Print this page
Monday, 05 February 2018 00:00

የኢንተርኔት አገልግሎት በመገደብ ኢትዮጵያ ከዓለም 2ኛ ነች ተባለ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(9 votes)

ኢትዮ ቴሌኮም ሪፖርቱ ተአማኒ አይደለም ብሏል

    ኢትዮጵያ የኢንተርኔት አገልግሎትን በመገደብ ከቻይና ቀጥሎ በአለም 2ኛ ደረጃ መያዟን “ፍሪደም ሃውስ” ያወጣው ሪፖርት ያመለከተ ሲሆን ኢትዮ ቴሌኮም በበኩሉ፤ አገልግሎቱ ተዘግቶ እንደማያውቅ በመግለፅ ሪፖርቱ ተዓማኒ አይደለም ብሏል፡፡
ከትናንት በስቲያ ይፋ የሆነው የፍሪደም ሃውስ የሃገራት የኢንተርኔትና ስልክ መገናኛ መንገዶች አጠቃቀምን ያመለካተ ሪፖርት ላይ ኢስቶኒያ እና አይስላንድ የኢንተርኔት ነፃነት የተረጋገጠባቸው ቀዳሚ ሀገራት መሆናቸው የታወቀ ሲሆን አፋኝ ናቸው ከተባሉት ውስጥ ቻይና፣ ኢትዮጵያና ሶርያ ቀዳሚውን ስፍራ ይዘዋል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት የመብት ጥያቄ በሚነሳባቸው አካባቢዎች በተለይም በኦሮሚያ ክልል የሞባይልና የኢንተርኔት አገልግሎት እንደሚቋረጥ የጠቆመው ሪፖርቱ ማህበራዊ ሚዲያዎችና ፖለቲካዊ ይዘቶች ያላቸው ድረ ገፆችም እንደሚዘጉ አመልክቷል፡፡  በርካቶች በኢንተርኔት አማካይነት በማህበራዊ ገፆች ላይ ሃሳባቸውን በመግለፃቸው እስር እንዳጋጠማቸው የጠቀሰው ሪፖርቱ፤ ሁለት ግለሰቦች ተከሰው እንደተፈረደባቸውም ገልጿል፡፡ ኢትዮጵያውያን የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች ከመድረኩ ለመታቀብና ራሳቸውን ሳንሱር ለማድረግ መገደዳቸውንም ሪፖርቱ ያመለክታል፡፡
የኢንተርኔትና የሞባይል ስልክ አገልግሎት በጣም ውድ ከሆኑባቸው የዓለም ሀገራት ኢትዮጵያ አንዷ መሆናን የጠቆመው ሪፖርቱ፤ የሀገሪቱ የቴሌኮም መሰረተ ልማት ደካማ መሆኑንና  በመንግስት ቁጥጥር ስር እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡
ኢትዮ ቴሌኮም በበኩሉ፤ “ሪፖርቱ ተአማኒነት የለውም” ብሏል፡፡ ኢንተርኔት ተዘግቶ አያውቅም ያለው ኢትዮ ቴሌኮም፤ ፌስቡክና ሌሎች ማህበራዊ ሚዲዎች ተዘግተው የሚያውቁት በብሄራዊ የተማሪዎች ፈተና ወቅት ብቻ ነው በማለት ሪፖርቱ አስተባብሏል፡፡
የሀገሪቱን የቴሌኮም ይዞታንም በብቃት መገምገም የሚችለው ፍሪደም ሃውስ ሳይሆን አለማቀፉ የቴሌኮም ህብረትና አይሲቲ አፍሪካ መሆናቸውን በመጥቀስ ሪፖርቱ ተቀባይነት የለውም ብሏል-ኩባንያው፡፡

Read 5244 times