Print this page
Monday, 05 February 2018 00:00

ኧረ የብሔራዊ ሠላም፣ ዕርቅና መግባባት ያለህ!!

Written by  ወርቅዓለማሁ ንጋቱ (ከነጌሌ-ቦረና) goldnegellebo@gmail.com
Rate this item
(0 votes)

    ዜጎች ለአገራችን በውዴታም ሆነ በግዴታ እንድናበረክትላት የሚጠበቅብን ውድ ስጦታ ምንድነው? ሀብት? ንብረት ወይስ ሕይወት? /ዳር ድንበር በጠላት ሲደፈር ዘምቶ መሞት፣ እጅ፣ እግር፣ ዓይን ማጣት/ ወይስ መለኛ /አስታራቂ/ አግባቢ ሀሣብ? ለአገራችን ማቅረብ ያለብን የቱን ነው ? ሁሉም ለአገራችን፣ ለምንወደውና ለምናከብረው ወገናችን፣ አስፈላጊና ጠቃሚ ቢሆኑም፣ በአገራችን ያጣነውና ኖሮንም የነፈግናት ውድ ስጦታ፣ አራተኛው ይመስለኛል፣ ሀሣብ፡፡ እሱንም ወደንና ሰስተን ሳይሆን፣ በምናገባኝና በፍርሃት ቆፈን፣ ራሳችንን በመደበቃችን ነው፡፡ ወደ ሠላማዊና የበለጸገ ኑሮ እየመራናችሁ ነው፣ወይም ልንመራችሁ እንችላለን፣ የሚሉን ወንድም እህቶቻችን፣ በብዙዎች ልብ ሞልቶ የተትረፈረፈውን ሀሣብ፣ ያለ ዋጋ እንዲጠቀሙበት ለማቅረብ ቢቻልም፣ ከሚያመልኩት ብቸኛና ግትር የፖለቲካ ርዕዮት ክልከላ የተነሳ፣  በአንድ ሀሣብ ልጓም ተለጉመን ክፉኛ ‹‹ወደ ቁልቁል› እየጋለብን እንገኛለን፡፡
ለአገራችን ልማትና ለሕዝቦቿ ዕድገት፣ የየድርሻችንን መዋጮ ስናቀርብ፣ የባንክ ደጆችም ይሁኑ የመንግሥት እጅ ክፍትና የተዘረጉ ናቸው፡፡ የታክስና ግብር ግዴታችንን ስንወጣ፣ የሰነድ ገጾች በፍጥነት፣ ስማችንንና የገንዘብ አሃዞችን በድምቀት ያቀልማሉ፡፡ በአሳዛኝ መልኩ ደግሞ፣ የተለየ ሃሣባችንን ስንሰነዝር፣ በሮች የወህኒ ደጅ፣ እጆችም የብረት ዘንግ ይሆኑና ሜዳው ገደል ይሆናል። ይህንን መጣጥፍ ያዘጋጀሁት ወዳጄ መምህር ታዬ ቦጋለ፣ በማህበራዊ ሚዲያ በጉዳዩ ዙሪያ የየበኩላችንን እንድንወረውር በጋበዘ ጊዜ ነበር፡፡ ሆኖም ግን ለ20 ዓመታት በኪራይ አለንጋ ስገረፍ ኖሬ የቀለስኳት ጎጆ፣ በገዛ አገሬ በ‹‹መሬት ወራሪ››ነት ተፈርጄ፣ ወደ ሜዳ መውደቄ፣ በፈጠረብኝ ድንጋጤና ሀዘን የተነሳ፣ ግራና ቀኙ ጠፍቶኝ ነበረና፣ በስደት ጥጌን እስክይዝ ዝም ብዬ አስቀመጥኩት፡፡ መጣጥፌ ዓመት ቢያልፈውም፣ ሀሳቡ አላረጀምና እነሆ!
ከወቅቱ የአገራችን አስጊና አሳሳቢ ሁኔታ አንጻር፡- በ‹‹ብሔራዊ ሠላም፣ ዕርቅና መግባባት›› ጉዳይ መነጋገር፣ ለገዢውም ሆነ ለተቀናቃኝ ፓርቲዎች ብቻ፣ በተለየ ኃላፊነት የምንተወው የሩቅ ጉዳይ ሳይሆን፣ ማናችንም የማዕበሉ ተጎጂ ዜጎች፣ ያሉንን አመለካከት፣ የአስተሳሰብ፣ የዕምነትና የማንነት ወሰኖች በማለፍ፣ ለሰከንዶች እንኳ ልናጣው ስለማንፈልገው፣ አንጡራ የጋራ ሠላማችን፣ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ፣ የዳር ተመልካችነታችንንና ዝምታችንን ሰብረን፣ በተለያዩ ክልሎች፣ በወገኖቻችን ላይ እየደረሰ ካለው ሰቆቃ አንጻር፣ የረፈደ ጥሪ ቢሆንም፣ በጎሣ ተለያይቶ ደም መፋሰስንና፣ በጅምላ መጎዳዳትን በቃ!! ልንል የሚገባበት አስጊ ምዕራፍ ላይ ደርሰናልና እንነጋገር፡፡
በሠላማዊ መድረክ፣ በይፋ እንድንመካከርበትና እንድንግባባት እያቀረብኩ ያለሁት፣ የብሔራዊ ሠላም፣ ዕርቅና መግባባት ጥሪ ደግሞ፡- በሰብዓዊ ተፈጥሯችን፣ በኢትዮጵያዊ ባህላችንና በዕምነታችንም ውስጥ፣ አብሮን ያለ ሠናይ መገለጫችን እንደመሆኑ፣ ያለምንም የፖለቲካ፣ የጎሣና ሃይማኖት ከልካይነት፣ በጋራ መድረክ በግልጽ ልንነጋርበት የሚገባ በመሆኑ ነው፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን ከ1960ዎቹ ወዲህ ከባህር ማዶ በተዋስነው ባዕድ ርዕዮት የተነሳ፣ ምን ያህል አበሳችንን እያየን እንደሆነ፣ ያለ ጧሪ የቀሩ ወላጆችና ያለ አሳዳጊ የተጣሉ ልጆች፣ የሰቆቃ ሕይወት በቋሚ ምሥክርነት በመካከላችን አለ። ዛሬም ከዚያ የሰብዓዊነት ቃና ከሌለው የ‹‹ገድሎ ነፃ አውጪ››ነት አባዜ አልተላቀቅንም። እኛ‘ኮ የማርክስም፣ የሌኒንም፣ የስታሊንም ኮሚኒስት ልጆች አይደለንም። እኛ ችግሮቻቸውን በብልሃት፣ በፍቅርና በእርቅ መፍታት የሚችሉ የጀግኖቹ፣ የሩህሩሆቹና የኩሩዎቹ፣ አያት ቅድመ አያቶቻችን ‹‹ልብ መግዣ ትምህርት አትንፈገን፤ እኛን ራሳችንንም ለሌሎች መማሪያ አታድርገን›› ብለው የሚያምኑ ፍሬዎች ነን፡፡ ስለዚህ ያቆዩልንን የከበሩ እሴቶች ጠብቀን፣ የጥላቻንና የመነጣጠል መንፈስን እንድናዳክምና፣ አንድነታችንን እንድናጸና፣ በብሄራዊ ደረጃ፣ በበሳልና የተረጋጋ ምክንያታዊነት፣ ልንነጋገርና ልንመካከር ይገባል፡፡
ምናልባትም፡- ይህንን የሁላችንንም ልቦና፣ ዕረፍትና ሠላም የነሳ አውዳሚ ችግር፣ ከጅምሩ ሁሉን በስፋት ሊያሳትፍ በማይችል፣ ውስን የጋዜጣ ዐምድ እንዳቀርብ የተገደድሁ መሆኑ አሳዛኝ እውነት ቢሆንም፣ የብሔራዊ ሠላም፣ የዕርቅና መግባባት ጥሪ፣ በይዘት ደረጃ፣ የመቶ ሚሊዮን አትዮጵያውያን ልቦች የሚናፍቁት፣ የተራቡትና የተጠሙት በኩር አጀንዳቸው ነው፡፡ በብሔራዊ ሠላምና መግባባት ላይ፣ የተዘጉ የዕድል በሮች ተከፍተው ማየትም፣ የነጋ ጠባ ናፍቆታቸውና የጋራ እምነታቸውም ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ምን ይደረጋል! እስካሁን ባለው ሁኔታ፣ የመልካም ዕድል በሮች ሁሉ በእምቢተኞች ተጠርቅመዋል፡፡ አይቻልም እንጂ፣ የየትኛውም ኢትዮጵያዊ ደም፣ በገዛ ወገኑና ወንድሙ ዕጅ በግፍ ሲፈስ ከማይና ከምሰማ፣ በተዐምር ወደ ሰማያት ተመንጥቄ፣ በደመና ፈረስ እየጋለብሁ፣ በምድረ ኢትዮጵያ ጥጋ ጥግ ሁሉ በሚሰማ አስገምጋሚ ድምጽ፣ ስለ አንድነት፣ ስለ ሠላምና ፍቅር፣ በአጠቃላይም ስለ ብሔራዊ ሠላም፣ ዕርቅና መግባባት የምሥራች ዐዋጅ ብናገር ፣ምንኛ ደስ ባለኝ፡፡
በዚህ የሠላም ጥሪ ጽሁፍ የሚንጸባረቀው ምክረ-ሀሳብ፣ በየግል የፖለቲካ ድርጅቶችና ቡድኖችን፣ በሚዘውሩና በሚመሩ፣ ተጽዕኖ ፈጣሪ ባለሥልጣናት አስተሳሰብ ውስጥም፣ ብርሃናዊ ነቁጥ በማሳረፍ ከጥቅማቸው፣ ከድፍረታቸውና ከፍርሃታቸው፤ ከክብራቸውና የሥልጣን ዘመናቸውን ማራዘምን ብቻ፣ ማዕከል ካደረገ ፍልስፍናቸው በላይ ተራምደው እንዲመለከቱ፣ የሕዝብ ከፍተኛ መሻት ለሆነው የሠላም ጥሪ፣ በድፍረት አዎንታዊ ምላሽ ሊሰጡ እንዲችሉ የሚገፋፋ፣ ተስፋ በቆረጠ ሁኔታ ውስጥም ቢሆን ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ይህንን የመሰሉም አንድ ሺህ የሠላም መድረኮች ተፈጥረው፣ ከስሜት ወጣ ባለ ማስተዋልና ትህትና፣ የአገራችንንና የህዝባችንን አሁንና ወደፊት አለቃና ምንዝር ሳይባል ብንነጋገርበት፣ ከመቶ ሚሊዮን ሕዝቦች አንድ ሰው እንኳ እንደማይጎዳ እርግጠኛ መሆን ይቻላል፡፡
በተለይ በኢትዮጵያ፣ ለውጥና መሻሻል እንዲኖር፣ ወሣኝ ሙያዊ ሚና ሲጫወቱ የነበሩና ያሉ በርካታ የምንኮራባቸው ምሁራን የመኖራቸውን ያህል፣ በፖለቲካው መስክ ደግሞ በመንግሥት የመዋቅር ጉያ ተሸጉጠውና ተሰግስገው፣ በራስ ወዳድነት፣ በአድርባይነት፣ በአስመሳይነትና በለየለት አረመኔነት ተሞልተው፣ አሉታዊ ሚና የሚጫወቱ ‹‹አማካሪ ምሁራን››፤ ትናንትም ሆነ ዛሬ፣ ለብዙ ወጣቶች ጉዳትና ሞት መነሻ መሆናቸውን ተረድተው፣ በግዴለሽነትና በጭካኔ ከተሞላ፣ ሁሉን ከሚንቅና ከሚያንኳስስ፣ አጉል ምሁራዊ ትምክህታቸውና መኮፈሳቸው ተላቀው፣ ለአዎንታዊ አስተዋጽዖ ቢነሱ፣ ከትውልድ ተጠያቂነትና ከፀፀት ይድናሉ። ለራሳቸው ብቻ ሳይሆን ለልጆቻቸውና ለልጅ ልጆቻቸው ሲሉ፣ ከራሳቸውም ሆነ፣ ተለያይተው እንደ ጠላት በሚተያዩ ወገኖቻቸው መሀል፣ እርቅ እንዲሆን፣ ምድሪቱ የንጹሀን ደምና ዕምባ በከንቱ እንዳይፈስባት፣ የበኩላቸውን ያበረክቱ ዘንድ አሳስባለሁ፡፡
‹‹ብሔራዊ ሠላም፣ ዕርቅና መግባባት›› ማለት ምን ማለት ነው? አስፈላጊስ ነው? ከእያንዳንዳችንስ ግላዊ፣ቤተሰባዊና ማኅበረሰባዊ ሕይወትስ ጋር ያለው ቁርኝትና የሚያስገኘውስ ጥቅም/በረከት ምንድነው? እንዴትስ ተግባራዊ ሊሆን ይችላል? ለሚሉ ጥያቄዎች ምላሽ የመሰለኝን ሀሳብ ከመሰንዘሬ በፊት፣ አንባብያን! ይህ ሀሳብ፣ ከሠላም ፈላጊ፣ በፍትህና ሚዛናዊነት  ከሚያምን ተራ ዜጋ ልብ የወጣ እንጂ፣ የፖለቲካ ሳይንስ ሊቃውንት፣ በጥልቅ አጥንተው በሚያስተነትኑት ደረጃ የተሰናዳ ስላይደለ፣ ግምታችሁና ሚዛኔ ቢራራቅ እንኳ፣ በጎደለ እየሞላችሁ እንድትመለከቱት ላስገነዝብ እወዳለሁ፡፡ ሆኖም ዝምታን ለመረጡና ለተገለሉ/መድረክ ለተነፈጉ/ የአገራችን ዐዋቂዎች፣ ጥርጊያና መቆስቆሻ እንደሚሆን በጽኑ አምናለሁ፡፡ የኔ አቀራረብ ለእያንዳንዳችን ቅርብና ለመረዳትም ግልጽ ከሆነው ነጠላ፣ ግን አጠቃላይ እውነት ይጀምራል፡፡
የማንም አዳማዊ ፍጡር፣ ሥጋዊም ሆነ መንፈሣዊ ኅልውናና ሰብዕና የተዋቀረው፣ የተለያየ ሚና ባላቸው ብልቶቹ ሕብረትና ቅንጅት ነው። (የልብን፣ የዓይንን፣ የጆሮን፣ የአንደበትን፣ የአዕምሮንና የሰራ አካላት የተለያዩ ብልቶችን የተቀናጀ ሚና ልብ ይሏል፡፡) እነዚህ የተለያዩ ግን አንድ የሆኑ የአካሉ ክፍሎች፣ ባለሥልጣንም ይሁን ተራ ዜጋ፣ ድሃም ይሁን ሀብታም፣ የተመራመረ ሊቅም ይሁን ማይም፣ በጎጆም ይኑር በተንደላቀቀ ቪላ/ቤተ-መንግሥት ፣የነዚህ የተፈጥሮ ብልቶቹ ፍጹምና ረቂቅ ሥራ አንድ ዓይነት ነው፡፡ በነሱም የማይዛነፍና የተባበረ የሥራ ውጤት የተነሳ፣ ሰው ኅያው ሆኖ፣ በሰብዓዊ ባሕሪውና ግብሩ፣ ብሎም በማኅበራዊ የተራክቦ መስተጋብር ውስጥ፣ የተሟላ፣ ጠቃሚና ተጠቃሚ እንዲሆን አስችለውታል። በሰዎች መካከልም እንዲሁ፡- በማኅበራዊ፣ ባህላዊ፣ ሥነ-ልቦናዊ፣ አስተዳደራዊ ተራክቦዎች ሂደት፣ ልማትም ይሁን ቴክኖሎጂ፣ የዚህ ተፈጥሯዊ ሥርዓት አካልና አምሣል ነውና  በመጀመሪያ ከተፈጥሯችን እንማር፡፡
የሰው ልጅ በታላቅነቱና በልዕልናው፣ ማኅበራዊ ግንኙነቶቹንና ኑሮውን፣ የመለኮታዊ ባህሪ መገለጫ ከሆኑ፣ ረቂቅ የመንፈሣዊነቱ ዕሴቶች አዋህዶ፣ ፍጹም ከተግባባና ከታረቀ፣ የተፈጥሮው ስምረት ጋር በሚነጻጸር ብቃት፣ የራሱንና የመሰሎቹን ግላዊና ማኅበራዊ፣ ቁሳዊና መንፈሣዊ ፍላጎት ማርካት የሰብዓዊነቱ ግብርና ልዩ መገለጫ ነው፡፡ በሠናይ ምግባሩም የሚታይና የማይታይ፣ ጊዜያዊና ዘላለማዊ ክብርና ጥቅምም ለራሱና ለመሰሎቹ ያገኛል ያስገኛል፡፡
ማንም ልቡ በፍቅር ነፃ የሆነ፣ እግሮቹ ለሁሉም የሰው ዘሮች ወደሚያስፈልገው፣ የብዙሃን ክብረ-ሥርዓት /የዴሞክራሲ/ አምባ ካልገሰገሱ፣ ማንም አዕምሮው በዕውቀት/በጥበብ የተገራ፣ የተሻለውን አውጠንጥኖ ለወገኖቹ ካላበረከተ፣ ለዛሬና ለነገ ትውልድ ያቀደውን ዕጁ ካልሰራ፣ የቀናውን ካላዳመጠ፣ አርዓያዊ ሰዎችንና ሥራዎችን ካልተቀበለና ካልተከተለ፣ ምን ዕውቀት፣ ምን ጉልበት፣ ምን ሀብት ቢኖረው፣ በራሱ የተሟላ እንደማይሆን የታወቀ ነው፡፡ በፖለቲከኞቻችን ክበብና ልብ ውስጥ ያጣነውም፣ ይህን አስፈላጊ፣ የአስተሳሰብና የእምነት፣ አጣማሪ ቅመም ነው። ይሄ ከሌላቸው ደግሞ፣ ዛሬ በአካል አብረናቸው ያለን ወገኖቻቸውን ብቻ ሳይሆን፣ ገና ከወንዶች አብራክና ከሴቶች ማኅፀን የሚወለዱልንን፣ የነገ ትውልዶችንም፣ ሕይወትና ተስፋ ጭምር፣ ወደ መከራ አዘቅት ከመወርወር በማይመለስ፣ ፖለቲካዊ የጭካኔ በሽታ ተይዟል ማለት ነው፡፡
ከዚህ እውነታ ስንነሳ፣ ሰው በመጀመሪያ ሠላምና መግባባት ማድረግ ያለበት፣ ከገዛ ራሱ/ ከውስጡ/ ነው። ልቡ ከጥርጣሬ፣ ትዕቢትና ንቀት፣ ከስስት፣ ከጥላቻ፣ ከጎሠኝነት፣ ከሙሰኛነትና ከአምባገነንነት አረሞች መጽዳት ይኖርበታል፡፡ አለበለዚያ የነፃ አውጪነትና የመሪነት ክብርና ሞገስ ሊጎናፀፍ አይቻለውም፡፡ ከራሱ ኅሊና ያልተግባባና ያልታረቀ፣ መሪም ይሁን ተመሪ፣ ሃይማኖተኛም ይሁን ኢ-አማኒ፣ በዙሪያው ካሉ በማንነት፣ በዕምነት፣ በባህል፣ በጎሣም ይሁን በፖለቲካዊ አቋሙ፣ ከተዋለዳቸው፣ ከተጎዳኛቸውም ይሁን ከተለያቸው፣ ቤተሰቦቹ፣ ዘመዶቹም ሆነ ሌሎች ወገኖቹ ጋር ሊታረቅና ሊግባባ፣ ሊያስታርቅና ሊያግባባም የሚችለው፣ ለሰው ዘር ሁሉ ከምታስፈልገው ሠላም ጋር፣  ራሱን በንጹህ መንፈሥ ሲያገናኝና ሲያስተዋውቅ ብቻ ነው፡፡
ክቡር የሆነው ሰብዓዊ ተፈጥሮ፣ እስከ ሞት ወደነው፣ በውርደትና በቀውስ ከሚያሰናብተን፣ ሥልጣንና ገንዘብ በላይ ፣ታላቅ እንደሆነ ከተረዳንና ካመንን፣ ቀሪው የጋራ አካፋይ ወደሆነው፣ የዜጎች ሁሉ የመነጋገር፣ የመወቃቀስ፣ የመግባባት፣ የይቅርታና የፍቅር አድማስ መመልከት ነው። ወደ ‹‹ብሔራዊ ሠላም፣ዕርቅና መግባባት›› የኢትዮጵያውያን ሁሉ የጋራ መድረክ ፡፡
ትናንት በሆነው ከመቆዘምና ከመጸጸት፣ ዛሬም እየሆነ ባለው ከማዘንና ወደ ሌሎች ጣቶቻችንን ከማመልከት ባለፈ፣ በሠላማዊ ድፍረት ተሞልተን፣ ጎጂ የዕብሪት፣ የንቀትና የጥላቻ እንዲሁም የፍርሃትና ዝምታ ኬላዎችን በመስበር፣ የነገውን የጋራ ሠላምና መግባባት፣ ቅርጽና ይዘት መንደፍ የእያንዳንዱ ዜጋ ቀዳሚ ጉዳይ መሆን ይኖርበታል፡፡ ከዚህ በኋላ እንመራለን ብለው ሥልጣን የያዙትም ሆነ፣ ለመምራት ብልሃቱና ብቃቱ አለን ብለው የሚፎካከሩት ፓርቲዎች (አንዳንዶቹ የዚህ ወይም የዚያ ወገን ፓርቲ ነን እያሉ ሳለ፣ ይዞታቸው ግን ከአንድ ጥሩ ሰው በማይሻል ደረጃ የሚገለጥ፣ ፖለቲካዊ ተፈጥሯቸው ያልተጠናቀቀ፣ ምናልባት ፓርቲ ከማለት ስብስቦች ማለት ይሻል ይሆን?) ሁሉ የ‹‹እናውቅልሃለን›› ፍካሬያቸውን ትተው፣ ሕዝቡን ቁጭ ብለው የሚያዳምጡበትና፣ አረማቸውንና አረማሟቸውን የሚነቅሉበትና የሚያጠሩበት፣ የጥሞና ጊዜ ሊሆንላቸው ይገባል፡፡  
በዚህ ወቅት ኢትዮጵያ ለገጠማት ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ቀውስ፣ ተመጣጣኝ የሆነ ብሔራዊ ሠላም፣ ዕርቅና መግባባት አስፈላጊ አይደለምን? ይህስ ከእያንዳንዳችን ግላዊ፣ ቤተሰባዊና ማኅበረሰባዊ ሕይወት ጋር ያለው ቁርኝትና የሚያስገኘውስ ጥቅም/በረከት ምንድነው? እንዴትስ ተግባራዊ ሊሆን ይችላል?
ብሔራዊ ዕርቅና መግባባት ያስፈልጋል ሲባል፣ አንዳንዶች ጽንሰ-ሃሳባዊ አድማሱን አጥብበው፣ በኢህአዴግና በተቃዋሚዎች መካከል ብቻ፣ ስምምነት የመፍጠርና፣ ወንበር-ገፍ አታካራቸውን ትተው፣ ሥልጣንን እንዲካፈሉ ወይም እንዲጋሩ የሚያግባባ፣ ውስን ድርጊት አድርገው ያስቡታል፤ በአደባባይም ይገልጹታል፡፡ እንደገባኝ ይህ ስህተት ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ምክንያቱም የሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች ተቋማዊ መሠረት ፣አቃፊና ደጋፊ ሕዝብ እንደመሆኑ፣ ጉዳዩ ሁሉንም ሕዝብ (ብሄር ብሄረሰቦች) ይመለከታል፣ በብዙ ሺ ዓመታት የትውልዶች የኑሮ ፍልሰትና የውኅደት መስተጋብሮች፣ በሥጋና በደም በመንፈስም ተሳስረናል፣ እንደ ሐረግ ተወሳስበናል፣ እንደ ሹሩባ ተጎናጉነናል፣ አንድ ሕይወትና ውበትም ሆነናል። ስለዚህ ሁላችንንም ያገባናል፡፡ ጥቅሙም ሆነ ጉዳቱ እንዴት እንደሚመለከተን እያየነው ነው፡፡ በመሆኑም ‹‹ብሔራዊ ሠላም፣ ዕርቅና መግባባት›› ሲባል፣ ባላንጣዎችን በይቅርታ የሚያስተቃቅፍና የተጎዱትንም በሚታመን አግባብ የሚጠግን፣ ብልሃትና ውጤት አለው፡፡ ብሔራዊ መድረኩ ታላቅና ተያይዞ ከመውደቅ የሚታደግ የአገራዊ ህመም መፈወሻ መድኃኒት ነው፡፡
ሠላም፣ ፍቅርና አንድነት የሚፈልገው ብዙሃን ሕዝብ፣ ‹‹መቻል ምን ይከፋል፣ ሆድ ከአገር ይሰፋል›› በሚለው ብሂሉ፣ በሚያስደንቅ ትዕግስት ፣ከእነዕምቅ ጉልበቱ፣ በትዝብትና ዝምታ ተዳፍኖ መቀመጡን፡-  ከፍርሃት፣ ከዕውቀት የለሽነት፣ ቅስሙ ከፈሰሰ ወራዳ ተገዢነት ጋር አዳምረው በማሰብ በ‹‹ምን ያመጣል?›› እና በ‹‹ምን ይሆናል?›› ትዕቢት ታጥረው የሚኮፈሱና፣ ‹‹ብትቀሰቅሰው የማይሰማ፣ ፈሪ ሕዝብ›› በማለት፣ የገደል ማሚቶ ሚና እንዲጫወትላቸው በመፈለግ የሚማረሩ ሁሉ፡- የራሳቸውን ስህተትና አላዋቂነት፣ በማያዳግም ሁኔታ የሚገነዘቡበት ዕድል የሚፈጠርበት፣ ለወደፊቱም አላግባብ በተመዘበረ ሀብትና፣ እከክልኝ ልከክልህ በተገነባ ሥልጣን፣ የሚፈስ ዕምባና ደም እንደማይኖር ዋስትና የሚሰጥ፣ አገራዊና ማኅበራዊ ውል ነው፡፡
መድረኩ እንደተለመደው የከሳሽ ተከሳሽ ችሎት ዓይነት ሳይሆን፣ ኢትዮጵያ በታሪኳ አስተናግዳ በማታውቀው፣ ዐዋቂ ልጆቿ መክረው በሚተልሙት ብልሃት የሚስተናገድ፣ በልዩ የሰላምና ዕርቅ መንፈስ የተቃኘ፣ የተጎዳ በፍትህ የሚካስበት፣ በሕግ ስምና ሽፋን፣ በአዲስ ጉልበተኛ ሰቆቃ በሌላ መልኩ የማይቀጥልበት፣ ለፍቅርና ለአንድነት፣ ተከትሎም ለጋራ ብልጽግና፣ ልብ ለልብ የምንተቃቀፍበት ታሪካዊ ክንውን ይሆናል፡፡ ለዚህም አብያተ ክርስቲያናት፣ መስጂዶች፣ ዩኒቨርሲቲዎች፣ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቶች፣ አገር በቀል ግብረ-ሠናይ ድርጅቶች የመከራው ገፈት ቀማሽ ሴቶችና ወጣቶች ሁሉ ያላቸውን አንጥረው የሚያቀርቡበት ይሆናል፡፡
የብሔራዊ ጥሪው መሪዎችና አስተባባሪዎች እነማን መሆን አለባቸው (መዋቅራዊ ሁኔታ)?
የፌዴራልና ክልል መንግሥታት ሂደቱን በፋይናንስ ከማገዝ ጀምሮ ለተግባራዊነቱ የሚያስፈልጉ ህጋዊና ቁሳዊ ድጋፎችን ቢያመቻቹ፣ የዕምነትና ባህላዊ መሪዎች፣ ሙያ ማኅበራት፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣ አገር በቀል ልማት ማኅበራት፣ የንግዱ ማኅበረሰብ፣ የኪነጥበብ ሰዎች፣ ታዋቂ ገለልተኛ ምሁራን፣ ሴቶችና ወጣቶች በሰፊው የመሪነት ሚና የሚጫወቱባቸው መድረኮች፣ ከማዕከል ጀምሮ እስከ ሀገሪቱ ዳርቻዎች ቢዋቀሩ፣ አንድ ከሁሉም አካላት የተውጣጣ በ‹‹ብሔራዊ ሠላም፣ዕርቅና መግባባት›› ላይ በማዕከልነት የሚሰራ አሰባሳቢ ግብረ-ኃይል ቢመሠረት ውጤታማ ይኮናል፡፡
በተለይ አገራችን ሳትጠቀምበት፣ በማይዳሰስ ቅርስነት፣ በዩኔስኮ የተመዘገበው ባህላዊው የኦሮሞ ህዝብ የገዳ ሥርዓት፣ ሲጠቀምበት የኖረውና ያለው የቅራኔዎች አያያዝና አፈታት ሥርዓት፣ የሶማሌና የአፋር አርብቶ አደር ማኅበረሰቦች በዘመናት ተሞክሯቸው ያዳበሩት የሠላምና እርቅ ብልሃት ቢፈተሸ፣ አንቱ የተባሉ የትግራይ የአማራ፣ የደቡብና ሌሎች ማኅበረሰቦች ጠቃሚና አኩሪ፣ አቻቻይና አፋቃሪ እሴቶች፣ ከቂምና ጥላቻ በጸዳ መንፈስ፣ በበቁ አባቶችና ወጣቶች፣ ወደ መድረክ መጥተው፣ የሕመማችን ፈውስ ቢሆኑ፣ የነዚህንም ነፀብራቆች፣ ሚዲያው ለሕዝብ እያቀረበ፣ አንዱ አርዓያዊ መድረክ ለሌላው ምሳሌ የሚሆንበት፣ የተመረጠ ተሞክሮ በቂ ሽፋን እንዲያገኝ እየተደረገ፣ በሌላ በኩልም የተለያዩ የፓርቲ ቡድኖች፣ ልዩ የሚያደርጋቸው የፖለቲካ ፕሮግራም ሳይኖር፣ በብሄረሰቦች ስም ሥልጣን ለመቋደስ ሲሉ ብቻ፣ የመሰረቷቸውን የፓርቲዎቻቸውን ሠነዶች፣ ለሕዝባዊ ሂስ አቅርበው የሚከስሙበት፣ የሚቀላቀሉበትና የሚቀናጁበት፣ አግባብ ቢፈጥሩና ተያያዥ የመዋቅራዊ ሁኔታ ችግሮችም፣ በሙያዊ ሂስ ቢተቹና፣ አገራችንን እግር ተወርች ያሰራት፣ ክፉ የአስተሳሰብ አናዋዥ ድፍድፍ ቢብላላና ቢጠራ፣ አንድ እርምጃ ሳይሆን፣ ብዙ እርምጃዎች ወደፊት የመሄድ ያህል ሊያስፈነጥረን ይችላል፡፡ የምክረ-ሀሳቡ አጠቃላይ ሂደትና አፈጻጸም፣የሚጠበቀውም ውጤት፣ ምን መምሰልና መሆን እንዳለበት፣ በምሁራንና ዐዋቂዎች ተጠንቶና ተብራርቶ፣ ተግባራዊ የሚሆንበት ዕድል ቢመቻች፣ አስፈሪው የኢትዮጵያ የፖለቲካ ቀውስ፣ በነፃ ሕዝባዊ ተሳትፎ፣ ወደ አዲስና ታላቅ እመርታ እንደሚሸጋገር እምነቴ ጽኑ ነው፡፡ ያን ጊዜ እውነትም ኅዳሴ ለኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ይሆንልናል፡፡ ያድርግልንም!!

Read 1434 times