Monday, 05 February 2018 00:00

“ከመጋረጃ ጀርባ”- ዘመኑን ነቃሽ ቲያትር

Written by  በታምራት መርጊያ
Rate this item
(1 Vote)

  ኪነጥበብ  ለአንድ ሐገር የሚኖረው በጎ አስተዋጽኦ እጅግ ከፍ ያለ መሆኑ አያጠያይቅም። ባንድ ጎኑ፤ የገሐዱን አለም  ማሕበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ በጎ ጎኖች አጉልቶ በማሳየት፥ ማሕበረሰባዊ በጎነቶች እንዲያብቡ ሲያደርግ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ማሕበረሰባዊ ህፀፆችን ነቅሶ በማውጣትና በመለየት እንዲወገዙና እንዲተቹ (Naming and fuming) ያደርጋል። በሌላ በኩል ድምፅ አልባ ለሆነው ማህበረሰብ፣ ውስጡን የሚያብጠውን መከፋቱን፣ ብሶቱን፣ ሕመሙን፣ ስቃዩንና ጭንቀቱን ወዘተ... አጉልቶ በማሰማት፤ ድምፃቸው መሰማት ላልቻለ የሕብረተሠብ ክፍሎች ድምፅ (voice of the voiceless) በመሆን ረገድ የሚኖረውም እጅግ የላቀ ሚናና አበርክቶ አሌ የሚባል ጉዳይ አይደለም።
በርግጥ ኪነጥበብ እጅግ ሰፈና ብዙ ፈርጆች ያሉት ሲሆን ቲያትርን፣ ሙዚቃን፣ ስነጥበብን ወዘተ... የሚያቅፍ ሰፊ የማሕበራዊ ሳይንስ ዘርፍ ነው። ይሁንና ለዚህ ፅሁፍ መነሻ የሆነንና በተለየ ትኩረት ለመመልከት የወደድነው፣ ሰሞኑን በአንጋፋው የሐገር ፍቅር ቲያትር ቤት መታየት የጀመረውን “ከመጋረጃ ጀርባ” የተሰኘ አዲስና ቀልብ ሳቢ ቲያትር ነው፡፡  ስለዚህም ለፅሁፉ ግብአት ይሆነን ዘንድ የቲያትር ጥበብ ላይ ትኩረት አድርገን፣ በሐሳብ ወደፊት ለመዘርጋት እንሞክር።
የቲያትር ባሕል  (theatrical culture) በጥንታዊቷ ግሪክ ከክርስቶስ ልደት በፊት ከ700 ዐመተ ዓለም ጀምሮ፣ በወቅቱ የዓለም የፖለቲካና የወታደራዊ ሐይል ማዕከል በነበረችው አቴንስ ከተማ ውስጥ እየተስፋፋ መምጣቱን የታሪክ መረጃዎች ያመለክታሉ። በዚህ ወቅት ተቋማዊ አደረጃጀት ይዞ ይታይ የነበረውም ግሪኮች ዳያኦንዚያ (Dionysia) የሚል ስያሜ ሰጥተውት በነበረውና ዳይኖይሱስ (Dionysus) የተባለን ጣኦት ለማክበር ያካሂዱት በነበረ ክብረ በዐል (festival) ላይ እንደነበረም ይነገራል። እንግዲህ ዓመተ ፍዳ አልፎ፤ ዓመተ ምሕረቱ ከገባም በኀላ ቢሆን እድገቱ እየተስፋፋ የመጣው የቲያትር ጥበብ መነሻ ታሪካዊ ዳራ፣ እጅግ በጥቂቱ እንዲህ ይመስል እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ይገልፃሉ። ለመንደርደሪያ ይህን ካልን፣ የዛሬ ጉዳያችን ወደሆነው  “ከመጋረጃ ጀርባ” ቲያትር ጉዳይ እንመለስ።  የዚህ ቲያትር ወጣኒና ደራሲ ቶፊቅ ኑሪ ሲሆን፤ አዘጋጁ ደግሞ ዳግማዊ አመለወርቅ ፈይሳ ይባላል። በቲያትሩ ላይ እንደነ ፍቃዱ ከበደና ይገረም ደጀኔ ያሉ ነባር ተዋናዮችም  እንዲሁም ሌሎች ወጣቶችም ይተውኑበታል።
ቲያትሩ ወቅታዊውን የኢትዮጵያ የፖለቲካና ማሕበራዊ ነባራዊ ሁኔታ ቁልጭ አድርጎ ያሳያል። አሁን በሐገራችን ስር ሰዶ እርስ በእርስ የሚያናክሰንን የዘውገኝነት ወይም የአክራሪ ብሔርተኝነት አዝማሚያና ዝንባሌ እንዲሁም የሚያስከትለውን መዘዝና የጋራ ዉድቀት አዙሪት በጉልህ በማሳየት፤ ከዘውገኝነትና ከጎሰኝነት በፀዳ መልኩ በኢትዮጵያ በብዝሐነት ላይ የተመሠረተ አንድነትን እንዴት ማስፈን እንደሚቻል፥ ብሎም በልዩነት ውስጥ የሚኖርን አንድነትና ውበት በምክረ ሐሳብነት ያቀርባል፡፡ ለዚህም ነው ኪነጥበብ እንደ ሌሎች የሳይንስ ዘርፎች ሁሉ ማሕበረሰባዊም ይሁን ፖለቲካዊ በጎ ሚና ይኖረዋል የሚባለው። በተለይም ቲያትርም ይሁን ሌሎች የኪነጥበብ ፈርጆች፤ ወቅታዊ ሁናቴዎች፣ ቦታንና ተመልካችን አገናዝበው፥ ያለ አንዳች መደመርና መቀነስ፣ ጉዳዮቻችንን በግልፅ በማንሳት፣ የመፍትሔ አቅጣጫዎችን ማመላከትና ማቅረብ ሲችሉ፤ ፋይዳቸው የነጭና ጥቁር ያህል በግልፅ  መታየት ይችላል። ይህንን ሐሳብ የሚያጠናክርልን እውቁ የማሕበረሰብ ሳይንስ ሊቂ ሶሲዎሎጂስቱ ኧርቪንግ ጎፍ ማን ነው። ጎፍ ማን፤  ድራማቱሮጂካል ባለው ንድፈ ሐሳቡ ማጠንጠኛ ላይ፥ የሰው ልጆች ባህርይና አጠቃላይ ሰዋዊ መስተጋብር፤ በጊዜ፣ በቦታና በተመልካች ላይ ጥገኛ ተባራይ (dependent domain) መሆኑን ያመለክተናል (elements of human interactions are dependent upon time, place, and audience)።
ለዚህ ነው ይህን ቲያትር የሰሩ ባለሞያዎች በእጅጉ ሊመሰገኑ የሚገባቸው። ዳሩ ምን ያደርጋል እንዳለመታደል ሆነና፣ በኛ ሐገር ያጠፋን የመተቸት እንጂ በጎ የሰራን የማመስገን  ባህል እምብዛም ያልተለመደ ነው። በአንፃሩ በሠለጠነው የምዕራቡ ዓለም፥ በማንኛውም መልክ በጎ ምግባር የሰራን ሰው ማድነቅና እውቅና መስጠት የተለመደ የስልጣኔ መገለጫ ነው። ለምሳሌ እንግሊዞች “የናንተ ምርጥ የኪነጥበብ ሰው ማነው?” ተብለው ሲጠየቁ፣ ታዋቂው ገጣሚያቸው ጆን ሚልተን እንደሆነ አስረግጠው ይናገራሉ። “ እንዴ እውቁን ዊሊያም ሼክስፒርን ወዴት አድርጋችሁት ነው?” የሚል ካጋጠማቸው ደግሞ፤ “እርሱማ የአለም ምርጥ ነው!!” ብለው በእርግጠኝነት ይመልሳሉ። ምዕራብያኑ በዚህ መልኩ የራሳቸውን ድንቅ ስራ የከወነ ሰው፣ ዕውቅና እየሰጡና እያንቆለጳጰሱ  ምርጦቻቸዉን ያጎላሉ።
እነ ቶፊቅ ኑሪ በቲያትራቸው ላይ ገላልጠው ያሳዩን በብዝሐነት ውስጥ ያለ ልዩነትን ያለማክበር መዘዝና በልዩነት ውስጥ ሊኖር የሚገባው መደማመጥ፣ መከባበር እንዲሁም አንድነት፤ ለወቅታዊው የሐገራችን ሁኔታ መፍትሔ ለማምጣት ግብአት ከመሆን ባለፈ፥ በርከት ያሉ አዎንታዊ ትሩፋቶች የሚኖሩት እንዲሁም አርአያነቱ እጅግ ከፍ ያለና ሊበረታታ የሚገባው ነው። የሆነው ሆኖ ግን ሙሉ በኩሌ የሚባል ምድራዊ ነገር የለምና፥ በእነ ቶፊቅ ኑሪ “ከመጋረጃ ጀርባ” ቲያትር ላይም የተወሰኑ ሊጠቀሱ የሚችሉ የይዘትና የአቀራረብ ውስንነቶችን ታዝበናል፡፡ ከዚህ አንፃር በቲያትሩ ላይ በዋነኛነት በይዘት ዉስንነት ሊነሳ የሚገባው አብይ ጉዳይ ውክልና (Representation) ነው። ይኸውም በቲያትሩ ከሰማንያ ብሔሮች በላይ መኖሪያ የሆነችው ኢትዮጵያ፤ የተወከለችው በአራት ብሔረሰቦች ማለትም፦ ኦሮሞ፣ አማራ፣ ትግሬ፣ ጉራጌና ከተሜ (urban society) ብቻ መሆኑ አንዱ ነው። ይኽም በኢትዮጵያ ገዢ ፓርቲ ኢህአዴግ ላይ የሚነሳውን የሌሎች ብሔሮችና ብሔረሰቦች የውክልና ጥያቄ እጥረት ጉዳይ በተመሳሳይ የሚያስነሳ ሆኖ እናገኘዋለን። ከዚህ አንጻር ቲያትሩ ሰማንያ ብሔሮችና ብሔረሰቦች አቅርቦ ማሳየት ይችላል ባይባል  እንኳን፥ ቢያንስ በተወሰነ ደረጃ ያልተወከሉትን ብሔረሰቦች በጥቅል ውክልና ስነባህርይ ወይም ካራክተር (character) ፈጥሮ ሊያሳየን ይገባ ነበር።
በሌላ በኩል ከመፍትሔ አቀራረብ (solution approach) አንፃር፣ ቲያትሩ ሊያሳየን የሚሞክረው በእውኑ አለም በተጨባጭ ሊተገበር የማይችለውንና በተለያዩ የማህበረሰብ ሳይንስ ሊቃውንት በእጅጉ የሚተቸውን “የቶማስ ሙሬ”  (Thomas More) ተምኔታዊና (utopian approach) ምናባዊ የችግር አፈታት፤ መሬት ላይ ሊወርድ የማይችል የምናብ ዓለም መፍትሔን ነው፡፡ በነገራችን ላይ ተምኔታዊ አቀራረብ (utopia approach) ሐሳባዊና እንከን አልባ ማሕበረሰብ የመፍጠር ሒደት ነው (an imagined community or society that possesses highly desirable or nearly perfect qualities for its citizens)።
በተጨማሪም የተምኔት ዓለም እንከን አልባ ሆኖ የሚቀረፅ ሲሆን፤ ፍፁም ችግር አልባ የምናብ አለም ነው (utopia is a perfect “place” that has been designed so there are no problems)። በመሆኑም ችግሮችን በተወሰነ ደረጃ ቀርፎና፥ ልዩነቶችን አቻችሎ መኖር ይቻል እንደሆነ እንጂ፥ ፍፁም ችግር አልባ ማሕበረሰብ የመፍጠር ሐሳብ በተለይም እንዲህ እንደ ኢትዮጵያ በሕብረብሔረ ጥንቅር የቆመ ሐገር ውስጥ ሐሳባዊ ከመሆን ያለፈ፥ ተጨባጭ የመሆኑ ነገር በእጅጉ አጠራጣሪ መሆኑ ልብ ሊባል ይገባው ነበር። የሆነው ሆኖ፤ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በሐገራችን የፊልም ስራዎች መበራከትን ተከትሎ፣ የቲያትር ተመልካች ቁጥር ተመናምኖ መቆየቱ በዘርፉ ባለሞያዎች ተደጋግሞ ሲነሳ ይሰማል። እጅግ የሚገርመው ነገር ደግሞ በአንድ ጀንበር በየጓዳው ከህፃናት ተረት ተረት የማይሻሉ እስክሪፕቶች አንደ አሸን ተፅፈው እያደሩ፥ “ጠዋት ተመርቶ ከሰዓት መርካቶ” እንደሚባለው በቅፅበት ወደ ፊልምነት የሚቀየሩ ፊልሞች የቀረቡለት የኢትዮጵያ ተመልካች፤ እንዲህ ከፍተኛ እውቀትና ለቅንጣት ስህተት የማይመች የመድረክ ብቃት ከሚጠይቀው የቲያትር ጥበብ ይልቅ እነዚህን ፋይዳ ቢስ ፊልሞች በመምረጥ፣ የቲያትሩን አለም ባይተዋር አድርጎት መቆየቱ ግራ የሚያጋባና እራሱን የቻለ ጥናት የሚጠይቅ ጉዳይ ነው።
በነገራችን ላይ ይህ አገላለፅ፣ ደረጃቸውን ጠብቀው የተሰሩና ፋይዳቸው የጎላ የፊልም ስራዎችን እንደማይወክል ልብ ይሏል። ግን እንደ ከመጋረጃ ጀርባ ያሉ ቲያትሮች በብዛት ቢሰሩ፤ ከቲያትር መድረክ የኮበለለውን ተመልካች መልሶ ለመሳብ እንደሚቻል ማንሳቱ ተገቢ ይሆናል።
ለማጠቃለል ያክል፥ ኪነጥበብ በአግባቡ የሚጠቀምበት እውነተኛ የኪነጥበብ ሰው ሲያገኝ፣ ምንም ነገር ለማድረግ የሚያስችል እጅግ ከፍተኛ አቅም ያለው የእውቀት ዘርፍ ነው። በኪነጥበብ እነ ሼክስፒር ከሐገራቸው አልፈዉ አለምን ቀይረውበታል። የሬጌው ንጉስ ቦብ ማርሌ ደግሞ የተጣሉና አይንና ናጫ የነበሩ የሐገራቸውን ፖለቲከኞች አስታርቀው፣ ለሐገራቸው ሰላምን ማውረድ ችለዋል። በሐገራችንም  የቀደሙትን ትተን፣ የጊዜያችን እንቁና እውቅ ከያኒ ቴዲ አፍሮ የተመለከትን እንደሆነ ሰላምን፣ አንድነትን፣ ፍቅርንና እርቅን በኪነጥበብ በመስበክ፣ የበኩሉን በጎ ሚና በመጫወት፣ የራሱን አሻራ በማኖር ላይ ይገኛል። ከዚህ ሁሉ መረዳት የሚቻለው ኪነጥበብ በየፈርጁ ማሕበራዊ በጎነትን ለማምጣት ያለውን ግዙፍ አቅም ነዉ። ሶሲዎሎጂስቱ ኧርቪንግ ጎፍ ማን እንደሚገልፅልን፤ የቲያትር ጥበብ ደግሞ ዘይቤ ነው (theatre is a metaphor)። በገሃዱ አለም ሁሉም ሰው ከሌላው ሰው ጋር በሚኖረው መስተጋብር ተዋናይ ነው። ትወናውን የሚያቀርበውም ማሕበረሰባዊውን ባሕልን፣ ልምድንና እምነት ጠብቆ ነው። ነገር ግን ሁሉም ትወናውን ጨርሶ ከመጋረጃ ጀርባ ሲገባ፥ እውነተኛ ማንነቱን ይላበሳል። ያን ግዜ ከመረጃው ጀርባ ያለውን እውነተኛ ማንነቱን ስንመለከተው፣ የሰውየውን ትክክለኛ ካራክተር እንረዳለን።
ከመጋረጃ ጀርባ ቲያትርም፥ ከላይ የተጠቀሱት ውስንነቶች እንደተጠበቁ ሆኖ፤ የቱንም ያህል ሠላም ነን፣ አንድ ነን፣ አልተለያየነም ብንል፤ አሁን ሀገራችንና ሕዝቦቿ ያለንበትን ነባራዊ ሁኔታ ከመጋረጃ ጀርባ ያለውን ነባራዊ እውነታ፥ ከመጋረጃ ፊት ስቦ አምጥቶ፤ ተጨባጭ አገራዊና ነባራዊ ሁኔታን በሚገባ (real existing) ገላልጦና አፍታቶ ለማሳየት የሚደረገው ጥረት በእጅጉ ሊደነቅ የሚገባው ነውና ደራሲውና የቲያትሩን አባላት ማመስገንና ማበረታታት ይገባል።

Read 1959 times