Saturday, 27 January 2018 12:30

ታሪካዊው የሙዚቃ ድግስ - (በወፍ በረር ቅኝት)

Written by 
Rate this item
(5 votes)

“ምስጋናዬና ፍቅሬ ከልብ ነው”
ከአራት ዓመታት በኋላ በኢትዮጵያ ውስጥ የመጀመሪያው የሆነው የሙዚቃ ድግሴ እጅግ ባመረ መልኩ ተጠናቋል። የባህርዳር ህዝብ ወደ ከተማዋ ስገባ ካደረጉልኝ አቀባበል ጀምሮ፣ በቆይታዬ ወቅት ባሳዩኝ ፍቅርና ክብር እንዲሁም መስተንግዶ ልቤ ተነክቷል - እወዳችኋለሁ! የዝግጅቱ ዕለት ስቴዲየም ተገኝታችሁ የታደማችሁ በሙሉ በተለይም ደግሞ ከሩቅ አካባቢዎች፣ ከአራቱም ማዕዘን መጥታችሁ ኮንሰርቱን ለተካፈላችሁ ሁሉ ምስጋናዬና ፍቅሬ ከልብ ነው።
የሙዚቃ ስራዎቼን ማቅረብ ከጀመርኩ ጊዜ አንስቶ፣ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ የማይገባኝን ሁሉ እንዳደረገልኝ በድጋሚ በመመስከር፣ ሁሌም በፍፁም ታማኝነት፣ እናንተን እንደማገለግል ሳረጋግጥ በታላቅ ኩራት ነው።
እግዜር ያክብርልኝ!
አመሰግናለሁ ባህር ዳር!
አመሰግናለሁ ኢትዮጵያ!
(ከቴዲ አፍሮ ፌስቡክ)
 እጅግ ከብዙ ተደጋጋሚ ሙከራዎች በኋላ በማስታወቂያ ብቻ ተገድቦ ያልቀረው፤ “ኢትዮጵያ ወደ ፍቅር” የተሰኘው የብላቴናው የሙዚቃ ኮንሰርት፣ እውን ሆኖ፣ በስኬት ተጀምሮ በስኬት ተጠናቋል። የኮንሰርቱ አዘጋጆች /በተለይም ቴዲ አፍሮ/ ከሙዚቃ ኮንሰርቱ አንድ ቀን ቀደም ሲል፣ በወልድያ ከተማ በተቀሰቀሰ ተቃውሞና እሱንም ተከትሎ፣ በሞቱት ሰዎች ምክንያት ፕሮግራሙ እንዲሰረዝ ብዙ ዓላማ ከነበራቸው “አዛኝ ቅቤ አንጓቾች” በኩል የተከፈተውን ፕሮፓጋንዳ፣ እንዳላየ ለማለፍ ተገደዋል። ሁሉን እሰማለሁ ካልክ ከሁሉም አትሆንም፤ ወዳጄ።
በዛሬ ጊዜ የላፕቶፓቸውን ኪ-ቦርድ፣ ለነገርና ለቦይኮት ያቀባበሉ የዘመናችን ተዋጊዎች ዘንድ አድመኝነት እንጂ ማስተዋል ብሎ ነገር የለም። ይህን የሙዚቃ ድግስ ለማዘጋጀት አርቲስቱና ተባባሪዎቹ ብዙ ድካምና መከራ ከፍለው ባህር ዳር በተገኙበት፣ የመድረክና ተያያዥ ውድ ዝግጅቶች በተጠናቀቁበት፣ ብዙ የብላቴናው አድናቂዎች ከመላው ኢትዮጵያ ባህር ዳር በታደሙበት፣ እጅግ ብዙ ትኬቶች ተሽጠው ባለቁበት--- 11ኛው ሰዓት ላይ የአባ ምን ገዴ ልጆች፤ የራሳቸውን መደበኛ የዕለት ተዕለት ተግባራቸውን አንድም ሳያዛንፉ እየከወኑና ጠቆር ያለ ማኪያቶኣቸውን እየላፉ፣ በሚነካኩት ሞባይላቸው፣ በድፍረት የኮንሰርቱን መሰረዝ ጠይቀዋል።
ሁኔታው ወዳጄ ናቲ ማን፣ ከወር ገደማ በፊት ያጫወተኝን እንባ አስጨራሽ ገጠመኙን አስታወሰኝ። ናቲ መኪና አልባ ተከራይን ፈልጎ ማግኘት በሚቸግርበት አንድ የሸገር ኮንዶሚኒየም ብሎክ ነበር እሚኖረው። የኮንዶሚኒየሙ ግቢ ሁሌም በጊዜ፣ በተከራዮቹ መኪና ጥቅጥቅ ብሎ ይሞላል። አንድ ቀን ናቲ ወደ ግቢው ሲገባ ከፊቱ ሌላ ባለ መኪና ቆሟል። የብሎኩ ዘበኛ፣ ሰውየውን፣ የግቢው መኪና ማቆሚያ ስለሞላ መኪናውን ውጭ እንዲያሳድራት በማመናጨቅ እጁን እያወናጨፈ ነገረው። ይሄኔ ሰውየው መስኮቱን ዝቅ አድርጎ፣ ዘበኛውን በመጥራት እንዲህ አለው፡-
“እንደው የአስር ብር ኮንጎ ጫማህን ውጭ እማታሳድር ሰውዬ፣ አፍህን ሞልተህ የሚሊዮን ብር መኪናን ውጭ አሳድር ስትል አይቀፍህም?”
መቼም ምን ለማለት እንደፈለግሁ፣ ይገባችኋል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ የሆነው ሆኖ፣ ቴዲ አፍሮ እጅግ በበዛ መሬት አንቀጥቃጭ የህዝብ ፍቅር ታጅቦ ድግሱን ከውኗል። ድግሱም፤ “Bahir Dar, are you ready?!” ከሚለው ከብዙ ናፍቆት በኋላ ከተሰማው የብላቴናው ድምፅ፣ ሶስት አራት ሰዓት ቀድሞ በኢትዮጵያዊነት ቀለማት እጅግ አሸብርቆ ቆይቷል። ከፍቅርና አንድነት ግምጃ ተራቁተን ባዶ በቀረንበት በዚህ ዘመን፣ እንደ ኢትዮጵያዊ፤ የቀረን አስተሳሳሪ ምልክት፣ አንድ ግለሰብ ብቻ መሆኑን ስታይ ሆድ ይብስሃል። እንደ ኢትዮጵያዊ ማሰብ፣ እንደ ኢትዮጵያዊ መኖርና እንደ ኢትዮጵያዊ መዘመርን ለተጠሙ ወገኖች ሁሉ ግን ምሽቱ በቀላሉ እሚረሳ ሆኖ አላለፈም።
በተለይም ወደ ስታዲየሙ በተወሰኑ ወጣቶች አማካኝነት፣ የኦሮሚያ ክልል ባንዲራ ሲገባ የተሰማው የህዝብ ድጋፍና ጭፈራ ልብን አብዝቶ እሚያሞቅ ነበር። ጭብጨባና ድጋፉን ተከትሎም፤ “ኦሮሚያ! ኦሮሚያ!” የሚለው የቀመር የሱፍ ዜማ፣ በታዳሚው አንደበት በጋራ ተዚሟል። ወዲያው ከመድረኩ የአሊ ቢራ ሙዚቃ ተከፍቶ በአንድነት ተጨፍሮበታል።
እንዲህ እንዲህ እያለ የቀጠለው ኮንሰርት፣ ወደ ሁለት ሰዓት አቅራቢያ፣ ከብዙ ጥበቃ ትዕግስትና ፈተና በኋላ የተናፋቂውን “ሰው!” ድምፅ ማሰማቱ አልቀረም።
“Bahir Dar, are you ready?!”
ወዳጄ፤ ልክ እንደኔ የመሬት መንቀጥቀጥን በህይወትህ አይተህ እማታውቅ ከሆነ፣ በዚህች ሰአት በዚህች ቦታ ባለመገኘትህ ልታዝን ይገባሃል። ቃላት በማይገልፀው ጩኸት፣ ሆታ፣ ግፊያና አጀብ፤ ብላቴናው እጅግ ያሸበረቀ ደማቅ መስቀል፣ ከፊቱ ያተመ ቲ-ሸርት ለብሶ፣ “አፍሪካዬ!” እያለ ወደ መድረኩ መጣ። እዚህ ጋ ዝም ብል ነው የሚሻለው፡፡ ምክንያቱም የሆነውን፣ የተሰማውን፣ የተደረገውን --- በቃላት ልገልጸው አልችልማ። አዝናለሁ!!
ከዚህ በፊት በተለያዩ ቦታዎች የብላቴናውን የሙዚቃ ድግሶች ታድሜአለሁ። ሁሉም ጋ አርቲስቱ ከህዝቡ የሚበረከትለት ድጋፍና ፍቅር ልክ የለውም፡፡ የእሁዱ ግን ይለያል፡፡ ቴዲ፤ ወደፊትም ይሄን በመሰለ የህዝብ የፍቅር ባህር ውስጥ ሰምጦ፣ መዝፈኑን እጠራጠራለሁ። እያንዳንዱ ሙዚቃ ሲጠናቀቅ በምትገኘው ፋታ መሃል፤ ”ቴዲ አንደኛ! ቴዲ የአንድነት መንፈስ!” የሚል የአድናቂዎች ሙገሳ ይንቆረቆርለት ነበር፡፡ አርቲስቱም በመሽኮርመምና በመደነቅ፣ ለተበረከተለት የፍቅር ሙገሳ፣ ምስጋናውን ሲያቀርብ አምሽቷል። አንዴ ደግሞ፤ “ዕድሜና ጤና ለቴዲ!” እያለ ህዝቡ ሞቅ ያለ ጭፈራውን አስነካው፡፡ ቴዲም በበኩሉ፤ ”ረጅም ዕድሜ ለሁላችን!” ሲል በአጸፋው መርቋል።
የባህርዳሩ ኮንርሰት በሙዚቃ ጥራት በኩልም ሊመሰገን የሚገባው ነበር። አቡጊዳ ባንድ፤ የሳክስፎን ትራምፔትና መሲንቆ ተጫዋቾችን እንደ አዲስ ጨምሮ ተገኝቷል። ከሮቤልና አበራ በተጨማሪም ሌላ ሶስተኛ የሊድ ጊታር ተጫዋች ነበረው፡፡ ሩፋኤል ያልተገኘበት ከበሮ፣ በሁለት ወጣቶች ሲደለቅ አምሽቷል። ባንዱ የስቱዲዮን “ኢፌክት” ለማምጣት በተጠጋ ውጤታማ “አኪውሬሲ”፣ ሙዚቃውን ሲጠበብበት  አምሽቷል። ብላቴናው፤ “አፍሪካ”፣ “ግርማዊነትዎ” እና “ጥቁር ሰውን” ከበፊት አልበሞቹ ላይ እንዲሁም “ኢትዮጵያ”፣ “ሰምበሬ”፣ “ማር እስከ ጧፍ”፣ “አናኛቱ”፣  “ያምራል”፣ “ታሞልሻል”፣ “እማ ዘንድ ይደር”፣ “ቴዎድሮስ” እና “ማራኪዬ”ን ከአዲሱ አልበሙ ተጫውቷል። በተለይ “አናኛቱ፣ ሰምበሬ፣ ኢትዮጵያ፣ ማር እስከ ጧፍና ቴዎድሮስ”ን ሲጫወት፣ የህዝቡ የዝማሬና አንድነት መንፈስ ለጉድ ነበር።
/Some awkward moments:)
ኮንሰርቱ በሁለት ምዕራፍ የተከወነ ነበር። በመሃል ቴዲና ባንዱ ለእረፍት ሲወርዱና በድንገት የዲጄው የሙዚቃ ግብዣ በቴክኒክ ብልሽት ምክንያት ሲቋረጥ፣ ከፍተኛ የተቃውሞ ድምፆች ከተለያዩ የስታዲየሙ ክፍሎች መስተጋባት ጀመሩ። እንዲህ ያለውን የተቃውሞ መንፈስ፣ ብዙም የፈለጉት እማይመስሉት የአርቲስቱ የቅርብ ሰዎች፣ በተለይም ማኔጀሩ አቶ ጌታቸው፣ ወደ መድረኩ ጫፍ ወጥቶ፣ ዲጄውን ሲቆጣው ተስተውሏል። “በሙዚቃ ያዝልን” አይነት ነው፤ ነገሩ። ይህ ትዝብት ግን ከመድረኩ በቅርብ ርቀት የተገኘ ያንድ ታዳሚ አረዳድ መሆኑ ይታወቅልኝ፡፡ ያም ሆኖ፣ የተቃውሞ ድምፆችን ማየል ከመድረክ ጀርባ (ባክስቴጅ) ሆኖ የሰማው አርቲስቱ፤ በተለመደ የሃይል መልዕክቱ እዛው ሆኖ፣ ትህትናን ባጀበ ድምፅ “ፍቅር ያሸንፋል!!!” ሲል አረጋግቷል። ቴዲ ዘፋኝ ብቻ እንዳልሆነ ለመመስከር፣ እንዲህ ባሉ አስጨናቂ ገጠመኞች መሃል መገኘትን ይጠይቃል።

ነገረ ጃ ያስተሰርያል
የጃ ጣጣ ሌላ የመድረክ ላይ ድራማ አሳይቶን አልፏል። ህዝቡ ከመጀመርያው አንስቶ በእያንዳንዱ የሙዚቃ ፋታ መሃል፣ “ጃ ያስተሰርያል”ን ሲጠይቅ ነበር ያመሸው። አርቲስቱ ወደ መጨረሻ፣ ዝግጅቱን በ“ጥቁር ሰው” ሊዘጋ በሚሰናዳባት ሰዓት ላይ ግን የህዝቡ ጥያቄ አይሎ፣ ግጥሞች ከፍ ባለ ድምፅ በዜማ ይሰሙ ጀመር።
ግርማዊነታቸው ከዚህ ሰረገላ
ወደ ዋገን ወርደው ሲተኩ በሌላ...
ከዚህ በኋላ የሆነው … አስፈሪ፣ አስደንጋጭ፣ በተወሰነ መልኩም አስቂኝ ነበር።
ቴዲ ህዝቡን ጠየቀ።
“ያስተሰርያል ይዘፈንላችሁ?”
ህዝቡ ከባህር ዳር ጎንደር ድረስ በሚሰማ ሃይለኛ ድምፅ “አዎ” አለ። ብላቴናው፤ ፊቱን አዙሮ ከጊታር ተጫዋቾቹ ጋር አጭር ምክክር አድርጎ ሲያበቃ፣ ወደ ህዝቡ ዞረና፡-
“እዘፍንላችኋለሁ” አለ።
በዚህ መሃል ሁኔታውን ከዳር ሆኖ ሲመለከት የቆየውና በቁጣና ብስጭት አቅሉን የሳተው የአርቲስቱ ማናጀር መድረክ ሰብሮ ገባ። ”እናንተ ናችሁ አማክራችሁ ዝፈን ያላችሁት!?” በሚል እየተጨቃጨቀ ይመስላል፡፡ ቴዲ አፍሮም ፈገግ እያለ፣ ጭቅጭቁን እንደኛው በዝምታ ነበር የታደመው፡፡
ለሰዓታት ሰላምና ፍቅር ሰፍኖበት የዘለቀው መድረክ፤ ከመቅጽበት ዝምታና ውጥረት ሞላው፡፡ በዚህ መሃል ህዝቡ፤ “ቴዲ አይፈራም!” እያለ መጮህ ጀመረ።
ቴዲም ወደ ህዝቡ በመዞር፤
“እኔ ፈርቼ አላውቅም!” መለሰ፡፡
ሌላ ሆታ፣ ሌላ ጭፈራ። አቶ ጌታቸው ቁጣና ብስጭቱን አራግፎ ከመድረክ ወረደ። አርቲስቱም፤ ጃ የፍቅር፣ የይቅርታና የእርቅ መልዕክት መሆኑን ጠቅሶ፣ ነገር ግን ማንም እንዲከፋው ስለማይፈልግ ኮንሰርቱን በ“ጥቁር ሰው” መዝጋቱ እንደሚሻል በትህትና አስረድቶ፣ ዝግጅቱን በባልቻ ከውኖ ህዝቡን አመስግኖ፣ ከበዛ ድጋፍና ፍቅር ጋር ታጅቦ ከመድረክ ወርዷል።
(ከEil jah ፌስቡክ)

Read 4963 times