Monday, 05 February 2018 00:00

የሰሜን ወሎ ከተሞች ተቃውሞና ግጭት በህግ ባለሙያዎች እየተጣራ ነው

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(7 votes)

 “በወልዲያ ወጣቶችና ባለሀብቶች በገፍ ታስረዋል”
         “የታሰሩት በወንጀል የተጠረጠሩት ናቸው”

   የአማራ ክልላዊ መንግስት በወልዲያ፣ መርሳና ቆቦ ለ15 ሰዎች ሞት ምክንያት የሆኑትን ግጭቶች የሚያጣራ የህግ ባለሙያዎችና አመራሮች ቡድን አቋቁሞ የማጣራት ሥራው የተጀመረ ሲሆን ወጣቶችና ባለሀብቶች በገፍ እየታሰሩ ነው ብለዋል - ምንጮች፡፡
የክልሉ መንግስት ኮሚኒኬሽን ኃላፊ አቶ ንጉሡ ጥላሁን በሶስቱ ከተሞች ከጥር 12 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ በተፈጠረው ግጭት የ13 ነዋሪዎችና የ2 የፀጥታ አካላት ህይወት ማለፉን ለአዲስ አድማስ ያረጋገጡ ሲሆን የሰው ህይወት አጥፍተዋል፣ የአካል ጉዳት አድርሰዋል፣ ሀብት ንብረት አውድመዋል፣ አቃጥለዋል ተብለው የተጠረጠሩ ግለሰቦች ከህብረተሰቡ ጋር በመተባበር፣ በህግ ቁጥጥር ስር እየዋሉ ነው ብለዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ሶስቱም ከተሞች ወደ መደበኛ እንቅስቃሴያቸው እየተመለሱ መሆኑን የተናገሩት አቶ ንጉሱ፤ የሀገር አቋራጭ የትራንስፖርት አገልግሎትና የከተማ ውስጥ ትራንስፖርት አገልግሎትም ከረቡዕ አንስቶ መጀመራቸውን አስታውቀዋል፡፡
በአጠቃላይ ነዋሪዎች የሚያነሷቸው ጥያቄዎች ምንነት፣ የግጭቱ መነሻ ምክንያት፣ የፀጥታ ኃይሉ ምን አይነት እርምጃ እንደወሰደ እና ሌሎች ዝርዝር ሁኔታዎችን እንዲያጠና የተቋቋመው የህግ ባለሙያዎችና አመራሮች ቡድን፤ በከተሞቹ ምርመራ እያደረገ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ንጉሱ፤ ከምርመራ ውጤቱ በመነሳት የክልሉ መንግስት በቀጣይ የእርምት እርምጃዎችንና የወደፊት አቅጣጫዎችን ያስቀምጣል ብለዋል፡፡
በጥምቀት ማግስት በተከበረው የቅዱስ ሚካኤል በዓል ላይ ከተፈጠረ ተቃውሞ ጋር ተያይዞ 7 ሰዎች በመገደላቸው ከፍተኛ ውጥረት ነግሶባት በሰነበተችው ወልድያ ከተማ ከሰኞ ጥር 21 እስከ ረቡዕ ጥር 23 ቀን 2010 ዓ.ም የቆየ የቤት ውስጥ መቀመጥ አድማ መደረጉን የገለፁት ምንጮች በበኩላቸው፤ በወቅቱም የፀጥታ ኃይሎች በርካታ ወጣቶችንና ባለሀብቶችን ማሰራቸውን ተናግረዋል።
እስከ ትናንት ድረስ ወጣቶች በስም ዝርዝር እየተለዩ፣ በከተማዋ መግቢያና መውጫ በሚደረግ የኬላ ፍተሻ እንዲሁም ቤት ለቤት በመዞር እየተያዙ መታሰራቸውን የጠቆሙት ምንጮች፤ ባለሀብቶችም ለተቃውሞና ግጭቱ ድጋፍ አድርጋችኋል በሚል በሼህ ሁሴን አሊ አላሙዲ ስታዲዬም ከታሰሩ በኋላ ከሐሙስ ጀምሮ ወደ መደበኛ እስር ቤቶች መዘዋወራቸውን ገልፀዋል፡፡
በወልዲያ ከሐሙስ ጀምሮ መደበኛ የትራንስፖርት አገልግሎት መጀመሩን፣ የንግድ መደብሮችም ተከፍተው ደንበኞችን እያስተናገዱ መሆኑንና ከተማዋ ወደ ቀድሞ እንቅስቃሴዋ እየተመለሰች መሆኑን ምንጮች ጠቁመዋል፡፡
በተመሳሳይ የ7 ሰዎች ህይወት ባለፈባት ቆቦ ከተማም መደበኛ እንቅስቃሴ መጀመሩንና የብአዴን ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አለምነው መኮንንም ከከተማዋ ነዋሪዎች ጋር መወያየታቸውን የተናገሩት ምንጮች ከ40 በላይ የታሰሩ ወጣቶችም መፈታታቸውን ገልፀዋል፡፡
ከአቶ አለምነው ጋር በተደረገው ውይይትም የከተማዋ ነዋሪዎች በዋናነት “መከላከያ ከከተማዋ ለቆ ይውጣ”፤ “የታሰሩ ወጣቶች በአስቸኳይ ይፈቱ”፣ “ከቀበሌ እስከ ወረዳ ያሉ የመንግስት አስተዳደሮች በሙሉ ከስልጣን ተነስተው በሌሎች ይተኩ” እንዲሁም “በከተማዋ ለሞቱ ወጣቶች መንግስት ኃላፊነቱን ይውሰድ” የሚሉ ጥያቄዎች መቅረባቸውን የጠቀሱት ምንጮች  አቶ አለምነው በጥያቄዎቹ መስማማታቸውን ገልፀው፤ ማስተካከያ እንደሚደረግ ቃል መግባታቸውን አመልክተዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት የፀጥታ ኃይሎች ከከተማዋ መውጣታቸውን ምንጮች ጨምረው ገልፀዋል። በመርሳ ከተማም በተመሳሳይ ወጣቶች እየታሰሩ ቢሆንም ከተማዋ ወደ መደበኛው እንቅስቃሴ መመለሷ ታውቋል።  በሶስቱ የሰሜን ወሎ ከተሞች ወቅታዊ ሁኔታ ላይ አዲስ አድማስ ያነጋገራቸው የአማራ ክልላዊ መንግስት የኮሚኒኬሽን ኃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን በበኩላቸው፤ ወጣቶችና ባለሀብቶች እየታሰሩ ነው መባሉን በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያ፤ ወንጀል ፈፅመዋል ተብለው የተጠረጠሩ በቁጥጥር ስር እየዋሉ መሆኑን አረጋግጠው፣ ተጠርጣሪዎች የሚከሰሱት ማስረጃ እስከቀረበባቸው ድረስ ብቻ ነው ብለዋል፡፡ ቤተሰቦች ታሳሪዎች የት እንዳሉ አውቀው እንዲጠይቋቸው እየተደረገ መሆኑንም ኃላፊው አክለው ገልፀዋል፡፡  

Read 5212 times