Print this page
Sunday, 11 February 2018 00:00

በሦስት ሳምንት ጊዜ ውስጥ 7ሺ122 እስረኞች በምህረት ተለቀዋል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(12 votes)

 · “የአንዷለም መፈታት ለልጆቻችን ትልቅ እፎይታን ይፈጥራል” - ዶ/ር ሰላም አስቻለው
          · “በአስተሳሰባቸውና በአመለካከታቸው የታሰሩ ሁሉ መፈታት አለባቸው” - የእስክንድር ነጋ ባለቤት

    ታዋቂውን ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋና ፖለቲከኛው አንዷለም አራጌን ጨምሮ ከትናንት በስቲያ 746 ፖለቲከኞችና ግለሰቦች በይቅርታና ክሳቸው ተቋርጦ እንዲለቀቁ የተወሰነ ሲሆን በሦስት ሳምንት ጊዜ ውስጥ በፌደራልና በክልል ከእስር የተፈቱ ግለሰቦች ቁጥር 7ሺ 122 ደርሷል፡፡
የአቶ አንዷለም አራጌ ባለቤት ዶ/ር ሰላም አስቻለው፤ የአንዷለም መፈታት ለሷም ሆነ ለቤተሰቦቿ፣ በተለይም የ10 ዓመት እና 7 ዓመት እድሜ ላላቸው ሁለት ልጆቻቸው ታላቅ እፎይታን የሚፈጥር መሆኑን ተናግራለች፡፡ ሲሆን በአሜሪካን ሀገር የምትገኘው የጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ባለቤት ወ/ሮ ሰርካለም ፋሲል በበኩሏ፤ “በዜናው በጣም ተደስቻለሁ፤ ትልቁ ደስታ ደግሞ አባቱን ለናፈቀው የልጃችን ናፍቆት ነው” ብላለች፡፡  በአጠቃላይ በአስተሳሰባቸውና በአመለካከታቸው ሳቢያ የታሰሩ ሁሉ እንዲፈቱም ወ/ሮ ሰርካለም ጠይቃለች፡፡
ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋና ፖለቲከኛ አንዷለም አራጌ፣ መስከረም 3 ቀን 2004 ዓ.ም መታሰራቸው የሚታወስ ሲሆን ከእነሱ ጋርም የፖለቲካ ፓርቲ አባላትን ጨምሮ 24 ግለሰቦች በሽብር ተከሰው እንደተፈረደባቸው ይታወቃል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ 16ቱ በውጭ ሀገር ሆነው ፍርድ የተላለፈባቸው ናቸው፡፡ አቶ አንዷለም ልጃቸውን አፀደ ሕፃናት አድርሰው ሲመለሱ ነበር ተይዘው የታሰሩት፡፡
ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ላይ ቀርቦ 3 ክሶች ሲሆን የመጀመሪያው ከግንቦት 7 አመራሮች ጋር በህቡዕ ግንኙነት በማድረግ ሁከትና ብጥብጥ ለመፍጠር ስብሰባ በማድረግ፣ የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ በመስማማት፣ የግንቦት 7 ልሳን ለሆነው ኢሳት መረጃ በመስጠትና ቀስቃሽ ፅሁፎችን በመፃፍና በማሰራጨት ወንጀል የሚል ነው፡፡
ሁለተኛው በጋዜጠኛው ላይ የቀረበው ክስ፤ የግንቦት 7 የሀገር ውስጥ ወኪል የመሆን ወንጀል ሲሆን በሶስተኛነት የቀረበበት ክስ፣ የኤርትራ መንግስትን የሽብር አጀንዳ ለማስፈፀም እንዲመቸውና እንዲቀናጅ በመርዳት፣ ከፍ ያለ የሀገር ክህደት የመፈፀም ወንጀል የሚል ነበር፡፡
የቀድሞ አንድነት ለፍትህና ለዲሞክራሲ ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ የነበሩት አቶ አንዷለም አራጌም ተመሳሳይ ክስ የቀረበባቸው ሲሆን በመዝገቡ የተካተቱ ተከሳሾች በአጠቃላይ አሸባሪ ተብለው ከተሰየሙ ድርጅቶች ጋር በመተባበር፣ ከኤርትራ መንግስት ወታደራዊና የፋይናንስ ድጋፍ በማግኘት፣ ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን በኃይል ለመጣል ተንቀሳቅሷል የሚል ነው፡፡ በዚህ የክስ መዝገብ የግንቦት 7 አመራር የሆኑት ዶ/ር ብርሃኑ ነጋና አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ መካተታቸው ይታወቃል፡፡
ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ በማረሚያ ቤት ሆኖ በቅርቡ ያገኘውን ዓለማቀፋዊ ሽልማት ጨምሮ ከ4 በላይ የሆኑ ከፍተኛ ሽልማቶች ተበርክተውታል፡፡ ፖለቲከኛው አቶ አንዷለም አራጌ  ደግሞ በማረሚያ ቤት ሆኖ “ያልተሄደበት መንገድ” እና “የሀገር ፍቅር ዕዳ” የተሰኙ ሁለት መፅሐፍትን ለአንባቢያን ማቅረባቸው ይታወቃል፡፡
ከትናንት በስቲያ እንዲለቀቁ ከተወሰነላቸው ፖለቲከኞችና ግለሰቦች መካከል 417 ያህሉ ተፈርዶባቸው የነበሩ ሲሆን በይቅርታ የተፈቱ ናቸው፤ ቀሪዎቹ 329 ታሳሪዎች ደግሞ ክሳቸው ተቋርጦ መፈታታቸው ታውቋል፡፡ በይቅርታ እንዲለቀቁ ከተወሰነላቸው 417 ታራሚዎች መካከል በኦነግ፣ በግንቦት ሰባት፣ አልሸባብ፣ ጋህነን፣ ሲአን ጉዳይ እና ከሃይማኖት አክራሪነትና ተቃውሞ ጋር በተያያዘ የተፈረደባቸው ነበሩ ተብሏል፡፡
ክሳቸው ከተቋረጠላቸው ታሳሪዎች መካከል 278 በፌደራል ደረጃ፣ ከትግራይ ክልል 33 እንዲሁም ከአማራ ክልል 18 መሆናቸው ተጠቁሟል፡፡ ሁሉም ከእስር እንዲፈቱ የተወሰነላቸው ግለሰቦችም የተሃድሶ ስልጠና እንደሚሰጣቸው ታውቋል፡፡
በሁለት ወር ጊዜ ውስጥ ጉዳያቸው እየተጣራ እስረኞች እንደሚለቀቁ አስታውቆ የነበረው የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ፤ ጥር 9 ቀን 2010 ዓ.ም ዶ/ር መረራ ጉዲናን ጨምሮ በፌደራል ደረጃ 115፣ ከደቡብ ክልል 413 በድምሩ 528 እስረኞችን ከመልቀቁ በተጨማሪ ጥር 23 ቀን 2010 ዓ.ም በፌደራል ደረጃ ታስረው የነበሩ 598 የአማራ ክልል ተጠርጣሪዎችን እንዲፈቱ ወስኗል፡፡ ከትናንት በስቲያ ደግሞ 746 እስረኞች  እንዲለቀቁ ወስኗል፡፡
የኦሮሚያ ክልል በበኩሉ፤ጥር 18 ቀን 2010 ዓ.ም ይፋ ባደረገው መረጃ፣2ሺ345 እስረኞችን በምህረት መልቀቁ የታወቀ ሲሆን የአማራ ክልልም በተመሳሳይ 2ሺ905 እስረኞችን በምህረት እንዲለቀቁ ወስኗል፡፡ በደቡብ ክልል ከተለቀቁት 413 ግለሰቦች መካከል 361 ያህሉ በጌዲኦ ዞን ከተፈጠረ ግጭት ጋር በተያያዘ የተጠረጠሩ  ሲሆን 52ቱ  ደግሞ በኮንሶ ግጭት ተሳታፊ ነበሩ ተብሏል።  
የፌደራሉ መንግስት ክሳቸውን ከአቋረጠላቸው 598 የአማራ ክልል ተጠርጣሪዎች መካከል ደግሞ 224 ያህሉ ከሰሜን ጎንደር፣ 176 ከአዊ ዞን፣ 107 ከምዕራብ ጎጃም፣ 41 ከምስራቅ ጎጃም፣ 17 ከደቡብ ወሎ፣ 14 ከኦሮም ልዩ ዞን፣ 13 ከደቡብ ጎንደር፣ 2 ከዋግህምራ እና 1 ከሰሜን ሸዋ ዞኖች መሆናቸው  ታውቋል፡፡
እስካሁን በፌደራል በጠቅላይ አቃቤ ህግ በኩል፣ አንድ ሺህ ስምንት መቶ ሰባ ሁለት (1872) እስረኞች ሲለቀቁ፣ ከአማራና ከኦሮሚያ ክልል በድምሩ አምስት ሺህ ሁለት መቶ ሃምሳ (5,250) እስረኞች ተለቀዋል፡፡

Read 7165 times