Sunday, 11 February 2018 00:00

ኢህአዴግ አለ ወይስ የለም?

Written by  ተፈሪ መኮንን
Rate this item
(9 votes)


     “--መሸማቀቅ በሌለበት ምሁራዊ ክርክር እውነት የሚፈለግበት፤ የማይደፈር የራስ ገዝ አስተዳደርና አካዳሚያዊ ነጻነት ያለው ዩኒቨርስቲ መፍጠር አልቻልንም፡፡ የመንግስት ፖሊሲዎችን አተገባበርና ተጨባጭ ውጤት በነጻነት እየተፈተሹ አማራጭ ሐሳብ የሚያቀርቡ ተመራማሪዎችን መፍጠርና ጠንካራ የሆኑ የከፍተኛ ትምህርት ወይም የምርምር ተቋማት መገንባት አልቻልንም፡፡ በዚህ ሁኔታ ዴሞክራሲ የጥፋት ጎዳና ነው፡፡--”
   
    መምህሩ ከአንድ ጅረት አጠገብ ቆሟል፡፡ ታዲያ አንድ ሰው፣ ቀን ከሌሊት ሳያቋርጥ፣ በዚህ ሁኔታ ለረጅም ጊዜ መዝለቅ ይችላል?! የሰው ልጅ ታሪክ፤ ሳቅና ለቅሶን በመሰለ ተለዋዋጭ ሁኔታ ለበርካታ ሺህ ዓመታት ተጉዟል፡፡ መምህሩም ይህን የሚያሰላስል ይመስላል፡፡ ጊዜ ልክ እንደ ጅረት ሲፈስ ይኖራል፡፡ ታዲያ እንዲህ እየከነፈ የሚፈሰው ጊዜ፤ ዝንተ ዓለሙን ለሰው ልጆች አንድ እና ተመሳሳይ የሆነ ጥያቄ ያቀርባል -- ‹‹ያለፉት ነገሮች አረዳዳችን (ግንዛቤአችን) ትክክል ነው?›› ይላል። ሆኖም ጥያቄውን የሚሰሙት ጥቂቶች ናቸው፡፡ በወንዙ ዳርቻ ቆመው ጥልቅና ሰፊ በሆነ የምልከታ አንጻር ነገሮችን ለማየት የሚችሉት የታደሉት ብቻ ናቸው፡፡  
ሰለሞን ደሬሳ ለ‹‹ልጅነት›› በጻፈው መግቢያ፤ ‹‹አንዳንድ ጥያቄ አለ፡፡ አስር ጊዜ ተጠይቆ፤ አስር ጊዜ መልስ አግኝቶ፤ ዳግመኛ አስር ጊዜ የሚጠየቅ›› ይላል፡፡ አንዳንዶቹ ጥያቄዎች ቁርጥ ያለ መልስ ስለሌላቸው፤ ሌሎቹ ልፊያ የሚፈልጉ ሰዎች ስለሚያነሷቸው ተደጋግመው ይጠየቃሉ፡፡ ልፊያ በሚወዱ ሰዎች፤ አስር ጊዜ ተጠይቆ፤ አስር ጊዜ መልስ አግኝቶ፤ ዳግመኛ አስር ጊዜ ከሚጠየቁ ጥያቄዎች አንዱ፤ ‹‹በኢትዮጵያ ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት አለ?›› የሚለው ጥያቄ ነው፡፡ በበኩሌ ዕድገቱ የሚታይ እና የሚዳሰስ ነው፡፡ ሆኖም አንዳንድ የገዢው ፓርቲ ተቃዋሚዎች ጥያቄ ያነሳሉ፡፡ በተለያየ የአተረጓጎም ቀዳዳ በመሹለክ ስኬቱን ሊያጣጥሉት ይሞክራሉ፡፡ ኢኮኖሚክስና ፖለቲክስ የህዝብ አስተያየትና ፍላጎትን የሚጠቅሱ አስቸጋሪ ጉዳዮች በመሆናቸው ለሸፍጥ ይመቻሉ፡፡
የሆነ ሆኖ የሐገራችን የኢኮኖሚ ዕድገት የሚታይና የሚዳሰስ ነው፡፡ ዕድገቱ ተከታታይነትና ፍጥነት ያለውም ነው፡፡ ኢኮኖሚያችን በአማካይ በ10 በመቶ ሲያድግ መቆየቱም እውነት ነው። የኢኮኖሚ ባለሙያዎች፤ የሐገር ኢኮኖሚ ከ15 በመቶ በላይ ሊያድግ አይችልም ይላሉ፡፡ ስለዚህ ከግለሰብ መብትና ከገበያ ጤንነት አኳያ የሚነሳ ችግር ካልሆነ በቀር፤ የሐገራችን ኢኮኖሚ አንድ ኢኮኖሚ ሊያድግ በሚችለው ከፍተኛ የዕድገት ምጣኔ እያደገ በመሆኑ፤ በበኩሌ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ለውጥ ለማድረግ የሚፈልግ ሰው ትክክል አይመስለኝም፡፡ አማራጭ ፖሊሲ አለኝ የሚል የፖለቲካ ድርጅት፤ ከያዘው አይዲዮሎጂ ጋር ፍቅር ስለያዘው ካልቀየረው በቀር፤ በኢኮኖሚያዊ ምክንያት የፖሊሲ ለውጥ ሊያደርግ አይችልም። የኢኮኖሚ ባለሙያ ባልሆንም፤ የፖሊሲ ለውጥ ተደርጎ ኢኮኖሚውን ከ15 በመቶ  በላይ ማሳደግ አይቻልም መባሉ፣ የፖሊሲ ለውጥ አስፈላጊ አለመሆኑን ይነግረኛል፡፡ ስለዚህ በኢኮኖሚያዊ ምክንያቶች የፖሊሲ ለውጥ ሊደረግ አይችልም። ሆኖም በፖለቲካው ዘርፍ ለሚታየው ከፍተኛ ችግር አስተዋጽዖ ያደረጉ የኢኮኖሚ አስተዳደር ጉድለቶች መኖራቸውን አምናለሁ፡፡ በዚህ የተነሳ ኢኮኖሚውም ሆነ ፖለቲካው አደጋ ውስጥ መግባታቸውንም አምናለሁ፡፡ ይህን የኢኮኖሚ ዕድገት ተዐምር በመፍጠሩ የሚኮራው ኢህአዴግም ችግሩን አምኗል፡፡
በነገራችን ላይ ኢህአዴግ በህይወት መኖሩን መመስከር ቸግሮኛል፡፡ አሁን ያሉት አባል ድርጅቶቹ እንጂ ኢህአዴግ የፖለቲካ አልጋ ቁራኛ ከሆነ ቆይቷል። በዚህ የተነሳ ሐገርን ለከፋ አደጋ የዳረገ የፖለቲካ ቀውስ ተፈጥሯል፡፡ ልፊያ በሚፈልጉ ሰዎች፤ አስር ጊዜ ተጠይቆ፤ አስር ጊዜ መልስ አግኝቶ፤ ዳግመኛ አስር ጊዜ የሚጠየቀውን ጉዳይ በዚህ እንለፈው፡፡
አሁን ቁርጥ ያለ መልስ ስለሌለው፤ አስር ጊዜ ተጠይቆ፤ አስር ጊዜ መልስ አግኝቶ፤ ዳግመኛ አስር ጊዜ የሚጠየቀውን ጉዳይ እንይ፡፡ የተጠቀሰው ዓይነት ዓመል የሚታይበት ጥያቄ፤ የብሔራዊ አንድነትና የብሔር ቡድኖች ጥያቄ ነው፡፡ ለዚህ ጥያቄ መልስ የሚሰጡ ፖለቲከኞች፤ ለብሔራዊ አንድነት ወይም ለብሔር መብት የሚያደሉ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ሁለቱም በሚሰጡት ትንታኔ እርግጠኞች  ይሆናሉ፡፡ ሆኖም የብሔራዊ አንድነትና የብሔር ቡድኖች ጥያቄ ለእርግጠኝነት የሚመች ጉዳይ አይደለም፡፡ ነገር ግን በሁለቱም ጎራ ያሉት ፖለቲከኞች፤ አንዳቸው የሌላቸውን ሥጋት ከግምት በማስገባትና በቅንነት በመነጋገር ፋንታ ይወጋገዛሉ፡፡ በሐሳብ ለመሸናነፍ ይሞክራሉ፡፡ አንዱ በሌላኛው መቃብር እንዲያብብ ይመኛሉ፡፡ ሆኖም ጥያቄው አስር ጊዜ ተጠይቆ፤ አስር ጊዜ መልስ አግኝቶ፤ ዳግመኛ አስር ጊዜ የሚጠየቅ በመሆኑ፤ በአንዱ ጎዳና ብዙ ገፍተን በሄድን መጠን የሌላኛውን አስፈላጊነት የሚያስረዳ ችግር ይገጥመናል፡፡ ስለዚህ የአንዱ መጨረሻ የሌላኛው መጀመሪያ ነው፡፡ በእነዚህ ሁለት አቋሞች መካከል የሚደረግ ክርክር ዘላለማዊ ነው፡፡ ነገር ግን ሁለቱም ወገኖች የተሻሉ፣ ትክክለኛና ብቸኛ አማራጮች መሆናቸውን ሊነግሩን ይሞክራሉ፡፡ በዚህም ይሳሳታሉ፡፡
ሁለቱንም አቻችለን ለመሄድ ስንሞክርም፤ ሚዛን መጠበቁ አስቸጋሪ ባህርይ ያለው በመሆኑ፤ ለዳኝነት ከሚያስቸግሩ የተለያዩ ጉዳዮች ጋር እየተጋፈጥን ዘወትር ስንፈተን እንኖራለን፡፡ የብሔራዊ አንድነትና የብሔር ቡድኖች ጥያቄ ዘላለም ወላዋይ አስተያየት የሚያስታቅፈን ነው፡፡ ነገሩ ያለቀለትና አንዴ ተመልሶ የሚያድር አይደለም። ባለፉት 26 ዓመታት የተረዳሁት ይህን ነው፡፡
በሌላ በኩል፤ የብሔር ጥያቄ ሲነሳ የኋላ ቀሮችና መሠረት የሌለው የፖለቲካ አጀንዳ አድርገው የሚመለከቱ ሰዎች አሉ፡፡ ሆኖም ጥያቄው የሰብአዊ መብት ሰነዶች፣ የፖለቲካ ሳይንስ፣ የፔዳጎጂ፣ የሥነ ልቦና፣ የማህበራዊና ባህላዊ ቁም ነገሮች ድጋፍ ያለው ጥያቄ መሆኑን አይቻለሁ፡፡ ታዲያ በቅርቡ የተነሱትን ችግሮች በመጥቀስ፤ ‹‹አሁን የብሔር ጥያቄን በመቀበል የደረስንበትን ሁኔታ ተመልከቱ። ሐገሪቱን አደገኛ ቀውስ ውስጥ እንደጣላት ማየት ለምን አቃታችሁ›› በሚል የሚከራከሩ አሉ፡፡ መፍትሔውም ከብሔር ፖለቲካ መውጣት ነው ይላሉ፡፡
ቀደም ሲል፤ የብሔራዊ አንድነት ጥያቄ ሸማች የሌለው የፖለቲካ አጀንዳ መስሎ ነበር፡፡ ዛሬ በተቃራኒው አቅጣጫ ለመሄድ የሚገፋፋው ነገር ተጠናክሯል፡፡ የብሔር ቡድኖችን ጥያቄ የመግፋት አመለካከት ሰፊ ድጋፍ የሚቸረው አመለካከት ሆኖ ይታያል፡፡ ገዢው ፓርቲም የብሔር ጉዳይን አብዝቼው ነበር ብሏል፡፡ የጎሳ ፖለቲካ ሐገሪቱን ከአደገኛ ቀውስ አፋፍ አቁሟታል የሚለው ሰውም በዝቷል፡፡ ሆኖም ከዛሬው ሁኔታ የደረስነው የብሔር ቡድኖች ጥያቄን ለመቀበል ፈቃደኛ ባልሆነ የፖለቲካ አስተሳሰብ ተመርተን መሆኑ የተዘነጋ ይመስለኛል። ነገሩ ውሃ ቅዳ ውሃ መልስ ሆኗል፡፡ እኔ አስር ጊዜ ተጠይቆ፤ አስር ጊዜ መልስ አግኝቶ፤ ዳግመኛ አስር ጊዜ የሚጠየቅ ጥያቄ መሆኑ ገብቶኛል፡፡  
ሆኖም አሁን እንደ ሐገር የምንገኝበት ቦታ፤ ወደ ኋላ ለመመለስም ሆነ ወደ ፊት ለመጓዝ ከሚያስቸግር ቦታ ነው፡፡ ወደ ኋላ በመመለስ ሆነ ወደፊት በመሄድ የሚታየን ገደል ነው፡፡ አሮጌው ሞቷል፡፡ ሊደግፈን አይችልም፡፡ አዲሱ ታሟል፡፡ ህክምና ይፈልጋል፡፡ ስለዚህ መፍትሔው በአዲሱ ስርዓት የተገኙትን መልካም ነገሮች ከጉዳት በመጠበቅ ማቆየትና ወደፊት ለመሄድ የሚያስችለን ጎዳና የት እንዳለ ለማወቅ ረጋ ብሎ ማሰብ መጀመር እንጂ በአንድነትና በብሔር ቡድኖች ጥያቄ ዙሪያ ክርክር ማድረግ አይደለም፡፡ በዚህ አጀንዳ ዙሪያ የምናደረገው ክርክር ለመሸናነፍ ሳይሆን ጉዳዩን በተሻለ ሁኔታ የመረዳት ዕድል ለማግኘት ሲባል የሚደረግ መሆን አለበት፡፡ አሁን ለገጠመን አሳሳቢ ችግር መፍትሔ የሚገኘውም ከዚህ የክርክር አዳራሽ ውጪ ነው፡፡
አሁን እንደ ህብረተሰብ ገና በውል ካልተረዳነው አንድ የሽግግር ሁኔታ ውስጥ ገብተናል፡፡ ይህ ሽግግር ከምን ወደ ምን እንደሆነ ለመረዳት የቻለ ሰው አልተገኘም፡፡ በተጨባጭ ያለውን ሁኔታ ለማንበብና ለመመርመር የሚሞክሩ ሰዎችን ግራ የሚያጋቡ አዳዲስ ክስተቶች እየተደራረቡ ይመጣሉ፡፡ ሁኔታዎች በፍጥነት እየተለዋወጡ የመረዳት አቅማችንን ይፈታተናሉ፡፡ እንቆቅልሹን ይበልጥ ያወሳስባሉ፡፡ በሰማይ የመብረርና በምድር የመሽከርከር ችሎታን የሚጠይቁ ነገሮች ሆነዋል፡፡
አሁን እንደ ህብረተሰብ ያለንበት ሁኔታ አሳሳቢ ነው፡፡ የህዝቡ ህይወት ቀውስ ውስጥ ገብቷል፡፡ የሐገር ምሰሶ የሆኑ እሴቶች ተርገድግደዋል፡፡ ይህን አደጋ ለመከላከል የሚደረጉ ጥረቶችም በድንገተኛ እርምጃ ተጎሳቁለዋል፡፡ በፖለቲካው ብቻ አይደለም የሐይማኖት ተቋማትም መንፈሳዊነት ተዳክሟል። የመንግስት ኃላፊነት የያዙ ሰዎች የሞራል ልዕልና እና ራዕይ የሌላቸው ሆነዋል፡፡ መሪዎቻችን ተራ ስሜቶች የሚነዳቸውና ሁኔታን የመገምገም ብቃት የሌላቸው ሆነዋል፡፡ የጽድቅና የኩነኔ፤ የጥሩና የመጥፎ ድንበር ተቀላቅሏል፡፡ እንደ ማህበረሰብ ድቀት ገጥሞናል፡፡ አሁን የስኬትና የውድቀት መመዘኛ ገንዘብ (ስለዚህም ሥልጣን) ብቻ ሆኗል። ገንዘብ ለማግኘት በየትኛውም መንገድ ለመሄድ ዝግጁዎች ሆነናል፡፡
የኢትዮጵያ ህዝብ በመሠረቱ ተለውጧል። የዴሞክራሲ ስርኣትን ለመለማመድ ጥረት ያደርጋል፡፡ በዴሞክራሲያዊ ስርዓቱ መጠቀም የሚፈልግ ህዝብና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ ለመቆም የሚፈልግ መንግስት አለ፡፡ ነገር ግን የስርዓቱ መሠረትና ዋልታ ለሆኑ ጉዳዮች ትኩረት ሰጥቶ፣ ቅደም ተከተል አስቀምጦ፤ የዴሞክራሲ እሴቶች እንዲዳብሩና እንዲጠናከሩ ለሚያደርጉ ተቋማት ትኩረት አይሰጥም፡፡ ታዲያ የዴሞክራሲ እሴቶችን የሚያጎለብቱና ከጉዳት የሚጠብቁ ተቋማት ሳይፈጥሩ፣ ዴሞክራሲን እንዴት መተግበር ይቻላል። በዚህ ሁኔታ የሚኖር ዴሞክራሲ ትርምስና ሞትን መጋበዝ ነው፡፡
የህዝብ አመኔታ ያላቸው ተቋማት እንዲፈጠሩና እንዲጠናከሩ ሳይደረግ ዴሞክራሲ ሊቆም አይችልም፡፡ ባለፉት ዓመታት የህዝብ አመኔታ ያለው ፓርላማ፣ የህዝብ ክብርን ያተረፈ ነጻና ገለልተኛ ፍርድ ቤት፣ የምርጫ ቦርድ፣ ሚዲያ፣ የእንባ ጠባቂ ተቋም፣ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን፣ የሙያ (ብዙሃን) ማህበራት መፍጠር አልቻልንም። እንዲሁም በህዝብ አገልጋይነት መንፈስ የሚመራ፤ ከፖለቲካ ድርጅቶች ጣልቃ ገብነት የተጠበቀና የፖለቲካ ትግል መሣሪያ ከመሆን የጸዳ የሲቪል ሰርቪስ ተቋማት መፍጠር አልቻልንም፡፡ መሸማቀቅ በሌለበት ምሁራዊ ክርክር እውነት የሚፈለግበት፤ የማይደፈር የራስ ገዝ አስተዳደርና አካዳሚያዊ ነጻነት ያለው ዩኒቨርስቲ መፍጠር አልቻልንም፡፡ የመንግስት ፖሊሲዎችን አተገባበርና ተጨባጭ ውጤት በነጻነት እየተፈተሹ አማራጭ ሐሳብ የሚያቀርቡ ተመራማሪዎችን መፍጠርና ጠንካራ የሆኑ የከፍተኛ ትምህርት ወይም የምርምር ተቋማት መገንባት አልቻልንም፡፡ በዚህ ሁኔታ ዴሞክራሲ የጥፋት ጎዳና ነው፡፡
በሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች ዘንድ ከፓርቲ ጥቅም በላይ ሆኖ የሚታይ ነገር የለም፡፡ በፖለቲካ ጥቅም ሒሳብ የፍርድ ቤቶች ነጻነት ይደፈራል፡፡ በአቋራጭ በመበልጽግ ሒሳብ ፍትህ ሸቀጥ ይደረጋል፡፡ ተራ የመንግስት አገልግሎት ሁሉ ለሽያጭ ይቀርባል። በአድሎ መሥራት አሳፋሪ ነገር መሆኑ ቀርቷል። የሰውን ህይወት በሚመለከቱ እንደ ህክምና ያሉ ሙያዊ አገልግሎቶች ጭምር የምናያቸው ጨካኝ አሰራሮች፣ እንደ ህብረተሰብ ከምን ደረጃ እንዳለን ይነግሩናል፡፡ የሐገር ደህንነት ጥበቃ ኃላፊነት በተጣለባቸው ተቋማት ውስጥ የሚሰሩ ሰዎች በውስብስብ ወንጀሎች ተሳታፊ መሆናቸውን አይተናል፡፡ በጥቅሉ ከፍተኛ ማህበራዊ ዝቅጠት ውስጥ ወድቀናል፡፡ እንዲህ ዓይነት ህብረተሰብ ለግጭት መዳረጉ የማይቀር ነው፡፡   
ኢትዮጵያ የህግ የበላይነት የተከበረበት ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለመፍጠር ትኩረት ካላደረገች፤ በዓለም አንደኛ በሚል የምንኩራራበት ፈጣን ኢኮኖሚ ትርጉም አይኖረውም፡፡ ዘላቂ የሚሆን ሐብት አይፈጠርም፡፡ እንዲያውም የተፈጠረው ትንሽ ሃብት እርስ በእርስ ያጋጨናል፡፡ ያባላናል፡፡ ሐገራዊ ቀውስን ያስከትላል፡፡
ብዙዎች የሚያውቁት ‹‹God Must be Crazy›› የሚል ርዕስ ያለው ድንቅ ፊልም አለ፡፡ ይህ ፊልም የውጭ ሰው ረግጦት በማያውቀው የተገለለ ምህዳር ውስጥ በደስታ ይኖር ስለነበረ አንድ ማህበረሰብ የሚተርክ ነው፡፡ አንድ ቀን ከበላያቸው ባለው ሰማይ ይበር ከነበረ አውሮፕላን የተጣለ የኮካኮላ ጠርሙስ በአካባቢያቸው ወደቀ፡፡ በዚህች የኮካ ጠርሙስ የተነሳ በተሟላ ሰላም ይኖር የነበረው ማህበረሰብ፣ የችግሩ ምንጭ የኮካ ጠርሙሱ መሆኑን ተረድተው፤ ጠርሙሱን ከአካባቢው አርቀው ለመጣል ወሰኑ። ከመካከላቸው አንዱ፣ ጠርሙሱን ለመጣል አገር አቋርጦ ሄደ፡፡ በጉዞው ብዙ ግራ አጋቢና ህይወቱን ለአደጋ የሚያጋልጡ ፈተናዎች ገጠሙት፡፡ ታሪኩ የሚታይ እንጂ የሚነገር አይደለም፡፡ ታዲያ እዚህ የጠቀስኩት፤ ጠንካራ የዴሞክራሲ ተቋማት በሌሉበት ጫካ የተፈጠረችው የኮካ ጠርሙስ የምታክል ትንሽ ሐብት፣ ሐገር እያተራመሰች መሆኑን በምሣሌ ለመናገር ነው፡፡
በዚህ ሁኔታ በቅርቡ የተሰማው ‹‹ኢትዮጵያ ወርቅ ላይ የተቀመጠች ሐገር ነች›› የሚለው ዜና፣ ሥጋት እንጂ ብስራት አይሆንም፡፡ መርገም እንጂ በረከት አይደለም፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ‹‹ወደ ጅቡቲ የሚዘረጋ የተፈጥሮ ጋዝ ወይም ነዳጅ ማስተላለፊያ ቧንቧ ለመገንባት ስምምነት ተፈረመ›› የሚል የቢሊዮን ዶላር ፕሮጀክት ዜና አያስደስትም። ሆኖም የሰላም ዋስትና የሚሆኑ የዴሞክራሲ ተቋማትን ለማጠናከር ከልብ ከሰራን፣ በአጭር ጊዜ የኢትዮጵያ ህዝብ ህይወት ሊቀየር እንደሚችል የሚያመለክት በመሆኑ፤ አሁን የሚታየው የሰላም መደፍረስ ይበልጥ ያስቆጫል፡፡ የዓለም ህዝብም፤ ‹‹የኢትዮጵያ ህዝብ ወደ ለመደው ትርምስ ይገባል ወይስ ችግሮቹን በማስተዋል ፈትቶ፣ የጀመረውን የልማት ጉዞ ይቀጥላል?›› በሚል በአንክሮ እያስተዋለን ይገኛል፡፡ ኢህአዴግም ከአልጋው እየተነሳ፤ ከወንዙ ዳር ቆሞ ይመለከታል። ምን እያሰበ እንደሆነ ለመናገር ያስቸግራል፡፡ ምናልባት አለሁ ወይም የለሁም እያለ ይሆናል፡፡

Read 3639 times