Print this page
Monday, 05 February 2018 00:00

አጓጉል ትውልድ ያባቱን መቃብር ይንድ

Written by 
Rate this item
(6 votes)

ከዕለታት አንድ ቀን አንድ አዋቂና አንድ አላዋቂ መንገድ ላይ ይገናኛሉ፡፡
አዋቂ፡- እንደምን ውለሃል ወዳጄ
አላዋቂ፡- እግዚሃር ይመስገን እንዴት ከርመሃል?
አዋቂ፡- እኔ ደህና ከርሜያለሁ፡፡
አላዋቂ፡- ይሄ ምሁር ነኝ ባይ ጉረኛ ሁሉ ሰፈር ውስጥ አላስቀምጥ አለን እንጂ እኛማ ደህና ነን፡፡
አዋቂ፡- እንዴት ነው ያስቸገረው?
አላዋቂ፡- አሃ አንተም ጀመርከኝ እንዴ?
አዋቂ፡- የማላውቀውን እንድታሳውቀኝ ብዬ እኮ ነው፡፡
አላዋቂ፡- ደህና፡፡ አሁን ወዴት እየሄድክ ነው?
አዋቂ፡- ወደ ገበያ
አላዋቂ፡- እንግዲያውስ አብረን እንሂድ- ግን አዋቂ ነኝ ብለህ እንዳትፈላሰፍብኝ
አዋቂ፡- እኔ እንደውም ካልጠየቅኸኝ አላስቸግርህም፡፡
ተስማምተው መንገዳቸውን ይቀጥላሉ፡፡
ጥቂት እንደሄዱ አንድ አጥር ላይ ያለ አውራ ዶሮ አጠገብ ይደርሳሉ፡፡ አውራ ዶሮው ይጮሃል። ይሄኔ አላዋቂው፤
“ይሄ አውራ ዶሮ እዚህ ሲጮህ፣ የዚህ ዓይነት ሌላ አውራ ዶሮ መንግሥተ-ሰማይ ውስጥ ይጮሃል” አለ፡፡
አዋቂው፡- መንግሥተ-ሰማይ ንፁህ ነው፡፡ እንደ ዶሮ ያለ ባለ ኩስ እዚያ ሊኖር አይችልም፡፡
አላዋቂው፡- አይ አውራ ዶሮ‘ኮ ሲጮህ፤ አፉን ወደ ገነት ቂጡን ወደ ሲዖል አድርጎ ነው፡፡
አዋቂው፡- ሲዖል‘ኮ የሰውን እርጥብ ሥጋ እንኳን ያነዳል፡፡ የዶሮ ላባ ካገኘማ ወዲያው ነው አቀጣጥሎ የሚያጋየው!
አላዋቂው መሟገቻ ነጥብ አጣ፡፡
አላዋቂው፡- ኦዎ! እኔ ምንቸገረኝ- ያባቴ ዶሮ አደለ ቢያንበገብገው!
*    *    *
የአንድ አገር አንዱ መልካም ገፅታዋ አዋቂዎቿን መንከባከቧና ከእነሱም በቂ ምክር መቀበሏ ነው። ያልተማረ አላዋቂ እየገነነ፣ የተማረ አዋቂ እየኮሰሰ በሄደ ቁጥር የሀገር እድገት ቁልቁል ይሆናል፡፡ ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሤ የፊደል ሠራዊት እስከ ደርግ የመሀይምነትን ጥቁር መጋረጃ መቅደጃ መሠረት ትምህርት ድረስ የተለፋው አላዋቂነትን ለመቀነስ ነው፡፡ ብዙ ተጉዘንበታል፡፡ ገና ብዙ ይቀረናል፡፡ ዛሬም ሙሉ ትኩረት ሰጥቶ ጥረቱን መቀጠል ተገቢ ነው፡፡ አላዋቂነት በእርግጥ የመማር ያለመማር ጉዳይ ብቻ አይደለም፡፡ ሳይማር በቂ ብስለት ያለው ሰው ብዙ አለ፡፡ ተምሮ በዘር፣ በሃይማኖትና በቀለም አባዜ ውስጥ የሚዳክር አያሌ ሰው አለ፡፡ ተምሮ እንዳልተማረ እያደር የሚደነቁር፣ እንደ ሽንቁር እንሥራ የሚያፈስ በርካታ ምሁር አለ፡፡ አስተዳደግ፣ አካባቢ ተፅዕኖ፣ የአቻ ዕድሜ ግፊት፣ የማህበረሰቡ የዕድገት ደረጃ፣ የግብረገብነት ጥልቀት ወዘተ … የማንነቱ መቀረጫ ሊሆኑ ይችላሉ። የሃገራችን የዕድገት አካሄድ በማንነት መለኪያ አንፃር በተለይ አሥጊ አካሄድ ላይ ያለ ይመስላል። የሚያባብስ እንጂ የሚያሻሽል በሌለበት ሁኔታ ከገባንበት እዘቅት የመውጣት ዕድል እየጠበበ እየመጣ ነው፡፡
ይህንን ጠንቅቆ የተረዳና የራሱን ጠጠር ጥሎ ለመሻሻል አስተዋፅዖ የሚያደርግ ማንኛውም ዜጋ፤ የለውጡ ሞተር አካል ይሆናል፡፡ በተለይ ወጣቱ ዐይኑን እንዲከፍት ይጠበቅበታል፡፡ ምንም ያህል ጊዜ ቢወስድ ከግዴለሽነትና ከተመልካችነት ወጥቶ፣ ወደ ተዋናይነት መሸጋገሩ አይቀሬ ነው! በየትኛውም ዘመን የነበረው ወጣት፤ ቀስ በቀስ ነው ለአገር አሳቢ እየሆነ የመጣው፡፡ ግብአቶቹ አያሌ ናቸው፡፡
በንጉሡ ጊዜ የነበረው ወጣት ወደ አብዮቱ የለውጥ ሂደት እስኪገባ ድረስ የሃያና የሰላሳ ዓመት ውጣ ውረድ ውስጥ አልፏል፡፡ አብዮተኛ ሆኖ የተፈጠረ ወጣት ኖሮ አያውቅም፡፡ እንዲያውም የ1966 ዓመተ ምህረቱ አብዮት ከመፈንዳቱ ዋዜማ “የጆሊ - ጃኪዝም” ዘመን ነበር፡፡ ቤል ቦተም (ቦላሌ-ከታቹ በጣም ሰፊ)፣ ሰፊ ቀበቶ፣ አፍሮ ፀጉር፣ ህልሙም ውኑም ሴት ጠበሳ፤ ጭሳ ጭሱን በየጥጉ ያከናውን የነበረ ትውልድ ማቆጥቆ የጀመረበት ሰዓት ነበር፡፡ እንደ ዛሬው “ሀንግ” ባይሆንም፣ የግሩፕ ፀብ ጣራ ነክቶ ነበር፡፡ ቀስ በቀስ ያ ሁሉ የተዛነፈ ጉዳይ ላይ የነበረውን ወጣት አብዮት ዋጠውና የለውጡ ሞተር ወደ መሆን ተሸጋገረ፡፡ መረሳት የሌለበት ከሞላ ጎደል የጥቂት የነቁ ወጣቶች መንቀሳቀስ ብቻ እንደነበር ነው፡፡ Change is an incremental process ለውጥ አዳጊ ሂደት ነው እንደ ማለት ነው፡፡ የሁሉም ወጣት ዐይን በአንድ ጊዜ አይከፈትም፡፡ ለውጥን እንደ ድቅድቅ ጨለማ ማየት ትልቅ እርግማን ነው፡፡ ትውልድ ቸኩሎ ለጥቅም ሲቆም ብዙ አገራዊ ጉዳዮችን ሊዘነጋ መቻሉ አይታበልም፡፡ ታላላቆች ታናናሾችን ለመግራት መዘጋጀት አለባቸው፡፡ መናናቁ የትም አያደርስም። ምንም ያልተማሩ ወላጆች፤ ልጆቻቸውን ለፍሬና ለወግ ማዕረግ ያበቁት ከእኔ የተሻለ ልጅ ላፍራ ብለው ነው! የጊዜ ገደብ አመለካከታችን መቀየር አለበት - የአንድ ጀንበር ድል የለምና፡፡ የረዥም ጊዜ ዕቅድ፣ ከትዕግሥትና ከሆደ - ሰፊነት ጋር አስፈላጊ ብቻ ሳይሆን ግዴታም ነው! ለዚህ ደግሞ ቁልፉ ዲሲፕሊን ነው፡፡ ያለ ዲስፕሊን እንኳን ዓመታት ሳምንታት መዝለቅ አይቻልም፡፡ ፕሮፌሰር ዐቢይ ፎርድ፤ የሀገራችን የጋዜጣ ሥርዓት ደረጃውን የጠበቀ እንዲሆን ምን ያህል ጊዜ ይፈጃል? ተብለው ተጠይቀው - “40 ዓመት ይበቃል” ማለታቸውን አንርሳ፡፡ ሩቅ የሚያይ አዕምሮና የቅርቡን በአግባቡ የሚራመድ እግር ያስፈልጋል፡፡ የየዕለቷን ድል በማጠራቀም ከጉራ በፀዳ ንቃት መንቀሳቀስ ያሻል። ይህ ሁሉ የዲሲፕሊኑ አካል ነው፡፡ የእስከዛሬው መንገድ “ሲሮጡ የታጠቁት ሲሮጡ ይፈታል” ነበር። ይህ እንዳይደገም ሁሉም የቀደምት ተዋንያን “በእኛ ይብቃ” ይበሉ፡፡ ወይም በዘመነኛው አባባል “አፉ በሉን” ይበሉ፡፡ ስህተትን አለማረም ለስህተት ደረጃ ማውጫ ካልሆነ በቀር ለማንም አይበጅም። ለተረካቢው ትውልድ የምንሰጠው የጠራ ታሪክ አይኖርም፡፡ ተረካቢውም ትውልድ ታሪክን መርማሪ፣ አመክንዮ የሚገባው፣ ከነችግሩ የነገን ብሩህነት የሚያይ፣ ትችትና ማጥላላትን ዋናዬ የማይል፣ ትምህርትን መሬት አውርዶ የት እደርስበታለሁ የሚል፣ እኔ ካልተለወጥኩ አገር አትለወጥም ብሎ የሚያስብ፣ ግብረገብነትን የዕለት ተዕለት ህይወቱ ለማድረግ የሚጣጣር፣ ከፖለቲከኝነት ይልቅ ሰው ለመሆን የሚተጋ፣ የሚማረው ከሁሉም በፊት ለራሱ መሆኑን የሚያውቅ፣ ትውልድ እንዲሆን ከመመኘት አልፈን የምናግዘው፣ የምናበረታታው፣ የምናማክረው ዜጎች መኖር አለብን፡፡ ወጣቱም ከማፈንገጥ ይልቅ አዳማጭ፣ ከአጉራ - ዘለልነት ይልቅ አደብ መግዛትን የሚመርጥ፣ ከሞቅ ሞቅ ይልቅ ላቅ ጠለቅ ማለትን የሚወድ መሆን ይኖርበታል፡፡ አለበለዚያ “አጓጉል ትውልድ ያባቱን መቃብር ይንድ” ይሆናል፡፡ ከዚያ ይሰውረን!!      

Read 4926 times
Administrator

Latest from Administrator