Monday, 05 February 2018 00:00

የእንባ ኳሶች

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(0 votes)


   እንደ ሀኪም አይደለም፤ እንደ ፖለቲከኛ ነው። የመጻህፍት ምርጫው ሳይቀር ለሚያውቁት ግር ያሰኛል፡፡ “አንተ ሰው በስልሳዎቹ ብትወለድ ጥይት ይበላህ ነበር!” ይሉታል፡፡ ይስቅና ያልፋል፡፡ መጽሐፍ ሲመርጥ፣ የኢህአፓ፤ የመኢሶን የደርግ--- ነው፤ ፖለቲካውን ሁሉ ያግበሰብሳል፡፡ ልብወለድ አይወድም፤ ቅዥት ይመሥለዋል፤ እንደ ሥራ ፈትነት ይቆጥረዋል፡፡  
ጎምላላ ቁመናው ከነጭ ጋወኑ ጋር ጥሩ ግርማ ቢሰጠውም ብዙ ጊዜ ይከፋዋል፤ ይተከዛል። ህመምተኞቹን በሚገባ በመንከባከቡ ስም ወጥቶለታል፡፡ አልማጭ አይወድም፡፡ ስንፍናን ይፀየፋል፡፡
“ዛሬ ደሞ የማንን መጽሐፍ ይዘሃል?”
“የኢህአፓ መጽሐፍ አድነህ ማንበብ ነው፣ መቼም?”
“የጓድ መንግሥቱንም አንብቦልህ የለ?”
“የቱን…ትግላችንን?”
ጓደኞቹ ተሳስቀው ሄደዋል፡፡ የሌሊቱን አጋማሽ ያህል አንብቦ፣ ኢትዮጵያ ስለምትባል ሀገር እየበሸቀ አድሮ ነበር የመጣው፡፡ ለዚህ ብሶቱ ሁለት ሲኒ ቡና ግጥም አድርጎ፣ ጭንቅላቱን ዘጋው፡፡
ታካሚዎችን በየተራ እያስተናገደ፤ እየመረመረ፣ ውሎ ወጣና፣ ቴሌቪዥን ሲመለከት፤ አሁንም ስለ ግርግር፣ አሁንም ስለ ረብሻ መወራቱ አመመው፡፡ መቼ ነው ከዚህ ሠንሠለት ሰብረን የምንወጣው?... ደርግ ንጉሡን ገደለ፤ ደርግን ኢህአዴግ ገደለ?... አሁን ደግሞ እርሱን ለመግደል… ከዚያስ?... እስከ መቼ…. ባንድ እጃችን ከፈረንጆች ዳቦ እየለመንን፣ በሌላው ጠመንጃ ይዘን፣ ወንድማችንን እየገደልን እንዘልቃለን?... ሳያስበው እንባው በጉንጩ ፈሰሰ፡፡… እስከ መቼ እንገዳደላለን?... እስከ መቼ እንራባለን?... እስከ መቼ የፈረንጅ እጅ እያየን እንኖራለን?... አያቶቻችን ከፈረንጅ ለመኑ፣ አባቶቻችንም ለመኑ፣ ዛሬም እኛ እንለምናለን... ነገም ልጆቻችን እንዲለምኑ እያመቻቸን ነው…
ጓደኛው መጣ፡፡… ዶክተር እስክንድር፡፡
“ምነው ፍቅሩ?... ምን ሆነሃል?...ሴንሲቲቭ አትሁን!...ፊትህ ትክክል አይደለም”
“ምንም አልሆንኩም!” አለና፣ለመነሳት ሞከረ፡፡
“ምን ላምጣልህ?” አለች፤ ፍልቅልቅ የክበቡ አስተናጋጅ፡፡
“በቃኝ!...ፍቅሩ፤ የሆነ ነገር ውሰድ!”
“ጠጥቻለሁ ቡና!”
“አትቆዝም!... እስቲ ዛሬ ምሣ ልጋብዝህ?”
“በልቻለሁ!”
“ኦ…ኬ ለሌላ ጊዜ አዛውረዋል፡፡ ግን keep your self safe!”
“ተወው እባክህ!... በእሣት ውስጥ ተወልደን፣ በእሣት ያደግን፤ በእንባ ተቀቅለን፣ የቆሰልን ነን፡፡..ጡጦና ደም እየተጋትን የኖርን ነን፡፡ መች እጣን አሸተትን! ..መች ሽቶ ታደልን… ባሩድ እየታጠንን አይደል እዚህ የደረስነው፡፡ የወላጆቻችን ደም ላይ የበቀል እርም እየበላን ኖረን፣ እኛም ለልጆቻችን ይህንኑ እርም ልናወርስ ነው፡፡… ግራ ገባኝ፤ አክሱም የማን ነበር?... ላሊበላን የሠራው ማነው?... ፋሲል ግንብ? የጢያ ትክል ድንጋይ…ቅዥት ነው?... በአስማት የተሠራ? በመልዐክት የተተከለ ነው…?
እና እኛ በማን ወጣን?...ከማን መጣን?…ያ ጥበብ የት ሄደ? ያን ህልም ማን ሠረቀን?... “አባትህ እውነት አንተን ወለደ?” ያለው እውነት ነው፤ ገጣሚው፡፡
ጓደኛውን ተሠናብቶ ሲሄድ እናቱ ትዝ አሉት። እንጀራ ጋግረው ሸጠው ነው ያሣደጉት፤ አንድ ወንድሙ  አሜሪካ ነው፡፡ ሌሎቹ ሞተዋል፡፡ አራት ነበሩ፡፡ ሁለቱ መታከሚያ አጥተው ነው የሞቱት። ሀኪም የሆነው በዚያ በቀል ነው፡፡ በዚያ ቁጭት ነው፡፡
አንድም ሰው አልረዳውም፤ አባቱ መምህር ነበሩ፡፡ አለታ ወንዶ መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የቋንቋ መምህር፡፡ እናቱም ያገቧቸው ገጠር ውስጥ መምህር ሆነው ሲሠሩ ነው። በሠርግ አላገቧቸውም፤… ምግብ ሊያበስሉላቸው፤ እንደ ሠራተኛ ከቀጠሯቸው በኋላ ወደዷቸው፡፡ በፀባይ፣ በሙያ ተሥማሟቸው፡፡ አንሶላ ተጋፈፉና የመጀመሪያ ልጃቸውን መለዱ፡፡ ከዚያ በኋላ እንዴት እንደሆነ አያውቁትም፤ ትዳር መሥርተው በልጆች ተከብበው ራሳቸውን አገኙት፡፡
አለታ ወንዶ ገብተው፤ እናትየው ትንሽ ተማሩ፤ አባትየውም ጥሩ ኑሮ ጀመሩ፡፡… አብዮት ፈነዳና ፍንጥርጣሪው ነካካቸው፡፡ ምቾት የሚሰጣቸው መሥሏቸው ነበር፡፡ አልተሣካላቸውም፡፡ ከነከናቸው፡፡ ቀነቀናቸው፡፡ እና ሳያሥቡት አንዱ ቡድን ውስጥ ተገኙ፡፡ ከዚያ ብዙ አልቆዩም፡፡ ነጋሽ የሚባል ሰው ነፍሳቸውን ነጠቀው፡፡ የአብዮቱ ጠላት አድርጎ ሠለባቸው፡፡
እናቱ ሁሌ “ነጋሽ፤ ፈጣሪ የጅህን አይንሣህ!” ሲሉ ያስታውሳል፡፡ “ነጋሽ” ለርሱ ቀፋፊ ሰው ነው። ደ’ሞ ብዙ ጊዜ መጻሕፍት ውስጥ ያገኘዋል። ሰውነቱን ይወርረዋል፡፡ ልቡን ይነክሰዋል፡፡ አባቱንም ባይነጥቀው፤ ያንን የጉስቁልና ዘመን  አያሣልፍም ነበር፡፡ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ቀዳዳ ጫማ አድርጎ አይማርም ነበር፡፡ ሣሙና መግዣ እያጣ አይባትትም ነበር፡፡… ግን ደግሞ ደጉ ፈጣሪ ዶክተር ሰለሞን የሚባሉ መምህሩን አስነስቶለት፣ በመጨረሻዎቹ አመታት፣ ሁሉም ነገር ተሟልቶለት ጨርሷል፡፡ ግን ምን ያደርጋል፤ የዶክተር ሰለሞንን ውለታ ሳይመልስ እርሳቸውም- ሞቱ... ህይወት ብሽቅ ናት!... ፎቃቃ!..
አንድ ሁለቴ አዛጋና ድልህ የመሠሉ ዐይኖቹን አሻሽቶ ወደ ሥራ ገባ፡፡
ስለ ታካሚዎች የደረሰውን መረጃ እያየ - እያነጋገረ፣ ምርመራ እያዘዘ፣ ጥቂት ቆየ፡፡
ከሰዓት በኋላ አራት የጉበት ታማሚዎች አስተናግዶ ሲያበቃ፣ ሌሎች ሁለት ወንዶች መጡ። ሁለቱ የኩላሊት በሽታ ተጠቂዎች ናቸው፡፡ የመጨረሻውን መረጃ ሲያይ ኩላሊቱ ተጠቅቷል፡፡
“በምን የተነሣ ተጎዳህ?”
“ከጤና አጠባበቅ ችግር ነው!”
“ለምን? ጤናህን አትጠብቅም?” ሊለው ነበር፤ ልብሱን አየና ገባው፡፡ ከዚያ ሥሙን ከፍ ብሎ ተመለከተ፡፡ እንደ እሣት ቦግ ቦግ የሚሉ ቃላት ሆኑበት፡፡ “ነ-ጋ-ሽ ታሪኩ!” ምን እንደነካው አያውቅም፤ ከወንበሩ ወድቆ ተዘረረ፡፡
“አይዞህ…አይዞህ… አይዞህ- ፍቅሩ” አለ፤ ዶክተር እስክንድር፡፡
“ምንድነው? ምንድነው?”
አፋፍሰው አነሱት፡፡
“እሱ ያባቴ ገዳይ፣ ሊታከም እኔ ጋ መጣ” ሲለው ክው አለ፡፡ ታካሚው ዓይኖቹን በልጥጦ ቀረ፡፡
“ያባቴ ገዳይ!” አለው፤ ዶክተር ፍቅሩ፡፡

Read 737 times