ፣ ይሄኛው ትክክለኛ የነፃ ገበያ አቋም፣ በተግባር ለማስፋፋትና ውጤታማነቱን ለማስመስከር፣ ረዥም ጊዜና ብዙ ጥረት ይፈጃል። ቢሆንም፣ ሁነኛ መፍትሄ ነው። በዚያ ላይ፣ ሌላ መፍትሄ የለም።
አሳዛኙ ነገር፣ እንዲህ አይነት አቋም ይዞ፣ በጥንካሬ ጎልቶ የወጣ ተቃዋሚ ፓርቲ የለም። እህስ?
“የሃብት ክፍፍል፤ የሃብት እኩልነት” የተሰኘው የውድቀት ድግስ ውስጥ ለመግባት የሚንጋጋና እዚያው የኢህአዴግ ሜዳ ላይ አብሮ ለመቀላቀልና ለመፎካከር የሚራኮት ተቃዋሚ ነው የበረከተው።
የጥፋት ድግስን ለማማሟቅ የሚደረግ እሽቅድምድም እንደማለት ነው። አንዱ በጀመረው የቁልቁለት ጉዞ ላይ፣ ሌላኛው ቀድሞ ለመሄድና አዲስ የቀውስ ሪከርድ ለማስመዝገብ መፎካከር!...
ተቃዋሚ ፓርቲ በፊናው፣ “የሃብት ልዩነት” እያለ ይለኩሳል።
ኢህአዴግም ብሶበት፣ “የሃብት እኩልነት” እያለ ያግለበልባል።
ኢህአዴግ፣… ሃብትና ስራ ፈጣሪዎችን በሰበብ አስባቡ ያዳክማል፣ በታክስ ጫና ያከስራል።
ለተቃውሞ የወጡ ሰዎችም በፊናቸው፣ በሰበብ አስባቡ መንገድ ለመዝጋት፣ ለማፍረስና ለማቃጠል ይቧደናሉ።   
ኢህአዴግ፣… “የህዝብ ጥቅም፣ የወጣቶች ተጠቃሚነት” እያለ ሆይታ ይጀምራል።
ለመቅደም የሚፍጨረጨር ተቃዋሚ ደግሞ፣  “የሕዝብ ጥያቄ፣ የወጣቶች ድምፅ” እያለ ያባብሳል።
በማን ነው የተማመኑት?       
አንደኛው በጀማሪነት አገሪቱን ሲያናጋት፣… ሌሎችም በተቀናቃኝነት፣ አብረው ለማናወጥ መንጋጋት!…
ግን ከዚያስ? አገሪቱ ምን ይዋጣት?... “እድሏ ያረጋጋት?”      

ቦታ ተጣበበ በሚባልባት በአዲስ አበባ ሳይቀር፣ በየከተማው ሁሉ፣ ለፋብሪካ ቅንጣት ቦታ መስጠት የአቀበት ያህል የሚከብደው መንግስት፣… በየከተማው አንድ ሶስተኛው ያህል መሬት፣… ፓርክና ጫካ አደርገዋለሁ ብሎ እቅድ ያወጣል። 20 በመቶው ያህል፣ ደግሞ ለመንገድ ስራ ይውላል። ያ ሁሉ ነዋሪው የት እየኖረ የት እንዲሰራ ነው? ቤት ያጣ ነዋሪ በበዛበት ከተማ ውስጥ፣… ከድስቱ ወደ እሳቱ እንዲሉ፣… ተጨማሪ ቤት አልባ ተፈናቃይ ነዋሪዎችን የሚያበራክት እቅድ? ለዚያውም፣ “ለፓርክ ቅድሚያ በመስጠት”!
ይህንን በስካር የጦዘ ክፋት ለማቆንጀት በወዶዘማችነት የሚሰለፉና፣ “አረንጓዴ ልማት” እያሉ ያለፋታ የሚያነበንቡ፣… ራሳቸውንና አድማጫቸውን ለማደንዘዝ “ዘወትር የሚለፍፉ” ወገኛ የመንግስት ጋዜጠኞች ደግሞ ሞልተዋል።
መንግስትና ባለስልጣናቱ እንዲህ ሲሳከርባቸው፣ “ኧረ ይሄ አይበጅም” የሚላቸውና ወደ ህሊና እንዲመለሱ የሚወተውታቸው ብዙ ሰው ደግሞ የለም። በተቃራኒው፣ በዚያው የተሳከረ ጎዳና ላይ፣ በተቀናቃኝነት ለመፎካከር፣ በተቃዋሚነት ለመሽቀዳደም የሚደናበር ሰው ይበዛል።
“መሬት ለመጤ አከራየህ” እያለ ነዋሪዎችን የሚያፈናቅል የተቃውሞ ሰልፈኛ፣ እዚህም እዚያም የሚታየው ለምን ሆነና? ይህንን ክፋት ለማቆነጃጀት የሚሯሯጥ ወዶገብ ዘማቾች ሞልተዋል - “የህዝብ ጥያቄ ነው” እያሉ ያነበንባሉ፣ ራሳቸውንና ተከታዮቻቸውን ለማታለል ይጣደፋሉ።
በርካታ ወዶዘማች የመንግስት ጋዜጠኞች በፕሮፓጋንዳ እጅጉን በመጠመድ ወይም በመራቀቅ፣… እነዚሁን በመቃወም የተጠመዱ ተቀናቃኝ ወዶዘማቾችም ተመሳሳይ የአሉባልታ ፕሮፓጋንዳን በማጦዝ ወይም በማራቀቅ፣… አዋቂነትንና ታዋቂነት የሚገኝ ይመስላቸዋል። ከእነዚሁ ተቀናቃኞች ጋር የሚመሳሰሉ ወገኛ ፖለቲከኞች እንዲሁ በየተቀናቃኝ ቦታ ላይ ሆነው፣ አንዱ የጀመረውን ሌላኛው እያባዛና እያራባ፣ አንዱ የለኮሰውን ሌላኛው እያራገበና እያጋጋለ… እርስበርስ እየተቀባበሉና እየተመጋገቡ፣ የነኩት ነገር ሁሉ እየባሰና እየተባባሰ ቀውጢ በቀውጢ ይሆናል።
በማን ተማምነው ነው? አገሬውን ስናቆስለው፣ በእድሉ ያገመግማል ይድናል? ባይድንስ? ደግሞስ፣ ከመነሻው ለማሻሻል፣ ለማስተካከል፣ ለመፈወስ እንጂ፣ ለምን ማቁሰል፣ ማደፍረስ፣ ማጣመም አስፈለገ? ሳጣምመው በእድሉ ይቃናል? ሳደፈርሰው፣ በእድሉ ይጠራል? ሳንገጫግጨው፣ በእድሉ ይስተካከላል? ስገነድሰው፣ በራሱ ጊዜ ይለመልማል? ስንነቃቅለው በራሱ እድል ያቆጠቁጣል? ሳደናቅፈው፣ በእድሉ ይጓዛል? ስፈጠፍጠው፣ በእድሉ ይነሳል?

Read 4051 times