Monday, 05 February 2018 00:00

ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ የአሜሪካ ቪዛ ተከለከለ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(3 votes)

   ከወራት በፊት ከእስር የተለቀቀው ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ፤ ቪዛ በመከልከሉ፣ በአሜሪካን ሀገር በክብር እንግድነት በተጋበዘባቸው ጉባኤዎች ላይ መሳተፍ አለመቻሉን ለአዲስ አድማስ አስታወቀ፡፡
በፃፋቸው መንግስትን የሚተቹ ፅሁፎች ምክንያት የተፈረደበትን የ3 ዓመት የእስር ጊዜ አጠናቅቆ ባለፈው ጥቅምት ወር ከዝዋይ ማረሚያ ቤት የተለቀቀው ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ፤ በአሜሪካን ሃገር በኢትዮጵያ ጉዳይ የሚንቀሳቀሱ የ25 ድርጅቶች ትብብር ባዘጋጀው የ3 ቀን ጉባኤ ላይ በክብር እንግድነት ተጋብዞ እንደነበር ለማወቅ ተችሏል፡፡
በተመሳሳይ “ግሎባል አላያንስ” የተባለ ተቋም፣ በ6 የተለያዩ የአሜሪካ ግዛቶች በዲሞክራሲ፣ በፕሬስ ነፃነትና በሰብአዊ መብት ጉዳዮ ባዘጋጀው ውይይት ላይ በአስረጅነትና በክብር እንግድነት እንዲሳተፍም ተጋብዞ ነበር፡፡
ከየካቲት 9 እስከ የካቲት 12 ቀን 2010 ዓ.ም በአሜሪካን ሀገር ሲያትል ከተማ በሚካሄደው የ25 ድርጅቶች ትብብር ጉባኤ ላይ በክብር እንግድነት መጋበዙን ለአዲስ አድማስ የጠቆመው ጋዜጠኛ ተመስገን፤ ከመጋቢት 2 ጀምሮ ደግሞ “የግሎባል አላያንስ” በ6 የተለያዩ ግዛቶች በሰብአዊ መብትና የፕሬስ ነፃነት ጉዳዮች ላይ ከኢትዮጵያውያን ጋር የመመካከሪያ መድረኮች ተዘጋጅተውለት እንደነበር አስታውቋል፡፡
ለእነዚሁ መድረኮች ወደ አሜሪካን ሀገር ለመጓዝ የሚያስችለውን የቪዛ ጉዳይ ለመጨረስ ከትናንት በስቲያ አዲስ አበባ ወደሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ የሄደው ጋዜጠኛ ተመስገን፤ ስለ ግል ሁኔታው ተጠይቆ ምላሽ ቢሰጥም የቪዛ ፍቃድ ሳያገኝ መቅረቱን አስረድቷል፡፡
ባለትዳር ስለመሆኑ እንዲሁም ልጆች እንዳሉት ከኤምባሲው መጠየቁንና የለኝም የሚል ምላሽ መስጠቱን የጠቆመው ጋዜጠኛው፤ ንብረት አለህ ወይ ተብሎ ለቀረበለት ጥያቄም፤ “እኔ ስታገል እንጂ ስነግድ አልኖርኩም” ሲል ምላሽ መስጠቱን ተናግሯል፡፡
ከእስር ከተፈታ በኋላ ከአውሮፓና ከካናዳ ተመሳሳይ ግብዣዎች እንደቀረቡለት ጋዜጠኛ ተመስገን ለአዲስ አድማስ ገልጿል፡፡
በአሁኑ ወቅት በጆሮው ላይ የነበረው ህመም መሻሻል ማሳየቱን፣ ነገር ግን በጀርባው ላይ የተከሰተው ህመም ለውጥ ባለማሳየቱ፣ በማስታገሻ እየታገዘ መሆኑን ጠቁሞ፤ የአሜሪካን ሃገር ጉዞው ቢሳካ ኖሮ የተሻለ ህክምና ለማግኘት አስቦ እንደነበረ ተናግሯል፡፡   
የአሜሪካ ኢምባሲ በጉዳዩ ላይ ለአዲስ አድማስ በኢ-ሜይል በሰጠው ምላሽ “በግለሰቦች የቪዛ ጉዳይ ላይ አስተያየት መስጠት አንችልም፣ ሁሉም የቪዛ አመልካቾች ተመሳሳይ መስፈርቶች ማሟላት ሲችሉ ነው የሚሰጣቸው” የሚል አጭር ምላሽ ሰጥቷል፡፡

Read 7026 times