Saturday, 27 January 2018 12:10

ኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት አያያዟን እንድታስተካክል ተጠየቀ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(4 votes)

በ7 ዓመት ውስጥ 85 ጋዜጠኞች ተሰደዋል

    የኢትዮጵያ መንግስት የዜጎቹን የሰብአዊ መብት አያያዝ እንዲያሻሽል የተባበሩት መንግስታት ድርጅትና አለማቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች የጠየቁ ሲሆን ሰሞኑን በወልድያ የተፈፀመው ግድያም በገለልተኛ ወገን እንዲጣራ ጠይቀዋል፡፡
የፈረንጆች ያለፈው ዓመትን  የኢትዮጵያ አክራሞት የዳሰሰው የሂውማን ራይትስ ዎች ሰሞነኛ ሪፖርት የፀጥታ ኃይሎች የሰብአዊ መብት ጥሰት መፈፀማቸውን ጠቁሞ መሰረታዊ የሰብአዊ መብቶችና ነፃነቶች ተገድበው መቆየታቸውን አመልክቷል፡፡
የፖለቲካ ምህዳሩ እንዲሰፋ፣ የፀጥታ ኃይሎች ግድያና በኃይል ማፈናቀል እንዲቆም ሲጠይቋቸው የነበሩ ዋነኛ ጉዳዮች ቢሆንም መንግስት ለእነዚህ ጥያቄዎች በቀጥታ ምላሽ ከመስጠት ይልቅ የፀረ ሙስና ዘመቻ፣ የካቢኔ ሽግሽግ እንዲሁም እምብዛም ተቀባይነት ከሌላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ድርድር ማድረግና የመልካም አስተዳደር ችግርን ለመፍታት ቃል በመግባት ብቻ መወሰኑን በሪፖርቱ ተጠቅሷል፡፡
“አሁንም የፖለቲካ ምህዳሩ እንደተዘጋ ቀጥሏል” ያለው የተቋሙ ሪፖርት፤ “በመንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ላይ የተጣለው ገደብና የነፃ መገናኛ ብዙኃን እጦት የሀገሪቱ ችግሮች ሆነው ዘልቀዋል” ብሏል፡፡ የፖለቲካ ፓርቲ አባላትና የመንግስትን እንቅስቃሴ የማይደግፉ ዜጎችም ከእስርና ከእንግልት እንዳላመለጡ ሪፖርቱ ጨምሮ አትቷል፡፡
በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የታሰሩ 8 ሺህ ያህል ዜጎች እስካሁንም እስር ላይ መሆናቸውን የጠቆመው ሪፖርቱ፤ አርቲስቶች፣ ፖለቲከኞች ጋዜጠኞች ከፖለቲካ ጋር የተገናኙ ክሶች ቀርቦባቸው በእስር ላይ ይገኛሉ ብሏል፡፡
መንግስት አሁንም የመገናኛ ብዙኃን ነፃነትን ገድቦ በመያዙ ጋዜጠኞች ራሳቸውን ሳንሱር በማድረግ እንዲጠመዱና ሙያዊ ኃላፊነታቸውን እንዳይወጡ አስገድዷቸዋል ብሏል ሪፖርቱ፡፡
እ.ኤ.አ ከ2010 ጀምሮ ባለፉት 7 ዓመታት ውስጥ 85 ጋዜጠኞች ከአገር መሰደዳቸውን፣ ከእነዚህ ውስጥ ስድስቱ በተጠናቀቀው የፈረንጆች 2017 ዓመት መሰደዳቸውን የጠቆመው ሪፖርቱ፣ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋና ውብሸት ታዬ ደግሞ በፀረ ሽብር ህጉ ተፈርዶባቸው በእስር ላይ እንደሚገኙ አስታውሷል፡፡
በጋዜጠኞች ላይ እየደረሰ ካለው ጥቃት ባሻገር ነፃ መገናኛ ብዙኃንን ማጥቂያ ስልቶች ተግባራዊ እየተደረጉ መሆናቸውን የጠቆመው ይኸው ሪፖርት፤ ማስታወቂያ አስነጋሪዎችን፣ ማተሚያ ቤቶችንና አከፋፋዮችን የማስፈራራት ስራ ይሰራል ብሏል፡፡
ጠንካራ ነጻ ሚዲያ በሀገሪቱ መታጣቱን ተከትሎም ማህበራዊ ሚዲያና መቀመጫቸውን በውጭ ሃገር ያደረጉ እንደ “ኢሳት” እና “ኦኤምኤን” የመሳሰሉ ሚዲያዎች የህብረተሰቡ ሁነኛ የመረጃ ምንጭ ሆነው መዝለቃቸውን ሪፖርቱ ያትታል፡፡
ይህን ለመከላከልም መንግስት የኢንተርኔት ግንኙነቶችን በማቆራረጥና የአየር ሞገዶችን በማወክ ሰፊ የመገደብ እንቅስቃሴ ማድረጉ ተጠቅሷል፡፡
የሰብአዊ መብት አያያዝ ጉዳዮችን በትኩረት የዳሰሰው ይኸው ሪፖርት፤ የስቃይ ምርመራ አሁንም ከፍተኛ ችግር ሆኖ መዝለቁን ጠቁሞ፤ በርካታ ታሳሪዎች ለረጅም ጊዜያት ፍ/ቤት ሳይቀርቡ፣ ታስረው የስቃይ ምርመራ እንደሚፈፀምባቸው ይገልፃል፡፡
እነዚህ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን የተባበሩት መንግስታት የምርመራ ቡድን እ.ኤ.አ በ2005፣ 2007፣ 2009፣ 2011 እና 2015 ለማጣራት ተደጋጋሚ ጥያቄ ቢያቀርብም ከመንግስት አዎንታዊ ምላሽ አለማግኘቱን በሪፖርቱ ተጠቅሷል፡፡
መንግስት የመብት ጥሰቶቹን በራሱ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን አጣርቶ ውጤቱን ይፋ እንደሚያደርግ በተደጋጋሚ ቃል ቢገባም ተፈፃሚነቱ አነስተኛ መሆኑን የጠቆመው ሂውማን ራይትስ ዎች፤ “በተቋሙ የሚቀርቡ የምርመራ ሪፖርቶችም ተአማኒነት ይጎድላቸዋል” ብሏል፡፡
የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብት ኮሚሽን በበኩሉ፤ ሰሞኑን በወልዲያ የተፈፀመውን ግድያ ባወገዘበት ሪፖርቱ፤ በፀጥታ ኃይሎች የሚፈፀሙ ግድያዎች እንዲቆሙና የሰብአዊ መብት አያያዝ እንዲሻሻል አሳስቧል፡፡
መንግስት የሰብአዊ መብት አያያዙን ለማስተካከልም የህግና የፖሊሲ ለውጥ እንዲያደርግና አለማቀፍ የሰብአዊ መብት አያያዝ መመዘኛዎችን ለፀጥታ ኃይሎች በማስተማር እንዲተገብር ኮሚሽኑ ጠይቋል፡፡
በዜጎች ላይ የተፈፀሙት ግድያዎች ውጤታማ እና ተአማኒነት ያለው ማጣራት በገለልተኛ አካል ተደርጎ ድርጊቱን የፈፀሙ ወገኖች ለህግ እንዲቀርቡ አሳስቧል - ተቋሙ፡፡
የመንግስት ኮሚኒኬሽን ኃላፊ ሚኒስትር ዶ/ር ነገሪ ሌንጮ በበኩላቸው ሰሞኑን በማህበራዊ ድረ ገፃቸው ባሰፈሩት መልዕክት፣ ክቡር የሆነው የሰው ህይወት ሳይጠፋ ችግሮችን ሰላማዊ በሆነ መንገድ መፍታት፣ ለዘላቂ ሰላም አማራጭ የሌለው መፍትሄ ነው ብለዋል፡፡
“የፀጥታ ኃይሎች የሰው ህይወት ሳይጠፋና አካል ሳይጎድል፣ የጋራ መግባባት ላይ መድረስ እንደሚቻል በመገንዘብ፣ የመፍትሄ አካል መሆን ይጠበቅባቸዋል” ብለዋል-ሚኒስትሩ፡፡

Read 4898 times