Print this page
Sunday, 11 February 2018 00:00

“እንዝናናለን” ሲባል ሀዲዱን መሳት!

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(5 votes)

  ክፋትና ተንኮል በዓለማችን በዝቷል፣ የአገራችንም እየባሰበት እንደሆነ እናውቃለን፡፡ ግን እኮ ከዛ አዙሪት መውጣት ነው የምንፈልገው፡፡
መልካምነት ክፋት ላይ ድል ሲቀዳጅ ማየት ነው የምንፈልገው፡፡ እውነት ቅጥፈት ላይ የበላይነቷን ስታረጋግጥ ማየት ነው የምንፈልገው፡፡


     እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ሴትዮዋ ከልጆቻቸው ጋር ሊግባቡ አልቻሉም …በቴሌቪዥን የተነሳ፡፡ ቤተሰቦች እንደውም ያልፈለጓቸውን ጣቢያዎች ይሰርዛሉ፡፡ ልጆቹ መልሰው ይጭናሉ፡፡ የምር ግን የእኛ አገር የብዙዎች ቤተሰቦችና ልጆቻቸው ግንኙነት ነገር ከአሳሳቢ ደረጃም እያለፈ ነው፡፡ ገና አስራዎቹ ሲገቡ በአካል ታዳጊ፣ በድርጊት እንደ ጎልማሳ በሚያደርጋቸው ዘመን ለትውልድ መጨነቅ ይገባል፡፡
ስሙኝማ …እንግዲህ ጨዋታም አይደል…ይሄ እነኚህ ወደ አማርኛ ተመልሰው በቴሌቪዥን የምናያቸው ፊልሞች አሉ አይደል…እንደ ዛራና ቻንድራ ሰሞን ባይሆንም፣ እንደ ኦማርና ኤሊፍ ጊዜ ባይሆንም… አሁንም ብዙ ተከታታዮች አሏቸው። እንኳንም አማራጭ አገኘን፡፡ አማራጭ የማግኘት ነገርን የመሰለ ነገር የለም፡፡ ሌሎቹም ጣቢያዎች ይብዙልን፡፡
እናላችሁ… የሆነ ወደ ሁለት መቶ ዘጠና አምስት ገደማ ክፍሎች የነበሩት ፊልም በጥቂት ቀናት፣ የመጀመሪያው ምዕራፍ የተባለው ተጠናቋል ተብሏል፡፡ እኔ የምለው… ድራማም ሆነ ፊልም ማየት የምንፈልገው በመጀመሪያ ደረጃ ለመዝናናት ነው፡፡ ይኸው ነው፡፡ በተለይ አሁን እንዳለንበት የምንሰማው፣ የምናየው ነገር አእምሯችንን በሚበጥብጥበት ጊዜ መላ የጠፋው በሚመስል ዘመን፣ አእምሯችን ትንሽም ቢሆን የፋታ ጊዜ ያስፈልገዋል፡፡ በሥራም፣ በምንም ሲለፋ ውሎ፣ ስንቱን ዳገትና ቁልቁለት ሲወጣና ሲወርድ ውሎ፣ ስንት ጉድና ጉዳጉድ ሲያይና ሲሰማ ውሎ መጨረሻ ቤቱ ምሽጉ ነው… አእምሮውን የሚያሳርፈበት፣ ከዕለታዊ የሰቆቃና የመከራ ወሬ ለትንሽ ጊዜም ቢሆን የሚርቅበት፡፡
በነገራችን ላይ ይሄ ድራማው ላይ ግምገማ፣ ትችት ምናምን አይደለም፡፡ እሱን ባለሙያዎቹ ሊያደርጉት ይችላሉ፡፡ እንደ ዜጋና ተመልካች ግን የምናያቸው ነገሮች ሃሳብ ውስጥ እየከተቱን ስለሆነ ነው፡፡
እናላችሁ …ከፍ ብለን የጠቀስነው ተከታታይ ድራማ የመጀመሪያው ምእራፍ መዝጊያ ላይ ያየናቸው ትእይንቶች፣ መለስ ብለን ሌሎች ብዙ ነገሮችን እንድናይ የሚገፋፉ ናቸው፡፡ በነገራችን ላይ በጣም የተረበሹ ተመልካቾች እንደነበሩ ሰምተናል። የምር የሚገርም ነው… ይሄን ሁሉ ጭካኔ ሲፈጸም ማየት አለብን እንዴ! እነኚህ በተለይ ከአታቱርክ አገር የሚመጡ ፊልሞች ላይ የምናያቸው የተንኮል የክፋት፣ የጭካኔ ተግባራት አልበዙም!
ፊልምም ድራማም መጀመሪያ መዝናኛ ሆኖ ትምህርትም፣ መልእክትም ወዘተ፡ ካለ እግረ መንገድ የሚተላለፉ ናቸው፡፡ ተንኮል፣ ክፋት ያለባቸው ድራማዎች አንይ አይደለም፡፡ ከህይወት እውነታዎች ልንሸሽ አንችልም…ዘንድሮ ህይወት፣ እኛም ዘንድ ሆነ ሌሎች ስፍራዎች፣ ከፍተኛ በሆነ የክፋት፣ የተንኮልና የጭካኔ ማእበል አየተናጠች ነውና፡፡ ቢያንስ ክፋትና ተንኮል በእውነትና በንጽህና ሊሸነፉ እንደሚችሉ፣ እንደሚሸነፉም የሚያሳዩ ነገሮች ብናገኝ አሪፍ ነው፡፡
ስሙኝማ፣ ችግራችን መከራችን እንዳለ ሆኖ…አለ አይደል ……ዓለም ‘የክፉዎች ብቻ ነች’ በሚል መልዕክት ህይወት፣ ላይ ተስፋ እንድንቆርጥ መሆን የለብንም፡፡ ንጽህና ደግነት፣ እውነት ፍለጋ የሚያስከፍለው ዋጋ ከባድ ነው የሚል መልእክት የተላለፈላቸው ወጣቶች፣ ታዳጊዎች ምን አይነት ስብእና ይዘው ነው የሚያድጉት! አሁን ይሄ እያሳሰበን ነው፡፡ አይደለም በለጋ እድሜ ላይ ያሉት የጎለመሰውና ጉልምስና ያለፈውን ስሜት ሁሉ እንዲህ የሚረብሹ ነገሮች ምንም አይነት ግለሰባዊም ሆነ ማህበራዊ ጠቀሜታዎች አይኖራቸውም፡፡ ማንንስ ይጠቅማሉ!
እናላችሁ …የጠቀስነው ድራማ መጀመሪያው አካባቢ መልካም የነበረ ቢሆንም፣ የእኛ የምንላችው፣ እጣ ፈንታቸው ያሳስበን የነበሩ፣ ቢሳካላቸው የምንመኝላቸው ገጸ ባህሪያት ነበሩት፡፡ እየቆየ ሲሄድ ግን ተንኮል፣ ክፋትና ጭካኔ መልካቸውን እየለዋወጡ ሲመጡ ስናይ ነው የከረምነው፡፡ ግን…እንግዲህ ጨዋታም አይደል …እነኚህ ድራማዎች የሚጻፉት የእኛን ህብረተሰበ ግምት ውስጥ ገብቶ ስልላሆነ ጸሀፊዎቹን ልንወቅስ አንችልም፡፡ ምን አግብቶን! “እናንተን ምን ይኮነስራችኋል?” ቢሉን ምን ብለን ልንመልስ! ግን እነኚህን ድራማዎች በራሳችን ቋንቋ እኛ እንድናይ ሲደረግ በምን መስፈርት እንደተመረጠ ብናውቅ ጥሩ ይሆናል፡፡ ክፉዎቹ፣ ተንኮለኞቹ ገጸ ባህሪያት ዝንባቸው “እሽ” ሳይባል፣ እኩይ ተግባሮቻቸው ረጅም መንገድ ሲያስኬዳቸው ሲታይ ምን መልእክት እየተላለፈ ነው እንላለን…በተለይም በለጋ እድሜ ላሉት፡፡
እንደገና …ይህ ግምገማ፣ ትችት አይደለም፡፡ ግን ረጋ ብለን ስናየው የሚያሳስቡን ነገሮች ስለበዙብን ነው፡፡ ምንጊዜም ንጹሀን፣ ሰናይ ገጸ ባህሪያት ደካሞች፡ አቅም የሌላቸው፣ መከራና ችግርን በእንባ ብቻ የሚቀበሉ አይነት ሆነው ሲታዩ፣ በተቃራኒው ደግሚ እኵይ ገጸ ባህሪያት የማንንም ህይወት እንደፈለጉ ቢያመሳቅል ምንም እንደማይደርስባቸው ሆነው ሲቀረጹ…አለ አይደል… አስቸጋሪ ነው፡፡
ስሙኝማ …እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታን ያነሳው የለ …የትርጉም ፊልሞች የተጀመሩ ጊዜ ብዙ ተቃውሞዎች ነበሩ፡፡ እኛም “አይ አልበዛም! ገና ምኑም ሳይጀመር ይሄ ሁሉ ተቃውሞ ምንድነው!” ብለን አምተን ነበር፡፡ በእርግጥ ሁሉም ተቃውሞዎች ለትውልድና ለአገር ከማሰብ ብቻ የተሰጡ ናቸው ለማለት ትንሽ ያስቸግራል፡፡ ምክንያቱም በወቅቱ አንዳንድ አስተያየቶች ለየት ያለ ቃና ነበራቸውና፡፡ ግን አሁን መለሰ ብለን ስናየው፣ በወቅቱ ከተነሱት አሳሳቢ የተባሉ ጉዳዮች ወጣቶች ስነ ልቡና ላይ ሊፈጠሩ ስለሚችሉ አሉታዊ ነገሮች የተባለው በእርግጥም አሳሳቢ መሆኑን አያየን ነው፡፡
ስሙኝማ …ምስጋና ለሚገባው ምስጋናም መስጠት አስፈላጊ ነው፡፡ አማራጭ ስለመጣልን፣ ማመስገን አለብን፡፡ በቋንቋ እጥረት የራቁን ነገሮች ስለቀረቡን ምስጋና ተገቢ ነው፡፡ በመዝናናቱ በኩል የተሸፈነልን ቀዳዳ ቀላል አይደለም፡፡ ግን ደግሞ…እንደ መድሀኒቶች ሁሉ የጥበብ ሥራዎች የጎንዮሽ ጉዳቶች ሊያመጡ እንደሚችሉ የሚታወቅ ነው… በተለይ በወጣቶች ላይ፡፡ እሱ ነገር ላይ ትኩረት ሊደረግ የሚገባ ይመስለናል፡፡ እናማ…ጊዜው ለሁላችን፣ በተለይ ደግሞ ለታዳጊዎችና ለወጣቶች ብዙ ገደላ ገደሎች፣ ብዙ የሚያደናቅፉ ነገሮች፣ ብዙ ግራ የሚያጋቡ ነገሮች ያሉበት ነው፡፡
በተለይ ይቺ አዲሰ አበባችን …በጣም አስቸጋሪ ከተማ እየሆነች ነው፡፡ ለወጣቶች መጎልመሻ፣ ለህጻናት ማደጊያ የማትመች ከተማ እየሆነች ነው። ልጆች ትምህርት ቤትም ሆነ ሌላ ስፍራ ወጥተው እስኪመለሱ “ደግሞ ምን ክፉ ነገር ተምሮብኝ ይመጣ ይሆን!”  “ልጄን ምን ይገጥማት ይሆን!” የሚባልባት ከተማ እየሆነች ነው፡፡ በየመንገዱ ስሜት የሚጎዱ፣ አንዳንዴ ብዙ ጊዜም ወዴት እየሄድን ነው የሚያሰኙ ነገሮች የበዙባት ከተማ እየሆነች ነው። የወሲብ ቪዲዮዎች በአደባባይ የሚሸጠባት፣ ከንጋት ጀምሮ ሰዎች ደጅ ሳይቀር ተሰብስበው አልኮል የሚጠጡባት ከተማ እየሆነች ነው፡፡ ይሄን ሁሉ አልፈው ቤታቸው የሚገቡ ወጣቶች፤ የሸሹት ነገር ለመዝናኛ ተብሎ በሚታይ ድራማ መልክ እንዳይመጣባቸው ጥንቃቄ ያስፈልጋል፡፡
እናላችሁ …የሌሎች አገሮች ፊልሞችን በሚገባን ቋንቋ ማግኘታችን አሪፍ ነው፡፡ የፊልም ዘርፋችን ወደ ኢንዱስትሪ ደረጃ አድጎ፣ በየሲኒማ ቤቱ በራፍ በማለዳ የሚያሰልፉና፣ የሚያጋፉ ፈልሞች እስኪበዙልን ድረስ፣ ካረፋፈድንባቸው፣ ከዋልንባቸው ስፍራዎች እያሯሯጡ ቤታችን የሚያስገቡን ድራማዎች እስኪበዙልን ድረስ የመዝናናት ጥማታችንን በከፊልም ቢሆን የሚያረኩልን፣ በሚገባን ቋንቋ የተዘጋጁ ፊልሞች ማግኘታችን አሪፍ ነው፡፡ አሁን በከፊልም ቢሆን ካለቀው ድራማ በመነሳት ምርጫ ላይ ትኩረት ይደረግ እያልን ነው፡፡ ማህበራዊ ሃላፊነት የሚባል ነገር አለ እኮ! ሁሉን ነገር ስንመርጥ፣ ይሄ ግምት ውስጥ የሚገባው ዋናው ጉዳይ መሆን አለበት እያልን ነው፡፡ “ይሄ ነገር የሚያመጣው የጎንዮሽ ችግር ይኖር ይሆን እንዴ!” ማለት ያስፈልጋል፡፡
የምር ግን…እኛ አገር ዜናዎች ላይ ስንሰማ ሲዘገንነን የከረመውን፣ ተጎጂዎችን በቴሌቪዥን ስናይ ሙሉ ቤተሰብ የተላቀሰበትን አሲድ ሰው ላይ የመድፋት የጭካኔ ጥግ፣ በድርጊት ማየቱ አያስቸግርም! ያውም የድራማው እጅግ ሰናይ የተባለችውና እንደተሰቃየች እዚህ የደረሰች ገጸ ባህሪይን! ሴትዮዋ የገዛ ወንድሟ ያለበትን ህንጻ የምታጋይበት ጭካኔ፣ ሰናይ የተባለው የወንድ ገጸ ባህሪና ሌሎች ያሉበት መኪና ተገጭቶ፣ ገደል ተወርውሮ ችቦ ሲሆን፣ ድራማውን ሙሉ በተንኮልና በክፋት ሲሄዱ የከረሙ ገጸ ባህሪያት፣ የምስኪኗን አራስ ልጅ ሰርቀው፣ የባህር ዳርቻ ንጹህ አየርን በነጻነት ሲተነፍሱ…ይሄ ሁሉ በአንድ ክፍል፣ ያውም ‘መዝጊያ’ በተባለው ክፍል ማየት አያስቸግርም! ያውም ልጆች፣ “መኝታ ቤትህ ግባና ተኛ!” የሚባሉበት ሰዓት ባልደረሰበት!
ጸሀፊዎቹ እኛን አስበው አልጻፉም፡፡ ሲመረጥ ግን የታሰብነው እኛ ነን፡፡ እዚሀ ላይ ነው ማህበራዊ ሀላፊነት የምንለው፡፡ ግን ወደ ሦስት መቶ የሚጠጉ ክፍሎች (በእኛ ‘በሳምንት አንድ ክፍል’ ልምድ ወደ ስድስት ዓመት ገደማ ማለት ነው!) ታይተው ሰናይ ገጻ ባህሪያቱ ሁሉ፣ አይደለም ሊሳከላቸው ጭራሽ ቀደም ሲል ከደረሱባቸው የባሱ ዘግናኝ ነገሮች ሲደርሱባቸው ማየት  “እውነት የምርጫው መስፈርት ምንድነው?” ያሰኘናል፡፡
እንኳን ቁስሉ ላይ ጨው ጨምረንበት እንዲህም ሆኖ አላማረብንም፡፡ ግራ የተጋባንበት ጊዜ ላይ ነን።  “ምን ብናደርግ ነው ይሄ ሁሉ መከራና ስቃይ እኛ ላይ፣” ብለን ከፈጣሪ ጋር ሙግት ውስጥ የገባንበት ላይ ነን፡፡ “ኦ፣  እውነትና ቅንነት የት ነው ያላችሁት!” የምንልበት ዘመን ነው፡፡
በነገራችን ላይ፣ ከፍ ተብሎ እንደተጠቀሰው… ጥሩ ነገሮች አላየንም ማለት አይደለም፡፡ ብዙ ቆንጆ ድራማዎች አይተናል፡፡ ፈረንጅ፣ ‘Give credit where due’ የሚላት ነገር አለች፡፡ ምስጋናችን እንዳለ ነው፡፡
እንዲህም ሆኖ ግን …እስካሁን ካለው ተሞክሮ ተነስቶ ምን አይነት ትርኢቶች እንደሚቀርቡልን…የምርጫዎቹ ነገር ወደፊት መሻሻል አለበት፡፡ በአንድ አካባቢ ብቻ ታጥረን መቆየቱ ውሎ ሲያድር ወደ መሰላቸት ይወስደናልና..አሁን ዳር፣ ዳር እያልን እንደሆነው ማለት ነው፡፡ አሁን ተዋናዮቹ ብቻ ሳይሆን ታሪኮቹ በጣም እየተመሳሰሉብን ነው፡፡ እንደውም ታሪኮችን ቀድመን የማወቅ ደረጃ ላይ ሁሉ እየደረስን ነው፡፡
መዝናናት እንፈልጋለን… ተስፋ የሚያስቆርጡ ነገሮች በበዙበት፣ ህይወት ትርጉምና አቅጣጫ እያጣች የመጣች በመሰለችበት ጊዜ…ተስፋችንን የሚያለመልሙ ነገሮች እንፈልጋለን። ወጣቶቻችንንን ወደ ገደሉ ጫፍ የሚገፉ ነገሮች በበዙበት፣ ወደ ትክክለኛው መስመር የሚመልሷቸው ነገሮች እንዲበዙልን እንፈልጋለን፡፡ በድራማ የጎንዮሽ ምት የወጣቶች ህልም፣ የወጣቶች ህይወት ‘መቀማት’ የለበትምና፡፡ “እንዝናናለን” ብለን ሀዲዱን መሳት የለብንምና!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 2068 times