Sunday, 11 February 2018 00:00

“የፖለቲካ ክስረትን በኢኮኖሚ እድገት ማካካስ አይቻልም”

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

 • ኢህአዴግ ለምንድን ነው ህዝቡን የማያምነው? ለምንድን ነው ምሁሩን የማያምነው?
     • የነፃ አውጪነት አስተሳሰብ፣ በህብረተሰቡ ዘንድ የአቅመ ቢስነት መንፈስ ፈጥሯል
     • ህዝቡ በደርግም በኢህአዴግም የነፃ አውጪዎች ድራማ ተመልካች ሆኗል
     • ዲሞክራሲና ልማት አይነጣጠሉም፤ መነጣጠልም የለባቸውም

    በቅርቡ “ምሁሩ” የተሰኘ መፅሐፍ ለንባብ ያበቁት ዶ/ር አለማየሁ አረዳ፤ የኢህአዴግ ዋና ችግር ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት አለመገንባቱ ነው ይላሉ፡፡ ኢህአዴግ ከአሁን በኋላ ራሱን እንደ ነጻ አውጭ መቁጠሩን መተው አለበትም ባይ ናቸው። እንዲሁም ሀገሪቱ በዲሞክራሲ ስርአት ግንባታ እየተጓዘችበት ባለው መንገድና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ጋር ተከታዩን ቆይታ አድርገዋል፡፡

    ገዥው ፓርቲ ችግሮች እንዳሉበት በይፋ አምኖ፣ ለውጥ ለማምጣት እንደሚሰራም መግለጹ ይታወቃል፡፡ ኢህአዴግ አሁን እየተከተለ ያለውን አቅጣጫ እንዴት ይመለከቱታል?
በኔ አመለካከት ኢህአዴግ አሁንም የችግሮቹን መንስኤ ሳይሆን ምልክቶቹን ነው የዘረዘረው፡፡ ለምሳሌ፤ ”እኔም የፖለቲካ እንቅስቃሴ ተሳትፎን የመገደብ ሚና ነበረኝ፣ የሲቪል ማህበረሰቡን እንቅስቃሴ አዳክሜያለሁ፣ መርህ አልባ የሆነ ግንኙነት እየተፈጠረ አሰራሬ ተበላሽቷል” ነው ያለው፤ ኢህአዴግ፡፡ ለኔ እነዚህ የችግሩ ምልክቶች እንጂ ዋና ችግሮች አይደሉም፡፡ ብዙ ከሄድን በኋላ “ትክክል አልመጣንም” ከተባለ፣ መመርመር ያለበት፣ ለምን ትክክል መምጣት አልተቻለም የሚለው ነው፡፡ ኢህአዴግ አሁን ሀኪም ጋ  ቀርቦ፣ የህመም ምልክቶቹን እንደሚናገር ህመምተኛ ነው።
ለእርስዎ የኢህአዴግ ዋና ችግሮች  ምንድን ናቸው?
ለእኔ አንዱ ችግር፣ ኢህአዴግ እየገነባው ያለው ስርአት ዲሞክራሲዊ አለመሆኑ ነው፡፡ እየገነባው ያለው ስርአት በተሳሳተ ርዕዮተ ዓለም የሚመራ ነው፡፡ ኢህአዴግ ይሄን ርዕዮተ ዓለም ቁጭ ብሎ መፈተሽ አለበት፡፡ ነፃ ሃሳብ በምሁሩና በህብረተሰቡ፣ በምሁሩና በፖለቲካ ኃይሎች እንዲሁም በህብረተሰቡ መካከል እንዳይፈስ መደረጉ ሌላው ችግር ነው፡፡ በእነዚህ ወገኖች መካከል ያሉ ድልድዮችን ኢህአዴግ ባይሰብር ኖሮ፣ የችግሩ ምልክቶች አይታዩም ነበር፡፡ አሁን ህብረተሰቡ መውሰድ ይገባ የነበረውን ኃላፊነት ኢህአዴግ እየተወጣው ነው፡፡ ዛሬም ኢህአዴግ ስለ ነፃነትና ነፃ ለመውጣት ስለተከፈለ መስዋዕትነት እያወራ ነው፡፡ ለምን ህዝቡ ራሱ  እንዲወያይ ዕድሉ አይሰጠውም? ምሁራን ለምን በሀገራቸው ጉዳይ በነፃነት እንዲወያዩ አይደረግም? ተማሪዎች ጎሳ እየለዩ ሲደባደቡ ይውላሉ፤ ለምን እንደባደባለን ብለው እንዲወያዩ ለምን ነፃ አይደረጉም? ከዚህ አንፃር ኢህአዴግ እየሄደበት ያለው አቅጣጫ፣ አሁንም ትክክለኛ ሃዲዱን የያዘ አይደለም፡፡ በአፋጣኝ እርምት ያስፈልገዋል፡፡ ህዝቡ ስለ ሀገሩ ከምንም በላይ በነጻነት መነጋገር አለበት፡፡ ኢህአዴግ ለምንድን ነው ህዝቡን የማያምነው? ለምንድን ነው ምሁሩን የማያምነው?
ለውጥ ከማን ይመጣል ብለው ያስባሉ? አንዳንዶች ለውጡ መምጣት ያለበት ከራሱ ከገዥው ፓርቲ ነው ይላሉ?
ይሄ የነፃ አውጪነት አስተሳሰብ የፈጠረው ነው፡፡ የነፃ አውጪነት አስተሳሰብ፣ በህብረተሰቡ ዘንድ የአቅመ ቢስነት መንፈስና የነፃ አውጪ ጠባቂነትን ፈጥሯል፡፡ ህዝቡ በደርግም አሁንም የነፃ አውጪዎች ድራማ ተመልካች ነው የሆነው። አሁንም ነፃ አውጪዎችን ነው እየጠበቀ ያለው። ኢህአዴግ ከአሁን በኋላ ራሱን እንደ ነፃ አውጪ መቁጠሩን ትቶ፣ የለውጥ አመቻች ነው መሆን ያለበት፡፡ ምሁራኑ ተማሪው፣ ህብረተሰቡ፣ ፖለቲከኞች እንዲወያዩ፣ የተዘጋውን ግንብ ሰብሮ ሊያገናኛቸው  ይገባል፡፡ ይሄን እስካላደረገ ድረስ ህብረተሰቡ ለውጥን ከሱ ብቻ የሚጠብቅ ጥገኛ ነው የሚሆነው፡፡ ህብረተሰቡ ከዚህ የጥገኝነት መንፈስ ተላቆ፣ በራሱ የለውጥ ኃይል እንዲሆን ገዥው ፓርቲ ኃላፊነት አለበት፡፡ ትልቁ የዲሞክራሲ ስርአት ግንባታ መርህ፣ ህብረተሰቡን ማንቃት ነው፡፡ ህብረተሰቡ አይተነትንም እንጂ ሁሉንም ያውቃል፡፡ ችግሮቹን ያውቃል፤ ነገር ግን እነዚህን ችግሮች ለማቃለል የሚያስችለውን መፍትሄ ማምጣት አይችልም፡፡ ይሄን ሊያደርግ የሚችለው ምሁሩ ነው፡፡ አንድ የአምባገነን ስርአት መለያው፣ ዕውቀት በሚያቀብል ምሁርና ዕውቀት በሚቀበል ህብረተሰብ መካከል ያለውን ድልድይ መስበር ነው፡፡ አሁን በኛ ሀገር የሆነውም ይህ ነው፡፡ የዚህ ድልድይ መሰበር ግን በኋላ ላይ ሰባሪውንም  አያድነውም፡፡ ይሄንን ደግሞ በደርግም አይተነዋል። ከዚያ መማር ያስፈልጋል፡፡
ባለፉት ዓመታት፣ ሀገሪቱ ካለፈችበት የፖለቲካ ሂደት ምን አትርፋለች?
ሀገሪቱ በፖለቲካ ሂደቱ  እስካሁን  የሚረባ ነገር አላገኘችም፡፡ እንደውም ከዚህ በፊት የነበረውን የቤት ስራ በከረረ መንገድ፣ መስዋዕትነት ከፍለን እንድንፈታ እየተደረገ ነው፡፡ በዳዩ አካል እያለ ምንም ያልበደለ ህዝብ የሚመታበት ሁኔታ ውስጥ ነው የገባነው፡፡ በዚህ ምንም የፖለቲካ ትርፍ አላገኘንም፤ ወደ ኋላ ነው የሄድነው፡፡ ዛሬ እያወራን ያለውን ስለ ነገዳዊ ብሄርተኝነት እንጂ ስለ ዲሞክራሲ መጎልበት አይደለም፡፡ እውነት ነው በኢኮኖሚ በኩል ብዙ ሄደናል፤ ግን እኮ ጀርመንም በሂትለር ዘመን ጠንካራ ኢኮኖሚ ነው የገነባችው፡፡ ቻይና ዲሞክራሲያዊ አገር አይደለችም፤ግን ጥሩ ኢኮኖሚ ገንብታለች፡፡ ስለዚህ የፖለቲካ ክስረትን በኢኮኖሚ እድገት ማካካስ አይቻልም፡፡ ዲሞክራሲና ልማት አይነጣጠሉም፤መነጣጠልም የለባቸውም፡፡
በቅርቡ “ምሁሩ” በሚል ርዕስ ባወጡት መፅሐፍ ላይ የብሔርተኝነት እንቅስቃሴንና የምሁሩን ሚና በተመለከተ ሰፊ ትንተና  አቅርበዋል፡፡ ነጻ አውጭዎች ለምንድን ነው፣ ህዝብን ለመቀስቀስ የብሔርተኝነት አጀንዳን  የመረጡት?
ሁሉንም አቅፋ ያለችው ኢትዮጵያ፣ ሁሉንም ብሔሮች ያስተናገደችበት መንገድ ትክክል አልነበረም፡፡ አንዱ የበላይ ሌላው የበታች የነበረበት ሁኔታ ነበር፡፡ በወቅቱ እንግዲህ የፈነዳው ይሄ ጥያቄ ነው፡፡ የዋለልኝ ሃሳብ አይደለም የብሔር ጥያቄን የቀሰቀሰው፡፡ የብሔር ጥያቄን በተማሪዎች ንቅናቄ ጀልባ ላይ ያሳፈረው ግን ዋለልኝ ነው፡፡ የትግራይ ህዝብ የብሔር እንቅስቃሴ የተነሳው፣ ከትግራይ ህዝብ ብሶት ነው፡፡
የብሔር ጥያቄ፣ ጥቂት ልሂቃን በብዙኃኑ ላይ የጫኑት አስተሳሰብ ነው የሚል ሙግት ይቀርባል፡፡ በዚህ ላይ የእርስዎ አስተያየት ምንድን ነው?
ልሂቃኑ ተበድለሃል፣ ተጨቁነሃል ብለው ነግረውት፣ ህዝቡ ልጆቹን እየመረቀ ወደ በረሃ ከላከ፣ አምኖበት ነው የላከው ማለት እንችላለን፡፡ ልጆቹ እኮ ለእኩልነት ለነፃነት እያሉ ነበር የሞቱት። መጨረሻ ላይ የደረሱት ሰዎች የሰሩት ስህተት ካለ፣ እነዚያ መስዋዕት የሆኑት ተወቃሽ አይሆኑም፡፡ ህውሓት እንደ ህውሓት የትግራይን ህዝብ ብሶት ይዞ መነሳቱ አይደለም ችግሩ፤ ትግሉ ሁሉ እሱ ብቻ ነው ሌላ የለም ብሎ መቀጠሉ ነው ችግሩ፡፡  ርዕዮተ ዓለም ሁልጊዜ የሚመጣው ከልሂቁ ነው፡፡ ይሄ መታወቅ አለበት፡፡ በመፅሐፌም የዋለልኝን ጉዳይ ሳነሳ፣ዋለልኝ የብሔርተኝነት አስተሳሰብን ፈጠረ ሳይሆን የተማሪዎች እንቅስቃሴ ላይ አስቀመጠው ነው ያልኩት፡፡
በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ የምሁራን ድርሻ ምን  ያህል ነው?
ከዘመን ዘመን ይለያያል፡፡ የመጀመሪያዎቹ ፋና ወጊ ምሁራን፣ ስርአቱ እንዲሻሻል ሃሳብ ያቀርቡ ነበር፡፡ አጀንዳቸው ሀገራዊ አጀንዳ ነበር። የፊውዳል ስርአቱ እንዲወድቅ አልፈለጉም፤ ነገር ግን በርካታ ማሻሻያዎችን ያመላክቱ ነበር። በጭሰኛና በባለመሬት መካከል ያለው ግንኙነት እንዲለዝብ ነው ሃሳብ ሲያቀርቡ የነበሩት፡፡ እነዚህ ምሁራን ከአፄ ምኒልክ ዘመን እስከ 1933 ዓ.ም ያሉት ናቸው። እነ ብላታ ተክለሃዋሪያት ይጠቀሳሉ፤ በዚህ ትውልድ፡፡ እሳቸው ናቸው የመጀመሪያውን ህገ መንግስት የፃፉት፡፡ ሁለተኛው የምሁራን ትውልድ የነበሩት፣ ከ1933 እስከ 1953 ያሉት ቢሆኑም፣ በጣሊያን ስለተፈጁ የምሁራን እንቅስቃሴ በሀገሪቱ አልነበረም፡፡ በኋላ በ1953 ነው፣ በመፈንቅለ መንግስት ሙከራው ወቅት የምሁራን እንቅስቃሴ ብቅ ያለው፡፡ የተማሪዎች እንቅስቃሴ እኔም ያለሁበት ነው፣ እሱ ሶስተኛው ትውልድ ነው፡፡ ኢህአፓ እና መኢሶንን የፈጠረ ትውልድ ነው፡፡ የህብረተሰቡን ጉዳት በመዘርዘር ምን ጎደለን? ህዝባዊ መንግስት ይመስረት፣መሬቱ ለአራሹ ይመለስለት ብለን ነበር የጮህነው፡፡ በወቅቱ ግን እንቅስቃሴያችን፣ በማርክሲዝም አጀንዳ መጠለፉ ነው ትልቁ ችግር፡፡ ከዚያ በኋላ የመናኛና የአርበኝነት ስራ ነው የሰራነው ማለት ይቻላል፡፡ ግን  በርካታ የትውልዱ አባል ለሀገሪቱ ሞቷል፡፡
ያ የምሁሩ እንቅስቃሴ ለምን ከሸፈ ታዲያ?
ለመክሸፉ ሁሉም አስተዋፅኦ አበርክቷል። በወቅቱ ተቃዋሚዎች ልዩነታቸው እዚህ ግባ የሚባል አልነበረም፤ በመነጋገር መፍታት ይቻል ነበር፡፡ አሁንም በፖለቲካ ጉዳይ ተነጋግሮ የመፍታት ባህል የለንም፡፡ ለምን ይሄ ባህል ሊዳብር እንዳልቻለ ሁሉም ሊጠይቀው የሚገባ ነው፡፡ በዚህ የተነሳ ዛሬ ምሁሩ የእውቀት ስንቅ፣ ለህብረተሰቡ ማቀበል አልቻለም፡፡
ችግሮችን  በመነጋገርና በውይይት የመፍታት ባህል መገንባት የሚቻለው እንዴት ነው?
አንደኛ የሃሳብ መፍሰሻ ቦዮች በሙሉ መከፈት ሲችሉ ነው፡፡ ሁሉም መከፋት አለባቸው፡፡ ሌላው ሚዲያው ነው፡፡ ሚዲያው መለወጥ አለበት፡፡ ሚዲያው ስፖርትን እንደሚተነትን ሁሉ ማህበራዊ ችግሮችን እንዴት መተንተን ያቅተዋል፡፡ በዚህ ረገድ ሚዲያው እስከ ዛሬ የሄደበትን መንገድ መፈተሽ አለበት፡፡ እነዚህ ነገሮች ሲጎለብቱ ነው ለውጥ ማምጣትም ሆነ  የመነጋገር ባህሉ መዳበር የሚችለው፡፡
በሀገር ውስጥና በውጭ ያሉ ምሁራን ተቀናጅተው፣ ለችግሮች መፍትሄ ማፍለቅ ያልቻሉት ለምንድን ነው?
ያለፉት 27 ዓመታት የሀገራችን የፖለቲካ ታሪክ ትልቁ የፈጠረው ነገር፣ በምሁሩ መካከል አለመተማመንን ነው፡፡ ምሁሩ ሃሳብ ሲያቀርብ ቀድሞ የሚነሳው፣ ሃሳቡ ሳይሆን ማን ልኮት ነው፣ ከጀርባው ማን አለ የሚል ጥያቄ ነው። እዚህ ሀገር ቤት ያሉ ምሁራን ላይ የመሰልቸት ነገር ይታያል። በውጭ ሀገር ያለው ደግሞ እርስ በእርሱም ተከፋፍሏል፡፡ ራሱን መሰብሰብና መግዛት አልቻለም፡፡ የአወናባጆችም ሲሳይ ሆኗል። የሆነ ህብረት ይፈጠርና ገንዘብ አዋጡ ይባላል፣ ያ ህብረት በሳምንቱ አይኖርም፡፡ ይሄ ነው ያለው ሃቅ፡፡ ትልቁ ማሻሻያ ሀገር ቤት ያለው እንቅስቃሴ ነው፣ ምሁሩን ከየትም የአለም ጫፍ እንደ ማግኔት ሊስበው የሚችለው፡፡
በሌላ በኩል፣ መንግስት በውጭ ሃገር ያሉ ምሁራንን፣ በጠላትነት ማየቱን መቀነስ አለበት። የተቹትን በሙሉ እንደ ጠላት ማየት ማቆም አለበት። መንግስት ሆደ ሰፊነት ሲያሳይ፣ ነገሮች ሊቀየሩ ይችላሉ፡፡ ይሄ ገዥ ስርአት፣ አብሪ ጥይቱን መተኮስ አለበት፡፡ ሌላውን ህዝብ ራሱ ይሰራዋል፡፡ ለዚህ ማረጋገጫው ደግሞ ሚዲያውን ነፃ ማድረግ ነው፡፡ አንድ ነገር ከመቅዳታችን በፊት ክዳኑን እንደምናነሳ ሁሉ መጀመሪያ፣ ስርአቱ ክዳኑን ማንሳትና መክፈት አለበት፡፡ ለውጥን ማምጣት ግን የምሁሩና የህብረተሰቡ ድርሻ ነው፡፡ ስርአቱ ክዳኑን ከፍቶ የሚጠበቅበትን ካደረገ በኋላ ለውጥ ካልመጣ እሱ አይወቀስም፡፡ እኔ ዛሬ ቃለ ምልልስ የሰጠሁት፣ ኢህአዴግ ችግሬ ብሎ ያነሳቸው ጉዳዮች በመጠኑ ተስፋ ስለሰጡኝ ነው፡፡ በተለይ በኦሮሚያ ኦህዴድ የሚያደርገው እንቅስቃሴ በመጠኑ ተስፋ ስለሰጠኝ ነው ዛሬ ለመናገር የፈለግሁት፡፡
ምንድን ናቸው እነዚያ ተስፋዎች?
እኔ ተወልጄ  ያደግሁት ኦሮሚያ ውስጥ ነው። የኦሮሞ ህዝብ፣ የኢትዮጵያ ህዝብ ዋነኛ ንጣፍ ነው፡፡ ዘመናዊት ኢትዮጵያ ስትፈጠር፣ የኦሮሞ ህዝብ አስተዋፅኦ ከፍተኛ ነው፡፡ የአድዋ ጦርነትን፣ የማይጨው ጦርነትን፣ ያለ ኦሮሞ ጀግኖች ማሰብ አይቻልም፡፡ ይሄ ህዝብ ክቡርና ትሁት ህዝብ ነው። ከማንም ህዝብ ጋር ተግባብቶ መኖር የሚችል ነው፡፡ የገዳ ስርአቱም ዘር መነጠልን አይፈቅድም። የኦሮሞ ህዝብን ለመምራት በታሪክ አጋጣሚ የመጡት ሰዎች፣ ይሄን መሳት የለባቸውም፡፡ አቶ ለማ መገርሳ፣ በየስብሰባው የሚናገራቸው ነገሮች መልካም ናቸው። እሱ የሚናገራቸው ሃሳቦች፣ አንድ እርምጃ ወደፊት እንዲሄዱ የኢትዮጵያ ህዝብ፣ የኦሮሞ ህዝብ ድጋፍ ያስፈልገዋል፡፡ ስለ ዲሞክራሲ ግንባታ፣ ስለ ስልጣን ምንነት የሚናገሩት ነገር፣ በኦህዴድ ታሪክ ውስጥ አዲስ አቅጣጫ ነው። ለኔ ይሄ ጅምር ጥሩ ነው፤ ሊበረታታ ይገባዋል። በተጨማሪ ቢያደርጉ ብዬ የማስበው፣ አንደኛ አዲስ አበባን እንዳያስጨንቋት እጠይቃለሁ፡፡ የልዩ ጥቅሙን ጉዳይ በልዩ ጥንቃቄ እንዲያዩት እጠይቃለሁ፡፡ ቢያንስ አሁን ጊዜው አይደለም፡፡
ሌላው አማርኛ ቋንቋ ላይ ያለው አተያይ መቀየር  አለበት፡፡ አማርኛ መግባቢያ ቋንቋ ነው፤ አለቀ በቃ፡፡ ለምሳሌ እኔ በአንድ ዩኒቨርሲቲ የገጠመኝ፣ 6 ልጆች የአማርኛ አስተርጓሚ ይዘው ነው የሚንቀሳቀሱት። ይሄ መፈተሽ አለበት፡፡ በተመሳሳይ የኦሮሚኛ ቋንቋን ሁሉም ሊማረው ይገባል ብዬ አስባለሁ፡፡ ኦሮሚኛ የፌደራል ቋንቋ እንዲሆንም  መታገል ይገባል፡፡
በሌላ በኩል፣ አቶ አስገደ ባለፈው ሳምንት በእናንተ ጋዜጣ፣ የሰጡትን ሃሳብ በሙሉ እቀበላለሁ። የትግራይ ህዝብ በማንነቱ ዘመቻ ሊካሄድበት አይገባም፡፡ ይሄን ሁሉም ሊያወግዘው ይገባል፡፡ እርስ በእርስ በመጣላት ምንም የምናገኘው ትርፍ የለም፡፡ እኔም  የአቶ አስገደን ጭንቀት እጋራለሁ፡፡      

Read 1906 times