Monday, 05 February 2018 00:00

አቶ አመሃ፤ በአገሪቱ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችና በጸረ ሽብር አዋጁ ዙሪያ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

  (በዓለማቀፍ ማንጸሪያ ሰፊ ትንተና ሰጥተዋል)

  · በዓለማቀፍ ደረጃ ሊያስጠይቁ የሚችሉ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች እየተፈፀሙ ነው
  · ከየትኛውም በላይ የተጣሰው፣ ሃሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት ነው
  · ህዝቡ ሃሳቡን እንዳይገልጽ የተደረገበት ሁኔታ ዛሬ ዋጋ እያስከፈለ ነው
  · የሽብር ወንጀል፣ የስርቆት ወንጀል ያህል ተቃልሎ እንዲታይ ተደርጓል
   
   አቶ አመሃ መኮንን በተለይ በሽብር ጉዳይ የተከሰሱ ጋዜጠኞችን፣ ፖለቲከኞችንና ግለሰቦችን በህግ በማማከርና በጥብቅና በማገልገል ይታወቃሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት በ24 መዝገቦች የተከሰሱ አንድ መቶ ያህል ግለሰቦችን ጉዳይ በፍ/ቤት እየተከራከሩ ይገኛሉ፡፡ ለአብዛኞቹ ተከሳሾች ነፃ የህግ ድጋፍ የሚያደርጉት አቶ አመሃ፤ በሰብአዊ መብት ተከራካሪነታቸውም ይታወቃሉ፡፡ የሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ (ሰመጉ) አመራርም ናቸው፡፡ የህግ ባለሙያው አቶ አመሃ መኮንን፣ በሀገሪቱ የሰብአዊ መብት ይዞታ፣ በፀረ ሽብር አዋጁና በተከሳሾች፣ እንዲሁም በይቅርታና በምህረት ከእስር በሚፈቱ ፖለቲከኞች ጉዳይ ዙሪያ ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ጋር በቢሮአቸው ተከታዩን ቃለ ምልልስ አድርገዋል፡፡ እነሆ፡-

     የሀገሪቱን ወቅታዊ የሰብአዊ መብት ይዞታዎች በተመለከተ ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ተቋማት በእጅጉ እያብጠለጠሉት ይገኛሉ፡፡ የእርስዎ አስተያየት ምንድን ነው? ከተቋማቱ ጋር ይስማማሉ?
የሰብአዊ መብት ጉዳይ ዘርፈ ብዙ ነው። የኢትዮጵያ ህገ መንግስት ብዙ አከራካሪ ጉዳዮች ቢኖሩትም ለዓለማቀፍ የሰብአዊ መብት ድንጋጌዎች እውቅና ከመስጠት አንፃር፣ መግባባት የተደረሰበትና አብዛኛውን የሰብአዊ መብት ያካተተ ነው፡፡ የህገ መንግስቱ አንድ ሶስተኛ ክፍልም የሰብአዊ መብት ጉዳይ ነው የሚደነግገው፡፡ መንግስት የሰብአዊ መብት ኮሚሽን አቋቁሟል፡፡ ይሄ ኮሚሽን ምን ያህል ድርሻውን ተወጥቷል የሚለው አከራካሪ ቢሆንም፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የምናያቸው እንቅስቃሴዎች አሉ፡፡ በሌላ በኩል መንግስት፣ የሰብአዊ መብት መርሃ ግብር ዘርግቶ ለመተግበር እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑን ይገልፃል፡፡ ከዚህ ውጭ  መሬት ላይ ያለውን ሃቅ ስንመለከት ግን በርካታ ችግር እንዳለ እንረዳለን፡፡  
ለምሳሌ አሁን በሀገሪቱ ለተፈጠረው ቀውስና መንግስት ራሱ ኃላፊነቱን ለወሰደበት ችግር ዋነኛው መንስኤ፣ ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብትን ተግባራዊ ማድረግ አለመቻሉ ነው፡፡ ነፃ ሚዲያዎች አለመስፋፋታቸው፣ በጅምር የነበሩ ጋዜጦችም ከገበያ እንዲወጡና ጋዜጠኞች እንዲሰደዱ መደረጉ የሀሳብ መንሸራሸርን ገድቧል ማለት ይቻላል። በእንዲህ መልኩ ህዝቡ ሃሳቡን እንዳይገልፅ የተደረገበት ሁኔታ ነው፣ ዛሬ ዋጋ እያስከፈለ ያለው፡፡
በሌላ በኩል በፀረ ሽብር ህጉ፣ በርካቶች “ከእገሌ ጋር ተፃፃፍክ፤ ይሄን ፃፍክ” እየተባሉ መከሰሳቸው ለአፈናው ማሳያ ነው፡፡ በዚህ ረገድ የዞን ዘጠኝ ጦማሪያንን ተሞክሮ ማየት ይቻላል፡፡ ዞን ዘጠኝ ጦማሪያን፣ በኢንተርኔት መንግስትን የሚተቹ ፅሁፎችን በማውጣታቸው ነው፣ በሽብርተኝነት የተከሰሱት፡፡ ይሄ ለሌላውም አሸማቃቂ ነበር። በኢትዮጵያ ውስጥ መንግስት ሃሳብን ከመግለፅ መብት ጋር በተያያዘ ዓለማቀፍ ግዴታውን አልተወጣም። ከየትኛውም በላይ የተጣሰው መብት፣ሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት ነው፡፡
ሌላው ለሰብአዊ መብት ይዞታዎች መዳከም ምክንያቱ በሰብአዊ መብት ጉዳይ ላይ የሚሰሩት ተቋማት እንዲዳከሙ መደረጉ ነው፡፡ ሰብአዊ መብት ላይ የሚሰሩ ድርጅቶች፣ከ10 በመቶ በላይ ገቢ ከውጭ እንዳያገኙ መደንገጉ ዋነኛ ተግዳሮት ነው። ለምሳሌ የሰብአዊ መብቶች ጉባኤና የኢትዮጵያ የህግ ባለሙያ ሴቶች ማህበር፣ ከውጭ አገር ያገኙት 11 ሚሊዮን ዶላር ያህል የገንዘብ ድጋፍ እንዲታገድ ተደርጓል፡፡ በዚህ ምክንያት አብዛኞቹ ተዳክመው ኃላፊነታቸውን መወጣት ባለመቻላቸው፣ የራሱን አሉታዊ አስተዋፅኦ አበርክቷል፡፡
በአገሪቱ የሚፈጸሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች እንዴት ይገለጻሉ?
መንግስት ህዝቡ የሚያነሳቸውን የተለያዩ ጥያቄዎች ያስተናገደበት መንገድ አንዱ ነው፡፡ ጥያቄዎችን አንግበው ጎዳና የወጡ ዜጎች፣ የኃይል እርምጃ ሲወሰድባቸው አሊያም ወደ እስር ቤት ሲላኩ አይተናል፡፡ ምናልባት የዓለማቀፉን ፍ/ቤት ያቋቋመው “የሮም ስምምነት” ተብሎ የሚታወቀው ድንጋጌ፣ በሰብአዊነት ላይ የሚፈፀም ወንጀል ብሎ ካስቀመጣቸው ጉዳዮች ጋር የሚስተካከል የሰብአዊ መብት ጥሰት እያደረሰ ነው የሚል እምነት አለኝ። ከሰብአዊ መብት አንፃር በሀገሪቱ የሚፈፀመው ጥሰት አስከፊ ደረጃ ደርሷል ማለት ይቻላል። መንግስትም ይሄን የተረዳ ይመስላል፣ እርምጃ ለመውሰድ ቃል ገብቷል፡፡ ጉዳዩ በዚህ ከቀጠለ ግን አገሪቷን አደጋ ላይ የሚጥል ነው የሚሆነው፡፡
ባለፉት 3 ዓመታት ከተቃውሞና ግጭቶች ጋር በተገናኘ በርካታ ዜጎች መሞታቸው ይታወቃል። በቅርቡ ጠ/ሚኒስትሩ ደግሞ “ጭፍጨፋ” ጭምር መፈፀሙን በኢቢሲ አስታውቀዋል፡፡ ይህ ከዓለማቀፍ ህግ አንፃር እንዴት ይታያል?
በመንግስትም እንደተገለፀው፣ ከፍተኛ ግድያና እልቂት ለመፈፀሙ ምንም ጥርጥር የለውም። በሺዎች የሚቆጠሩ የጥይት ሰለባ ሆነዋል፡፡ ይሄ ድርጊት በአማራና በኦሮሚያ ቁጥሩ የበዛ ሊሆን ይችላል ግን በደቡብ፣ በጋምቤላና በሌሎች አካባቢዎችም በዚህ መንገድ ሰዎች ሞተዋል፡፡ አብዛኞቹ ግድያዎች የተፈፀሙትም በመንግስት የፀጥታ ኃይሎች ነው፡፡ ግድያው ደግሞ ያልለየ ነው፡፡ ከተመጣጣኝ ኃይል ጋር በተደረገ ፍልሚያ የተፈፀመ ግድያ አይደለም፡፡ ህፃናት ተማሪዎች፣ ገበያ ላይ ያለች ሴት፣ እርሻ ላይ ያለ ገበሬ፣ መምህር -- ወዘተ ሞተዋል፡፡ ግድያው ያልለየ (Indiscriminate) ነው። በሀገሪቱ የተፈፀመው የህይወት መጥፋት ከዓለማቀፍ ህግ አንፃር ምን ደረጃ ላይ ደርሷል የሚለው፣ራሱን የቻለ ምርመራ የሚጠይቅ ነው፡፡ የዘር ማጥፋት ተፈፅሟል የሚሉ አሉ፤ይሄ መጣራት ያለበት ነው፡፡ በሰብአዊነት ላይ የተፈፀመ ጥፋትም አለ፤ ይሄ በዓለማቀፍ ደረጃ የራሱ ትርጓሜዎች አሉት፡፡ ከሮም ስምምነት አንፃር በሀገሪቱ የተፈፀመው የሰብዓዊ መብት ጥሰት የተሟላ ማስረጃ ያለው ነው የሚል አቋም አለኝ፡፡ የተፈፀመው የጥፋት መጠንም፣ የሮም ስምምነትን የሚያሟላ ነው። ሶስተኛው የሮም ስምምነት መስፈርት፣ ድርጊቱ ሆን ተብሎ የተፈፀመ የመሆኑ ጉዳይ ነው፡፡ በዚህ በኩል ምርመራ ማድረግ ይጠይቃል፡፡ ዋናው ቁም ነገር ግን፣ ግድያው ከፍተኛ የሚባል መሆኑ አያከራክርም፡፡ ግን በዓለማቀፍ ህግ ስር ይወድቃል፣ አይወድቅም የሚለው በገለልተኛ አካል መመርመር አለበት፡፡ ድምዳሜ ላይ መድረስ የሚቻለው በገለልተኛ አካል ሲመረመር ነው። በገለልተኛ አካል ለመመርመር ደግሞ በቂ ምክንያት አለ። ይሄ ጉዳይ በቸልታ የሚታይ መሆን የለበትም።
አሁን ላይ እየተለመደ ያለው፣ በአንድ አካባቢ ተቃውሞ ይደረጋል፤ ሰዎች ይገደላሉ፡፡ በነጋታው ሌላ ቦታ ሰዎች ይገደላሉ፡፡ ይሄን እየቆጠርን ነው ያለነው። ይሄ ጉዳይ ከፍተኛ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ነው፡፡ መንግስት ለዚህ ጥፋት ተጠያቂ የሆኑ አካላትን ተጠያቂ እያደረገ ከወዲሁ ካልሄደ፣ ነገ ራሱ መንግስት እንደ መንግስት ተጠያቂ ይሆናል፡፡
የሰብአዊ መብት ኮሚሽኑ ግጭት በተከሰተባቸው አካባቢዎች ምርመራ ካደረገ በኋላ በሚያቀርባቸው ሪፖርቶች ላይ ተጠያቂ መሆን አለባቸው ያላቸውን አካላት በዝርዝር ማስታወቁ ይታወሳል፡፡ እስካሁን በፍ/ቤት ተጠያቂ የሆነ አካል መኖሩን ያውቃሉ?
ኮሚሽኑ የተፈፀሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን በድፍረት የማውጣት እንቅስቃሴ አሳይቷል። የመብት ጥሰት የፈፀሙ፣ ይጠየቁ ሲልም ተደምጧል፡፡ እስካሁን ድረስ ምናልባት ኮሚሽኑ የራሱ መከታተያ መንገድ ሊኖረው ይችላል፤ ነገር ግን በእኔ በኩል የመንግስት የፀጥታ ኃይሎች ወይም ሌሎች የሰብአዊ መብት ጥሰት ፈፅመዋል የተባሉ ወገኖች፣ በፍ/ቤት ሲጠየቁ አጋጥሞኝ አያውቅም፡፡
የፀረ ሽብር አዋጁ፣ለሰብአዊ መብት ጥሰት ሰበብ ሆኗል በሚል የሚተቹ ወገኖች አሉ፡፡ እርስዎ ይህን ትችት እንዴት ያዩታል?
ስለ ሽብር ወንጀል በዓለማቀፍ ሁኔታ ስናይ፣ ትርጉሙ በኛ ሀገር ካለው የተለየ ነው፡፡ ሽብርተኝነት ከዓለማቀፍ ትርጓሜውና ከታሪካዊ አመጣጡ አንፃር ስንመለከተው፣ እጅግ ከባድ ወንጀል ነው፡፡ ተራ ወንጀል አይደለም፡፡ እጅግ ጥንቃቄ የሚጠይቁ መመዘኛዎች ያሉትም ነው፡፡ አንደኛው፤ የሰው ህይወትን በጅምላ አደጋ ላይ የጣለ ወይም ለመጣል የታቀደ መሆን አለበት። ንብረት በተመለከተም፣ በመንግስትና በህዝብ ንብረት ላይ አደጋ ያደረሰ ወይም ለማድረስ የተቃጣ መሆኑ መረጋገጥ አለበት። በንፁሃን ላይ ያነጣጠረ፣ መንግስትን የማንበርከክ እንቅስቃሴ መሆን ይኖርበታል። ነገር ግን ወደኛ ሀገር ስንመጣ፣ የሽብር ወንጀልን የቀለለ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ተራ ወንጀል በሽብር ነው እያስከሰሰ ያለው፡፡ ይሄ ነገሩን በህብረተሰቡ ዘንድ ቀላል እንዲሆንና ከመንግስት ጋር እንዳይተባበር ያደርገዋል፡፡
እኔ ባለኝ መረጃ የፀረ ሽብር አዋጁን መነሻ አድርገው የሚቀርቡ ክሶች፣ከዓለማቀፍ መመዘኛዎች አንፃር ከ2 በመቶ አያልፍም፡፡ ቀሪው በወንጀል ህግ ሊታይ ይገባው የነበረ ነው፡፡ በአብዛኞቹ “በኢንተርኔት ህዝብን ለማነሳሳት ፅፋችኋል”፣ “በሀገሪቱ የሚፈፀሙ ተቃውሞዎችን ለሌሎች አካላት በመረጃ መልክ አስተላልፋችኋል” እንዲሁም “በሽብርተኝነት ከተፈረጁት ኦነግ እና ግንቦት 7 ጋር ተገናኝታችኋል፣ በስልክና በኢ-ሜይል ከአባላቱ ጋር ተነጋግራችኋል፣ ተልዕኮ ተቀብላችኋል” የሚሉ ናቸው፡፡ ይሄ ከዓለማቀፍ የሽብር ትርጓሜ አንፃር ብዙ የሚቀረው ነው፤ ምናልባት በወንጀል ጉዳይ ሊታይ ይችል ይሆናል፡፡ በዓለማቀፍ ደረጃ ለሽብር ከተሰጠው ክብደት አንፃር፣ ብዙዎቹ በኛ ሀገር የሚቀርቡ ክሶች የሚመጣጠኑ አይደሉም፡፡ የሽብር ወንጀል፣ የስርቆት ወንጀል ያህል ተቃልሎ እየታየ ነው፡፡ መንግስት በዚህ በኩል ጉዳዩን የተረዳው አይመስለኝም፡፡ የሽብር ወንጀልን ህብረተሰቡ በሚገባው መጠን አክብዶ እንዳያየው፣ የሚቀርቡ ክሶች መንገድ ከፍተዋል፡፡
አስታውሳለሁ፤ አዋጁ እንደወጣ አካባቢ፣ ብዙዎቹ የተከሰሱ ሰዎች፣ ከባድ ቅጣት ነው የተጣለባቸው፤ በኋላ ላይ ግን ጠንካራ ክርክሮች እየተካሄዱ፣ ፍርዶች  እየቀነሱ እንዲሁም የሽብር ክሶች ወደ ወንጀል እየተቀየሩ የመጡበት ሁኔታ አለ፡፡ አሁንም ቢሆን መንግስት የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት ከፈለገ፣ ይሄን አዋጅ በድጋሚ፣ በጥልቀት መመርመር አለበት፡፡ ይሄ አዋጅ ከተፈተሸና በተለይ ለክሶቹ መነሻ የሆኑ በሽብር የተፈረጁ ድርጅቶች ላይ መንግስት የያዘውን አቋም ማለሳለስ ካልቻለ፣ ዛሬ በርካቶች ክሳቸው ተቋርጦ ቢፈቱም፣ ነገ በዚያው ልክ ሌሎች ላለመግባታቸው ዋስትና የለም፡፡ ይሄ በቅጡ ሊጤን ይገባዋል፡፡
በፍ/ቤት በሚደረገው የአቃቤ ህግና የተከሳሶች የማስረጃ ክርክር፣ በተለይ በአቃቤ ህግ በኩል ምን ያህል ውጤታማ ማስረጃዎች ይቀርባሉ?
አዋጁ ከማስረጃ መርህ አንፃር አዳዲስ ነገሮችን ይዞ የመጣ ነው፡፡ ከተከሳሽ መብቶች አንፃር ጫና የሚያደርጉ ድንጋጌዎችን ይዟል፡፡ ለምሳሌ ለደህንነት መስሪያ ቤቱ፣ በፍትህ ስርአት ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ሃላፊነት እንዲኖረው የፈቀደው ይህ አዋጅ ነው፡፡ የደህንነት መስሪያ ቤቱ፣በፍ/ቤት ፍቃድ፣ የተጠረጠሩ ሰዎችን የስልክ ወይንም የኢ-ሜይል ግንኙነት መጥለፍና አገኘው የሚላቸውን ማስረጃዎች ማቅረብ ይችላል፤በተጨማሪም ክትትል አድርጎ ማስረጃ ያቀርባል፡፡ ይሄ የደህንነቱ ማስረጃ ደግሞ አቃቤ ህግ፣ ለክሱ ጠንካራ ብሎ የሚያቀርበው ማስረጃ ነው፡፡ ነገር ግን ኋላ ላይ በዝርዝር ሲታይ ጉድለቶች ያሉበት ሆኖ ይገኛል። የሰው ምስክርን በተመለከተ፣ አቃቤ ህግ፣ ሁለት ዓይነት ምስክሮች ያቀርባል፡፡ አንደኛው፤ ቀጥታ ወንጀሉን ሲፈፅም አይቻለሁ የሚሉ እና ሁለተኛ ደግሞ የደረጃ ምስክር የሚባሉ፣ ተጠርጣሪው ያለ ተፅዕኖ ቃሉን ሲሰጥና የሠነድ ማስረጃዎች ከእሱ ንብረቶች መሃል ሲወጣ ተመልክቻለሁ የሚሉ ናቸው፡፡
እነዚህ ሁለተኞቹ ምስክሮች፣ በእኔ በኩል፣ የህግ ድጋፍ የሌላቸው ናቸው የሚል አቋም አለኝ። በተግባርም ስንመለከት፣ ምስክር ተብለው የሚመጡት አብዛኛዎቹ፣በመንግስት መስሪያ ቤቶች የሚሠሩ ናቸው፡፡ እንደውም እንደ መደበኛ ስራው አድርጎ፣ እኔ በተከታታልኩት ጉዳይ፣ በ17 መዝገቦች ላይ በተለያየ ጊዜ የደረጃ ምስክር ሆኖ የቀረበ ሰው አጋጥሞኛል። ይሄ ሰው፣ በሁሉም መዝገብ ላይ ነበርኩ እያለ ቀርቧል። ይሄን ተቃውመን ነበር። ቀጥተኛ ምስክር ተብለው የሚቀርቡት ደግሞ “በጉዳዩ ነበርኩበት” የሚሉ ናቸው፡፡ ይሄ ደግሞ አዋጁ የፈቀደው ነው፡፡ አቃቤ ህግ ከተጠርጣሪዎች መሃል የተወሰኑትን ነፃ አድርጎ፣ በሌሎቹ ላይ ማስመስከር ይችላል፡፡ ግን በዚህ በኩልም የአካሄድ ስህተቶች ይታያሉ፡፡ አዛዡን ነፃ አድርጎ ተከታዩ ላይ የማስመስከር ሁኔታዎች ያጋጥማሉ፡፡ በዚህ ረገድ ጥንቃቄ ሲደረግ አይታይም፡፡
በሌላ በኩል ተጠርጣሪ ተብለው ለረጅም ጊዜያት ከታሠሩ በኋላ አቃቤ ህግ በቂ ማስረጃ ባለማቅረቡ፣ መከላከል እንኳ ሳያስፈልጋቸው በነፃ የሚሰናበቱ አሉ። በዚህ በኩል፣ የዞን ዘጠኝ ጦማሪያንን ጉዳይ ማየት እንችላለን፡፡
መንግስት በሽብር የተከሰሱትን ጨምሮ የታሳሪ ፖለቲከኞችን ክስ በማቋረጥ በምህረት መፍታቱ፣ ከህግ የበላይነት አንፃር እንዴት ይታያል?
በምንም ይሁን በምን የታሰሩ ሰዎችን የመፍታት እርምጃ ጠቃሚ ነው፡፡ አንደኛ ለታሠሩ ሰዎች፣ ሁለተኛ ለፍትህ ስርአቱም ጠቃሚ ነው፡፡ ፍ/ቤት የራሱ አቅም አለው፡፡ ነገር ግን ከሚቀርቡ ጉዳዮች ብዛት አንፃር፣ ለፍ/ቤት ባህሪ የሚመጥኑ ናቸው ወይ የሚል ጥያቄ ያጭራል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሽብር ጉዳይ ከሁሉም የሃገሪቱ ክፍሎች፣ ተጠርጣሪዎች እየቀረቡ ነው፡፡ ይሄን ለመታዘብ አንድ ቀን ብቻ ልደታ ፍ/ቤት መገኘት በቂ ነው፡፡ ግቢው አሁን ፍርድ ቤት ሳይሆን የአውቶቡስ መናኸሪያ ነው የሚመስለው፡፡ በርካታ እስረኞችን ይዞ የሚመጣ አውቶብስ ግቢውን ያጨናንቀዋል፡፡ ለምሳሌ የመጀመሪያው፣ አውቶብሱ ሙሉ የአማርኛ ተናጋሪ ይሆናል፡፡ ቀጥሎ አንድ አውቶቡስ ሙሉ የኦሮሚኛ ተናጋሪ፣ ሌላ አውቶቡስ ሙሉ ደግሞ ወይ ከጋምቤላ አሊያም ከቤኒሻንጉል የመጡ ተከሣሾች ይገባሉ። ከብሔር ተዋፅኦ አንፃር ሲታይ፣በርካታ ብሔሮች የሚወክል ሰው፣ ፍ/ቤት ተከሶ ይቀርባል፡፡ እኔ ይሄን ስመለከት፣ በአሁን ወቅት፣ “ህዝብ ፍ/ቤት እየቀረበ ነው” የሚል ግንዛቤ ነው ያለኝ፡፡ በአጠቃላይ በየችሎቱ ከምናየው አንፃር፣ ጉዳዩቹም ለፍ/ቤቶች የሚመጥኑ አይደሉም፡፡ በሚያሰቅቅ ሁኔታ ፍ/ቤቶች ሲዘለፉ እያየን ነው፡፡ ይሄ የፍ/ቤትን ክብር ለሚጠብቅ ሰው አስደንጋጭ ነው። ከዚህ አንፃር ፍ/ቤቶች፣ ለሃገር ከፍተኛ ስጋት ባላቸው ወሳኝ ጉዳዮች ላይ እንዲያተኩሩ ቢደረግ ይመረጣል፡፡
የመንግስት ታሳሪ ፖለቲከኞችን የመፍታት እርምጃ፣ በዚህ በኩል መልካም ጎን አለው፡፡ ከህግ የበላይነት አንፃር ካየነው፣ በእርግጥ የተጠረጠሩ ሰዎች፣ ከእስር መውጣት ያለባቸው ተከራክረው ነው፡፡ እርግጥ ነው አቃቤ ህግ ክስ የማቋረጥ መብት አለው፡፡
ክሱም የራሱ መመዘኛዎች አሉት፡፡ ግን አንዳንዴ ተጠርጣሪው ወደ እስር የገባው ያለ አግባብ ከሆነ፣ በይቅርታ ወይም ክሡ ተቋርጦ ቢፈታ፣ከህግ የበላይነት ጋር የሚጣረስ አይሆንም፡፡ አሁንም ክስ በማንሳት ሰዎች ለሃገራዊ መግባባት በሚል ከእስር ቢወጡ፣ ከህግ የበላይነት ጋር አይጣረስም። ምክንያቱም ሰዎቹ መጀመሪያም ሳይገባቸው ወደ እስር ስለገቡ፣ በዚህ መልክ ቢወጡ፣ ከህግ የበላይነት ጋር አይጋጭም፡፡

Read 3518 times