Sunday, 11 February 2018 00:00

በዘር የመደራጀት፣ በጭፍን የመቧደን “ትርፍ” እና ኪሳራ

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(4 votes)

 • ሲያደራጅህ ወይም ሲያቧድንህ፣ ምን ያተርፋል፣ ምን ትከስራለህ?
              
   1. “የራሱን ቀሽም አስቀያሚ ንግግር ያጋራሃል፣ ያንተን ተአማኒነት ይጋራል”።
   2. “የራሱን ጥፋት ሊያጋራ ያሸክምሃል፤ ያንተን ስኬት ሊጋራ፣ ሊወርስ፣ ሊያራቁት”።
   3. “የራሱን ወራዳ ባህርይ ያወርድብሃል፤ ያንተን ብቃትና ክብር በጋራ ለማውረድ”።
የጋጠወጡ ንግግር… ተጀምሮ የማያልቀው ንግግር፣…  ቀሽም፣ አስቀያሚና አስፀያፊ መሆኑ ብቻ አይደለም ችግሩ።
ነገረ ሥራው ሁሉ፣… የተቃናውን ማጣመም፣ የፀዳውን ማቆሸሽ፣… ያማረውን ማበላሸት… ማበላሸት ካልቻለም፣ ያየውን ሁሉ ማፈስ!… ድንበሩን የማያውቅ፣ ስድ፣ ብልሹ ነው - ጋጠወጡ።
ባህርይውም የወረደ… በጣም የወረደ ቀፋፊ ባህርይ!
ስታዲዮሙ ውስጥ አጠገቡ ከተቀመጡት ኳስ ተመልካቾች መካከል፣… ከአንዳንዶቹ ጋር ለማውራትና ለመቀራረብ ሞክሯል። ለጊዜው አልተሳለትም እንጂ።
ጆሮ የሚሰጠው፣ መንገድ የሚከፍትለትም ሆነ፣ ፊት የሚያሳየው ሰው፣… ገና አላገኘም። ደግሞም አይገርምም።
ገና አፉን ሲከፍት… የቃላት ሳይሆን የጭቃ እሩምታ የሚዘራ ነው የሚመስለው - የሚያስጠላ አስቀያሚ ቀልድ፣…. ከዚያም ስድብ፣… እና ዘለፋ። ለዚህ ቀፋፊ ጋጠወጥነት ጆሮ መስጠት ሞኝነት ነው።
ጆሮ ከሰጡት፣ በዚያ አያቆምም።
በር ሲያገኝ፣… እንደራሱ ንብረት የሰው ቤት ውስጥ ዘው ብሎ መግባት… እንደ መብት የሚቆጥር ጋጠወጥ አስቸጋሪ ነው። ትንሽ መንገድ ከከፈቱለት፣… ፍሬን የለውም፤… የሰው ኪስ ላይ ማጉረጥረጥና ማሰፍሰፍ ነው። መንገድ ከከፈቱለትና ካስለመዱት… በቃ ፊት አየ ማለት ነው።
እንኳን አስለምደውት ቀርቶ፣ በትንሽ ጭላንጭል፣ ትንሽ ፊት ካሳዩት፣… አናት ላይ ካልወጣሁ ይላል። ሰውን እንደ በግ የሚነዳ እረኛ ለመሆን፣ ወይም አለቃ ለመምሰል ይጣደፋል። አለቃ መሆን ማለት፣ ሰውን ማንቀጥቀጥና ማራወጥ ይመስለዋል። እና፣ ቁጭ ብድግ የሚልለት ሰው ቢያገኝ፣ ምን ያተርፋል? ምንም! ግን በዚያ አያቆምም። “ተንበርከክ፣ ተንፏቀቅ” እያለ ሰውን በማሰቃየት ትልቅነትን የሚያገኝ ይመስለዋል። ሰውን ከፍ ዝቅ ማድርግ!… ታዲያ ለክፋት ያህል ብቻ ነው - የክፋቱ ክፋት። “የእንቁራሪት ድምፅ ናፈቀኝ፣ እንደእንቁራሪት ጩኽ” ብሎ ሰዎችን በማዋረድ ለመርካት እስከመሞከር የሚደርስ ነው - የእኩይ ሱስ።… ምናለፋችሁ። ጋጠወጡ፣ ፊት ካየ፣… ማቆሚያ የለውም።
ፊት ካላሳዩትስ? ኮስተር ሲሉበትስ?፣… መከባበር ይሻላል ብሎ አይቀመጥም። መንገድ ካልከፈቱለትስ? ጆሮ ካልሰጡትስ? ተከባብሮ ለመኖር ይሞክራል? ጋጠወጡ አልሞከረም።
ጆሮ የሚሰጥ ሰው ቢያጣ፣… እናም ሰውን መሳደብና መዝለፍ ባይችል፣… ራሱን እየሰደበ በራሱ ላይ መቀለድ ይጀምራል። የባጥ የቆጡን ሁሉ እየመዘዘና እየሸመጠጠ፣ በማይጨበጡ ነገሮች ለማንቆለጳጰስም ይቅበዘበዛል። እጅ-ጅ የሚል አሰልቺ አወዳሽና ከንቱ አጨብጫቢ ለመሆን ይሟሟታል - ሰሚ  ጆሮ ለማግኘት። በቃ፣…. እየዘባረቀ እረፍት ይነሳል። ግን፣ በዚህ ሙከራውም፣ ሰሚ ጆሮ ላያገኝ ይችላል። ምን ይሄ ብቻ!
መንገድ ሲከፍቱለት የሰው ኪስ ውስጥ ዘው ለማለት እያማረው ሲያጉረጠርጥ የነበረው ጋጠወጥ፣… መንገድ ካጣ የሰው ኪስ ላይ መቁለጭለጭና መልከስከስ ያምረዋል። ይህም ብቻ አይደለም።
ፊት ሲያሳዩት፣ አናት ላይ ካልዋጣሁ፣ ካልጨፈርኩ ሲል የነበረው ወራዳ ሰው፣… ኮስተር ሲሉበት፣… ተንበርክኬ ጉልበት ካልተሳለምኩ እያለ ያዋክባል። መሬት ተደፍቼ ልስገድላችሁ፣ እግር ስር ተዘርግቼ አናቴ ምንጣፍ ይሁንላችሁ ይላል። ይሄም ያስጠላል። ራሱን ሲያዋርድ ሌሎች ሰዎች በክብር ይረካሉ የሚል ነው ሃሳቡ።
ያው፣… ከነባሩ የውርደት ስሌት አልተላቀቀም - “ክብር የሚገኘው፣ በማዋረድ ነው” የሚል ወራዳ ስሌት ላይ ተጣብቋል።
ከነባሮቹ ወራዳ አማራጮችም አልተላቀቀም - ማዋረድ ወይም መዋረድ ብቻ ናቸው እንደ አማራጭ የሚታዩት። ሌሎችን በማዋረድ በክብር ለማርካት፣… ወይም ራሱን በማዋረድ ሌሎች ሰዎችን በክብር ማርካት! ገዢ ወይም ሎሌ መሆን… ተሸካሚ ወይም ሸክም መሆን… አባራሪ ወይም ተባራሪ የዱር እንስሳ… በቃ!
ሰው የመሆን፣ ተፈጥሮው ጋር የሚጣጣምና የሚመጣጠን ክቡር ሕልውና፣… የ“ሰው”ነት ክብር አይታየውም።… ማለት፣… በራሱ ብቃት ተማምኖ፣ አንገቱን ቀና አድርጎ መቆም፣… በራሱ ጥረት የራሱን የግል ማንነት ገንብቶ፣ የእኔነት ክብርን ተቀዳጅቶ፣… የራሱን ክብር ጠብቆ፣ የሌላ ሰውንም የግል ማንነትና ክብር ሳይነካ ሳይዳፈር መኖር፣… ጨርሶ እንደአማራጭ እንዲታየው አይፈልግም።
ሁሉም ሰው በግል ተግባሩና በባህርይው የሚመዘንበት፣ በቅንነትና በፍትህ፣ በጎ በጎውን እየወደደ፣ ብቃትን እያደነቀ በፍቅርና በመከባበር መኖር፣… ቢያንስ ቢያንስ ደግሞ የግል ማንነትንና ክብርን ከመንካት የራቀ ጤናማ አኗኗርና ቅዱስ ሕይወት… እንዲህ አይነት አማራጭ አይታየውም፣ አይኑን ጨፍኗል።
እና ምን ያድርግ? በየት ያምልጥ? የክፋት ዘዴ ሞልቷል!
ለዘባራቂና ለተሳዳቢ… ጆሮ የሚሰጥ የለም? አሰፍስፎ ለሚያጉረጠርጥና ለሚልከሰከስ ጋጠወጥ፣... ትንሽዬ መንገድ የሚከፍት ሰው አልተገኘም? አናት ላይ ልውጣ ወይም እግር ስር ልነጠፍ ለሚል ወራዳ፣… ትንሽዬ ፊት የሚሰጥ ሰው ጠፋ?
ስታዲዮም ውስጥ፣ በዙሪያው ያሉ ብዙ ተመልካቾችን ይቃኛቸዋል። በአብዛኛው፣ ጨዋነታቸውን ሳይጥሉ፣ የኳስ ተጫዋቾችን ሃይለኛ የብቃት ውድድር ለማየት የሚጓጉ ይመስላሉ። በቃ፣ ለጋጠወጥ መፈናፈኛ አይሰጡም? ለአፍታ ያህል እንኳ… ጆሮ፣ መንገድና ፊት አይሰጡም?
ችግር የለውም። ለጋጠወጡ የሚመች ዘዴ ሞልቷል። አዎ፣… ይሄኛው ጋጠወጥ፣… አዲስ የክፋት ዘዴ ለመፍጠር አቅምም ሆነ ችሎታ የለውም። ግን ነባር ዘዴዎች አሉለት - ተፈጭተው፣ ተቦክተው፣ ተጋግረው ያለቀላቸው ቀላል ዘዴዎች። ከሱ የሚጠበቀው፣ ትንሽ ነገር ብቻ!
ስታዲዮም ውስጥ፣ ከወዲህ በኩል ሆኖ፣ ወደዚያ ወደ ማዶ አቅጣጫ እያጉረጠረጠ፣ ጋጠወጥ አፉን ከፍቶ የሚተፋት አንዲት ቀፋፊ ስድብ፣… ብዙ ነገር ትለውጣለች።
እዚህ ከመሃላችን ሆኖ፣ እንደመናኛ ሰብዕናው ቁልቁል ወርዶ ከአፈር ስር የቧጠጣትና ወዲያ ወደ ማዶ የወረወራት አንዲት ድንጋይ፣… ብዙ ብዙ ነገር ትለውጣለች።
በአንድ በኩል፣ ያቺ ስድብና ድንጋይ፣… ጭፍን አፈንጋጭነት ናት - በመንጋ የመቧደን ጭፍንነትን ለማግኘት የታለመች።
ሰሚ ጆሮ አጥታ የቆየችው የጋጠወጡ ስድብ፣… አሁን ወዲያ ማዶ በጅምላ ስለተወረወረች፣… የጋጠወጥ ስድብ መሆኗ ተረስቶ… ሰሚ ጆሮ ታገኛለች? ይሄኛው መንጋ እና ያኛው መንጋ የሚል ቡድን ለመፍጠር የምታገለግል፣ ተፈጭታ ተቦክታና ተጋግራ የተዘጋጀት ነባር የዘረኝነት ዘዴ ናት።
የኛ ወገን እና የነኛ ወገን እያለ፣ የጅምላ የሚደራጅና የሚታጎር፣ በጅምላ የሚቧደንና የሚንጋጋ መንጋ እንዲፈጠር ያደረገው ሙከራ እንዲሳካለት ከፈቀድንለት፣… አዎ፣… ከጋጠወጥ አፍ የተተፋች ስድብ፣… በጭብጨባ የታጀበ ድጋፍን ታስገኝለታለች። አልያም በዝምታ አሜን ብለን ተቀብለንለታል ማለት ነው።
የተወረወረችው ድንጋይም፣ የጋጠወጥ ክፉ ጥፋት መሆኗ ተሽሯል። በሆይሆታ የሚንጋጋ ድጋፍና አድናቆት የሚጎርፍላት፣ አልያም የዝምታ ይሁንታን የምታስገኝ፣ ልዩ ድንጋይ ሆናለች።
የጥፋት ቁልቁለቱ ተከፈተ ማለት ነው - ለሌላ ተመሳሳይ ጋጠወጥ፣ በጣም አስጎምጂ ግብዣ ይሆንለታል።  
ከወዲያ ማዶ በጨዋነት ሲመለከቱ ከነበሩ እልፍ ሰዎች መሃል የተቀመጠ ሌላ አንድ ጋጠወጥ፣… ይህን አጋጣሚ ሲያገኝ፣… የስድብ ድምፅ ሲሰማ፣ የተወረወረ ድንጋይ ሲያይ፣… ምንም አይከፋውም። በተቃራኒው፣ ሲሳይ የዘነበለት ያህል ይወራጫል።
“ተሰደብን፣… ሰደቡን፤ አዋረዱን፣… ተዋረድን፤ ድንጋይ ተወረወረብን፣… በድንጋይ ፈነከቱን” - ይላል በደስታና በእርካታ። ይሄኛው ጋጠወጥ ቁጥር2፣… ከጋጠወጥ ቁጥር 1 ጋር የሚመሳሰል ወራዳ ባህርይ አለው። ልዩነታቸው፣… ከወዲህና ከወዲያ ማዶ መቀመጣቸው ነው።
ጋጠወጥ ቁጥር1 ከወዲህ በኩል ሆኖ፣ ወደዚያ ማዶ፣ ስድብና ድንጋይ በመወርወር ጀመረ።
ወዲያ ማዶ ያለው ጋጠወጥ ቁጥር2፣ አስፀያፊ ስድብ የመትፋት አመሉን፣… ሰውን በመጉዳትና ሰውን በማዋረድ የመርካት ክፉ ሱሱን ለመወጣት፣… ሰበብ አገኘ። በዙሪያው የተሰኑ ሰዎችን በጅምላ ለማቧደን፣ አመቺ አጋጣሚ ይሆንለታል። ሰሚ ጆሮና አጨብጫቢ፣ በድጋፍ የሚንጋጋ፣ በዙሪያው የሚቧደን አጀብ ሲፈጠርለት፣… እንዳሻው ወደ ማዶ አቅጣጫ፣… መሳደብ፣ ድንጋይ መወርወርና፣ ሰዎች ማዋረድ ይጀምራል - ከጋጠወጥ ቁጥር2 የተሰጠ አፀፋ መሆኑ ነው።
የዚህኛው ጋጠወጥ አፀፋ፣ ለጋጠወጥ ቁጥር1 የአፀፋ መልስ ሰበብ እየሆነለት፣… አካባቢው በስካር እየጦዘ ይቀወጣል።
የኛ ወገን፣ የኛ አውራ ብሎ በጋጠወጡ ነውጠኛ ዙሪያ የሚባደን አጀብና የሚታጎር መንጋ ቢፈጠርም፣ ቁጥራቸው ጥቂት መሆኑ አያጠራጥርም።
ግን፣… ብዙ ተመልካች፣ በዝምታ እዚያው በተቀመጠበት ቦታ ምክንያት የተነሳ ብቻ፣ እዚያው የመንጋ አባል ለመሆን ይገደዳል።
አካባቢው ከተቀወጠ በኋላ፣… “የጋጠወጥ ስድብ አስቀያሚ ነው፤ ድንጋይ የመወርወር ጋጠወጥነት ክፉ ጥፋት ነው” ብሎ መናገር ለብዙ ሰው አስፈሪ ነው። “ከሃዲ፣… ሰርጎ ገብ፣… ባንዳ…” ተብሎ የክፋት ሰለባ ሊሆን እንደሚችል ያጠራጥራል?
ለዚያም ነው አብዛኛው ሰው፣ ቀስ ብሎ በጤና ቦታውን ለቅቆ ውልቅ ብሎ የሚሄደው። ከእንደዚያ አይነት የተሳከረ፣ የከሰረና የረከሰ አካባቢ፣… ወደፊትም ለመራቅ ይወስናል። ሜዳውን ለጋጠወጦቹና ለጭፍሮቻቸው አስረክቦ ይጠፋል።

Read 4393 times