Sunday, 28 January 2018 00:00

እውነትም ግሩም!

Written by  ከኪዳኔ መካሻ
Rate this item
(7 votes)

(የመፅሐፍ ዳሰሳ)
የመፅሐፉ ርዕስ፡- ግሩም - የዓለማችን ምርጥ ታሪኮች
የገፅ ብዛት - 256
የታተመበት ጊዜ - ጥር፣ 2010 ዓ.ም
ፀሐፊ - ግሩም ተበጀ
 ታላላቅ የፈጠራ ሰዎችን፣ ሥራዎችና ሳይንሳዊ ሐሳቦች ፀሐፊው እንዴት አቀረባቸው ?
ፅሁፎቹ ከጋዜጣ ዘገባና ከምርምር ፅሁፍ በምን ሊለዩ ቻሉ ?
ከታላቁ አይንስታይን እስከ አንድ ተራ የጃፓን ወታደር፤ ከኖቤል ሽልማት፣ ከኮካ እና ፔፕሲ ትንቅንቅ እስከ አስቂኙ እና አስገራሚው የካርጎ አምልኮ እንዴት ባንድ ላይ ቀረቡ…
ምኑ ይገርማል?
አቀራረቡ፣ ምጣኔው፣ የተመረጡት ይዘቶችና በታሪኮቹ ውስጥ የተላለፉት መልዕክቶች መፅሐፉን እንደ ስያሜው አስገራሚ አድርጎብኛል፡፡ ምናልባት በቀላል አገላለፅ ለማስቀመጥ፣ መፅሐፉን በእውቅ ባለሞያ እንደተከሸነ ለአምሮታችሁም፣ ለሰውነታችሁም፣ ለዓይናችሁም የሚያስፈልጋችሁን ይዞ እንደቀረበ ‘በየአይነቱ’ ወይም ‘ማህበራዊ’ አድርጋችሁ ውሰዱት፡፡ የተለየ የጣዕም ወይም የምርጫ ጉዳይ ከሌለ በስተቀር በእነኚህ ምግቦች ውስጥ የአማካዩን ተመጋቢ ፍላጎትና ምርጫ ከግንዛቤ ያስገቡ የምግብ ሰሪው ምርጫዎች፣ ምጣኔዎችና እያንዳንዳቸው ማባያዎች ከእንጀራው ጋር ከአቀራረቡ እስከ አበሳሰሉና ጣዕሙ ድረስ ተሟልተው የሚቀርቡላችሁ ናቸው፡፡
ለእኔም የግሩም ተበጀ መፅሐፍ ያስገረመኝ፣ በአንድ መፅሐፍ ውስጥ በይዘት፣ በመልዕክት፣ በአቀራረብ፣ በምጣኔና በዓይነት የመደበኛውን አንባቢ ብቻ ሳይሆን ማንኛውንም ማንበብ የሚችልና የሚፈልግ ሰው ያማከሉ ሆነው ስላገኘኋቸው ነው። ብዙውን ጊዜ እንዲህ አይነት ለሁሉም የሚሆኑ መፅሐፍት በመፅሐፍት ገበያዎቻችን ላይ አይታዩም፤ ወይም እኔ አላጋጠሙኝም፡፡ ለዚህ መገረሜ መነሻ የሆኑ የመፅሐፉ ዓይነተኛ ገፅታዎችን፣ የሥነ ፅሁፍ ባለሞያ ባልሆንም እንደ አንድ አንባቢ ለመዳሰስ ሞክሬያለሁ…
‘ግሩም’ነቱን ስንመዝነው
ከ15 ገፆች እስከ አንድ ገፅ ከግማሽ የሚረዝሙ አርባ አምስት የተለያዩ ትረካዎች በመፅሐፉ ውስጥ ተካትተዋል፡፡ ፀሐፊው ለጓደኞቹ ከፃፋቸው ሁለት ደብዳቤዎችና ከአንድ አጭር ልቦለድ በስተቀር ሌሎቹ ትረካዎች በእውነታ ላይ የተመሰረቱ ማለትም በግለሰቦች የሕይወት ታሪክ፣ በሳይንሳዊ የምርምር ውጤቶች፣ በተጨባጭ በተከሰቱ ኹነቶች ላይ የተመሰረቱ ኢ-ልቦለዳዊ (Non fictional creative writing) ሥነፅሁፎች ናቸው፡፡ ከነኚህ በተጨማሪ ጥቂት ቦታቸው እዚህ ነው ብሎ ለመመደብ የሚያስቸግሩ አስቂኝ የቃላት ፍቺዎች፣ ዘና እያደረጉ አግራሞት የሚያጭሩ፣ ከሕፃናትና ከተማሪዎች የተሰባሰቡ ሳይንሳዊ አባባሎችና በተለያዩ ሰዎች ስም የተነገሩ ቀልዶችም ይገኙበታል፡፡
ኢ-ልቦለዳዊ ሥነ ፅሁፍ፣ ከደረቅ ኢ-ልቦለዳዊ ዘውግ ከሆኑት የምርምር ወይም ቴክኒካዊ ፅሁፎች ወይም ከጋዜጠኝነት ዘገባ የሚለይበት የራሱ ባህሪዎች አሉት፡፡ ይህ ዘውግ በእውነታ ላይ የተመሰረተ ቢሆንም በአፃፃፍ ለዛና በሥነፅሁፋዊ ቅመም ተዋዝቶ መቅረቡ ከደረቅ ኢ-ልቦለዳዊ ፅሁፎች ይለየዋል፡፡
የሥነፅሁፍ ሐያሲዋ ባርባራ ለውንስቤሪ፤ The Art of Fact በሚለው መፅሐፋቸው ላይ በኢ-ልቦለዳዊ ሥነፅሁፍ ዘውግ ውስጥ የሚካተቱ አራት መለያ ጠባዮች እንዳሉ ፅፈዋል፡፡
ከእነዚህ አራት ባህሪዎች አንፃር እስቲ ‘ግሩም’ን እንመልከታት…
የመጀመሪያው በኢ-ልቦለዳዊ ድርሰት ላይ የሚታየው ባህሪ፣ በደራሲው ምናብ የሚፈጠረው ሳይሆን በገሃዱ ዓለም በተጨባጩ ከተመዘገቡና ሊጠቀሱ ከሚችሉ ጉዳዮች መርጦ የሚፅፈው ነው፡፡ ማለትም የሚፅፋቸው አርዕስተ ጉዳዮችና ኩነቶች፣ በዓለም ላይ ያሉና እውነትነታቸው ሊረጋገጥ የሚችሉ ናቸው፡፡ ሁለተኛው መገለጫ ደግሞ ከ‘ጥልቅ ጥናት ወይም እውቀትና ንባብ’ የሚመነጩ ናቸው፡፡ ይህም ፀሐፊውን በጉዳዮቹ ላይ አዲስ ወይም ወጥ እይታ እንዲኖረው እንደሚያደርገውና በተጨማሪም በፅሁፉ ውስጥ በሚጠቅሳቸው ሊረጋገጡ የሚችሉ ማጣቀሻዎች፣ ትረካውን ተዓማኒነት እንደሚያላብሰው፤ ሐያሲዋ ባርባራ ለውንስቤሪ ይገልፃሉ፡፡
ሦስተኛው መለያ ባህሪው ደግሞ ከጋዜጠኝነት ዓይነተኛ ሥራ ከሆነው፣ ጉዳይ ላይ ብቻ ያነጣጠረ ዘገባ በተቃራኒው ‘የክስተቱን ትዕይንት’ በመግለፅ፣ ቁልጭ አድርጎ የነበረውን ሁኔታ፣ ነፍስ ዘርቶ መከሰት መቻሉ ነው፡፡
አራተኛና የመጨረሻው መገለጫ ባህሪውን በተመለከተ፣ “የጥበብ ፅሁፍ ወይም ሥነፅሁፋዊ የሆነ ቋንቋን የሚጠቀም ዝርው ፅሁፍ መሆኑ ነው” የሚሉት ሐያሲዋ፣ “እውነታነቱ ሊረጋገጥ የሚችል ርዕሰ ጉዳይነቱና የሚደረግበት ጥልቅ ምርምር የኢ-ልቦለዳዊ ድርሰቱን፣ ኢ-ልቦለዳዊ ገፅታ የሚያረጋግጥ ሲሆን ትረካዊ ቅርፁና መዋቅሩ የፀሐፊውን የሥነ ፅሁፍ ክህሎት ይገልፃል፡፡ በመጨረሻም ውብና የጣፈጠ ቋንቋው የታሪኩን ሥነ ፅሁፋዊነት ወይም ጥበባዊ ፅሁፍነት ገልፆ ያሳየናል” ይላሉ፡፡ በእነኚህ የባለሞያዋ መስፈሪያዎች ‘ግሩም’ን ገለጥ ገለጥ እያደረግን፣ እየለካን፣ እየሰፈርናት እንቀጥላለን፡፡
የደራሲው ምርጫና ሚና፡- ንዑስ ርዕሱን “የዓለማችን ምርጥ ታሪኮች” ቢለውም ዓለማችን በዘመናት በቃልም በፅሁፍም የተላለፉ እጅግ በርካታ ምርጥ ታሪኮች አሏት፡፡ ሁሉንም ሊያቀርብልን ባይችልም ፀሐፊው ሰፊ ንባቡንና መመዘኛውን እንዲሁም ዝንባሌውን ተጠቅሞ ምርጥ ያላቸውን አቅርቦልናል፡፡
መፅሐፉን ስናነብ ፀሐፊውን የምናደንቀው እውነተኛ ታሪኮችና ክስተቶች ስለቀረቡበት ብቻ ሳይሆን ከእልፍ እውነቶች መሀል ለእኛ ለተደራሲያኑ ተስማሚና አስፈላጊ የሚሆኑትን ታሪኮች የመረጠበትንና መጥኖ ያቀረበበትን መንገድ ነው፡፡ በሳይንስና በፈጠራ ሰዎች የሕይወት ታሪክ፣ በሳይንሳዊ ጥናትና ምርምር ውጤቶችና የተለያዩ አስገራሚ ክስተቶች ላይ አብዛኞዎቹ ትረካዎች ሊያጠነጥኑ የቻሉት በዚህ የፀሐፊው ምርጫ የተነሳ ነው፡፡
ጥልቅ እና ሰፊ ንባብ ወይም ጥናት
ኢ-ልቦለዳዊ ሥነፅሁፋዊ ሥራዎች አንዱ ባህሪያቸው፣ በተጨባጭ ከተከሰቱ ወይም እንደተከሰቱ ከተዘገቡ ታሪኮች ውስጥ ደራሲው፤ ለተደራሲያን ተስማሚ ናቸው ብሎ የሚመርጣቸው እንጂ በአእምሮው የሚፈጥራቸው አለመሆናቸውን ከላይ ጠቅሰናል፡፡ ይህን ለማድረግ ደግሞ ጥልቅና ሰፊ ንባብና የእውቀት ክምችት ያስፈልጋል፡፡ ፀሐፊው በዚህ በዚህ የታደለ በመሆኑ ነው፤ የተለያዩ ዘመናት፣ ዘርፍና ክስተቶችን የሚመለከቱ ታሪኮችን መርጦ ሊያቀርብልን የቻለው፡፡
ከፃይሉንና ከታንሰን የሩቅ ምስራቅ የሩቅ ዘመን ታሪኮች አንስቶ እስከ ኢርዶስ፣ ቴስላና ሲዲስን መሰል የዘመናችን ድንቆች፤ ከለስላሳ መጠጥ እስከ ኖቤል ሽልማት አስደማሚ እውነታዎች፤ በፓስፊክ ውቅያኖስ ባለ ደሴት ላይ ካለው አስገራሚው የካርጎ እምነት እስከ ላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት አሰራርና ከ16ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ ተሸፍኖ ስላለው የላሊበላው ቤተ ማርያም ምሰሶ፤ ከጥልቅ የሳይንስ ንደፈ-ሃሳቦች፣ እንደ ዕድልና ምርጫ ያሉ የዕለት ተለት ሥነልቦናዊ ጉዳዮቻችን፤ እምነት፣ ፍቅር፣ ሐቀኝነትን ቁልጭ አድርገው ከሚያሳዩ አጫጭር አስገራሚ ታሪኮች፣ በየዕለቱ በእያንዳንዳችን ሕይወት ውስጥ ከማይጠፉ ዝነኞችና ሌሎችንም አስገራሚ ነጥቦችን የዳሰሱ ዓይነተ ብዙና መልዕክታቸው የነጠሩ ትረካዎችን ሊመርጥልን የቻለው፣ከሰፊና ጥልቅ የንባብ ተመክሮ የተከማቸ እውቀት በመነሳት መሆኑን ለመገንዘብ መፅሐፉን ማንበብ ብቻውን በቂ ነው፡፡
ከዚህ ቀደም ለንባብ የበቁ በእውነተኛ ታሪኮች ላይ የተፃፉ የተለያዩ መፅሐፍትን አንብበናል፡፡ በልጅነት ካደግንባቸው የክብር ዶ/ር ከበደ ሚካዔል ታሪክና ምሳሌዎች፣ የጳውሎስ ኞኞ የተለያዩ አስደናቂ ክስተቶችን የያዙ መፅሐፍትና የሌሎችም አሁን ያልጠቀስኳቸው ተመሳሳይ ይዘት ያላቸው መፅሐፍት አሉ፡፡
ነፍሱን ይማረውና ደራሲ ስብሃት ገብረእግዚአብሄር ለዓመታት በተለያዩ መፅሄቶችና ጋዜጦች ላይ አጣፍጦ ያስነብበን የነበሩት ከሰፊና ጥልቅ የንባብ ባህሩ የተጨለፉ፣የተለያዩ ታሪኮቹም በብዙዎች ዘንድ የማይረሱና የተጨማሪ ንባብና የማወቅ ጉጉትን የፈጠሩ ናቸው፡፡
ግሩምም በመፅሀፉ ውስጥ ከሽኖ ያቀረበልን ትረካዎች፣ ከሰፊና ጥልቅ ንባቡ ከገበያቸው እውቀቶች ሊያካፍለን ምርጥ ምርጡን ለአንባቢዎቼ ብሎ አጣፍጦና መጥኖ ያቀረበልን ናቸው፡፡ ለዛም ነው የዘመናችንን የፈጠራና የቴክኖሎጂው ዓለም ሥመ-ጥር፣ የአፕል ኮምፕዩተር መስራች ስቲቭ ጆብስን፣ የሁለተኛው የዓለም ጦርነት ‘አልሰሜ’ን የጃፓን ወታደር ሂሮ ኦኖዳን፣ የእኛውን የላሊበላን ታሪክ በአንድ መፅሐፍ ውስጥ እንድናገኛቸው ያስቻለን፡፡
ዘጋቢ ሳይሆን ተራኪነቱ…
በግሩም መፅሐፍ ውስጥ የቀረቡት አብዛኞቹ በአንድ ወይም በሌላ ወቅት ታትመው ወይም ተዘጋጅተው መፅሐፍትን ጨምሮ በተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎች ከቀረቡ ሥራዎች ላይ ተጨምቀውና ተመጥነው የቀረቡ ታሪኮች ናቸው፡፡ ሆኖም ግን ፀሐፊው ታሪኮቹን አንብቦ፣ ከራሱ ጋር አዋህዶ፣ ለእኛ መርጦ የተረከበት መንገድ በተለይ ለእንደኛ አይነቱ ሂሳብ፣ ሳይንስና ፈጠራ የልዩ ተሰጥኦ ጉዳይ ሆኖ በአብዛኛው ዘንድ በሚታይበት ማህበረሰብ፤ የሳይንስን ውበት፣ የቁጥሮችን አማላይነትና የታላላቅ የፈጠራ ሰዎችን ከታላቅ ሥማቸው ጀርባ ያሉ ሰዋዊ ባህሪያትና ሌሎችንም አስገራሚ ሰብዕናዎችና ‘እንዲህም ኖሯል እንዴ … ወቸ ጉድ’ የሚያስብሉንን ክስተቶችና የጥናት ውጤቶች እንድናነባቸው ብሎም ተረድተን እንድናጣጥማቸው አድርጎናል። ፅሁፎቹን ያቀረበበት አተራረኩም፣ ከጋዜጠኛ ዘገባነት ወይም ከአንድ ተመራማሪ ፅሁፍነት አልፈው የሁላችንንም ቀልብ የሚገዙ ትረካዎች እንዲሁኑ አስችሏቸዋል፡፡
ሥነ ፅሁፋዊ ውበቱ
የግሩም ትረካዎች ከርዕሳቸው አንስቶ እስከ አጀማመራቸውና አጨራረሳቸው ድረስ፤ ከቋንቋቸውና ከአገላለፃቸው አንስቶ ለማጣፈጫነት ወይም ለማዋዣነት እስከሚጠቀምባቸው በባለታሪኮቹ ወይም ከታሪኩ ጋር በተያያዘ እስከተነገሩት ቀልዶች ድረስ የአንባቢውን ቀልብ ገዝቶ የሚይዝ፣ ሥነፅሁፋዊ ለዛ አላቸው፡፡
‘አንድ ሰው ነበር እገሌ የሚሉት’ የሚለው የዓለማችንን ታዋቂና እጅግ አስገራሚ ሰዎችን ታሪኮች የዳሰሰበት ክፍል ርዕስ ብቻውን እንድናነበው፣ የሚገፋፋ የቋንቋ ውበት ተላብሷል፡፡
ግሩም፣ የካህሊል ጂብራንን የሕይወት ታሪክ የተረከልን በተለመደው በዚህ ጊዜ፣ በዚህ ሥፍራ ተወለደ በሚል መግቢያ ሳይሆን በገፅ 34 ላይ ባሰፈረው በአንድ ፖሊስና በደራሲው መካከል ከሌሊቱ 9 ሰዓት፣ በኒውዮርክ የሴንትራል ፓርክ መናፈሻ በተካሄደ ቃለ ምልልስ ነው፡፡ የፖሊሱ ባለቤት የጂብራን ቀንደኛ አድናቂ የመሆኗ ነገርን፣ ጂብራን መሆኑን ያላወቀው ፖሊስ፤ ለራሱ ለጂብራን አማርሮ ይነግረዋል፡፡ በዚህ መግቢያ ስለዚህ ጂብራን ስለተባለ ደራሲ፣ ለማንበብ እንድንጓጓ አድርጎ፣ ምኑንም ሳናውቀው ወደ ታሪኩ ይዞን ጠልቋል…
ይህ የግሩም ታሪኩን አጓጊ ከሆነው ክፍል ላይ በቀጥታ ‘ወደ ገደለው’ እንደሚሉት የመግባት ስልትን በገፅ 52 ላይ ባለው “የሽብር ጠበቃው - ጃክዊ ቨርጄዝ” ታሪክ ላይም እናገኘዋለን፡፡
“እና ለሒትለርም ቢሆን ጥብቅና እቆማለሁ ነው የምትለው ?”
“እንክት !!”
“ለቢንላደንስ ?”
“እንዴታ…! እኔ ጥብቅና አልቆምልህም የምለው አንድም ሰው የለም፡፡ ለማንም - ለሁሉም እቆማለሁ፡፡ አንተ ቢንላደን ትላለህ ለጆርጅ ቡሽም ቢሆን ጥብቅና ለመቆም ዝግጁ ነኝ - ጥፋተኝነቱን ካመነ ነው ታዲያ” እያለ አደገኛ ብለን ለምናስባቸው ሰዎች ጥብቅና እቆማለሁ የሚለውን የሞገደኛውን ጠበቃ ታሪክ ጀምረን እንዳናቋርጠው በአጀማመሩ፣ በቋንቋውና በሌሎችም የሥነፅሁፍ ቅመሞች እያጣፈጠ ይዞን ወደ ታሪኩ ጭልጥ…
አጀማመሩ ብቻ ሳይሆን አጨራረሱም ታሪኩ እንደጣመን አልቆ የሚፈጥርብን ጣዕምና እርካታ እንዲቀጥልና እንድናስታውሰው የሚያደርገን ነው፡፡
ለምሳሌ፣ በገፅ 59 ላይ…
“ጃክዊ ቨርጄዝ ለትዳር አጋሩም ሆነ ለጓደኞቹ እዚህ ነኝም፣ ወደዚህ ሄጃለሁም ሳይል ድንገት ጠፋ!!
አዎን … በቃ … ጠፋ … ጠፋ!
እምጥ ይግባ ስምጥ ሳይታወቅ ቨርጄዝ ጠፋ!” ብሎን ከባለታሪኩ መጥፋት እኩል የአጠፋፍ አገላለፁ እንዲያስገርመን አድርጎ ሲያበቃ፣ ቨርጄዝ ከ8 ዓመታት በኋላ በ1978 ተመልሶ የአወዛጋቢ ጠበቃ ሕይወቱን ኖሮ በ2013 ሲሞት፤ በገፅ 64 ላይ ባሳፈረው አንድ የትዊተር ተጠቃሚ የቨርጄዝን ሕልፈት እንደሰማ በፃፈው፤ “ቨርጄዝ ዳግም ጠፍቷል፡፡ አሁንም ወዴት እንደሄደ ምንም የነገረን ነገር የለም” በሚለው አስገራሚ አባባል አስገርሞን ነው ታሪኩን የሚዘጋው፡፡
ከነኚህ የፅሁፎቹን ተነባቢነትና ሥነፅሁፋዊ ደረጃ እንዲልቅ ካደረጉት የአፃፃፍ ቴክኒኮች በተጨማሪ በትረካዎቹም ውስጥ የሚነሱ ማንኛችንንም እንደ ሰብዓዊ ፍጡር፣ በሕይወታችን ሊያጋጥመን የሚችሉ ስኬትና ሽንፈቶች፣ የፍቅር ገጠመኞች፣ ዝና እና ገንዘብ፣ ሱስና ቤተሰባዊ ሕይወትንና የባለታሪኮቹን የተለያዩ ተሰጥኦዎችና ባህሪያትን፣ ቀልዶችና ገጠመኞቻቸውን ሳይቀር አካትቶ ማቅረቡ፣ የበለጠ ሳቢና ማራኪ አድርጎታል። ይህም አቀራረቡ ታላላቅ ሳይንቲስቶችንና የሳይንስ እሳቤዎችን በቅርባችን ያሉ ቀላል እና የተለመዱ ነገሮች መስለውን እንድናነባቸው አድርጎናል፡፡
በመጣጥፍ መልክ “ዕድል” ብለን ስለምናስበው ነገር፤ ዕለት ተለት እድሜ ልካችንን ስለምናደርጋቸው ምርጫዎቻችንና ማነፃፀሪያዎቻችን፣ ስለ እንስሳት የማሰብ ብቃት፣ በሳይንሳዊ ጥናቶችና ማስረጃዎች እንዲሁም በቀላሉ ፅንሰ-ሃሳቡን እንድንረዳው በሚያደርጉ ምሳሌዎች ተደግፈው የቀረቡት ሥነ ልቦናዊ ትንታኔዎች በእጅጉ አስፈላጊና ለዘመናት የነበሩንን የተሳሳቱ አስተሳሰቦች እንድንለውጥ የሚያደርጉ ወይም ጥያቄዎቻችንን የሚፈቱ ናቸው።
በተለይ “በለስላሳ ታሪክ…” ውስጥ በየቀኑ በመላው ዓለም እንደ ጉድ ስለሚቸበቸቡ የፍጆታ እቃዎችና አምራቾቻቸው ትርፋቸውን ለማናር ስለሚያደርጉት ትንቅንቅ፤ በዚህም ዋንኛ ኢላማ፣ እኛ ሸማቾች መሆናችንን እንድናስተውልና በአዲስ ዓይን እንድናየው ያደርገናል፡፡ “አምልኮተ ሥመጥር” ግሎባላይዜሽንና መገናኛ ብዙሃን፣ በረቀቀ ቴክኖሎጂ እየታገዙ፣ የፈጠሩብንን ተንትኖ፣ በተለይ በእግር ኳስ፣ በሙዚቃና ፊልሞቻቸው፣ባህሎቻቸውንና አስተሳሰቦቻቸውን (ጥሩውንም መጥፎውንም) ከእነ ዝነኞቻቸው እንዴት እንደሚጭኑብን ወለል አድርጎ አሳይቶናል፡፡ የሮናልዶና የአንጀሊና ጆሊ እንዲሁም የሌሎች መሰል የምዕራቡ ዓለም ክዋክብት፣ ከእኛ ጉዳይ ገዝፈው፣ በየአፋችን የሞሉበትን ምክንያት ሹክ ይለናል፡፡
በመጨረሻም ከትረካዎቹ ጋር የቀረቡት የባለታሪኮቹ ወይም የታሪኮቹ ፎቶግራፎችም ለትረካዎቹ የበለጠ ውበትና መስህብ አጎናጽፈዋቸዋል፡፡ ቃላት ብቻ ሳይሆን “ይናገራል ፎቶ” እንዳለው ገጣሚ፣ ግሩም ከጠቀሳቸው ትረካዎቹን ያጣፈጠበት ቅመሞችና አቀራረቦች በተጨማሪ ፎቶዎቹም የራሳቸውን አስተዋፅኦ አበርክተዋል፡፡
እናሳ? ‘እውነትም ግሩም’ ያልኩበትን ምክንያቴን ባልጨርሰውም የተወሰነውን አጋርቻችኋለሁ። እናንተም አንብቡትና ተገረሙ፡፡ በሃሳቤ ካልተስማማችሁም ጣፍ ጣፍ አድርጉ፡፡…
ከአዘጋጁ፡- (ጸሃፊውን በኢ-ሜይል አድራሻው፡-  This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል።)


Read 3808 times