Sunday, 11 February 2018 00:00

የቅበላው ምስጢር!

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(1 Vote)

የፍም ኮረቶች ፊት ለፊቱ ይፍለቀለቃሉ፤ ከወናፉ ከርስ ሥር ሁለቱ የቀርከሃ ዋሽንቶች ንፋስ እየተፉ፣ እሳቱን በሙዚቃ ይኮረኩሩታል፡፡ በደቻ ግን ፊቱን ክርችም አድርጎ ዘግቶ፣ ጣቶቹን በጠፍር የታሰረው የወናፍ አፍ ላይ ጠርቅሞ ያርገበግባል፡፡
በሲጋራ ጢስ መስመር የሰሩ ጥርሶቹ፣ በወሬው መሃል ብቅ ቢሉም መልሶ ይቋጥራቸዋል፡፡ ጢም ከሸፈነው ፊቱ የተረፈው ነፃ ቦታ፣ አፍንጫውን እንደ ተራራ ከፍ አድርጎታል፡፡
“መከራ ነው እንግዲህ ቅበላ ብለው ቢለዋውን ከምረውታል!”
ዝም ልለው አሰብኩና፤ “ላንተ ጥሩ ነዋ፣ ገበያህ አይደል?”
“ተወው ባክህ! መቸም አይሞላ! … ጋራዥ እየሰራሁ ያላለፈልኝ፣ ብረት ቀጥቅጬ ሊያልፍልኝ ነው?”
ጋራዡን የተወበት ምክንያት ገርሞኛል፤ ሌሊት መነሳት ታክቶት እንደሆነ ነግሮኛል፡፡ ቀን ሲሰራ ውሎ፣ ማታ ሲጠጣ ያመሽና አርፍዶ ይነሳል። የጋራዡ ሥራ ያንን ነፃነት ነስቶታል፡፡ ብር አለ፣ ነፃነት የለም፡፡ “… ግን ብሩ አይሻለውም ነበር? …”
“የቅበላ ቀን፣ የቀጥቃጭ ቤትና የሴተኛ አዳሪ ሰፈር ወረፋው ልክ የለውም! … ሰው ሲሻማ የሚያገኝ አይመስለውም፡፡ … ሁዳዴ ደግሞ ሳንቲም መከራ ነው!”
ፊቱን ቅጭም አደረገና፤ “ያንተን ቢላ ለመቼ ነው የፈለከው?” አለኝ፡፡
“ለቅበላ ነዋ! …”
“ሁሉም ሰው፣ ሁሉንም ነገር ለቅበላ ነው!”
“ታዲያ ጎመን አይከተፍበት!” አልኩት፡፡
“ለኛ ሀገር ሰው ሁዳዴ ጤና ነው፡፡ እንደ አንበሳ ያለ ስጋ የማይውል ሁሉ ሳይወድ በግዱ አትክልት ይበላታል!”
አነጋገሩ እየገረመኝ ሳለ፣ ቢላዋዎቹን በቅደም ተከተል እሳቱ ውስጥ ከተታቸውና፤ “ይህ የዛገ ቢላ ሁሉ ነፃ ይወጣል! … ጠማማውን እሳት ያቃናዋል።…” አለና በመቆንጠጫ እየያዘ መኮፍ ላይ አጋድሞ ደለቃቸው፡፡ ደወሉ የድሮ ትምህርት ቤቴን እያስታወሰኝ፣ ከበደቻ ጋር ጨዋታዬን ቀጠልኩ፡-
“ልጆች አሉህ?”
“የለኝም!”
“ሚስትስ?”
“ነበረችኝ!”
ውስጤ ቀዘቀዘ፡፡ ከውጭ ድምፅ ይሰማል፡፡
“በደቻ …በደቻ!”
“እሜት”
“ቡና አትጠጣም?”
“ያለ ቡናማ እንዴት ይቻላል? … ትንሽ ሥራ ይዞኝ እንጂ!”
“በል እልክልሃለሁ!”
“እንግዲያው ሁለት አድርጊው!”
“እኔ አልጠጣም!” አልኩት፡፡
መለሰና፣ አንድ ስኒ ቡና እንዲያመጡለት ተናገረ።
“ቡና፣ ሲጋራ፣ መጠጥ … ሌላ ምን ቀረህ?”
“ያው ነው ባክህ… ለዚች ጤዛ ህይወት!”
“ሚስት ብትኖርህ ግን ጥሩ ነው፡፡ ደክመህ ስትገባ …”
“ነበረችኝ፣ ድህነት አስጠልቷት ጥላኝ ጠፋች። እኔም መለኪያዬን አቅፌ አመሽና አልጋ ላይ እወድቃለሁ”
ቀይ ፍም የመሰለውን ብረት ቀጠቀጠው፡፡
“ድሮ ድሮ ቢላዋ የሚያሰሩት መምህራን ነበሩ፡፡ አሁን ደሞ የቀበሌ ሹሞች ናቸው፡፡ … በነገራችን ላይ ልጅ እያለሁ ነው ቀጥቃጭ የሆንኩት፡፡”
“የእጅ ባለሞያ ብትል ይሻላል!”
“ምን ልዩነት አለው? … ህዝቡ ቀጥቃጭ እያለ ነው የሚጠራን፡፡ እኛ ደሞ ቀጥቃጭ እንደሆንን እናውቃለን፡፡ ችግር የለውም፡፡ በቀጥቃጭነታችን ባይሰድቡንና ባይፈርዱብን ግን ደስ ይለኛል፡፡”
“የሚሰድባችሁን ባለጌ ነው፡፡ እንዴ… ሰርታችሁ ባበላችሁት ለምን ይሰድባችኋል? … እናንተ ባትኖሩ የት እንገባ ነበር?”
“ተወኝ እባክህ!” አለና፤ ጆሮው ላይ ያጋደማትን ሲጋራ ለኩሶ ማጤስ ጀመረ፡፡
ለዚህ ያበቃኝ ስድብ ነው፡፡ ተማሪ እያለሁ፣ አንድ አባት የሰደቡኝ ስድብና ያወሩልኝ ታሪክ፣ በዚህ በቅበላ ቀንና በፋሲካ ሰሞን ትዝ እያለ ይረብሸኛል፡፡
“ምንድን ነው?”
ፈገግ አለ፡፡ ጨለማን እየቆራረሰ፣ እያራገፈ እንደሚወጣ የብርሃን ፀዳል፣ ከንፈሩ አካባቢ የተለኮሰችው ብርሃን እስከ ግንባሩ ድረስ ፈካች፡፡
“ስድስተኛ ክፍል ተማሪ እያለሁ … አንዲት የሰፈራችን ልጅ ፍቅር አስይዛኝ ነበር፡፡ ዲላ አፄ ዳዊት ትምህርት ቤት ነበር የምማረው፤ ጎበዝ ተማሪ ነኝ፡፡ መምህራን ጥያቄ ጠይቀው፤ በዐይናቸው የሚጠብቁት የኔን እጅ ማውጣት ነው። አንዳንዶቹም ‹በደቻ ምን ትላለህ?› ይሉኛል፡፡ ፈጣን መልስ ነበር የምሰጠው፡፡ … ሂሳብማ ተወው! ማሽን ነበርኩ፡፡”
ፊቱ እንደ ገና በጉም ተከበበ፡፡ እንደ ገና ሀዘን አጠላበት፡፡ እንደ ገና እንባ ቋጠረ፡፡ እንደ ገና ወደ ውስጥ ሸሸ፡፡
ዐይኖቹን ፍም የመሰለው ብረትና ትርክክ ያለው ፍም ላይ ወረወረ፡፡
“ዕድል ክፉ ነው፡፡ … ኢንጂነር እሆናለሁ ብዬ አስብ ነበር፡፡ አሁን ብረት…”
“አይዞህ! … ያለህበትን ሁኔታ ተቀብለህ፣ ወደተሻለ ህይወት መቀጠል ነው!”
“በሃምሳ ዓመቴ?” … አሁን በሚቀጥለው ሚያዝያ ሃምሳ ዓመት ይሞላኛል!”
ትንሽ ዝም አለና፤ “የገደሉኝ ግን የሳምራዊት አባት ናቸው፡፡ ትምህርት ቤት እንዲያስጠላኝ ያደረጉኝ የሳቸው ንግግርና ስድብ ነው፡፡”
“ምን አሉህ?”
“ተወኝ እባክህ! … በተለይ በዚህ ሰሞን ትዝ ይለኛል፡፡ በያመቱ ቅበላ ሲመጣና የህማማቱ ሰሞን ይረብሸኛል፡፡ ስለዚህ እጠጣለሁ፡፡ እግዜር ያናድደኛል፡፡ ሰው ያስጠላኛል፡፡”
“ምንድነው ያሉህ? ልትነግረኝ አትችልም!”
“የኔን ልጅ ማፍቀርም ማግባትም አትችልም፤ ምክንያቱም የቀጥቃጭ ልጅ ነህ፡፡ ቀጥቃጭና አናፂ የተረገመ ነው፡፡ … በዚያ ላይ ደሃ ነህ” አሉኝ፡፡
“ታዲያ ምን ቸገረህ?”
“እንዴት?” ሲጋራውን ምጎ፣ ጢሱን በሰፊው ለቀቀው፡፡
“ከዚህ በላይ ምን ሊሉኝ ይችላሉ? ገብቶሃል ዝርዝሩ?”
መልስ አልሰጠሁትም፡፡
“እርግማን ያሉት ምኑን መሰለህ! … ቀጥቃጮች ኢየሱስ ሲሰቀል የመስቀያውን ችንካር አዘጋጅተው ሰጥተዋል፡፡ አናፂዎች ደግሞ እንጨቱን ጠርበው መስቀል ሰርተዋል፡፡ … ስለዚህ የተረገሙ ናቸው ማለታቸው ነው፡፡ አንተም ርጉም ነህ! … የተረገምክ ሰው፣ የኔን ልጅ ልታገባ አትችልም ነበር ያሉት፡፡”
“እና ምን አልካቸው?”
“ምን እላለሁ! ሰማይ ተደፋብኝ፣ ስቅስቅ ብዬ አለቀስኩ፡፡ የምድር ሁሉ ጠላት የሆንኩ መሰለኝ፡፡ … ከዚያ ከትምህርት ቤት ቀረሁ፡፡ ብረት መቀጥቀጥ ግን አልተውኩም፡፡ ይለይለት ብዬ ቀጠልኩ፡፡ በኋላ ግን አንድ መምህሬ መንገድ ላይ አገኘኝና፣ ስለ ሁሉም ነገር ጠየቀኝ፡፡ ነገርኩት፤ ምክንያቴ ስላላጠገበው ከት ብሎ ሳቀብኝና ምን አለኝ መሰለህ?”
“….ተሳስተሃል! … ቀዳሚ ቀጥቃጮች ምስማር ወይም ችንካር መስራታቸው ያለውን ጥቅምና ክብር ካለማወቅ ነው፡፡ … ኢየሱስ ባይሞት ክርስትና ሆነ ቅበላና ፋሲካ መች ይኖር ነበር?...”ዕድሜ ለአናፂው መስቀሉን ቀጥቅጦ መስራቱ፣ ቀጥቃጭም ችንካሩን ማበጀቱ ነው የእምነታችን ህያውነት! … ሃዋርያው ጴጥሮስ ኢየሱስን የመሰቀሉን ሀሳብ ሲነግረው በመቃወሙና እንዳይሞት በመመኘቱ ተቆጥቶ “ሂድ አንተ ሰይጣን!” ያለውን አትነግረውም ነበር። ኢየሱስ ራሱ መሰቀል፣ የድል መንገድ እንደሆነ ያውቅ ነበር፡፡ ስለዚህ ተሳስተሃል …. ትምህርትህን ማቆም አልነበረብህም!” አለኝ፡፡
ዝም ብዬ ሰማሁት፡፡
 “በቃ ምክንያትህ ይኸው ነበር!!”
“አዎ!”
“መምህሩ ጥሩ ነግሮህ ነበር፡፡ ደግሞ ኢየሱስ አናፂ አልነበረ እንዴ? … የዮሴፍን ሥራ አትነግረውም ነበር፡፡”
“ተሳስቻለሁ! … ለካ የቅበላና የፋሲካ ምክንያቶች እኛ ቀጥቃጮቹ ነበርን? … አናፂው መስቀሉን ባይሰራው ከባርነት አንወጣም ነበር?!”
ሲጋራውን ወረወረ …
“ቢላዋህን አሁን አድርስልሃለሁ! … ዕድሜ ለአያቶቼ … ለፋሲካም … ለቅበላም .. ያበቃናችሁ እኛ ነን!”
“በደቻ!”
ሴትየዋ ቡና ይዛለት መጣች፡፡
“ዛሬ ደግሞ በወተት ነው? … የተባረከ ቀን!”

Read 707 times