Sunday, 28 January 2018 00:00

በሀሳብ መንገድ ላይ

Written by  ተመስገን
Rate this item
(5 votes)

 “እምነት ያለው ሞት አይፈራም!!”
                  
    “እምነት ምንድነው?” ተብለህ ብትጠየቅ … ምናልባት ‹ህሊና› …ብለህ ትመልስ ይሆናል፡፡ … በኔ በኩል አልተሳሳትክም፡፡ “ሰውን በአምሳላችን ፈጠርን” … ሲባል … የመልክና የቁመና ጉዳይ አይመስለኝም፡፡ … ንፁህ፣ ሁለንተናዊና ሚዛናዊ ለማለት ይመስላል፡፡ … በዚህ መንገድ “ህሊና አምላክ ነው” ቢባል ያስኬዳል፡፡ ኢ-አማንያንን ጨምሮ በርካታ የተለያየ እምነት ተከታዮች፣ ከዚህ ሀሳብ ብዙ አይርቁም፡፡
እነዚህ…. ህሊና፣ እምነት፣ አምላክ የምንላቸው ረቂቅ እሳቤዎች፤ በእጆቻችን የምንዳስሳቸው፣ በዓይኖቻችን የምናያቸው አይደሉም፡፡ ነገር ግን በደንብ እናውቃቸዋለን፡፡ … ስናጠፋ እንዲፀፅተን፣ በጎ ስንሰራ ደስ እንዲለን፣ እንዲመቸን----የሚያደርገን መንፈስ የነሱ ነው፡፡
በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ከነዚህ ጋር የሚያያዙ አንዳንድ ጥያቄዎች ግን ምቾት አይሰጡንም፡፡ … አንደፍራቸውም፣ እንሸሻቸዋለን፡፡ … ለማስረዳትም፣ ለመረዳትም ዐቅም ይፈልጋሉ፡፡ … በማስረጃ የዳበረ ዕውቀት፣ አለመዋሸት፣ አለመፍራት፣ ለራስ አለማዳላትና የመሳሰሉትን…፡፡
ለምሳሌ አንድ ህፃን ልጅ …. (ኢትዮጵያዊ፣ አሜሪካዊ፣ ህንዳዊ፣ ቻይናዊ፣ አረብ ወይም አይሁድ ሊሆን ይችላል) ወላጆቹን፣ መምህሩን፣ ጎረቤቱን ወይም አንተ ወዳጄን፡- “እንዴት ተፈጠርኩ? … ሰው ከየት መጣ? …እናንተ ለኔ ምኔ ናችሁ? … እግዜር የት ነው የሚኖረው?... እግዜርን ማን ፈጠረው? … ሰይጣን ምንድነው? … የት ነው የሚኖረው? …. እንስሳት ለምን አይስቁም? … ለምን አያለቅሱም?” ብሎ ቢጠይቅ፣ መልስ ለመስጠት ቀላል አይሆንም።
ሕፃን … ሕፃን ነው፡፡ … አትጠይቅ አይባልም። መመለስ ስለሚያቅተን፣ ጥያቄው መልስ የለውም ማለት አይደለም፡፡ ጥያቄ ያለ መልስ፣ መልስ ያለ ጥያቄ ኖረው አያውቁም፡፡ …
“ልጄ ሆይ፤ ብዙ አትመራመር፣ በጥቂቱ ይበቃሃል፡፡”  ተብሎ የተፃፈው እንኳ ለሚፈልጉት መልስ ነው፡፡
እምነትን ወደ ጎን ትተን፣ በተፈጥሮና በሕብረተሰብ ሳይንስ ለሚዳሰሱ ሃሳቦችና ለሚነሱ ጥያቄዎች፤ ብዙ ሊቃውንት ወደ እውነት ሊወስዱን የሚችሉ የተለያዩ መንገዶችን ጠቁመውናል፡፡ ለምሳሌ የእድገት ሚስጢር፣ የተቃራኒዎች አንድነትና ልዩነት (The law of contradiction, unity and development) መሆኑን በዲያሌክቲካዊ መርህ አጋዥነት፣ መርምረን ልንረዳ እንችላለን፡፡ ፍሬዴሪክ ሄግል፤ ይህንን ዲሲፕሊን በአስር ቅጽ መጽሃፍቱ ይተነትነዋል፡፡
“በልዩነት ልዩነት በአንድነት ውስጥ” የሚለውን ሃሳብ፤ ዕውቀትና ፍልስፍናውን መሰረት ያደረገ ቁምነገር ትቶልናል፡፡ … አጠቃላይ መንፈሱ ባጭሩ እንዲህ የሚል ነው፡-
“The function of the mind, and the task of philosophy, is to disconer the unity that lies potential in diversity; the task of ethics is to unify character and conduct; and the task of politics is to unify individuals in to state. The task of religion is to search and feel that absolute in which all opposites are resolved into unity, that great sum of being in which matter and mind, subject and object, good and evil are one”
(የኤቲክስ ስነምግባር ግመልና ባህሪ ተቻችለው አንድ የሚሆኑበትን ዕውነት ወይም ቁርኝት ማሳየት ነው፡፡ የፖለቲካም ኃላፊነት በየግላቸው የቆሙትን አመለካከቶች፣ ወደ አንድነት መሰብሰብ፣ ሐይማኖትም እንደዚሁ ሃሳብና አእምሮ፣ ክፋትና ደግነት በሚል ተቃርኖ የታነፁትን አስተሳሰቦች፣ ፍፁም ወደምንለው መንፈሳዊ አንድነት ማምጣት ይሆናል፤) የሚል ነው፡፡
*       *     *
ወዳጄ፤ ብርሃንና ጨለማ፣ ጦርነትና ሰላም፣ ወንድና ሴት፣ ለቅሶና ሳቅ፣ ህይወትና ሞት --- ውስጥ አንድነት አለ፡፡ አንድነታቸው ባይኖር ልዩነታቸው አይታወቅም፡፡ …አንድነታቸው፤ ማንነታቸው ነው፡፡ አንድነታቸው፤ እውነትና ውበት ነው፡፡ አንድነታቸው፤ በመኖር ዙሪያ የሚፈጠር ትግል ነው፡፡ አንድነታቸው፤ ዓለምን ፈጥሯል፡፡
ነገሮች ሁሉ የሚለያዩበት፣ የሚስማሙበት፣ የሚጣመሩበትና ወደ አንድነት የሚያመሩበት ህግና ስርዓት ወይም ምክንያት አላቸው፡፡ ፍጥረትን ያለ ህግ፣ አንድነትን ያለ ምክንያት ማሰብ ከንቱ ነው፡፡ ሰውም ሰው፣ ሃሳብም ሃሳብ፣ አገርም አገር፣ ዕቃም ዕቃ የሚሆነው፣ በዚሁ ተፈጥሯዊ ዑደት ነው!! …. ሎርድ ባይረን እንደሚለው፡-
“Nothing in the world is single;
All things by a law divine
In one spirit meet and mingle.”
ብቸኛ ነገር የለም - በዚህች ውብ ምድር ላይ!!
በህግና በፍቅር - ሁሉም ተጠምዷል አንድ ላይ
ወዳጄ፡- የድሮ ገንዘብ (የወረቀት ብር) ቢኖረን ልንገበያይበት እንችላለን? … ለጌጥ ወይ ለታሪክ ብቻ ካልተጠቀምንበት በስተቀር? .. ሹካና ቢለዋ፣ ምጣድና ድስት፣ መክተፊያና ማማሰያ … ምግብ ካላዘጋጀንባቸው፣ ወይ ካልተመገብንባቸው … ምንድን ናቸው? ክራርና በገና፣ መሲንቆና ዋሽንት፣ ፒያኖና ጥሩምባ --- ክሮቻቸው ቁልፎቻቸው ወይም እኛ ካልተቃኘን፣ ሙዚቃ መፍጠር ይቻላል? ቀለማት ያለ ህብር ቢለቀለቁ ጥበብ ይሆናሉን? … የተራራቁ አበባዎች ናቸው? ወይስ በህብር የቆሙ? አይናችንን የሚስቡ፣ ደምቀው የሚያስጎመጁ?!! የአእምሮ እድገትና ኃይልም የሚገኘው ነፃነት፣ ፍትሃዊነትና ዴሞክራሲ ሲያብቡ ነው፡፡ አለበለዚያ ጭንቀትና ፓራኖያ ይነግሳል፡፡    
በማናቸውም ሀሳብና ነገር ውስጥ የሚታይ ግለኝነት፣ ያረገዘው ትልቅ ዐቅም አለ፡፡ … እያደገ፣ እየገዘፈና እየሰፋ የሚዘልቅ አንድነት!!
… የመጀመሪያ ሰው ብቸኛ ነበር፡፡ … ከዚያስ? … ቤተሰብ፣ ማህበረሰብ፣ ጎሳ፣ ህብረተሰብ፣ አገር፣ አህጉር .. በነገሮችም ውስጥ እንዲሁ!! ... የለውጥ መነሻ (driving force) የምትባለው ቅንጢት (atom) … (በሰው ውስጥ ሲሆን አንዳንድ ፈላስፎች will power) ይሉታል፣ የተገነባችው፣ በኤሌክትሮንስ፣ ፕሮቶንስ፣ ኒውትሮንስና በሌሎች ኤለመንቶች ነው፡፡ በዓይን እንኳ ልናያት የማንችላት፣ ይቺ ቅንጢት ናት ዞራ … ፕላኔት፣ ሶላር ሲስተም፣ ጋላክሲ፣ ዩኒቨርስ፣ መልቲዩኒቨርስ …. የምትባለው፡፡
የዲያሌክቲክስ አባት የሚባለው ሄግል የተወለደው እ.ኤ.አ በ1970፣ ጀርመን፣ ሽቲትጋፍት ውስጥ ነው። የተወለደበት ቀን ከሌላ ጀርመናዊው ባለቅኔ፣ ዎልፍ ጋንግ ገተ የልደት ቀን ማግስት ጋር በመመሳሰሉ፣ አገራቸው ጀርመን የሁለቱንም ሊቃውንት ልደት፣ በተከታታይ ቀናት፣ በየዓመቱ ታከብርላቸዋለች። ሄግል በሚያስተምርበት ዩኒቨርሲቲ፣ በአንድ እግር ጫማ፣ ክፍል እስከ መግባት በመድረሱ፣ “ልበ ቢስ” ነበር ይሉታል፡፡ ከመንግስት ጋር ባለው ቅርበትም ባልደረቦቹ፤ (Contemporaries) ኦፊሺያል ፊሎዘፈር (Official philosopher) እያሉ ሲጠሩት፣ ሾፐንሃወር ደግሞ “አድር ባይ! …. “You sing the song whose bread you eat” በማለት ፅፏል፡፡
ታስታውሳለህ ወዳጄ፤ የዚች ፅሁፍ መነሻ “እምነት” የምትል ቃል ነበረች፡፡ ጓደኛዬ ሲያጫውተኝ፡-
“እምነት፣ እሳትና ነፍስ፤ ጓደኛሞች ነበሩ አሉ። በአጋጣሚ በተፈጠረ ግርግር ተለያዩና በየፊናቸው ተሰደዱ፡፡ ሆኖም አንዱ ሌላውን ከመፈለግ አልቦዘኑም። እሳት መንደዱ፣ ነፋስም መንፈሱ አይቀርምና፣ እሳትና ነፋስ ዞረው ተገናኙ፡፡ ጓደኛቸው እምነትን ግን ፈልገው አጡት፡፡ ምክንያቱም እምነት ስለማይታይና የትም ቦታም ስለማይገኝ፣ አንዴ ከጠፋ .. ጠፋ ማለት ነው” አለኝ፡፡
“እምነት ያለው ሞት አይፈራም!! … ሞትን የሚፈራ … እሱ … በውስጡ አያምንም!!” ይላል፤ አንድ ፀሐፊ፡፡
ሠላም!!

Read 5606 times