Monday, 05 February 2018 00:00

የገጣሚው ጩኸትና ውበት- በማራኪ ግጥሞች!

Written by  (ደ.በ)
Rate this item
(0 votes)

“ጥበብ፣ የከያኒውን ስሜትና ሁኔታ መግለጫ እንጂ የትክክለኛው እውነታ ቀጥተኛ ተተኪ አይደለም” ያሉት ሊቅ፣ ትዝ ይሉኛል፡፡ ምክንያቱም ጥበብ በጥሬው ሳይሆን በምናብ አድጎ፣ ስዕል ሰርቶ፣ ሙዚቃ ፈጥሮ ወዘተ … በሌላ መልክ ስለሚመጣ ነው፡፡
ለምሳሌ ዛሬ የምዳስሰውን የአሌክስ ግጥሞች ሳስብ፣ የኢ.ኤ.ግሪኒንግ ላምቦርን አባባል ብልጭ ይልብኛል፡፡
“To a poet in a lovers mood, the sea smiles with him in his joy, the winds wisper the name of his beloved, the stars look down on him like friendly eyes.”
በጥሩ ስሜት ውስጥ ሲዋኙ እንዲህ ነው፣ … ባህር በፈገግታ ደስታውን ያጅባል፣ ንፋስ በፉጨቱ ፍቅረኛውን ያቆላምጥለታል … ክዋክብት በፍቅር ዐይኖች ያባብሉታል …
በተቃራኒው ሲሆን ደግሞ ሌላ ነው፡፡ እንዲህ ይላል ግጥሙ፡-
ውብ ጨረቃ ከሰማዩ
ውብ አበባ ከመሬቱ
የጠፈር ላይ ህብረ ትዕይንት
የደመና ሰንሰለቱ
እንዲህ ሆኖ - ያምራል ህዋው
እንዲህ ሆኖ - ያምራል ሌቱ

ጠፈር ላይ ሲደንስ - ነፋሱ እያፏጨ
ሌቱ ሲጎመራ ኮከብ እየረጨ
ህይወት ባለው መዐዛ
ሠርኔን ሲዳብሰው - የአበቦቹ ትንፋሽ
ጨረቃም ነበረች
ክዋክብትም አሉ
አንቺ ብቻ ጠፋሽ
በፍቅር የተጠቀለለ ናፍቆት - ድምፅ ነው፡፡ በውብ ቃላትና ዘይቤ አሳምሮ፣ ተፈጥሮን በናፍቆት አቅፎ እሽሩሩ እያለ ነው፡፡ ሰማይና ምድርን አሳስሞ፣ ሁሉን ውበት ቀብቶታል - ገጣሚው፡፡
ነፋሱን ለድምፅ፣ ጨረቃውን ለእፎይታ፣ መዐዛውን ለሽታ … ሁሉን ደርድሮታል፡፡ ግና በዚህ ሁሉ ውበት መሀል፣ አንዳች ጉድለት አለ። በዚህ ሁሉ ፌሽታ መሀል ቅሬታ አለ፡፡ የአበባው እምብርት፣ የብርሃኑ ፀዳል የለችም፡፡
እንዲህ ነው የግጥም ከፍታ! … የቋንቋው ልዕቀት፣ የተደራሲውን ልብ ያስደንሳል፡፡ ቃላቱ ይስቃሉ፣ ዘይቤዎች ከበሮ ይደልቃሉ፡፡ ይኼኔ ነፍስ ታፏጫለች!
አሌክስ ግጥሙን አላቆመም፡፡ ይቀጥላል …
ትዝ ይልሽ እንደሆን - ከዕለታት ባንዱ ቀን
እንዲህ ነበር ያልሺኝ
“ፍርሀት ማዕበል ሆኖ - ከውስጥ እየገፋኝ
ሲያንኳኩ ስዘጋ - ሲሄዱ ሲከፋኝ፣
ስጋት ያቆመውን
አጥሩን ይፈሩና - “ተዘግቷል” እያሉ
ከእውነት ጋር ተላልፈው
በይሆናል ጓሮ “ፀሐዮች” ያልፋሉ፡፡
# አየህ …
ድሮ በበግ መንጋ
ነጣቂ እንዳይገባ
በምናልባት ዐይንህ - ተኩላ ታስሳለህ፣
ዛሬ አውሬዎች በዝተው
ከተኩላ ጉባኤ በግ ትፈልጋለህ፡፡”
#ያልሺኝን እያሰብኩ …
በአስቀያሚ እጆቹ ፍርሃት እያቀፈኝ
የብዙ ከዋክብት
ብዙ ዓይነት ብርሃን - ሳልሞቀው አለፈኝ፡፡
ትዝታው በደመቀው ህዋ ውስጥ መጥቶ፣ በሚያስፈራ ጥፍሩ ሊቧጭረው ነው፡፡ አሁን ካለው ፀዳል ይልቅ የኋላው ድምፅ፣ ከዛሬው ትዕይንት ወዲያ የትዝታው መረዋ ልቡን ሊያሸብረው ነው። አበባው ከጀርባው ጥላ አለ፤ ጨረቃዋ ደመና ሊያሥራት ነው፤ ሁሉም ነገር ሊሸሽ ነው፡፡ የዚህ ሁሉ መነሻ ግን ያቺ ገፀ - ሰብ ናት፡፡ ያቺ ባህርይ ናት፡፡ ህይወት አድማቂ፣ ስሜት ሰራቂም ያው እርሷ ናት፡፡
ፍርሃት ፍርሃት ብሎታል - ተራኪው፡፡ እንባው አይታይም፣ ሳቁ ግን ተሰርቋል፡፡ በነዚህ ሁሉ ኮከቦች መሀል ሆኖ፣ ነገውን የመነተፈው ትዝታ አለ፡፡ የትዝታው እናትና እመቤት ደግሞ ያቺው ፍቅር ሰገነቱ፣ ያቺው የህይወቱ ውበት ማማ ናት፡፡ የርሱ ዐለም እርሷ ናት፡፡ የርሱ ሳቅ እርሷ ናት፡፡ የርሱ ወጥመድም ራሷ!
ሰዐሊው ናት፡፡ ነፍሱ ሰሌዳ ላይ የዘረጋችው ሸራ፣ የቀባችው ቀለም አለ፡፡ ብዙ በጎች መካከል ይገኙ ስለነበሩ ጥቂት መንጋዎች አሳይታው ሳያበቃ፤ ወደፊተኛው ዘመን ደግሞ በብዙ ተኩላዎች መሀል በግ የመፈለግ ፍዳ እንዳለ አሳይታዋለች፡፡ … በዚህ ፈርቷል፡፡ በዚህ ነፍሱ ሸሽቷል፡፡
ግጥሙ በታሪክ ውስጥ ታሪክ ይዟል፡፡ ስለዚህ እንዲህ ይላል፡-
ደመናው ህዋ ላይ … ጥሩ ምስል ሳለ
ከክዋክብት ጥቅሻ
ነፍስን የሚገዛ - ውበት ኮበለለ
ሁሉም ነገር ነበር
ሁሉም ነገር አለ፣
አንቺ ሥትቀሪ ግን - ያ - ውበት ጎደለ፡፡
(የደበበ ሰይፉን ግጥም ያስታውሳል፡፡)
ብትቀሪ ጊዜ
የጣልኩብሽ ተስፋ
እኔን ይዞኝ ጠፋ፡፡
…ዓይነት ስሜት አለው፡፡ ተፈጥሮን፣ ማለትም ደመናን፣ ሰማይን፣ ክዋክብትን፣ ፀሐይን በማንፀር፣ ረቂቁን በተጨባጭ ለማግዘፍ የሞከረ ገጣሚ ነው፡፡ ለዛና ውበቱም ሰርግ ቤት አስመስሎታል፡፡ ሁሉ አለ … ሙዚቃው፣ ሥዕሉ፣ ድግሱ ሁሉ፡፡
ግና “Emotion must be translated into music and visual images, clear and beautiful” ያሉትን በምልዐት ማምጣት ይችል ይሆን? ማን ያውቃል!
አሌክስ ወደ ዘመኑ ፊቱን አዙሮ፣ አንዳች ወቀሳ የሚያቀርብበት ግጥምም አለው፡፡ ልብ የሚነካ፣ ስሜት የሚቆሰቁስ ይመስለኛል፡፡ ይህን የዘመኑን ቀውስ ምን አመጣው? .. የማህበረሰቡን መልክ ምን አጨቀየው? የቆየ ውበቱን፣ የኖረ ሥርዐቱን ምን ነጠቀው? ብሎ ማጥናት፣ የስነ ልቡና ምሁራን የቤት ስራ ቢሆንም፣ ከያኔው አመዱን እፍ ብሎ፣ ረመጡን መቆስቆስ አለበትና እንዲህ ቆስቁሶታል፡-
ሰው ከክብሩ ይልቅ - ስጋውን ወደደ
ሞራሉን አንጥፎ
ኩርማን ለመቀበል - ሰግዶ ተራመደ …
(ይለኛል ይህ ዘመን)

የታል የአንቺ ሚና…?
“ሴት የላከው … ጅብ አይፈራም..”
ሲባል ነበር - እኔ ‘ማቀው
ታዲያ ይህን ዕውነት
ዛሬ ምን ወሰደው - እሺ ማን ደበቀው?
አሁን - ላይ!
ሺህ ጊዜ - ብትልኪኝ
ሺህ ጊዜ - እቀራለሁ
ካንቺ ትዕዛዝ ይልቅ - ጅቡን እፈራለሁ፡፡
# ለምን?!
ጅቡን ደጅ ላይ ያሰረው ምን እንደሁ ባናውቅም፣ ተራኪው የፈራው ነገር አለ፡፡ ያንን ፍርሃት የሚሰብር የፍቅር አቅም የለኝም፣ የፍርሀቱን ሰንሰለት የሚበጥስ የፍም ኮረት አላኖርሺም፣ እያለ ወደ ጎን የሚወቅሳትን የሚከሳት የፍቅር ተካፋይ አለች፡፡ ፍቅሯ ለምን ቋት አልሞላም? … ለምን ቅጥር አልዘለለም? የሚለውን አንባቢው ይፈትሽ! .. አንባቢው እያንዳንዱን ሰገነት ያሥሥ… የያንዳንዱን ሀሳብ ደጅ ያንኳኳ! … ያኔ ይከፈታል፡፡ …
ብቻ ዘመኑንን ወደ ጥበቡ ሰፈር ስንመጣ፣ ሰዐሊውን ከእነ ሥዕሉ፣ ደራሲውን ከእነ ድርሰቱ፣ ገጣሚውን ከእነ ግጥሙ የምናገኝበት ገበታ ተዘጋጅቷል፡፡ ሁሉም ሰው የማተሚያ ቤት ደጅ ካልረገጠ፣ ሥራው የማይታይበት፣ ጽሑፉ የማይነበብበት ጊዜ አልፏል፡፡ አሁን አዲስ ዘመን፣ አዲስ ቴክኖሎጂ ዓለምን እጅ ለእጅ አጨባብጦ፣ እንዲህ ያሉ ግጥሞችን የሚያስነብቡ፣ ሥዕሎቻቸውን የሚያሳዩ ወጣትና አንጋፋ ጥበበኞች በፌስ ቡክ እናገኛለን፡፡ … የዘመኑ ቴክኖሎጂ ትሩፋት!!

Read 976 times