Sunday, 11 February 2018 00:00

የሠርጌ’ለታ

Written by  ሌሊሳ ግርማ
Rate this item
(3 votes)

 በአዲስ አበባ ከተማ ሁሉም ነገር ብዙ ነው፡፡ ሁሉም ነገር ሰፊ ነው፡፡ ብዙ መኪናዎች አሉ፡፡ በየመንገዱ ሲርመሰመሱ የሚውሉ፣ የሚያብለጨልጩ የዲኦዶራንት ብልቃጥ የመሰሉ ቪትዝ የሚባሉ መኪኖች አሉ፡፡
ከቪትዝ መኪና ጋር በራሽን ካርድ የታደሉ ቲ-ሸርት እና ትንሽ  ቦርጭ ያላቸው ሾፌሮች፤ ከጎናቸው እርጉዝ ሚስቶቻቸውን ይዘው ሲመላለሱ ይውላሉ፡፡ አዲስ አበባ ከተማ ሁሉም ነገር ተመሳሳይ ነው፡፡ መንገዱ ረጅም ነው፤ ግን ይሰለቻል፡፡
በአለፈው ሰሞን የአጭሯን ሚስቴን እጅ ጨምድጄ መንገድ ሳቋርጥ፣ እሷ ዘና ብላ ከኋላ እየተሳበች አስቸግራኛለች፡፡  መጀመሪያ ላይ የገለፅኩት አይነት ወጣት፣ በቪትዝ መኪናው ክላክስ እያጮኸ፣ የተዝናናችዋን እጮኛዬን ለማስደንበር ሞክሮ ሳይሳካለት አለፈ፡፡
ከማለፉ በፊት ዝቅ ባደረገው መስኮት አንድ ስድብ ብጤ ወርውሯል፡፡ የአዲስ አበባ የመኪና ሾፌር፣ የመንጃ ፈቃዱን ከስድብ ፈቃድ ጋር አንድ ላይ አውጥቶ የሚገለገል መሆኑ ግልፅ ስለሆነ ብዙም አልገረመኝም፡፡
‹‹እንደ አህያ ምን ይጎትትሻል… አለኝ እኮ ሰማኸው›› አለችኝ፤ የመንገዱን ጎርፍ ተሻግረን ዳርቻው ላይ ከወጣን በኋላ፡፡ እጮኛዬን በመስደቡ ሾፌሩና እኔ ከሌሎቹ ተራ የቪትዝ ባለቤቶች የተለየ ቅርበት ፈጠርን፡፡ በስድብ እሷን በመንካቱ ልብ ብዬ መኪናውን አየኋት፡፡ የመኪናዋ ቀለም ‹‹ሲልቨር›› የሚባል አይነት ነው፡፡ በጥቁር ልቤ ሳያት ግን ሌላ የጠየመ ቀለም ተላብሳ ታየችኝ፡፡ የሰሌዳ ቁጥሯ በሶስት ተመሳሳይ ቁጥሮች ነው የሚጀምረው። ያው ሰይጣን ቀኔን ለመልከፍ የላከው ነው ብዬ፤ በውስጤ በግኜ ጭጭ አልኩኝ፡፡ ምንም ላደርገው አልችልም፡፡ እሱ በመኪና፣ እኔ በእግር ነኝ፡፡ ለነገሩ በመኪናም ብሆን ክላክስ እየነፋሁ መሪዬን እየደበደብኩ፣ ጥላቻዬ ከመግለፅ በዘለለ ምንም ማድረግ አልችልም፡፡
‹‹ከፋህ /አልከፋህም?›› የሚል ጥያቄ ‹‹መንጠቆ›› የተባለው የጥላሁን ጉግሳ ገጸ ባህርይ በተውኔቱ ላይ እየደጋገመ ሲጠይቅ ትዝ ይለኛል፡፡ ድራማውን ያየሁት ልጅ ሆኜ ትምህርት ቤቴ መጥቶ በቀረበልን ወቅት ነበር፡፡ የድራማው ጠቅላላ ጭብጥ ፈፅሞ ተረስቶኛል፡፡ ጥያቄዋ ብቻ አብራኝ አድጋለች፡፡ አንድ የሚያስከፋ አጋጣሚ ሲከሰትብኝ… እና ያንን የተከሰተ አጋጣሚ በእኩሌታ አፀፋ ማጣፋት ሳልችል ስቀር በሆዴ ‹‹ከፋህ?...›› ብዬ ራሴን እጠይቅና… ወዲያው ደግሞ ‹‹አልከፋኝም!›› ብዬ ራሴው እመልሳለሁኝ፡፡ የጨዋታው አሸናፊ ሆኜ መቀጠል እንድችል ‹‹አልከፋኝም›› ብዬ ጥርሴን ነክሼ፣ በውስጤ በግኜ ግን የተፅናናሁ መስዬ ወደፊት መቀጠል ይኖርብኛል፡፡
እና እጮኛዬን ይዤ ወደ ቤቴ ገባሁኝ፡፡ አጋጣሚውም ተረሳ፡፡ ለነገሩ እኔ እና እሷ በቀጣይ በሚመጡ ሳምንታት ከፍተኛ ፕሮግራም ነበረብን፡፡ አራት የትውውቅ አመታችንን ወደ ቀጣይ ምዕራፍ ለማሻገር ደፋ ቀና በማለት ላይ ነበርን፡፡
በጣም አነስተኛ ፕሮግራም ነው የያዝነው…፡፡ ዋናው አላማችን ቤተሰቦቻችንን ማስተዋወቅ ነበር፡፡ አብረን መኖር ከጀመርን ቆይተናል፡፡ ግን ብቻችንን ተከራይተን እንደምንኖር ነው፣ ቤተሰቦቻችን ያውቁ የነበረው፡፡
ፕሮግራማችን ልብስ ያስፈልገዋል፤ ያለችንን ጥሪት አጠራቅመን፣ ለእኔ ሙሉ ሱፍ እና ለእሷ የአበሻ ቀሚስ መግዣ አዋልነው፡፡ ካራቱ ዝቅ ያለ ቀለበት ተለክተን ገዛን፡፡ በቀለበቱ ላይ ስማችንን አፃፍን፡፡ እኔ የማደርገው ላይ የሷ ስም፣ እሷ የምታደርገው ላይ የኔ ስም ተነቀሰ፡፡
ለፕሮግራሙ ሦስት ሳምንት ሲቀር፣ ለሁለቱም ቤተሰብ ያቀድነውን ነገርናቸው፡፡ እኔ እሷ ቤተሰብ ዘንድ፣ እሷ እኔ ቤተሰብ ዘንድ ቀርበን ታየን፡፡ ወደዱም ጠሉ፤ ‹‹እኛ ወደናል ይሁን!›› አሉ፡፡
የፕሮግራሙ ቀን ደረሰ፡፡ የድሮ ጋብቻ በቄስ ፊት የሚከናወን ይመስለኝ ነበር የዘንድሮ በወረዳ ፊት የሚከናወን ነው፤ ያውም ወረዳው በቢሮ ጥበት ውስጥ በኮምፒውተር ካካታ ታጅቦ፡፡ የሙሽራ ልብስ ለብሰን መታወቂያችንን ተሯሩጠን ፎቶ ኮፒ ስናስነሳ ለተመለከትን ሳናስቅ አንቀርም፡፡ በዛ ላይ ‹መረጃ አላሟላችሁም› በሚል የጋብቻ ሰርተፍኬት አንሰጣችሁም… ብለው ከለቅሶ መለስ ብዙ አስለመኑን። ሚዜ ብለን ያመጣናቸው ጓደኞቻችን፣ ወደ ምስክር ቀይረው እኛን እንዳሯሯጡን እነሱንም አንገላቷቸው፡፡…
…ብቻ የማይጠናቀቅ ነገር የለም ተጠናቀቀ፡፡ ቀጣዩ ፕሮግራም የምሳ ስለሆነ ወደ ሚስቴ ወላጆች ቤት ተንቀሳቀስን፡፡ እኔም ሆነ እሷ የሙሽርነት ስሜት ለማጣጣም ወከባው አልፈቀደልንም፡፡
የወላጆቿ ቤት ሰፊ ነው፡፡ የእኔ ቤተሰቦች፣ የእሷን ቤተሰብ ቤት ሲያዩ ዘፈን ጠፋባቸው፡፡ ታዳሚ በሁለቱም ወገን ስንጠራ፤ ‹‹ከሀያ ሰው መብለጥ የለበትም›› ብለን የተነጋገርነው መቼ እንደተዘነጋ እርግጠኛ አልነበርኩም። ዘመድን እንደ አንጀት መዞ የሚያወጣ ነገር ሰብስቦ አምጥቷቸዋል፡፡ ቤቱ በሙሉ በሁለት የልብስ ዘርፍ የተከፈለ ነው፡፡ ወንድ በሙሉ ጥቁር ሱፍና ምላስ የመሰለ አጫጭር ክራባት አንጠልጥሏል፡፡ ሴቶቹ በሙሉ ከሽሮሜዳ ያሸመኑትን የሀገር ልብስ በሂል ጫማ አድርገዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ ‹‹ሜክአፕ›› በሚባል ዘመናዊ ምትሀት፣ የሴቶቹ ፊት ተለቅልቆ ሐውልት መስለዋል። ደግነቱ መሳሳም እንዳይበዛ ለማገድ መቀባታቸው ጠቅሟል፡፡ በፍጥነት የምሳው ፕሮግራም ተጀመረ፡፡ በሁሉም ተግባር ጋባዡ ቤተሰብ፤ ለተጋባዡ ቤተሰብ ለመንገር የፈለገው መልዕክት እንዳለ ማሰብ ጀምሬ መቀጠል ግን አቃተኝ፡፡ ወከባው በጥንቃቄ ነገራትን ለማሰላሰል መተንፈሻ ክፍተት አልነበረውም፡፡ ቶሎ -ቶሎ? ዋጥ-ዋጥ እያደረገ፣ ወደ ቅምቀማ መግባት የቸኮለው ብዙ ነው፡፡ ግን ምግቡ በበሰለ ቅቤ የታሸ ክትፎ በመሆኑ፣ እንደ ቆሎ ቃም ቃም ለማድረግ አላመችም። ምግቡ እስኪወራረድ ሲሰማ የቆየው ለስላሳ የሰርግ ሙዚቃ የቱ ጋር ጉሮሮው ላይ እንደታነቀ ሳይታወቅ፣ እስፒከሩ ጮክ ያሉ የብሔር ብሔረሰብ ሙዚቃዎች ማፍለቅ ጀመረ፡፡
ሙዚቃዎቹ በሀገሩ ላይ ያሉትን ብሔሮች የሚዘክሩ እንዳልሆኑ ግልፅ ነው፡፡ የእኔ እና የባለቤቴ ዘረ-መል የተገኘበትን ብሔር የሚነኩ ዘፈኖች በጥንቃቄ እየተመረጡ፣ በወፍራሙ በሚጮኸው እስፒከር ቧንቧ በኩል ያለ ቅጥ ተለቀቁ፡፡
የባለቤቴ ቤተዘመዶች ለካ ቀላል መንቀሳቀስ አያውቁም! የቤቱ ሳሎን የእምነበረድ ወለል መሆኑ እንጂ መሬት እየረገጡ ወደ አየር በሚጎኑት እግሮች ብዛት ቤቱ በአቧራ ጉም መሸፈኑ አይቀርም ነበር፡፡ አቧራው ጨሰ!... አልኩኝ ለራሴ፡፡ ወከባው ሁሉ በሰላም እንዲጠናቀቅ ከመፈለጌ የተነሳ ሰዓትን በፍጥነት ጠምዝዞ የማሳለፊያ መንገድ መፈለግ ጀመርኩኝ፡፡
ከእለታት በአንዱ ቀን፣ አንዱ ሱሰኛ ጫት ለምን እንደሚቅም ተጠይቆ በመለሰበት አልባሌ ቃለ መጠይቅ ላይ፤ ‹‹ጫት ቃሚ ከሌላው ምንም የሚለየው ነገር የለም… ለምሳሌ በክፍለ ሀገር አውቶብስ፣ አንድ ጫት የሚጠቀምና የማይጠቀም ሰው በአንድ ወንበር ላይ ተቀምጠው ቢጓዙ የመረቀነው ቀድሞ ይደርሳል እንጂ ሌላ ምንም ጥቅም የለውም›› ብሎ ነበር አሉ፡፡
እና እኔም ቀድሜ የፕሮግራሙ መልካም መጠናቀቂያ ላይ መድረስ ከመፈለጌ የተነሳ ከቢራ ጋር የሚቀዳልኝን ውስኪ እንደ ትኩስ ሻይ ‹‹እፍ›› ሳልል ‹‹ጭልጥ›› ማድረግ ጀመርኩኝ፡፡ ተው የሚለኝም አላገኘሁኝም፡፡ ከቆይታ በኋላ የገባው ሁሉ መልካም እንደሆነ አየሁኝ። በአፌ የገባው ምግብም ሆነ መጠጥ፤ አለሙን ሁሉ ጥሩ አደረገልኝ፡፡ የተጠሩትን ሰዎች እየተዟዟርኩ መተዋወቅና መልካም ምኞት መቀበል ጀመርኩኝ፡፡ ሁሉ ሰው ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ እንደሚወደኝ ያረጋገጥኩኝ መሰለኝ፡፡… ሁሉ ነገር ተመቸኝ፡፡ ሰርጌ ላይ መሆኔን አመንኩኝ፡፡ እንደ መወለድ ወይንም እንደ ሞት ከአንድ በላይ የማይደገም አጋጣሚ ነው ብዬ እንደ መፈላሰፍም አደረገኝ፡፡ ውልደትና ሞትን ደግሞ የሙሽራ ልብስ ለብሼ፣ የውስኪ ብርጭቆ ጨብጬ፣ እየተደሰትኩ የማጣጥመው ክስተት አይደለም፡፡
ቀስ እያለ ወደ መድረኩ ለእንቅስቃሴ ስጋበዝም፣ ማቅማማት እየተውኩኝ፤ ‹‹እሺ›› ማለት ጀመርኩኝ፡፡
በአራቱም አቅጣጫ የሁሉም ሰው እንቅስቃሴ፣ በተደገኑ ካሜራዎች እየተመዘገበ መሆኑ መዝለልና መፈንጠዝ ከጀመርኩ በኋላ ትዝ ሲለኝ… የጀመርኩትን የትከሻ ሰበቃ ትዕይንት ትቼ ዳር እወጣለሁኝ፡፡
ፕሮግራሙ ያልተፃፉ ህጎች ነበሩት፡፡ የእኔ ወላጆች በክብር ቀማምሰው፣ ፎቴ ላይ በረድፍ ተቀምጠው ከቆዩበት አስር ሰዓት ሊሆን ገደማ፣ ድንገት ተነስተው ምርቃት አዥጎድጉደው… እንደ አገባባቸው ወጥተው እብስ ለማለት ሲሞክሩ፤ እግራቸውን ተከትዬ መኪና ድረስ ሸኘኋቸው፡፡ የሸኘኋቸው ግን ስለ ፕሮግራሙ የተሰማቸውን ጥቅል አስተያየት ለመቀበል ስለጓጓሁ ነው፡፡… መቶ በመቶ መደሰታቸውን ሲነግሩኝ፣ ትከሻዬ ላይ የተጫነው የጭንቀት ርዝራዥ በአጠቃላይ ተኖ ጠፋ፡፡
እነሱን ሸኝቼ ስመለስና… ሚዜ ይሁኑ ሽማግሌ አልያም ምስክር ብዬ የጠራኋቸው ጓዶቼን ስቀላቀል፣ በጣም ለመስከር ዝግጁ ሆኜ ነበር፡፡ አጠጣጣችንን አይተው ስለተበረታቱ ወይ ስለፈሩ… በግልፅ በማይታወቅ ምክንያት የሚስቴ ወላጆች ለክፉ ቀን ያስመጡትን መጠጥ በሙሉ አራግፈው፣ በእኛ ብርጭቆ ቁመት ልክ ይቀዱት ጀመር፡፡ እኛም አላሳፈርናቸውም… ያፈሰሱትን ሁሉ አፍሰን ጨለጥንላቸው፡፡
ጨዋታውና ጭፈራው መጀመሪያ ላይ ደርዝ ነበረው፡፡ ግን ወደ ምሽት ገደማ ሚስቴ አንዳንድ ማስጠንቀቂያ ወደ ጆሮዬ እየመጣች ስታስታውሰኝ ትዝ ይለኛል፡፡ ‹‹መጠጥ ከመጠን በላይ አትጠጣ!›› የሚል ነው፣ ማስታወሻው ሲጠቃለል፡፡
‹‹አትስጊ… ሁሉም ጥሩ ነው›› የሚል ምላሽ እየሰጠሁ፣ ስሸኛት ቆየሁኝ፡፡… በመሐል ሰዓት እንዴት እንዳለፈ አላውቅም፡፡ ከሰዓቱ ጋር… ቀደም ብሎ የመመቸት ስሜት የተሞላ ጥቅል መንፈሴ፣ የሆነ መጨናነቅ ሲፈጠርበት ትዝ ይለኛል፡፡ ጭንቀቴ ደግሞ የሚዜዎቼ ወይንም የጓደኞቼ ቅጥ ያጣ የዳንስ አይነት ነበር፡፡ ‹‹ሰዓታቸውን አልፈዋል… እስካሁን ተሰናብተው መሄድ ነበረባቸው›› ብዬ ተጨንቄአለሁኝ፡፡ ግን ጭንቀቴን አልነገርኳቸውም።
ለነገሩ ብነግራቸውም እኔን የሚሰሙበት የጆሮ ሁኔታ ላይ አልነበሩም፡፡ ድንበር ዘለው ሰክረዋል፡፡ ድንበር ስተው በሚስቴ በኩል የመጡ ወጣት ልጃገረዶችን፣ በዳንስ ስልት ማስቸገር ጀምረዋል፡፡ በባህል ሙዚቃው ጭፈራ መሀል እንደ ማይክል ጃክሰን ልሽከርከር እያሉ ነው፡፡ ግን ይኼም ያልፋል፡፡ ብጥበጣቸው እንደ ቀልድ ተቆጥሮ ተሳቀላቸው እንጂ ማንንም አላስኮረፈም፡፡
በብዙ ትዕግስት ወደ ቤታችን እንሂድ ብለው ተነሱ.. ተነስተው በር እስኪደርሱ አንድ ሰዓት ፈጁ፡፡ በሩን ወጥተው እንደማይሄዱ እርግጠኛ ስሆን የማባብል መስዬ እየገፈተርኩ፣ መኪናቸው ዘንድ ለማድረሰ ስገፋቸው ቆየሁኝ፡፡ ለካ በእኔ መጠን ለሰከረ ሙሽራ መግፋት መገፍተር ነው፡፡ አንዱን በአፍጢሙ ደፋሁት። የተደፋው ተነስቶ ደነፋ፡፡ የደነፋው በካልቾ ተመታ፡፡
…ብቻ ታሪክ አንዴ ከተጀመረ በቀላሉ አያልቅም።… አንባጓሮው ድንጋይ ሁሉ ከተወራወርን በኋላ ተፈፀመ። በእኔ እምነት ይህ ሁሉ ከተዘጋ የግቢ በር ተገን ጀርባ በጨለማ በመከናወኑ፣ የቤተሰብ አባላት ያየው አልመሰለኝም ነበር፡፡ ለካ የሚስቴ ወላጆች ቤት ባለ ሁለት ፎቅ መሆኑን ዘንግቻለሁኝ፡፡ ከፎቁ ከፍታ በካሜራ የታገዘ ፊልም ስንሰራና ስንቀረፅ ቆይተናል፡፡ ግን የተቀረፀውን ያየሁት ስካሬ ካለፈልኝ በኋላ ነበር፡፡
ሙሽሮቼን… ወይንም ጓደኞቼን ሸኝቼ… ወይንም አሳድጄ ስመለስ እንደተረጋጋ ሰው የሚስቴን ወንድምና ጓደኞቹን ተቀላቀልኩኝ፡፡ ይኼ ሁሉ ችግር የመነጨው ከጠጣሁት መጠጥ መሆኑን ያወቅሁት ከስካሬ ከነቃሁ በኋላ እንጂ በፊት የእውነት አልተገለጠልኝም ነበር፡፡ ስለዚህም፤ ከሚስቴ ወንድም እና ጓደኞቹ ጋር  እንደ አዲስ መጠጥ እየቀዳሁ መጠጣት ያዝኩኝ፡፡ ምን እንደተከሰተ ሳላውቅ ይኼም ጠረጴዛ ተበጠበጠ፡፡ የበጠበጠው ማን እንደሆነ ለማጣራት ስሞክር፣ ምክንያቱ እኔ ራሴ ስለመሆኔ ሁሉም እየዛቱ ነገሩኝ፡፡ ተሰደበ የተባለው ሰው ተቆናጥሮ ሲወጣ፣ እንዳልከተለው ከለከሉኝ፡፡ የእኔ ፍላጎት ምን ብዬ እንዳስቀየምኩት ለመጠየቅ ነበር። በቪዲዮ ሰውን እየተከተልኩ በካልቾ ስመታ፣ በካሜራ ቀርፀው የያዙት፣ ለቤቱ ሰው ድርጊቴን አሳይተው ኖሮ የተቀየመውን የሚስቴን ወንድም ጓደኛ የተከተልኩት ያንኑ ብልሹ ተግባር ልደግም መስሏቸው ኖሯል፤ እንዳልከተል የያዙኝ፡፡
ተቀይሞ የሚሄደው ሰው ተለምኖ ተመለሰ፡፡ ተመልሶ ግን አልቀመጥም አለ፡፡ እንዲቀመጥ ወይንም ከመቀመጡ በፊት እኔ ይቅርታ እንድጠይቀው መፈለጉ ተደጋግሞ ተነግሮኝ መልዕክቱ ገባኝ፡፡
ግን እንቢ አልኩኝ፡፡ ‹‹ያጠፋሁትን ሳላውቅ ይቅርታ አልጠይቅም›› ያልኩ መሰለኝ፡፡ እዚህ ላይ እግዜር ለእኔ ያላት ሚስቴ፣ መልአክን ተመስላ መጥታ፣ ክንዴን ይዛ እየጎተተች መኝታ ቤት ታግላ አስተኛችኝ፡፡ እንቅልፍ ወሰደኝ፡፡
በእንቅልፍ ልቤ  ሰርጉ ተጠናቅቆ መጥታ ከጎኔ ስትተኛ ባንኜ ነቃሁኝ፡፡ የወንድሟን ጓደኛ ‹‹አህያ›› ብዬ መሳደቤን፣ ይሄኔ ነው የነገረችኝ፡፡ ለምን እንደሰደብኩት እንባ እያጠባት ጠየቀችኝ፡፡ የተሰደበው ሰውዬ ባለስልጣን ሳይሆን አይቀርም፡፡ ሚስቴ ከትዳር በፊት ባሳለፍነው የአራት አመታት ቆይታ አንድም ቀን ሰው ተሰደበ ብላ ስታለቅስ አጋጥማኝ አታውቅም፡፡
…ለምን እንደተሳደብኩ ስትጠይቀኝ አእምሮዬን ሳልጠቀም አንድ መልስ ሰጠኋት፡፡ መልሱ አጥጋቢ ይሁን አይሁን… በስካር መንፈሴ ውስጥ ስላለሁኝ ማገናዘብ አልቻልኩም፡፡
‹‹ትዝ ይልሻል ያኔ አንድ ቀን መንገድ ስንሻገር፣ ቪትዝ መኪና እየነዳ አንቺ ወደ ኋላ ቀረት ስትይ የሰደበሽን ሰው…፡፡ እሱ ሰውዬ ነው እኮ የወንድምሽን ጓደኛ ተመስሎ የመጣው፡፡ …እና ያኔ በመሰደቤ ቂም ይዤ ነበር.. ዛሬ ሰክሬ ሳገኘው አፀፋው መለስኩኝ… ከፋው እንዴ? እኔ ያኔ አልከፋኝም›› ብዬ ተመልሼ እንቅልፌን ተኛሁኝ፡፡
ከዛ ምሽት በኋላ የተከሰተውን ስካሬ ከለቀቀኝ በኋላ ፈፅሞ ማሰብ አልፈልግም፡፡ የቤተዘመዱ መሳቂያ ሆንኩኝ፡፡ በሰርጌ ቀን አይጋለጥም ብዬ የሸሸግሁ መጥፎ አመሌ፣ በካሜራ ተደጋፎ፣ ለመላው ታዛቢ ቀረበ፡፡ የጠፋውን ስሜን መልሼ ሳላገኘው ቀረሁኝ፡፡

Read 803 times