Saturday, 27 January 2018 11:52

‹‹…ጤናማ እናትነ ት….››

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

 እናት ሁሉም ነገር ነች፡፡ እናት መፍትሔ ነች፡፡ እናትነት ዘመን የማይሽረው መቼም የማይቀየር ነገር ነው፡፡ እናትነትን ምንጊዜም …ምንም አያደበዝዘውም። -
ወ/ሮ በለጥሻቸው ታደሰ
ከላይ የምትመለከቱት ፎቶግራፍ በፊስቱላ ሕመም ምክንያት ሲሰቃዩ የነበሩ ወጣት ሴት ልጆች እና ከሕመሙ ጋር ለረጅም አመታት አብረው የኖሩ አረጋዊት ሴት ታክመው በመዳናቸው የሚያሳዩት የደስታ ሳቅ ነው። የሐምሊን ፊስቱላ መስራች ዶ/ር ካትሪን ሐምሊን በታካሚዎቹ መካከል ምስላቸው ይታያል፡፡
በዚህ እትም የምናስነብባችሁ የፊስቱላ ታካሚዎች ከሆስፒታሉ ከወጡ በሁዋላ የሚያርፉበት በታጠቅ አካባቢ የሚገኘው የደስታ መንደርን የስራ እንቅስቃሴ ነው፡፡ በመንደሩ ካነጋገርናቸው ባለሙያዎች መካከል ወ/ሮ በለጥሻቸው ታደሰ  የድርጅቱ ስራ አስኪያጅ ይገኙበታል። ወ/ሮ በለጥሻቸው የደስታ መንደር ምን ስራ እንደሚሰራ አብራርተዋል፡፡አንዲት ታካሚ የነገረችንን ታነቡ ዘንድ እነሆ፡፡
‹‹….እኔ እንደተዳርኩ ነበር በአመቱ ያረገዝኩት። ስዳር የአስራ አምት አመት ልጅ ነበርሽ ብለውኛል። ታዲያ በአመቱ ልጅ ተረገዘ፡፡ የመውለጃ ቀኔ ሲደርስ ግን ጭንቅ ሆነ፡፡ በአካባቢዬ የነበሩ የልምድ አዋላጅ እንደገናም በዘመናዊው የማዋለድ ተግባር ሰልጥነዋል ተብሎ ተጠርተው መጡ፡፡ እንግዲህ እሳቸው ተጠርተው የመጡት በሁለተኛው ቀን ነበር፡፡ እሳቸውም አይተው …አ.አ.ይ ቀላል አይመስለ ኝም፡፡ ነገር ግን ልሞክር ብለው አንድ ቀን አደርኩ፡፡ ከዚያ በሁዋላ ቅርብ ወደሆነው ጤና ጣብያ በሸክም በቃሬዛ ወሰዱኝ፡፡ ታዲያ የተረገዘው ልጅ ሞቶ እኔም እንዳልሆን ሆኜ ተገላገልኩ፡፡ ከዚያ በሁዋላ ግን ወደቤቴ ተመልሼ ሳለሁ ዝም ብሎ ልብሴ ይበሰብሳል። ሽንትም አይይዘኝም፡፡ የሚበላ የሚጠጣ ሲሰጡኝ ታዲያ ሽንቴ እየበዛ እንዲያውም እየሸተተ አስቸገረ፡፡ እኔም ለሁለት ወር ከተሰቃየሁ በሁዋላ በቃኝ አልበላም አልጠጣም አልኩኝ፡፡ ለምን ቢሉኝ … የሆንኩትን ነገርኩዋቸው፡፡ የአራስነት መስሎኝ እንጂ የሚፈሰው ፈሳሽ ሽታው አስቸግሮኛል አልኩዋቸው፡፡ እንዲያው በሰው ፊት ልቁም ወይም ልቀመጥ …ብቻ ስነሳ ልብሴ በስብሶ በእግሬ ላይ ሽንት ፈስሶ ይገኛል፡፡  ባለቤቴም ወደቤተሰቦቼ ዘንድ መለሰኝ፡፡ የባህል ሕክምናው… ጸበሉ… ሁሉም አልቀረኝ። አንዱም መፍትሔ አልሆነም፡፡ ውሎ አድሮ ግን የሐምሊን ፊስቱላ ሐኪሞች ወደኛም መንደር ደርሰው ነበርና ለሕክምና አመጡኝ፡፡ በ2001/ዓ/ም እንደመጣሁ ታከምኩ፡፡ ለሁለት አመት ከሆስፒታል ከቆየሁ በሁዋላ ወደደስታ መንደር በ2003/ዓ/ም ተዛወርኩ፡፡ አሁን በካፌው ስራ ሰልጥኜ እየሰራሁ እገኛለሁ፡፡ ወደአገሬም እንዳልመለስ ከሕክምናው መራቅ አልችልም፡፡ አሁን ግን ቤት ተከራይቼ ስራዬን እየሰራሁ ይኼው እኖራለሁ። እግዚአብሔር ይመስገን ሽንቴንም በላስቲክ ከረጢት አድርገውልኝ ከሰው ጋር እውላለሁ፡፡…››
የታካሚ ምስክርነት
ደስታ መንደር ማለት በፊስቱላ የተጎዱ ወገኖች ዘለቄታዊ  የሆነ እገዛ የሚያገኙበት …እራሳቸውን ችለው የሚኖሩበትን ሙያ የሚቀስሙበት …ከህብረተሰቡ ጋር ተመልሰው ለመቀላቀል የሚያስችላቸውን የተለያየ የእደጥበብ ትምህርት የሚማሩበት ተቋም ነው፡፡ ይህ ቦታ በመንግስት ስር ይተዳደር የነበረ ሌላ ተቋም የነበረ ሲሆን በሁዋላ ግን ለዶ/ር ካትሪን ሐምሊንና ለሆስፒታሉ በተለይም የፊስቱላ ሕመማቸው በቀላሉ ለማይድንላቸው ሴቶች የተሰጠበት አላማ ከፊስቱላው ጋር ሲኖሩ በምን ሁኔታ እራሳቸውን ደግፈው መኖር አለባቸው ለሚለው ነበር፡፡ አሁን ግን የታካሚዎቹ ቁጥር እየጨመረ በመሄዱ እና በዘላቂነት ለማኖር ከፍተኛ በጀት በማስፈለጉ ምክንያት በዘላቂነት ማኖር አልተቻለም፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በማህበራዊውም አቅጣጫ ከተለያዩ አካባቢዎች የመጡት ታካሚዎች ወደየመጡበት ህብረተሰብ ቢመለሱ የበለጠ ሊጠቀሙ እንዲሁም ሞራላቸው ሊታደስ ይችላል የሚል እምነት ስላለ አስፈላጊው ሕክምና ከተደረገላቸው እና ለመቋቋም የሚያስችላቸው በቂ እውቀት ካገኙ ወደመጡበት አካባቢ በመውሰድ ማቋቋም ይሻላል ወደሚለው ዝንባሌ መሄድ ግድ ሆኖአል፡፡ ስለዚህም ደስታ መንደር ጠንከር ያሉት ታካሚዎች እየተመረጡ ወደሀገራቸው በመሄድ ጤናቸውን ጠብቀው የራሳቸውን ስራ እየሰሩ እንዲኖሩ የሚበቁበት ማእከል ሆኖአል፡፡  ደስታ መንደር የተባለበትም ምክንያት በቆይታቸው ወቅት እስኪያገግሙ ድረስ ደስ እያላቸው ስለሚታከሙ ነው፡፡
ወ/ሮ በለጥሻቸው በመቀጠል እንደገለጹት ከ100 %ታካሚዎች መካከል 4% እና 5 % የሚሆኑትን ታካሚዎች በቀዶ ሕክምና ምንም እንከን ሳይወጣለት ለማዳን እንደማይቻል ሐኪሞች ይመሰክራሉ፡፡ ስለዚህም  ወደመንደሩ የሚላኩት የፊስቱላ ታካሚዎች ከ2-3 ወር ወይንም እስከ አመት ድረስ ሊሆን በሚችል ጊዜ ከፍ ያለ የህክምና ስራ የሚደረግላቸው እና እንዲሁም ከቤተሰቦቻቸውም ሆነ ከራሳቸው ጋር በመመካከር በዘላቂነት ሽንትን በውጭ ሰውነታቸው በኩል ከልብሳቸው ስር በሚንጠለጠል የላስቲክ ከረጢት  እየተቀበሉ በዘላቂነት እንዲኖሩ የሚመቻችላቸው ናቸው፡፡  ስለዚህም እነዚህ ሴቶች በተፈጥ ሮአዊው መንገድ ሽንታቸውን ማስወገድ የማይችሉ ሲሆን በሚሰጣቸው የላስቲክ  ከረጢት ግን እየተ ቀበሉ በሚኖሩበት ጊዜ ከአሁን ቀደም በሕመም በነበሩበት ጊዜ የነበረው ከማህበረሰቡ መገለል እንዲሁም የጤና እውክታ እና ማህበራዊ ጫና በማይደርስባቸው ሁኔታ እራሳቸውን በመቆጣጠር እና በአቅራቢያ ቸው በሚገኝ የጤና ተቋም የህክምና ክትትላቸውን በማድረግ በጥሩ ሁኔታ ሕይወታቸው እንዲቀጥል አስፈላጊው ሁሉ ይደረጋል፡፡ ከእነዚህ ሴቶች መካከል ድጋሚ ትዳር የሚመሰርቱም አሉ፡፡ በእርግጥ ሽንትን ለማስወገድ የሚጠቀሙበት የላስቲክ ከረጢት የሚመጣው ከውጭ ሀገር ሲሆን እስከአሁን የሚሰጣቸው ግን ከሆስፒታሉ ነው፡፡ አጠቃቀሙም አንዱ ከረጢት ምናልባት ለሶስት ወይም አራት ጊዜ ያህል ሲሆን ከዚያ ባለፈ የሚጣል ነው፡፡ ታካሚዎች በዚህ ሁኔታ የወደፊት ሕይወታቸውን እንዲቀጥሉ ለማድረግ በቅድሚያ አስፈላጊው የምክር አገልግሎት ተሰጥቶአቸው ተስማምተው እንዲወስኑ ይደረጋል፡፡
ከዚህ ውሳኔና የቀዶ ሕክምና በሁዋላ ግን ለሶስት ወር በደስታ መንደር ተቀምጠው በቅርብ የህክምና ክትትል እያደረጉ በምን ሁኔታ መገልገል እንዳለባቸው ትምህርት ይሰጣቸዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ የተለያዩ ለኑሮ የሚያግዙ ትምህርቶችን እንዲወስዱ ይደረጋል። በደስታ መንደር ቆይታቸው በጤና በተመሳሳይም ወደፊት እራሳቸውን በምን መንገድ ችለው ወደ ትውልድ መንደራቸው ቀረብ ብለው መኖር ይችላሉ የሚለውን በጥናት በመመስረት ተግባራዊ በመደረግ ላይ ይገኛል። ሀሳቡ የሚጀምረው ከእነሱ ጋር በመመካከር ሲሆን በአካባቢያቸው ምን ቢሰሩ ያዋጣቸዋል? የሚለው ከግንዛቤ ይገባል፡፡ አነስተኛ ቢሆንም ለስራ መነሻ የሚሆናቸው ገንዘብም ይሰጣቸዋል፡፡
አቶ ጉቱ ሰቦቃ በደስታ መንደር ለሶስት ወር ያህል ከቆዩ በሁዋላ ወደየመንደራቸው ወይንም አካባ ቢያቸው የሚሄዱ ታካሚዎች ከሄዱ በሁዋላ ያለው የኑሮ ሁኔታቸው ምን ይመስላል የሚለውን ክትትል እና ድጋፍ የሚያደርጉ ባለሙያ ናቸው፡፡ እሳቸው እንደሚሉት ሕመሙ በዚህ አካባቢ ተብሎ የማይወሰን በሁሉም ክልል የሚፈጠር እንደመሆኑ ታካሚዎች ወደመንደራቸው የሚሰማሩትም በሁሉም የኢትዮጵያ ክልል ነው፡፡ ስለዚህም ወደመጡበት ማህበረሰብ ተመልሰው ኑሮአቸውን እንዲጀምሩ …ተቋርጦ የነበረውን ሕይወት እንዲቀጥሉ ይደረጋል፡፡ ሕመሙ ሲገጥማቸው ትዳራቸው የመፍረስ… ንብረታቸው የመበተን አደጋ የሚደርስበት በህብረተሰቡ ዘንድ መገለል እና የማህበራዊ ውም ሆነ ኢኮኖሚያዊው ኑሮአቸው ስለሚ ቋረጥ ይህ ድርጅት ወደአካባቢያቸው ሲመልሳቸው እነዚህ ነገሮች መቶ በመቶም እንኩዋን ባይሆን በተቻለ መጠን ሴቶቹ እራሳቸውን የሚያስተዳድሩበትን መንገድ በመፈለግ እንዲቋቋሙ በማድረግ ነው፡፡ ይህ ስራ የሚሰራው ከባለድርሻ አካላት ጋር ነው፡፡ ስራ መስሪያ ቦታ ማግኘት አለባቸው፡፡ የገበያ ትስስር እንፈጥራለን የሚል ቃል ኪዳን ስናገኝ ገንዘብ እንዲደርሳቸው ይደረጋል፡፡ እነዚህ ነገሮች የሚሰሩት ከሴቶች ጉዳይ ቢሮ… ከሀይማኖት ተቋማት … በቅርብ ከሚገኙ መንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች እንዲሁም ለጉዳዩ ቅርብ ከሆኑ ግለሰቦች ጋር በትብብር እንሰራለን፡፡ እነዚህ ሴቶች ተቋቁመው ስራ ከጀመሩ በሁዋላ በተወሰኑ ጊዜያት ከቤታቸው ድረስ እየሄድን እውነት በአይን የሚታይ ነገር አለ ወይ ? ተግባሩ ከምን ደርሶአል? የሚለውን ክትትል እናደርጋለን፡፡
ወ/ሮ በለጥሻቸው ታደሰ የደስታ መንደር ስራ አስኪያጅ በስተመጨረሻው የገለጹት አንዲት ሴት ልጅ ተድራ ልጅ ለመውለድ ስትደርስ ጀምሮ ያለው ጥንቃቄ በአካባቢው የሚኖር ሰው ሁሉ ኃላፊነት መሆ ኑን ነው፡፡ የትዳር ጉዋደኛ …ቤተሰብ እንዲሁም የመንደር …አካባቢው ሰው ሁሉ ስለዚያች ልጅ መጨ ነቅ አለበት፡፡ ችላ ማለት አይቻልም፡፡ ምክንያቱም አንዲት እናት ደህና ሆነች ማለት ሰፈር ጎረቤቱ… ቤተሰቡ… ዘመድ አዝማዱ ሁሉ ደህና ነው ማለት ስለሆነ ነው፡፡
እናትነት ዘመን የማይሽረው መቼም የማይቀየር ውድ ነገር ነው፡፡ እናትነትን ምንጊዜም …ምንም አያደበዝዘውም፡፡

Read 2331 times