Monday, 05 February 2018 00:00

“ምስራቃዊት ኮከብ” እንዴት እውን ትሁን?

Written by  ደሳለኝ ሥዩም
Rate this item
(2 votes)

  “-- እንደ ሀገር ትርጉም ያለው ሀገራዊ ማዕቀፍ - ይህንን መሠረት ያደረገ ጥራትና ወጥነት ያለው ርዕይ፣ ግብ፣ተልዕኮ፣ ዓላማ፣ ስትራቴጂ፣ ፖሊሲና መመሪያ ያለን አይመስለኝም፤ ገና ከገዥ አስተሳሰብ ወደ መሪነት አስተሳሰብ፣ ከጊዜያዊ እይታ ወደ አርቆ አሳቢነት ስርዓት፣ ከሃይል ፖለቲካ ወደ ሐሳባዊ ፖለቲካ አልተሸጋገርንም፡፡--”
            
   የመጽሐፉ ርዕስ… ምስራቃዊት ኮከብ
ደራሲ…. ጸጋዘአብ ለምለም ተስፋይ
የህትመት ዘመን …. 2010 ዓ.ም
በዚህ መጽሐፍ ላይ ዳሰሳ ለማካሄድ ሳስብ አስቀድሞ የሚመጣብኝ ነገር፣ የኢትዮጵያ ሥነ-ጽሑፍ በኢትዮጵያ ማህበረ-ፖለቲካዊ ሲልም፣ ምጣኔ ሀብታዊ ጉዞ ውስጥ ያለው ወይም የነበረው አስተዋጽኦ ተጠንቷል ወይ? የሚለው ጥያቄ ነው፡፡ እንደ መታደል ወይም አለመታደል ሆኖ፣ የኢትዮጵያን ስነ-ጽሑፍ ጉዞ የሚዳስሱ ምሁራን፣ ትኩረታቸውን የሚያደርጉት (በእኔ ንባብ ውሱንነትም ሊሆን ይችላል) ሥነ-ጽሁፋችን ከምን ወደ ምን አደገ? በቅርጽ፣ በቴክኒክ፣ በትርጉም፣ በርዕሰ ጉዳይ ወዘተ. እንጂ ከዚህ ሲያልፍ፣ አሁን ወይም በፊት የኢትዮጵያ ስነ-ጽሑፍ በኢትዮጵያ ሁለንተናዊ እድገት ወይም ልማት ላይ ያለው ቀጥተኛና ቀጥተኛ ያልሆነ አስተዋጽኦ ምን ይመስላል? የሚለው ትኩረት የተሰጠው አይመስለኝም፡፡ (በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ወደፊት እንደ እግዚአብሔር ቸርነት እንወያይበት ይሆናል)
ዛሬ ልዳስሰው የወደድኩት መጽሐፍ ልቦለድ ነው፤ ልቦለድ ይሁን እንጂ ልክ እንደ ማክሲም ጎርክይ “እናት” ሁሉ፣ ነባራዊ ሀቅን መሠረት አድርጎ የተጻፈ የፖለቲካ ማኒፌስቶም ይመስላል። ደራሲው ጸጋ ዘአብ ለምለም ተስፋይ ይባላል። መጽሐፉ ደግሞ “ምስራቃዊት ኮከብ” ይሰኛል፡፡ ደራሲውን በቅርብ እንደማውቀው፣ የኢኮኖሚክስ ተማሪ እንጂ የፖለቲካ ተማሪ አይደለም፤ በመጽሐፉ ውስጥ የተንጸባረቀው ጥልቅ ፖለቲካዊ ምልከታ ግን ስለ ሀገር አብዝቶ ከመጨነቅ፣ ብዙ ከማንበብና ከማብሰልሰል የመጣ ይመስላል፡፡
የጸጋ ዘአብ መጽሐፍ፣ መስፈንጠሪያ ታሪኩን (እውቂያ) የሚጀምረው እንዲህ በመተረክ  ነው፡-
‹ለእኔ ሀገራችን ከመቸውም ጊዜ በላይ አስከፊ ሁኔታ ላይ ያለች፣ ህዝብ እንደ ህዝብ የተከፋፈለባት፣ ዘረኝነት የነገሰባት፣ ማን አለብኝነት የጎለበተባት፣ ፍቅረ ነዋይ የዳበረባት፣ ሀገራዊ ፍቅር በእጅጉ የከሰመባት፣ በባህል ማንነት መጥፋትና የማንነት ቀውስ የሚናጥ ትውልድ የተበራከተባት፣ ምሁርና የሃይማኖት አባት ከመቸውም ጊዜ በላይ አድር ባይ የሆኑባት፣ ተስፋ ማጣትና ታሪክን አለማወቅ መለያው የሆነ ህብረተሰብ የተፈጠረባት ሀገር ሆናለች›
በዚህ የታሪክ እውቂያ የሚጀምረው መጽሐፉ፣ መፍትሄን ሊያፈላልጉ በሚሹ የተለያየ ሰብእና እና ማንነት ባላቸው ገጸ-ባህርያት አማካኝነት ታሪኩ ወደፊት ይገሰግሳል፡፡ ጸጋ ዘአብ አንድን ፓርቲ ስለ ማቋቋም የሚሰብክ ወይም የሚተርክ ይመሰል እንጂ በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ሊያሳየን የሚሞክረው፣ እውነት ሀገራችንና ዜጎቿ ያሉበትን መያዣ መጨበጫ ያጣ ነባራዊ ሁኔታ ነው፡፡ አስራ ስድስት ሰዎች አንድ ፓርቲ ለመመስረት በሚመስለው ሀሳብ ውስጥ ሊሳተፉ ሲፈልጉ ወይም ሲያስቡ አሊያም ሲነሳሱ እናስተውላለን፡፡ ይሁንና አስራ ስድስቱ፣ አንዴም ምሉዕ ሆነው ተሰባስበው አይገኙም፡፡
‹‹….. አንዳንዱ የሚመጣው ለማውራት ብቻ ነው፣ አንዳንዱ ጊዜ ለማሳለፊያ፣ አንዳንዱ ፕሮግራም ከሌለው ብቻ፣ አንዳንዱ ሲመቸው ብቻ ……››
ፖለቲካን መማርና ፖለቲከኛ መሆን ልዩነት ያለውን ያህል፣ ጀማሪ መሆንና ፈጻሚ መሆን መሰረታዊ የትርጓሜ ልዩነት አለው - በፖለቲካ ጉዞ ውስጥ! የጸጋ ዘአብ መጽሐፍ፤ የፖለቲካ ፓርቲ ምስረታ ደብር እንደሚገባ (ተዓማኒነት ያለው ባይመስልም ቅሉ) ወይም ከዓምላኩ ምህረትን እንደሚለምን ንጹህ አማኝ፤ በቅን ልቦና በንጹህ ህሊና የሚገባበት የአገልጋይነት መድረክ ነው። ያ ካልሆነ በቀር ይላል ደራሲው፤ ምስራቃዊት ኮከብ ልትሆን የምትችለውን ኢትዮጵያ እውን ማድረግ ይቅርና አደገኛ ቁልቁለት ውስጥ ያለውን የማህረሰባዊ እሴት መሸርሸር መታደግ እንዲሁም ሀገሪቱንም ከመንሸራተት ማዳን  አይቻለንም፡፡
የጸጋ ዘአብ “ምስራቃዊት ኮከብ”፤ በርካታ ደራሲያን እንደሚያደርጉት፣ ከነፋሱ ጋር ለመንፈስና ገንዘብ ለመቃረም ታልሞ የተጻፈ አይደለም። እንዴት ቢሉ? የታሪክ ጥብቅነት (validity) እንዲሁም የማይበረዝ ፍሰት (coherence) ያለው መጽሐፍ በመሆኑ ነው፡፡ ንግበይኪ ሀበ ጥንተ ነገር እንዲሉ አበው፡፡ ወደ ቀደመ ነገራችን እንመለስ!
‹‹ እንደ ሀገር ትርጉም ያለው ሀገራዊ ማዕቀፍ - ይህንን መሠረት ያደረገ ጥራትና ወጥነት ያለው ርዕይ፣ ግብ፣ተልዕኮ፣ ዓላማ፣ ስትራቴጂ፣ ፖሊሲና መመሪያ ያለን አይመስለኝም፤ ገና  ከገዥ አስተሳሰብ ወደ መሪነት አስተሳሰብ፣ ከጊዜያዊ እይታ ወደ አርቆ አሳቢነት ስርዓት፣ ከሃይል ፖለቲካ ወደ ሐሳባዊ ፖለቲካ ገና አልተሸጋገርንም፡፡ በመሆኑም እነዚህ ባለመኖራቸው የሚታዩ ህመሞች በርካታ ናቸው፡፡ የዴሞክራሲያዊ የሰብአዊ መብት ረገጣ ኢ-ፍትሀዊ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት፣ የስልጣንና የገንዘብ ሙስና መብዛት፣ ሐሰተኛነትና አድር ባይነት የስርዓቱ አመራሮች አንድ እሴት መሆኑ ….. ምልክቶች ይመስሉኛል››  ይለናል፤ ደራሲው በዋናው ገጸ-ባህርይ በሙሴ አፍ፡፡  
“ምስራቃዊት ኮከብ” መጽሐፍ አብዝቶ የሚተርከው ወይም የሚያነሳሳው ገዢውን ፓርቲ ስለ መውቀስ  ወይም ከምድረ ገጽ ስለ ማጥፋት አሊያም ‹ቅንጅት›ን ስለ መደገፍም አይደለም፡፡ እንደ ሀገር አዲስ የፖለቲከኝነት ባህርይ ስለመያዝና አዲስ የፖለቲካ መንገድን ስለመቀየስ እንጂ፡፡ በጸጋ ዘአብ እይታ፤ የገዥም ሆነ የተቃዋሚ ፓርቲ አባል መሆን፣ ለአሁኗ የኢትዮጵያ ማህበረሰቦች ጽቅድም ኩነኔም ሆኖ መታየት የለበትም፡፡ አስቀድሞ ነገር ለፖለቲካና ለፖለቲከኝነት ያለን አረዳድ፣ የተንሻፈፈ ሆኖ ሳለ፣ ማን ወቃሽ፣ ማን ተወቃሽ ሊሆን ይችላል?
‹‹….በጦርነት ለምን ጀግና ሆንን? አያችሁ፣ የአሸናፊነት ታሪክ ስላለን፣ ለምን በትርጉም ያለው ሐሳብ በፖለቲካችን እንዲያ (ድሃ) ሆንን? የተሸናፊነት ታሪክ ስላለን፡፡ አለማወቃችን ነው እንጂ፣ ከችግሮቻችን ውስጥ ዋነኛው ችግራችን ይህን አለመረዳታችን ነው፡፡ ችግራችን - አውቀናል ያልነውን፣ ትርጉም ባለው መልኩ አለማወቃችን ነው፡፡ ……››
አውነትም ይህ መጽሐፍ ምን እያለን ነው ብለን፣ የሀገራችንን፣ የህዝባችንን፣ የገዥዎቻችንን፣ የተቃዋሚዎቻችንን እውነታዎች ለማየት የታደልን ብንሆን፣ “ምስራቃዊት ኮከብ” የሚተርከው የእኛን አውነት መሆኑን እንደርስበታለን፡፡ የዚህ መጽሐፍ ትልቁ ቁም ነገር፣ ሌሎች በላያችን ላይ አሻጥር ሰርተዋል ወይም ሊሰሩብን ነው የሚል ጥርጣሬ አዘል ክስ አለማንጸባረቁ ነው፡፡ ገዥ ሆንን ተገዥ፣ መሪ ሆንን ተመሪ፣ አሰሪ ሆንን ሰራተኛ፣ በዚህ መጽሐፍ ዕይታ፣ አንዳችን ከአንዳችን ልዩነት የለንም። ሁላችንም የታነጽነው በተንሸዋረረ የፖለቲካ አተያይ ነው፡፡
ፖለቲካችን የተቃኘው ወይም እንዲቃኝ የምንፈልገው በምእራቡ ዓለም ባህል ነው፡፡ በምእራቡ ዓለም መስፈሪያ ነው፣ በምእራቡ ዓለም አይዲዮሎጂ ነው፡፡ ዳሩ እኛ እትዮጵያዊያን ብቻ ሳንሆን፣ እኛ አፍሪካዊያን፣ ይሄ ተሸናፊ እንጂ አሸናፊ እንድንሆን አላስቻለንም፤ ይሄን እውነታ የምናይበት ዓይን ደግሞ ተሸፍኗል፡፡ ለዚህ ነው መሪዎቻችን፤
‹‹በአፍሪካ መሪ፣ በምዕራብ ተመሪ፣ በአፍሪካ ታጃቢ፣ በምዕራብ አጃቢ፣ በአፍሪካ ተለማኝ፣ በምዕራብ ለማኝ፣ በአፍሪካ አዋቂ፣ በምዕራብ አላዋቂ፣ በአፍሪካ አስፈሪ፣ በምዕራብ ፈሪ፣ በአፍሪካ ብዙ ተናጋሪ፣ በምእራብ ብዙ አድማጭ፣ በአፍሪካ ተከባሪ፣ በምዕራብ አክባሪ፣ በአፍሪካ አምላክ፣ በምዕራብ አምላኪ፣ በአፍሪካ ገዥ፣ በምዕራብ ተገዥ፣ በአፍሪካ ወቃሽ፣ በምዕራብ ተወቃሽ…›› የሆኑት፡፡
ለዚህም ነው አዲስ አተያይ ያለው፣ የአዲሲቷ ምስራቃዊት ኮከብ መስራች የሆነን ፓርቲ የመመስረት  ፋይዳን የሚጠቁመን፡፡ መጽሐፉ፤ ስለተሸነሸነች ኢትዮጵያ ሳይሆን፣ ስለ አንዲት ታላቅ ኢትዮጵያ ይነግረናል፣ ስለ ህዝቦች ሳይሆን ስለ ህዝብ ይነግረናል፣ ስለ ሐሳብ ሳይሆን፣ ትርጉም ስላለው ሐሳብ ይነግረናል፣ ስለ ወቀሳ ሳይሆን፣ ስለ ሀሳብ ይነግረናል፣ ስለ ጥላቻ ሳይሆን፣ ስለ ዕውቀት ይነግረናል፣ ስለ ቁርሾ ሳይሆን፣ስለ ታሪክ ይነግረናል፣ ስለ ብዙ ነገር ሳይሆን፣ ስለ አንዲት ታላቅ ኢትዮጵያ ይነግረናል፣ ስለ ሃይማኖት ሳይሆን፣ ስለ እምነት ይነግረናል፣ ስለ ተግባር ሳይሆን፣ዘላቂነት ስላለው ተግባር ይነግረናል፡፡ የዚህ ሁሉ መነሻው ይላል ደራሲው፤ የዚህ ሁሉ መነሻው፣ የምናወራላትን ኢትዮጵያ፤ በራሷ በኢትዮጵያ  አይኖች ማየት መሆኑን ይጠቁመናል፡፡  
‹‹….ኢትዮጵያዊነት ሰው መሆን ነው፡፡ ኢትዮጵያዊ ጠባያት፡- ፈሪሃ ፈጣሪ፣ ቃል አክባሪነት፣ ትህትና፣ ይሉኝታን … መላበስ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነት የነጻ ፈቃድ ሰው የመሆን ማንነታዊ መገለጫ ነው። ባህሪያዊ ማንነት በፈጣሪውና በፍጡር መሃከል፣ በፍጡርና በፍጡር መሃከል የነበረ፣ ያለና የሚኖር ነውና፣ ከዚህ ታላቅ መንፈስ፣ በህብረትና በአንድነት እንድንሳተፍ ማን አዚም እንዳደረገብን በማስተዋል ልንመረምር ይገባል…… ኢትዮጵያዊነት ሰው የመሆን ህይወት … ኢትዮጵያዊነት ምንጊዜም ያሸንፋል…››
እንግዲህ ደራሲው በመጽሐፉ፤ አስቀድመን ያለንን ማወቅና ወደ ነባራዊ ማንነታችን መመልከት እንጂ ከኬንያ የጸረ ሽብር ህግ የተቀዳ፣ ከፊሊፒንስ የልማት ፖሊሲ የተኮረጀ፣ ከቻይና የስለላ ጥበብ ልምድ የተቀመረ ወይም ከሶቭየት ህብረት የጎሳ ፌደራሊዝም የተቀዳ ---- እያሉ ማምታት፣ ትርፉ ጥፋት፤ ውጤቱም ሽንፈት መሆኑን ይነግረናል፡፡
መጽሐፉ የልቦለድን ባህርይ መላበሱ፣ ልቦለድ ያሰኘው ይሆናል፤ ቀደም ሲል እንዳልኩት፣ የማክሲም ጎርኪን የኮሚኒስት ማኒፌስቶ፤ ልቦለድ ብለን እንደምናነበው፣ የጸጋ ዘአብ መጽሐፍ ደግሞ ከልቦለድነቱ ይልቅ ፖለቲካው ላይ ያመጣው አዲስ አተያይ ይጎላብኛል፡፡
“ምስራቃዊት ኮከብ”፣ ከሚዳስሰው ጭብጥ አንጻር፣ በተለይ በአሁኑ ወቅት ሁሉም ያነበው ዘንድ አጥብቄ እመክራለሁ፡፡ እንደ ሥነ-ጽሑፍ ስራ ግን ከስህተት የጸዳ ነው ለማለት አይዳዳኝም። ሥነ-ጽሑፍን ለሥነ-ጽሑፋዊ ውበቱ ሲል ብቻ ለሚያነብ ሰው፣ ከመጽሐፉ ሙሉ እርካታ ያገኝበታል ብዬ አላምንም፡፡ የአተራረክ ውበት ማነስ፣ አብዝቶ ገላጭነትና ማብራራት እንደ ድክመት የሚጠቀሱ ሲሆን መሰረታዊ የቋንቋ ስህተቶችም ይስተዋልበታል፡፡  
በተለይ ደግሞ በአማርኛ ቃላትና ፊደል አጠቃቀም በኩል፣ እንደ ወረርሽኝ የመጣው የዘመኑ በሽታ፤ በዚህ መጽሐፍ ላይ ጎልቶ ይስተዋላል። ምሳሌዎችን ለመጥቀስ ያህል፡- ‹ኧረ› ለማለት ‹ኸረ›፣ ‹ብያለሁ› ለማለት ‹ብያለው›፣ ‹ግድግዳ› ለማለት ‹ጊድጊዳ›፣ ‹በኋላ› ለማለት ‹በኃላ› ወዘተ. ዓይነት ስህተቶች፣ እዚህም እዚያም ይታያሉ፡፡ በስተመጨረሻ፣ ይህ መጽሐፍ፣ ያለ ምንም ግነት፣ በይዘት ደረጃ ዘመኑን ብቻ ሳይሆን የሀገሪቱን ዕጣ ፈንታ የሚዋጅ ሥራ መሆኑን በመናገር ለአንባቢያን ሁሉ ጋብዤ እሰናበታለሁ፡፡

Read 2566 times