Error
  • The RokSprocket Module needs the RokSprocket Component enabled.
Sunday, 11 February 2018 00:00

የጥር ትዝታ

Written by  ስለሺ ነጋሽ
Rate this item
(4 votes)

  የጥር ወር፣ በገና በዓል ማግስት፣ በዓሉ ሳይደበዝዝ ብርድና ውርጩም ሳይቀንስ፣ በውስጡ ብዙ ትዝታዎችን አዝሎ የሚመጣ ወር ነው። አብዝቼ ሳስበው፣ ለሴቶች የሚያደላ ወርም ይመስለኛል፡፡ ከልጅነት ጀምሮ በጥምቀቱ አምረው ደምቀውበት፣ አብዛኛዎቹም የሚኳሉበትና የሚዳሩበት ነውና፡፡
ሄኖክ አልጋው ላይ በደረቱ ተኝቶ፣ የመሃሙድን፣ “አይ ወዳጅ ያልኩት ሰው …. ወይ ጉድ ያሰኘኛል”የሚለውን ሙዚቃ  ዓይኑን ጨፍኖ ያደምጣል፡፡ ሁሌም ከተቻለው በጥር ወር፣ ጥምቀት ከመድረሱ በፊት፣የዓመት ፈቃድ ወስዶ ቤቱ ክትት ማለት ነው የሚወደው፡፡ ሰርግም እንኳን  መሄድ አይሆንለትም፡፡
ሄኖክና ሉሊት ከዛሬ አምስት አመት በፊት አብረው በሚሰሩበት መሥሪያ ቤት ካፌ ውስጥ ቁጭ ብለው፣ እሷ ቋጥራ ያመጣችውን ምግብ፣ እሱ ከካፌው ካዘዘው ምግብ ጋር ደባልቀው እየተመገቡ እያለ፣ ሉሊት “ሁሌም የካፌ ምግብ ስትበላ ሳይህ ታሳዝነኛለህ፤ ዛሬ እንኳን አብሬህ ልብላ ብዬ ነው፤ ግን ለምን እንደ ሌሎቹ ከቤት አስቋጥረህ ወይም ቤትህ ቅርብ ከሆነ ሄደህ አትበላም”አለችው፡፡
ሄኖክም፤ “አይ ሉሊት፤ ማን የሰራውን ላምጣ፣ ወንደላጤ እኮ እንደዚህ ነው”አላት፡፡ አለማግባቱን እንኳን እሷ፣ የመሥሪያ ቤቱ ሰው ሁሉ ያውቃል፡፡
ሉሊት፤ “ማግባት ነዋ! “ ስትል መለሰችለት፡፡
ሄኖክ፤ “ለኔ የምትሆን ጠፋች”አላት፡፡
እንዲህ እየተባባሉ ተግባቡ፡፡ ከስራ ሲወጡም መገባበዝ ጀመሩ፡፡ እሱም ደስታው በዛለት፤ የሷም እንደዛው፡፡ ይህ ግንኙነትም ለትዳር አበቃቸውና፣ በጥር ወር የጥምቀት ሰሞን፣ ብዙም ባልተጋነነ፣ ነገር ግን ደስ በሚል ዝግጅት ተጋብተው መኖር ጀመሩ፡፡ ከተጋቡ ሁለት አመት ቢሞላም፣ ልጅ መውለድ ግን አልቻሉም፡፡ ሉሊት በዚህ ጉዳይ አብዝታ ብትጨነቅም፣ ባለቤቷ ከሷ ባገኘው ፍቅር፣ ደስታና ሰላም እረክቶ የሚኖር ስለሆነ፣ “ልጅ የእግዚያብሄር ስጦታ ነው፤ ፍቅራችንን እናጣጥም ውዴ”ብሎ ያረጋጋታል፡፡ በተጋቡ ሶስተኛው ዓመት ላይ፣ የጥቅምት ከተራለት፣ ሉሊት ሽክ ብላ ልትወጣ ስትል አብሯት ስለማይሄድ ክፍት እያላት፣ ሄኖክን  ግንባሩ ላይ ስማ፣ “ቶሎ እመለሳለሁ፤ አንተም እስክመለስ እንዲሻልህ ማስታገሻውን ውስድና አረፍ በልበት”አለችው፤ እሱም እሺ ብሎ አይኑ እየተንከራተተ ሸኛት…
እውነትም ሉሊት እንደ ብዙ ቆነጃጅት አምሮባት፣ ውብ ሆና ነበር፡፡ እባህሉ ቦታ ከመድረስዋ በፊት በመንገድ ላይ አንድ ወጣት ቀለበትዋን እያየ፣ ባህልና ወጉ በማይፈቅድለት ሁኔታ፣ ያውም ባለትዳርን፣ “ሄሎ ቆንጆ፤ እንዴት ታምሪያለሽ፤ እውነት እውነት እልሻለሁ--- የጥምቀት በረከቴ ነሽ አላት “አልመለሰችለትም፤ ግን ከዚያ በኋላ ለካስ አሁንም ውብ ነኝ፤ ፈላጊ አለኝ የሚል ስሜት በውስጧ ቀሰቀሰባት፡፡  
 አንዳንዱ ወግና ስርአቱን እንዲሁም ባህሉን ከማበረታታት ይልቅ ቃላትን ወርውሮ፣ እንደዚህ እሰው ትዳር ውስጥ አንዳች ነገር ይጨምራል፡፡ ተቀባይና ሰሚ ካገኘ፡፡ ደስታዋ ጨምሮ ቀጠለች። የጥምቀትን በዓል አስታኮ የመጣ አንድ ፈረንጅ፣ ስርአቱንና ታዳሚውን በካሜራው ሲያስግር፣ እሷንም ደባልቆ አስገባትና ወደ አጠገቧ ተጠግቶ፣ በበአሉ አከባበር እንደተገረመና ባየው ነገር መደሰቱን በረጅሙ ደሰኮራት፡፡ ወደ አገሩ ከመመለሱ በፊት ሌሎች የኢትዮጽያ ታሪካዊ ቦታዎችንም የመጎብኘት ዕቅድ እንዳለው ነግሯት፣ የአድራሻ ካርዱን ሰጣት፤ እንድትደውልለት፡፡ ካርዱን ቦርሳዋ ዶለችው፡፡
ከዕለታት ባንዱ ቀን ብዙ አስባ ደወለችለት። አወራት፡፡ ወደ ሰሜን ለጉብኝት እንደሄደና ሲመለስ አዲስ አበባ እንደሚገናኙ ቃሉን ሰጣት፡፡ መደዋወሉም በዚሁ ቀጠለ፡፡ ባለትዳር  እንደሆነች ነግራው፣ ባሏ ሌላ ነገር እንዳይጠረጥር፣ እሷ ሲመቻት ብቻ ነበር የሚያወሩት፡፡ ጉብኝቱን ጨርሶ ሲመጣ በሚመቻት ሰአት አግኝታው አወሩና፣ የቫይበርና ፌስቡክ አድራሻ ተለዋውጠው ተለያዩ፡፡ ከለታት ባንዱ ቀን በሚገናኙበት አድራሻ እንደተለመደው ብዙ አውርተውና አቅደው የሚደረገውን ሂደት ጨረሱና፣ ሄኖክ  ወደ መስክ ሲያቀና፣ እሷ ደሞ በግብዣ ካርድ በኩል ወደ ፈረንጅ ሃገር እብስ አለች፡፡
 ሄኖክ ከሄደበት መስክ ቢደውልላት፣ ለሁለት ቀናት ስልኳ አልሰራ ስላለው፣ ምን አጋጥሟት ይሆን ብሎ ስራውን አቋርጦ ሲመለስ፣ ከቤት አጣት፡፡  “ዲር ሄኒ፤ አትፈልገኝ እርቄ ሄጃለሁ፤ ሌላ ሚስት አግብተህ እንድትወልድ ምኞቴ ነው፤ እኔም የዕድሌን ልሞክር፤ እውድሃለሁ፤ ያንተው ሉሊት”የሚል፣ የከናፍርዋ ቅርጽ ያረፈበት ካርድ፣ ጠረጼዛው ላይ አገኘ፡፡ ጥምቀት በዓሉን ለሚያከብሩ የኢትዮጽያ ህዝቦች፤ የደስታና ሃይማኖታዊ በረከት ምንጭ፣ የቱሪስት መስህብ ሲሆን ለሄኖክ ግን መጥፎ ትዝታ ነው፡፡  

Read 2660 times