Saturday, 27 January 2018 12:50

“ሀገሬን ሰቀሏት”- ጥልቀቱና ብስለቱ!

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(0 votes)

 የወይን ጠጅ የማይወድ ሰው ስለ ወይን ጣዕም ዳኝነት መስጠት አይችልም፡፡ የትኛውንም ነገር፣ ይልቁንም ግጥምን ለማጣጣምና ስለ መዐዛና ጣዕሙ፣ ስለ ልዕቀቱና ዝቅጠቱ ለመናር መጀመሪያ በፍቅር መውደቅ የግድ ነው- ይላሉ፤ የስነ ግጥም ሊቃውንት፡፡
ይህ ብቻ አይደለም፤ ግጥምን ወድዶ ደጋግሞ ማንበብ፣ ውስጡን ለመፈተሽና ጣዕሙን ለመለካት  በእጅጉ ይጠቅማል፡፡ ሰሞኑን ከእጄ የገባውን “ሀገሬን ሰቀሏት” የግጥም መድበል፣ በጥሞና ለማንበብ ሞክሬያለሁ፡፡ በንባቤም ጥሩ ስሜት የሰጡኝና ያዝናኑኝ፣ የቀለሉብኝና ምነው እንደዚህ ባይሆኑ ያሰኙኝም አሉ፡፡ ግጥሞቹ የተሻለ አተያይ ያላቸውና በምትና ምጣኔያቸው የተሻሉ የሚባሉትንም ይዘዋል፡፡ የጋዜጣው ቦታ በፈቀደልኝ መጠን ለልቤ የቀረቡን በጥቂቱ ለማስቃኘት እሞክራለሁ፡፡ በዚህ ዘመን ብዙዎች ሀሳቡን ብቻ በመመልከት የጥበብ ሥራን “ግጥም ነው” ለማለት ይሞክራሉ፡፡ እኔ ደግሞ የግጥም መለኪያው ግጥምን ከስያሜው ጀምሮ “ግጥም” ያሰኙት መመዘኛዎች ሊሟሉለት ይገባል እላለሁ፡፡ “ግሩም ሀሳብ ብቻውን ግሩም ግጥም ሊባል አይችልም” እንዲሉ፣ የስነ ግጥም ተመራማሪው ፔሪኔ፡፡
“ዕድሜ” የሚለውን ግጥም እንመልከት፡-
ጊዜ እንደጢያራ
ዘመን እንዳሞራ
ይበራል ይከንፋል፣
በህይወቴ ደጃፍ እያፏጨ ያልፋል
በክንፍ ባክናፉ ትቢያ እያቦነነ
ነፍሴን ያሳድፋል
ስጋዬን ያጎድፋል፣
የህይወት ጥድፊያ፣ግራ ያጋባው ገፅ ሰብ ይታያል፡፡ ጊዜን የሚያነፅረው፣ ከአሞራና ከጢያራ ጋር ነው፡፡ ሁለቱም በአየር ላይ በራሪዎች ናቸው። ብርታታቸውም በሰማይ ነው፡፡ ከሰው በላይ፣ ከተራሮች በላይ፣ አንዳንዴም ከደመናም በላይ፡፡--
የዚህ ግጥም፤ ጢያራና አሞራ፣ ፍጥነታቸው ቀላል አይደለም፡፡ ይበርራሉ፤ ይከንፋሉ፡፡ የነርሱ መክነፍ ደግሞ የዚህን ሰው ነፍስና ስጋ ጎድቷል፣ በደጁ እያፏጨ ስለሚያልፍ፣ አቧራውን እየከመረበት ነው፡፡ በዚህ አገባብ አቧራው (ትቢያው) ምናልባት ትዝታ ሊሆን ይችላል፡፡ ትዝታው ደግሞ ሰቀቀን፣ ቁጭት፣ ይሆናል፡፡ የደስታ አይደለምና ከስኬት ጋር ልናስተያየውና ልናነፅረው አንችልም፡፡ ገጣሚ ደበበ ሰይፉ ጊዜ በረርክ በረርክ/ ጊዜ በረርክ በረርክ/ግና ምን አተረፍክ --- እንደሚለው ይመስላል፡፡ ትርፉ አቧራ መቃም ነው፡፡ አቧራው ደግሞ በዘመን ክንፎች ሲበተን፣ የራሱ አሻራ አለው፤ አሻራው ግን አይጣፍጥም፡፡
…ገፀ ሰቡ ለዚህ ምክንያት አለው፡፡ ለምን ከጊዜ ጋር እኩል እንዳልሄደ፣ ዘመን ላይ እርሱ ታሪክ መቆለል ሲገባው፣ በሰናይ ስራው ቀለሙን ሊያሳምር ሲችል ለምን እንዳመለጠው፣ በስንኝ ድርደራ፣ በዜማ ጌጥ ይናገረዋል፡፡ እንዲህ፡-
ተራማጅ ህይወቴ
ወይ ከዘመን ጋራ አብሮ አልበረረ
ወይ ካቧራ ሚያድን ጥበብ አልቀመረ
መንገደኛ ህይወቱ፣ ቀርፋፋ ሆኖበታል፣ ከዘመን አልተጣጣመም፣ ከዘመን አልገጠመም። ይባስ ብሎ ደግሞ፣ ኋላ ቢቀር እንኳ ዘመን ዕዳ እንዳይጭንበት፣ጭራሽ ለአቧራ እንዳይቀብረው መከላከል አልቻለም፡፡ ስለዚህ እንዲህ ሆኗል፡-
ይህ በራሪ ዘመን
ሰርክ በደጃፌ የሚመላለሰው
ክንፍ ያላበቀለ እግረኛ ህይወቴን፣ አፈር አለበሰው፡፡
ልዩነቱና መቀዳደሙን ያመጣው፣ እግረኛና ክንፈኛ መሆን ነው፡፡ እግረኛው ከክንፈኛው ጋር እኩል ለመብረር ክንፍ ማብቀል ነበረበት፡፡ ዘመን ይዟቸው የመጣውን አዳዲስ ነገሮች፣ በትናንትናው አኗኗር ስልትና ጥበብ መቋቋም ባለመቻሉ ተሸንፏል፡፡ ድል ተነስቷል፡፡ እናም፤ “እኔን ያየህ ተቀጣ!” የሚል መልዕክት አለው፡፡ … አትንቀራፈፍ! … “ፈጣን ነው ባቡሩ፣ ፈጣን ነው ባቡሩ፣ ቆራጥ ያልሆናችሁ እንዳትሳፈሩ” እንዳሉት ነው፤የወሎ ኪነት ሰዎች፡፡
ጊዜም እንደጢያራ፣ ይበርራል … አብሮ ያልበረረ፣ አቧራ ይቅማል ነው ነገሩ! የዚህ ግጥም ችግር ሥርዐተ ነጥብ አልባ መሆኑ ነው፡፡ አንድም ቦታ ሥርዐተ ነጥብ የለውም፡፡ ሥርዐተ ነጥብ የሌለው ግጥም ደግሞ ሁሉም ነገሩ የፈረስ ነው። የእምቧይ ካብ! … መልዕክቱ ይዛነፋል፣ ጣዕሙ ይጠፋል፣ … ስንኙ ክፍት ይሁን ዝግ የመለየት ወሰን ተሰብሯል፡፡ ድምፀቱ ዜሮ ነው--- ወዘተ (ይህ የመጽሐፉ አጠቃላይ ዋነኛ ችግርና ድክመት ነው፡፡)
 ግጥሙ “መልአከ ሀገር ፩” በሚል ርዕስ ከተፃፈው ግጥም ጋር በሀሳብ ተመሳሳይነት ያለው ይመስላል፡፡ ልዩነቱ እዚህኛው ግጥም ላይ ለጊዜው መባከን ሰበብ የሚሆኑ፣ ሌሎች ወገኖች መኖራቸው ነው፡፡ ሰበቡ ሌሎች ትከሻ ላይ ይወድቃል፡፡

በታሪክ መቅደስ ላይ “ጨዋ” እያቀረሸ
“ትናንት” የምንለው ላይጸዳ ቆሸሸ

ዕውነት ለመቀበል ህዝብ ዓይኑን ስላሸ
በጎደፈ ትናንት “ዛሬ” ተበላሸ

በባከነ ዛሬ ዕድሜያችን ስንገፋ
“ነገ”ም ክንፍ አውጥቶ ካ‘ይናችን ስር ጠፋ
“ጨዋ” አቀርሽቶ፣ ህዝብ አይኑን አሽቶ (እውነትን ለመቀበል አሻፈረኝ ብሎ) ገፀ-ሰቡና የዚህ ችግር ውጤት ተካፋዮች ሁሉ ዕድሜያቸው ባክኖ፣ ቀን ብቻ ሲቆጥሩ፣ ነገአቸው ክንፍ አውጥቶ በርሯል፡፡ ተስፋ ቆርጠዋል፡፡ ተሸንፈዋል፡፡ አሳዛኝ ነው፡፡ ጊዜና ሰው፣ ትከሻ ለትከሻ ተቃቅፈው ካልተራመዱ፣ለቀጣዩ ትውልድ የሚቀመጡ፣ አዳዲስ ነገሮች ይጨነግፋሉና--- የሚል ይመስላል።
ወንድዬ ዓሊ፤ ስለ ጊዜ እንዲህ ብሎ ነበር፡-
ሳላየው በቅጡ
ቀኑ - መሸምጠጡ
ወሩ - መፈርጠጡ
ሽበት - መፈርቀጡ - ያስቀኛል፡፡
ብዙ ገጣሚያን ያልነኩትን ወይም ነገሬ ያላሉትን አንድ ጉዳይ፣ ደሱ ፍቅርኤል ያነሳው ይመስለኛል፡፡ “እርግብ ጋዜጠኛ” በሚል፡፡ እነሆ፡-
እንደህብስተ መና እንደ‘ለት እንጀራ
አርባ ቀን አርባ ሌት ዘንቦብን መከራ
በሰርገኛ ሀገር
በየጓዳው ታርዶ ሰው እንደፍሪዳ
በመደዳ ታጭዶ ወጣት እንዳ‘ገዳ
ካለቅን በኋላ
ለረዥም ጊዜያት የሰርግ ድንኳን ተጥሎ፣ ሰው እየታረደ፣ ወጣት እንዳገዳ እየታጨደ፣ ጋዜጠኛው ዝም ብሎ ይከርማል፡፡ አላየም፣ አልሰማም፡፡ በኋላ ግን ከአርባ ቀን በኋላ፣ ላንዱ ሰርግ፣ ለሌላው የልቅሶ ድንኳን የነበረው ሲፈርስ፣ ቀጣዩን የጋዜጠኛ ስራና ጥሩንባ እንዲህ እያለ ያሽሟጥጣል፡-
ለአፍታ ለቅፅበት ቀየው ቢረጋጋ
አፈ ሙዝ ተከፍቶ - አፈሰብ ቢዘጋ
ዝምታውን እንጂ እልቂቱን ያላዬ
እርግብ ጋዜጠኛ …
ካራጆች ገበታ እጁ ያልተለዬ
“ሀገር ተረጋግቷል ሰላም ነው” እያለ
ዘንባባ ቀንጥሶ - አፉ ላይ አዋለ
ይህ ግጥም፤ ዝምታና ሰላምን ያልለየውን “ልማታዊ ጋዜጠኛ” ያንጓጥጣል፡፡ ደም ፈሶ፣ እንባ ረክሶ፣ በፍርሃትና በአፈሙዝ ሰው ዝም ስላለ፣ ያንን ዝምታ “ሰላም ነው” ብሎ የራሱን ዘንባባ ባፉ ያንጠለጠለውን ጋዜጠኛ ይተቻል፡፡ ዘንባባው ግን ንፁህ አይደለም፡፡ ደም የተነከረ፣ እርም ያጠወለገው ነው፡፡ ይህን ጋዜጠኛ የገጣሚውን ያህል ብናውቀውም፣ ደግሞ አስታውሶናል፡፡ በተለየና በአዲስ መንገድ ባይገልጠውም፡፡ ትዝብቱን በልቡ አቆይቶ፣ በትኩስነት አቅርቦታል፡፡ ገጣሚ ዳዊት ፀጋዬ፤ከዚህችው ጋር ተመሳሳይ ግጥም አለችው፤ አቀራረባቸው ግን ይለያያል፡፡
 “ሰላም vs ጸጥታ” ይላል - ርዕሱ፡፡
ጩኸትና ረብሻ ስላልታየ
ቤትና ንብረት ስላልጋየ፣
ዓመፅና ሁካታ
ዋይታና ኡኡታ ስለሌለ፣
“ሰላም ነው” ተባለ፡፡
ኧረ ተዉ!
ሕዝቦች በፍርሃት ጸጥ ስላሉ፣
ጸጥታ ሰላም ነው አትበሉ፡፡
ገጣሚው በደብዳቤ መልክ ለፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም የጻፈውን ግጥም በከፊል እንየው፡፡ ርዕሱ፡- “የአማራው ደብዳቤ፣ ለፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም” የሚል ነው፡፡
ይህ የት ነው? ሲባሉ - ኦሮሞ ነው ሲሉ
ይን የት ነው? ሲባሉ - ትግራዋይ ነው ሲሉ
ይህ የት ነው? ሲባሉ - ሺናሻ ነው ሲሉ
ከኔ ላይ ሲደርሱ ቃል አነቀዎት አሉ
ምነካዎ ጋሼ አፍዎ ተሳሰረ
በስሜ ሊጠሩኝ “አማራ ነው” ሊሉኝ ልሳንዎ አፈረ
---እያለ ይቀጥላል፡፡ ምናልባት ፕሮፌሰሩ “አማራ የለም” ያሉበትን አውድ ካለማወቅ፣ ይሁን፣ በቀና ካለማየት ገጣሚው አዝኖባቸዋል፡፡ … ስለዚህም በግጥሙ የመጨረሻ ስንኞች፣ ለፕሮፌሰሩ ምርጫ ይሰጣቸዋል፤  
ለታላቁ መምህር ለፅናት አርአያ
እኔ የርስዎ ልጅ ይህ ነው ጥያቄዬ
ሀ - በመኖሩ አምነው
ከፊትዎ የቆመውን ይህን የርስዎን ልጅ ይጥሩት እንደ ስሙ
ለ “የለም” ካሉ ደግሞ
“የለም” ያሉትን ሰው ልብስ እየገፈፉ ለሌላ ይሸልሙ
መ - ሁሉም መልስ ናቸው
ክቡር ፕሮፌሰር!
ይህ የኔ ጥያቄ ካ“ስር” ይታረማል
ውጤትዎ ደግሞ
እንደምላሽዎ አስር ይደፍናሉ - ወይ ዜሮ ይሆናሉ፡፡
ይህ ግጥም አጠቃላይ ውበቱ ደካማ ቢሆንም፣ ባነሳው ነገር ታሪካዊነትና ትልቅነት፣ መዝዤ  ለማሳያነት አውጥቼዋለሁ፡፡ ከዚህ የተሻለ ጥበብና ሀሳብ ያላቸው ግጥሞች ቢኖሩትም፣ ነገሩ ሁላችንንም ይከነክናልና መፈተሹ አይከፋም። አንዳንዴ የምንናገራቸው ነገሮች፣ በሰዎች ልብ ውለው ሲያድሩ የሚፈጥሩትን  ስሜት ያሳያልና ሙሉ ግጥሙን ብናነብበው ደግ ይመስለኛል፡፡
የሽፋኑና የውስጥ ዲዛይኑ እንዲሁም የፊደሎቹ ፎንት፣ በፍፁም ሳቢ አይደሉም፡፡ የውስጡን ፎንት ያን ያህል መጠቅጠቅና ማሳነስ፣ ጠቀሜታው ምን እንደሆነ ሊገባኝ አልቻለም፡፡ “ሀገሬን ሰቀሏት” የሚለው የመጽሐፉ ርዕስ የሆነው ግጥም፣ ከክርስቶስ የመስቀል ሞት ጋር የተመሳሰለበት መንገድ ማለፊያ ነው፡፡

Read 887 times