Print this page
Saturday, 03 February 2018 12:56

የማህጸን መንሸራተት …

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ /ከኢሶግ/
Rate this item
(1 Vote)

  ከጥር 1-3- ድረስ የእናቶች ደህንነት ማለትም (Safe motherhood) በሚል በአገራችን በኢፊድሪ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስተባባሪነት እና ሌሎች አጋር ድርጅቶች ተሳትፎ የሚከበር መሆኑን ባለፉት ህትመቶች ማስነበባችን እሙን ነው፡፡ የኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበርም የእናቶችን እና ጨቅላዎቻቸውን ደህንነት በመጠበቁ ረገድ ያላሰለሰ ጥረት የሚያደርግ በመሆኑ እነሆ ለአንድ ወር ያህል በጉዳዩ ዙሪያ ግንዛቤ እንዲሰፋ ለማድረግ የበኩሉን በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ በተለይም ‹‹ ለጤናማ እናትነት ይብቃ ማርገዝ በአፍላ ወጣትነት›› በሚለው መርህ መሰረት በልጅነት ጋብቻ ፈጽመው ሰውነታቸው ሳይጠና ለማርገዝ የበቁት አፍላ ወጣቶች የደረሰባቸወን ሕመም በተከታታይ አስነብበናል፡፡  በዚህ እትም ደግሞ ከዛ ወጣ እንልና እናቶች ስለሚደርስባቸው የማህጸን መንሸራተት በአሰላ ሆስፒታል ቆይታችን ካገኘናቸው ሐኪም እንዲሁም ታካሚዎችና ቤተሰቦች ያገኘነውን እውነታ እናስነብባችሁዋለን፡፡
የእናቶች ደህንነት ሲባል በተለይም ከእርግዝናና ከልጅ መውለድ ጋር በተያያዘ እንደሚገለጽ እሙን ነው፡፡ እናቶች በቁጥር በርከት ያለ ልጅ ከመውለድ እና ጫና ያለው ስራ ከመስራት ወይንም በምጥ ጊዜ በሚፈጠረው ከፍተኛ ግፊት እንዲሁም ሌሎች የጤና ሁኔታዎች ጋር በተያያዘ የማህጸን መንሸራተት ይደርስባቸዋል፡፡ ከዚህ በታች የምትመለከ ቱት ምስል በመጀመሪያ ጤናማው የማህጸን አቀማመጥ ሲሆን ተከትሎም ማህጸን ተንሸራተተ ሲባል ምን ማለት እንደሆነ የሚያሳይ ነው፡፡
‹‹…እኔ እድሜዬ ወደ 25/አመት ነው፡፡ አሁን የወለድኩት 2ኛ ልጄን ነው፡፡ ነገር ግን ሁለተኛዋን ልጅ በምወልድበት ጊዜ ያማጥኩት በቤቴ የነበረ ሲሆን በሁዋላ ግን መወለድ ስላልቻለ ወደሆስፒታል ሄጄ በኦፕራሲዮን ተገላግያለሁ፡፡ከወለድኩ ጀምሮ ግን ጤና አይሰማኝም፡፡ በብልቴ በኩል በጣም አየር ይወጣኛል። ስቀመጥ ወደላይ የሚገፋኝ ነገር አለ፡፡ ባጠቃላይም ይከብደኛል፡፡ ስለዚህ ወደሐኪም ቤት ስመጣ ግን ማህጸንሽ ተንሸራቶአል አሉኝ፡፡ አሁን ሐምሊን ኢትዮጵያ ፊስቱላ ሆስፒታል ሕክምና እየተደረገልኝ ነው፡፡…››
ከላይ ያነበባችሁት የአንዲት ታካሚ ምስክርነት ነው፡፡ እናቶች የማህጸን መንሸራተት ለምን ይደርስ ባቸዋል? ምን ማለትስ ነው? የሚለውን የሚያብራሩት ዶ/ር ዋሲሁን አለማየሁ የማህጸንና ጽንስ ሕክምና እስፔሻሊስት እና በአሰላ ሪፈራል እና ቲቺንግ ሆስፒታል የፊስቱላ ሕክምና ክፍል አስተባባሪና ኃላፊ ናቸው፡፡
እንደ ዶ/ር ዋሲሁን አገላለጽ የማህጸን መንሸራተት በየትኛውም እድሜ ሊከሰት የሚችል ሲሆን በአብዛኛው ግን በተፈጥሮአዊው መንገድ ልጆችን በምጥ የወለዱ እና የወር አበባ መቋረጥ እድሜ ላይ በደረሱት ያይላል። የማህጸን መንሸራተት የሚደርሰው ብዙ በመውለድ ወይንም ጫና ያለው ከባድ ስራ በመስራት በመሳሰሉት ምክንያቶች ሲሆን ማህጸን ካለበት ተፈጥሮአዊ ቦታ በመልቀቅ በወሊድ አካል በኩል ወደውጭ የመውጣት ችግር ነው፡፡ ይህም የሚሆነው በጡንቻዎች መላላት እና መዳከም ምክንያት ነው፡፡ይህ የጤና መጉዋደል በኢትዮጵያም በብዛት የሚስተዋል ነው፡፡   
ምክንያቶቹም፡-
እርግዝና
አስቸጋሪ የሆነ ምጥ እና ወሊድ
ክብደቱ ከፍተኛ የሆነ ልጅ መውለድ
እናትየው እራስዋ ከመጠን በላይ ወፍራም ከሆነች
የወር አበባ ከተቋረጠ በሁዋላ ኢስትሮጂን የተባለው ሆርሞን ማነስ
ኃይለኛ ሳል ወይንም ብሮንካይትስ
የሆድ ድርቀት ሕመም ወይም ሌሎች ሆድ ውስጥ እንደውሀ መጠራቀም የመሳሰሉ እና ግፊት የሚኖራቸው ሕመሞች
ከባድ ነገር በተደጋጋሚ መሸከም…ወዘተ ናቸው፡፡
የማህጸን መውጣት በራሱ ብዙውን ጊዜ እንደ ሕመም ተቆጥሮ ወደ ሐኪም ቤት እንዲመጡ ሲያደርጋቸው አይታይም፡፡ ነገር ግን ማህጸን በመሸራተቱ ምክንያት…
የሽንት ፊኛ አብሮ ሊንሸራተት ይችላል፡፡ የሽንት ፊኛ ሲንሸራተት ሽንት ለመሽናት ይቸገራሉ፡፡ እንዲያውም አንዳንድ ጊዜ ሽንትን መቆጣጠር እንዳይችሉም ወይንም ሙሉ በሙሉ እንደጤነኛ ሰው እንዳይሸኑ ሊያደርጋቸው ይችላል፡፡
ከማህጸን መንሸራተት ጋር ትልቁ አንጀት አብሮ ሊንሸራተት ይችላል፡፡ ይህም ለሆድ ድርቀትና ለተመሳሳይ ችግሮች ሊያጋልጣቸው ይችላል፡፡
የሚወጣው ማህጸን ተለቅ ሊልና ለጉዞ ሊያስቸግር ይችላል፡፡ በሁለት እግሮች መካከል ስለሆነ በመፈጋፈግ ሊቆስል ይችላል፡፡
የሚወጣውን ማህጸን በማየት ከፍተኛ የሆነ የስነልቡና ችግር ይደርስባቸዋል፡፡ በመሆኑም ወደሐኪም ቤት መምጣት ወይንም ለቤተሰብ ጉዳዩን ማማከር ብዙ ጊዜ አይታይም፡፡
የግብረስጋ ግንኙነት ለመፈጸም ይቸገራሉ፡፡
‹‹…እኔ የስምንት ልጆች እናት ነኝ፡፡ የማህጸን መንሸራተት ደርሶብሻል ስለተባለ ይኼው ሕክምና ላይ ነኝ፡፡ ልጆቼን ለማሳደግ ብዙ ስራ እሰራለሁ። ውሀ መቅዳት …. እንጨት መስበር…የቤት ውስጥ ማናቸውም ስራ መስራት ከቤት ውጭም ባለቤቴን በእርሻ ስራ እረዳለሁ፡፡ የሁዋላ ሁዋላ ግን ምንም መንቀሳቀስ እያቃተኝ መጣ፡፡ ታመምኩኝ፡፡ ስለዚህ ከባለቤቴ ጋር ስንነጋገር እንዲህ አለኝ…‹‹…አንቺን ወደሕክምና እወስድሽና ከልጆችሽ ጋር ትቀመጫለሽ። እኔ ግን ሌላ ሚስት አገባለሁ አለኝ፡፡ እኔም ምንም ማድረግ ስለማልችል አልቅሼ ተውኩኝ፡፡ አሁን ግን እየታከምኩ ነው፡፡…››
የአንዲት ታካሚ ምስክርነት
በስፍራው የነበሩት ታካሚዎች ብቻም አይደሉም። ወንዶችም ባለቤቶቻቸውን ለማሳከም የመጡ ነበሩ፡፡ አንደኛው ሰው ስለሁኔታውም ሲያስረዱ …
‹‹…ባለቤቴ ከልጅነትዋ ጀምሮ ከእኔ ጋር አብራ ኖራለች፡፡ 7/ልጆችንም አፍርተናል፡፡ ዛሬ እኛ የወለድናቸው ልጆች ጠምደው ያርሳሉ፡፡ ትዳርም የመሰረቱ አሉ፡፡ ይህች ባለቤቴ ልጆቼን ወልዳ ከማሳደግ አልፋ ተርፋ የእኔን የእርሻ ስራ ስትረዳ…እኔንም ስትንከባከብ ኖራለች፡፡ ታዲያ ደህንነትዋ ሲቃወስ እኔም የድርሻዬን ማበርከት አለብኝ፡፡ እነሆ ቤቴን ትቼ እስዋን ሆስፒታል አስተኝቼ እኔ በየበረንዳው አድራለሁ። ሆቴል እንዳልገባ ገንዘብ የለኝም፡፡ ይሁን እንጂ እኔ ለህመምዋ ሕክምናው ስለተገኘ በጣም ደስተኛ ነኝ። እኔ እስዋን ትቼ ሌላ ትዳርማ አልመ ሰርትም ፡፡ አብሬ ያረጀሁትን የልጆቼን እናት እየደገፍኩ እሱዋም እየደገፈችኝ እግዚሐር እስከፈቀደ ድረስ እንኖራለን፡፡››
እንግዲህ ሁሉም ሰው አንድ አይደለምና ከላይ እንዳነበባችሁት አይነት የትዳር አጋር የልጆቹን  እናት ሕመም ህመሜ ብሎ አብሮ የሚንገላታ ባል መኖሩን ያሳያል፡፡ እናቶች ደህንነታቸው ወይንም ጤናቸው በሚቃወስ ጊዜ አብሮ መገኘት ካለባቸው ሰዎች መካከል የመጀመሪያው ሰው የትዳር ጉዋደኛዋ መሆኑ ምን ያህል ትክክል እንደሆነ ይጠቁማል፡፡
የማህጸን መንሸራተት እንዳይደርስ ለመከላከል፡-
በተለይም ልጅ ከወለዱ በሁዋላ በተወሰነ ጊዜ ማህጸንን ጭምቅ ጭምቅ እያደረጉ የማጠናከሪያ እስፖርት መስራት
የሆድ ድርቀት ሕመም እንዳይደርስ ማድረግ፡፡ ለዚህም ብዙ ፈሳሽ መጠጣት ሆድ የሚያለሰልሱ እንደ ፍራፍሬ አትክልት ወይንም አንደ ባቄላ ያሉ ጥራጥሬ እና አጃ ..ገብስ የመሳሰሉትን መመገብ
ከባድ እቃ መሸከምን በጀርባ አዝሎ መሄድን ማስወገድ…ወዘተ
የእናቶችን ደህንነት በመጠበቁ ረገድ የህክምና ባለሙያው ብቻ ሳይሆን በዘርፉ የተሰማሩ ባለሙያዎች ሁሉ ኃላፊነት ነው፡፡ በተለይ ሐኪሙ ግን ብቃት ያለውና በስነምግባር የታነጸ እንዲሆን ይጠበቅበታል፡፡

Read 3112 times