Sunday, 28 January 2018 00:00

በሳምንቱ በተቃውሞና በግጭቶች 15 ያህል ዜጎች ህይወት ጠፍቷል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(6 votes)

 በቆቦ ከተማ የተቀሰቀሰው ግጭት የሰው ህይወት ቀጥፏል

    በአማራ ክልል በምትገኘው ቆቦ ከተማ ባለፈው ረቡዕና ሐሙስ በተፈጠረ ተቃውሞ የ7 ሰዎች ህይወት ማለፉንና የመንግስት ተቋማትን ጨምሮ የግለሰቦች የንግድ መደብሮችና መኖሪያ ቤቶች መውደማቸውን ምንጮች ለአዲስ አድማስ የጠቆሙ ሲሆን በአጠቃላይ በሳምንቱ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በተፈጠሩ ተመሳሳይ ግጭቶች የ15 ሰዎች ህይወት ጠፍቷል፡፡
ባለፈው ሳምንት የጥምቀት ማግስት በተፈጠረ ግጭት የ7 ሰዎች ህይወት ከጠፋባት ወልዲያ ከተማ በ50 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ቆቦ ከተማ፣ ረቡዕ አመሻሽ 11 ሰዓት ላይ በከተማዋ ሚስማር ተራ ተብሎ ከሚጠራው አካባቢ በርከት ባሉ ወጣቶች ተቃውሞ መቀስቀሱን የጠቆሙት የአዲስ አድማስ ምንጮች፤ ተቃውሞው ሌሊቱን ቀጥሎ 25 የልብስ መሸጫ መደብሮች፣ 4 ወርቅ ቤቶችን ጨምሮ የሸቀጣ ሸቀጥ መደብርና ተሽከርካሪዎች በቃጠሎ መውደማቸውን ገልፀዋል፡፡
የከተማው ማዘጋጃ ቤት ሙሉ ለሙሉ እንዲሁም የቆቦ ወረዳ ፍ/ቤት በከፊል መውደሙን የጠቆሙት ምንጮች፤ የቆቦ ማዘጋጃ ቤት ኃላፊ እና የከተማዋ ከንቲባ መኖሪያ ቤት በድንጋይ መደብደቡን ተናግረዋል፡፡ በእለቱም አንድ ሰው በጥይት ቆስሎ፣ ሆስፒታል መግባቱን ምንጮች ተናግረዋል፡፡
ረቡዕ እለት ከቆቦ 17 ኪ.ሜ ርቀት ላይ በምትገኘው ሮቢት ከተማም በተመሳሳይ በተቀሰቀሰው ተቃውሞ፣ የሶስት ቀበሌዎች ጽ/ቤቶችና የሮቢት ማዘጋጃ ቤት መቃጠላቸውን ምንጮች ጨምረው ገልፀዋል፡፡
ሐሙስም ቀጥሎ በዋለው ተቃውሞና ግጭት የተለያዩ የእርሻ ኢንቨስትመንቶችና የእርሻ ልማት ጽ/ቤት እንዲሁም መጋዘኖች ከእነ ንብረታቸው መቃጠላቸውን የጠቆሙት ምንጮች፤ በእለቱ 7 ወጣቶች በግጭቱ ህይወታቸው ማለፉን አስታውቀዋል፡፡ ከሟቾች መካከል የ7 እና የ13 አመት ህፃንና ታዳጊ እንደሚገኙበትም ምንጮች ጠቅሰዋል፡፡ ህፃናቱ በመኖሪያ ቤታቸው በር ላይ እንዳሉ መገደላቸውንም ምንጮች ጠቁመዋል፡፡
በቆቦ እና በአቅራቢያው ባሉ ሌሎች ከተሞች ሐሙስ እለት አመሻሽ ድረስ ከየአቅጣጫው ተኩስ ድምፅ ይሰማ እንደነበር ምንጮች ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡
በትናንናው ዕለት አመሻሽ ድረስ በቆቦ ከተማ ተቃውሞና ግጭቶች ረገብ ያሉ ቢሆንም ምንም አይነት የትራንስፖርትና የንግድ እንቅስቃሴ ሳይኖር መዋሉን ምንጮች የጠቆሙ ሲሆን ሮቢት ከተማ ላይ ግን ተቃውሞና ግጭቱ ቀጥሎ 3 ሰዎች ቆስለው ሆስፒታል መግባታቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡
የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው፤ በወልዲያና በቆቦ እንዲሁም በአቅራቢያው ባሉ ከተሞች የተፈጠረው ተቃውሞና ግጭት፣ የመንግስት አመራሮች የህዝቡን የመልካም አስተዳደር ጥያቄ በአግባቡ ባለመመለሳቸው የተፈጠረ መሆኑን በመጥቀስ፤ “እየጠፋ ያለው ህይወት፣ እየወደመ ያለው ንብረት ህብረተሰቡ ከፀጥታ ኃይሎችና ከሀገር ሽማግሌዎች ጋር ተባብሮ በመስራት ማስቆም አለበት” ብለዋል፡፡ “ሁሉም ለሰላም ዘብ መቆም አለበት” ሲሉም አክለዋል፡፡
በዚህ ጉዳይ ላይ ተጨማሪ ማብራሪያ ከክልሉ መንግስት ኮሚኒኬሽን ለማግኘት አዲስ አድማስ ያደረገው ተደጋጋሚ ሙከራ፤ የኃላፊው አቶ ንጉሡ ጥላሁን የእጅ ስልክ ስለማይነሳ አልተሳካም፡፡
ጥር 12 ቀን 2010 ዓ.ም በወልዲያ ከተማ የ7 ሰዎች ህይወት ማለፉን መንግስት ያስታወቀ ሲሆን ከኬንያ ጋር አዋሳኝ በሆነችው ሞያሌ ከተማም 1 ሰው ተገድሎ 3 መቁሰላቸው ታውቋል፡፡ በአጠቃላይ በሳምንቱ በአገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች 15 የሚደርሱ ዜጎች ህይወታቸው ማለፉ ለማወቅ ተችሏል፡፡
በሌላ በኩል በዚሁ ሳምንት በወልቂጤ ከተማ በሺዎች የሚገመቱ ነዋሪዎች የተሳተፉበት  የተቃውሞ ሰልፍ መካሄዱን ምንጮች የጠቆሙ ሲሆን በተቃውሞው ሳቢያ የደረሰ ጉዳት መኖሩን ለማረጋገጥ አልተቻለም፡፡  

Read 6624 times