Sunday, 11 February 2018 00:00

የጤፍ ባለቤትነትን ለማስመለስ እንቅስቃሴ ተጀምሯል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

  የባህል ህክምናን ጨምሮ ባህላዊ እሴቶችን ለመመዝገብ ረቂቅ ህግ ተዘጋጅቷል

    ኢትዮጵያ በውጭ ሀገር ኩባንያዎች የተነጠቀችውን “የጤፍ” ባለቤትነት መብት ለማስመለስ አዳዲስ ስትራቴጂዎችን ነድፋ እየተንቀሳቀሰች መሆኑን የኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ጽ/ቤት ያስታወቀ ሲሆን የኢትዮጵያን የባህል ህክምናዎችና ሌሎች ማህበራዊ እውቀቶችን ለማስጠበቅ የሚያስችል ረቂቅ ህግም መዘጋጀቱን ጠቁሟል፡፡  
የኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ጽ/ቤት በጉዳዩ ላይ በሰጠው መግለጫ፤ መገኛው ኢትዮጵያ የሆነውና ከኢትዮጵያውያን ጋር የ3 ሺህ ዓመታት ታሪክ ያለውንና የህብረተሰቡ ዋነኛ የአመጋገብ ባህል ምንጭ የሆነውን “ጤፍ”፣ የባለቤትነት መብት፣ አንድ የኔዘርላንድ ኩባንያ መንጠቁን የጠቆሙት የጽ/ቤቱ ጊዜያዊ ዋና ዳይሬክተር አቶ ኤርሚያስ የማነብርሃን፤ መንግስት በሶስት መንገዶች የሀገሪቱን መብት ለማስመለስ እየተንቀሳቀሰ ነው ብለዋል፡፡
የጤፍ የባለቤትነት መብትን ለማስመለስ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴርን ጨምሮ ጽ/ቤቱ፣ በጤፍ ጉዳይ አዲስ ዓለማቀፋዊ የዲፕሎማዊ ስልት መንደፋቸውን፣ በዚህ መንገድም ባለቤትነቱን የነጠቁት ራሳቸው ጉዳዩን ተረድተው፣ በፍቃደኝነት እንዲመልሱ ግፊት ለመፍጠር መታሰቡን፤ በሁለተኛነትም በዓለማቀፍ ደረጃ በጉዳዩ ላይ ህዝባዊ ቅስቀሳ ለማድረግም መታቀዱን አስረድተዋል፤ ኃላፊው፡፡
ከእነዚህ አማራጮች ጎን ለጎንም በዓለማቀፍ ፍ/ቤት በኩባንያዎቹ  ላይ ክስ ለመመስረት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም አቶ ኤርሚያስ ጠቁመዋል፡፡ የ“ጤፍ” ባለቤትነትን መነጠቃችን አስተምሮናል ያሉት አቶ ኤርሚያስ፤ከዚህ በመነሳት በዘላቂነት ጤፍንም ሆነ ሌሎች ሀገራዊ ሰብሎችን፣ ባህላዊ እውቀቶችን፣ የባህል ህክምና እውቀቶችን ለማስጠበቅ የሚያስችል “የማህበረሰብ እውቀት ጥበቃ” ረቂቅ ህግ መዘጋጀቱን አስታውቀዋል፡፡
በሌላ በኩል፣ የፈጠራ ሃሳብን በማስያዝ፣ ከባንክ ብድር አግኝቶ፣ የፈጠራ ስራውን ወደ ተግባር መቀየር የሚቻልበትን መንገድም ጽ/ቤቱ እያመቻቸ መሆኑ ታውቋል፡፡

Read 2645 times