Print this page
Sunday, 11 February 2018 00:00

2ኛው የዓለም ዋንጫ የኢትዮጵያ ጉብኝት በኮካ ኮላየሁለቱ የዓለም ዋንጫዎች ወግ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 የፊፋ ዓለም ዋንጫው ከ50 በላይ ሀገራትን ሲያካልል ወደ ኢትዮጵያ በታሪክ ለሁለተኛ ጊዜ በኮካ ኮላ ኩባንያ አማካኝነት መምጣቱ ለስፖርት አፍቃሪው ትልቅ ክብር ነው፡፡ የታላቁ የስፖርት መድረክ አካል የመሆን እድልን ይፈጥራል፡፡ ለአሸናፊ የሚበረከት ዋንጫ በቅርበት ለማየት መቻል በህይወት አንዴ የሚመጣ እድል ነው።   በኢትዮጵና በአፍሪካ ቀንድ የኮካ ኮላ ብራንድ ማናጀር የሆኑት ወ/ት ትዕግስት ጌቱ “የዓለም ዋንጫውን ወደ ኢትዮጵያ ለሁለተኛ ጊዜ ማምጣት በመቻላችን ትልቅ ኩራት ይሰማናል ብለው የኢትዮጵያ ህዝብ ለእግር ኳስ ስፖርት ላለው የማይሞት ፍቅር የሰጠነውን እውቅናና ክብር የሚያሳይ ነው” በማለት ተናግረዋል፡፡ “እግር ኳስ በባህል፣ በሀይማኖት እና ፖለቲካ ሳይገደብ ህዝቦችን አንድ የማድረግ ሀይል አለው፡፡ ኮካ ኮላ ይህንን የፊፋን አለም ዋንጫ የመመልከት የተለየ አጋጣሚ ለኢትዮጵያውን መፍጠሩ ትልቅ ስኬት ነውም” ብለዋል፡፡ ኮካ ኮላ በዓለም ግዙፉ የመጠጥ ካምፓኒ ሲሆን ወደ 500 የሚደርሱ የተለያዩ የመጠጥ ብራንዶችን ከ200 ሀገራተ በላይ ለሚገኙ ለደንበኞቹ ያደርሳል፡፡ ከሁለት መቶ በላይ የሆኑ ሀገራት የሚገኙ ተጠቃሚዎቻችንን በቀን በ1.7 ቢሊዮን መስተንግዶዎች በማዝናናት ላይ ይገኛል፡፡
ኢስት አፍሪካን ቦትሊንግ ሊሚትድ ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንና ከወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር በሳምንቱ አጋማሽ ላይ ስለ ዓለም ዋንጫ የኢትዮጵያ ጉብኝት መግለጫ ሰጥተው ነበር፡፡ ኢትዮጵያውያን የእግረ ኳስ አፍቃሪዎች ተወዳጁ ዋንጫ ወደ ሀገሪቱ በሚመጣ ወቅት ለመመልከት የሚችሉባቸውን የለተያዩ እድሎች ያመለከተ መግለጫ ነበር፡፡ በመጀመሪያ ከሱዳን ቆይታው በኋላ ዋንጫው ወደ ኢትዮጵያ የካቲት 17 ቅዳሜ ጠዋት ሲደርስ አዲስ አበባ ኤርፖርት ታላላቅ ባለስልጣናት፣ ሚኒስትሮች እና የኮካ ኮላ ኩባንያ በኢትዮጵያ ሀላፊዎች በተገኙበት የደመቀ አቀባበል ይደረግለታል፡፡ በመቀጠልም በብሄራዊ ቤተመንግስት የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ ዋንጫውን የሚረከቡት ስነ ስርዐት የሚከናወን ሲሆን፣ ከቤተ መንግስት ቆይታው በመቀጠል የዓለም ዋንጫው ለጋዜጣዊ መግለጫ ወደ ሂልተን ሆቴል የሚያመራ ይሆናል፡፡ ከጋዜጣዊ መግለጫው በኋላ የፎቶ ፕሮግራም የሚኖር ሲሆን፣ በዚህ ስነ ሰርዐትም ጋዜጠኞች ከዋንጫው ጋር የማስታወሻ ፎቶ መነሳት የሚችሉበት አጋጣሚ ተፈጥሮላቸዋል፡፡ በሁለተኛ ቀን እሁድ፣ የካቲት 18፤ 2010 ዓ.ም የፊፋ አለም ዋንጫ የኢትዮጵያ ቆይታ መላው የስፖርተ አፍቃሪ ህዝብ ከፊፋ የአለም ዋንጫ ጋር የማይረሳ ቀን የሚያሳልፉበት አስደሳችና አዝናኝ ውሎ በግዮን ሆቴል ይካሄዳል፡፡
የጁሊየስ ሪሜት ዋንጫ
የዓለም ዋንጫ በፊፋ ዋና አዘጋጅነት በ1930 እ.ኤ.አ ላይ በደቡብ አሜሪካዋ ኡራጋይ መካሄድ ከመጀመሩ ሁለት ዓመት በፊት የውድድሩ  ደንብ ሲቀረፅ ለአሸናፊ ለየት ያለ የክብር ዋንጫ እንዲሸለም ውሳኔ ላይ ተደረሰ፡፡  ይህንኑ የዋንጫ ሽልማት በጥሩ ዲዛይን እንዲሰራ ታላቁና ከባዱ ታሪካዊ ኃላፊነት ለፈረንሳዊው ቀራፂ አቤል ላፍሌዌር ተሰጠው፡፡ ፈረንሳዊው ቀራፂም የተሰጠውን የታሪክ አደራ ባግባቡ በመወጣት አስደናቂዋን ዋንጫ አዘጋጅቶ ሊያቀርብ ቻለ፡፡ የፊፋ ፕሬዚዳንት ለነበሩት ፈረንሳዊው ጁሊየስ ሪሜት መታሰቢያ ሆና ‹የጁሊየስ ሪሜት ዋንጫ› ተባለች፡፡
የጁሊየስ ሪሜት ዋንጫ ለዓለም ዋንጫ አሸናፊዎች ከ1ኛው የዓለም ዋንጫ አንስቶ መሸለም ከጀመረች በኋላ የተለያዩ ታሪካዊ ክስተቶች ተፈራርቀውባታል፡፡ 1ኛው የዓለም ዋንጫ በኡራጓይ በ1930 እ.ኤ.አ ላይ ተካሂዶ ተጀምሮ እስከ 1938 እ.ኤ.አ በፈረንሳይ እስከ ተዘጋጀው 3ኛው የዓለም ዋንጫ ሶስተኛው ሻምፒዮና ከዘለቀ በኋላ 2ኛው የዓለም ጦርነት ፈነዳ፡፡  በዚያ ወቅት የፊፋ ም/ፕሬዚዳንት የነበሩት ጣሊያናዊው ዶ/ር አሪኖ ባራሲ ውድድሩ በተቋረጠባቸው 12 ዓመታት የጁሊየስ ሪሜት ዋንጫ በኃላፊነታቸው ስር ሆና በአደራ ያስቀመጧት ነበረች፡፡ ጣልያናዊው የዓለም ዋንጫዋን ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት ወራሪ ኃይሎች ዘረፋ ለመጠበቅ ሲሉ በጫማ ሳጥን ውስጥ አኑረዋታል፡፡ በአንድ አጋጣሚ በቤታቸው ፋሽቶች ፍተሻ ሲያደርጉ አልጋ ስር በመደበቅም አትርፈዋታል፡፡
በ1966 እ.ኤ.አ ላይ ደግሞ የጁሊየስ ሪሜት ዋንጫ በጊዜው የውድድር አዘጋጅ በነበረችው እንግሊዝ ያጋጠማት አስደንጋጭ ታሪክም ነበር፡፡ ለዓለም ዋንጫው መስተንግዶ ማሟሟቂያ ይሆናል ተብሎ የጁሊየስ ሪሜት ዋንጫ ለጉብኝት ቀርባ ከነበረችበት የኤግዚቢሽን ማዕከል በመጥፋቷም ነበር፡፡ ያን ጊዜ የዋንጫዋ መጥፋትና መሰረቅ ከታወቀ በኋላ  በዋናው የውድድር መድረክ ላይ አለመረጋጋት እንደሚፈጥር ስጋት ሆኖ ነበር፡፡ ባልተጠበቀ ሁኔታ ግን ለኤግዚቢሽን ቀርባ ከነበረችበት ግዙፍ ህንፃ ብዙም ሳይርቅ የሚገኝ ትልቅ ዛፍ ስር መሬት ውስጥ በጋዜጣ ተጠቅልላ እንደተቀበረች ተገኘች። ለሕዝብ እይታ ቀርባ ከነበረችበት ስፍራ የጠፋችው ባልታወቁ ሌቦች ተሰርቃ ነበር፡፡ አንዲት ብልህ ውሻ ግን ከጌታዋ ጋር ስትንሸራሸር ዛፍ ስር የሚገኘውን መሬት ምሳ የተቀበረችውን ዋንጫ አግኝታለች፡፡ ለእንግሊዝና ለእግር ኳሱ አለም ታላቅ ውለታን ያደረገችው ውሻዋ ፒክልስ ትባል ነበር፡፡
በ1970 እ.ኤ.አ በሜክሲኮ ተደርጎ እስከ ነበረው 8ኛው የዓለም ዋንጫ የዓለም ሻምፒዮናነቱን ብራዚል ለሶስተኛ ጊዜ በማሸነፏ የጁሊየስ ሪሜት ዋንጫ የዘላለም ንብረት አድርጋት ነበር፡፡ የጁሊየስ ሪሜት ዋንጫ ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በታላቁ የስፖርት መድረክ ህልውናዋ ያበቃው በ1983 እ.ኤ.አ ላይ በብራዚል ዋና ከተማ ሪዩዲጂኔሮ በዘራፊ ወሮበሎች ከተሰረቀች በኋላ ነበር። በወቅቱ ዋንጫዋን የሰረቁት ወሮበሎች ሌብነታቸው እንዳይነቃ  በማለት የጁሊየስ ሪሜት ዋንጫን በፍም እሳት አቀለጧት እናም ወደ ሌላ ቅርፅ እንደቀየሯት በመላው ዓለም ተወስቶ ነበር፡፡ ብራዚል በዚህ ዘመን ዋንጫዋን ለሶስት ጊዜ ለማሸነፍ በመቻሏ ለዘላለም ማስቀረት የምትችላትን ኦርጅናል የጁሊዬስ ሪሜት ዋንጫ ማጣቷ ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር ፊፋን ያስደነገጠ ታሪካዊ ክስተት ነበር፡፡ የብራዚል ወሮበሎች የታሪክ ሌብነት የብራዚልን የዓለም ዋንጫ ስኬት ያሰናከለው ቢመስልም፤ በወቅቱ የነበረው የሀገሪቱ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ለፊፋ ባቀረበው ጥያቄ መሰረት ተመሳሳይ የጁሊየስ ሩሜት ዋንጫ እንዲሰራ ተደርጎ ምትኳ የጁሊየስ ሪሜት ዋንጫ ለብራዚል ብሄራዊ ቡድን ተበርክቷል፡፡
ኦሪጅናሏ የጁሊየስ ሪሜት ዋንጫ በመጠኗ አነስተኛ ነች፡፡ 35 ሴ.ሜ ቁመት ያላት ስትሆን እስከ 3.8 ኪ.ግ. የክብደት መጠን ነበራት፡፡ የዋንጫዋ አብዛኛው ክፍል የተቀረፀው በጠራ የብር ማዕድን ሲሆን ዙሪያዋን በተወሰነ የወርቅ ለምድ የተለበጠች ነበረች፡፡ የዋንጫዋ መሰረት ሰማያዊ ቀለም የነበረው ሲሆን በከፊል የከበረ ድንጋይ Lapis Lazuic  ከተባለ ማዕድን የተሰራ ነው፡፡ በዋንጫዋ ታችኛው ክፍል ያሉት አራት ጎኖች ዙሪያቸውን በወርቅ የተለበጡ ሲሆን ስፍራው የአሸናፊዎች ዝርዝር እንዲሰፍርበት የተዘጋጀ ነበር፡፡ ዓለም ዋንጫ በጁሊየስ ሪሜት ዋንጫ ሽልማትነት ከ1930-70 እ.ኤ.አ የተካሄደች ሲሆን በዋንጫዋ ታችኛው ክፍል በሚገነው በዚሁ የወርቅ ለምድ ላይ በእነዚያ ጊዜያት በውድድሩ ሻምፒዮን ለመሆን የበቁ ዘጠኝ ሀገራት ብሔራዊ ቡድኖችም ስም ተቀርጾ ሰፍሮበታል፡፡  ብራዚል በ1958, 1962, 1970፣ ኡራጋይ በ1930, 1950፣ ጣሊያን በ1934, 1938፣ ምዕራብ ጀርመን በ1954 እና እንግሊዝ በ1966 እ.ኤ.አ የጁሊየስ ሪሜት ዋንጫን አሸንፈዋል፡፡
አዲሷ የፊፋ ዓለም ዋንጫ
አዲሷ የፊፋ የዓለም ዋንጫ በ1970 እ.ኤ.አ ላይ ሜክሲኮ ባዘጋጀችው 9ኛው የዓለም ዋንጫ ብራዚል የዓለም ሻምፒዮናነቱን ለሶስተኛ ጊዜ ማሸነፍ በመቻሏ የጁሊየስ ሪሜት ዋንጫ የዘላለም ንብረቷ በማድረግ ከሰረቀች በኋላ የተፈጠረች ናት፡፡ ፊፋ የውድድሩን አዲስ የዋንጫ ሽልማት ለማዘጋጀት ውሳኔ ከላይ ከደረሰ በኋላ፤ የዓለም ዋንጫን ሽልማት በመቅረፅ ከ7 ሀገራት የተውጣጡ ቀራፂዎች የሰሯቸው 53 የተለያዩ ዲዛይኖች ለውድድር ቀርበዋል፡፡ በመጨረሻም የፊፋ ኮንግረስ ባሳለፈው ውሳኔ የጣሊያኑን ቀራፂ ሲልቪዮ ጋዚንጋን የዋንጫ ቅርፅና የስራ ሃሳብ ተቀባይነት አገኘ፡፡ በዚህ መሠረት በ1974 እ.ኤ.አ በተከናወነው 10ኛው የዓለም ዋንጫ ላይ ፊፋ አዲሷንና ዛሬ ድረስ የዘለቀችውን የዓለም ዋንጫ ለታላቋ የስፖርት መድረክ ለማቅረብ በቃ፡፡  አዲሲቷ የፊፋ የዓለም ዋንጫ የዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር ንብረት ሆኖ ለዘላለም የምትቆይ ናት፡፡ ፊፋ በመተዳደሪያ ደንቡ እንደሚያመለክተው ዋንጫዋን ያሸነፈ ብሔራዊ ቡድን ሙሉ በሙሉ በወርቅ የተሰራችውን ሽልማት ለተወሰኑ የፌሽታ ሰሞናት ጠብቆ እንዲያቆይ ቢፈቀድለትም ኦርጅናሌዋን ዋንጫ አስረክቦ በፊፋ የተዘጋጀውን ተመሳሳይ ዋንጫ እንዲወስድ ይደረጋል፡፡ አዲሷ የዓለም ዋንጫ ሽልማት ዛሬም ድረስ ከውድድሩ ጋር አብራ እንደቆየች ትገኛለች፡፡ የዓለም ዋንጫዋ 36 ሴ.ሜ ርዝማኔ ሲኖራት የተሰራችው 4 ሺህ 970 ግራም ክብደት ከሚመዝን 18 ካራት ንፁህ ወርቅ ነው፡፡ የዋንጫዋ የታችኛው ክፍል በከፊል የከበረ ድንጋይ ከሆነው ማልቺይት ከተባለ ማዕድን የተለበጠና የተዘጋጀ ነው፡፡ በዚሁ የዋንጫው ክፍል ላይ በ2014 እኤአ እስከተከናወነው 20ኛው ዓለም ዋንጫ ድረስ በሻምፒዮናነት ታሪክ የሰሩ አገራት ተቀርፀው ሰፍረውበታል፡፡ የዓለም ሻምፒዮናዎቹ ዝርዝር የሚፃፍበት ይኸው ቦታው እስከ 2030 እ.ኤ.አ ለሚያሸንፉ ብሔራዊ ቡድኖች ቦታ እንዳለው ቢታወቅ የዓለም ዋንጫ 100ኛ ዓመት ሲከበር አዲስ ዲዛይን ሊሰራ እንደሚችል ይጠበቃል፡፡
የአሁኗን ዋንጫ ለመጀመሪያ ጊዜ  በድል ሊስማት የቻለው የጀርመን ብሔራዊ ቡድን አምበል ፍራንዝ ቤከን ባወር ነበር፡፡ በ1974 እ.ኤ.አ በተካሄደው በዚህ ዓለም ዋንጫ የፍፃሜ ጨዋታ የተደረገው በሆላንድና በአዘጋጇ ምዕራብ ጀርመን መካከል ነበር፡፡ ጀርመንም ይህችኑ ዓለም ለመጀመርያ ጊዜ ያሸነፈች የአውሮፓ አገር ሆናለች፡፡ በ1978 እ.ኤአ ላይ ደግሞ በሞናሞናታል ስታድዬም ቦነስ አይረስ ከተማ ላይ ይህችኑ ዓለም ዋንጫ አርጀንቲና ተቀዳጅታ የመጀመሪያዋ ደቡብ አሜሪካ ሀገር ለመሆን በቅታለች፡፡
ጣሊያናዊው ቀራፂ ሲሊቪዮ ጋዚንጋ የሰሯት የፊፋ ዓለም ዋንጫ በታሪኳ በርካታ የዓለማችንን ታላላቅ ከተሞችን በሻምፒዮኖቹ እና በአዘጋጆቹ አገራት አማካኝነት ጎብኝታለች፡፡ ቦነስ አየረስ፤ ሳንቲያጎ፤ ማድሪድ፤ ሮም፣ ሎስ አንጀለስ፣ ፓሪስ፣ ዮክሃማ፤ በርሊን፤ ጆሃንስበርግና ሪዮዲጄኔሮ ይገኙበታል፡፡ የዓለም ዋንጫ ሽልማት የእግር ኳስ ስፖርትን ዓለም አቀፋዊነትና ታላቅ ውበት ተምሳሌት ተደርጋ የተቀረፀች ዋንጫ መሆኗን ቀርፂዋ ሲልቪዮ ጋዚንጋ ይናገራሉ፡፡ ስለ አንዱ የዓለም ዋንጫ ትዝታቸው ሲናገሩ “ጣሊያናዊ እንደመሆኔ” ስኳድራ አዙራ የተባለውን ብሔራዊ ቡድናችንን እደግፋለሁ፡፡ ስለዚህም በ1982 እ.ኤ. በሳንቲያጎ በርናባኦ ስታድዬም ማድሪድ ከተማ ውስጥ የጣሊያን ቡድን ዋንጫውን በማንሳት የፈፀመው ገድል ምንጊዜም አልዘነጋውም፡፡ ግብ ጠባቂው ዲኖ ዞፍ በጣሊያናዊ የተሠራቸውን ይህችን ዋንጫ ሲያነሳ በጣም ኮርቻለሁ። ዓለም ዋንጫዋ በገጽታዋ ጣሊያንን ብታንፀባርቅ አይደንቅም” ብለው ነበር፡፡ ከ1974 እ.ኤ.አ ወዲህ የአሁኗን የፊፋ የዓለም ዋንጫን ሶስት ጊዜ በመውሰድ ግንባር ቀደም የሆነችው ጀርመን (በ1974 ፤ በ1990ና በ2016 እ.ኤ.አ) ላይ በማሸነፍ ነው፡፡ ሁለት እኩል ያሸነፉት ደግሞ ብራዚል (በ1994 እና በ2002 እ.ኤ.አ) ፤ (ጣሊያን በ1982 እና በ2006 እ.ኤ.አ)  እና  አርጀንቲና (በ1978 እና በ1986 እ.ኤ.አ) ላይ ሲሆን፤እንዲሁም  ፈረንሳይ በ1998ና ስፔን በ2010 እ.ኤ.አ የዓለም ዋንጫዋን እኩል አንዴ በሻምፒዮናነት አንስተዋል፡፡
የዓለም ዋንጫ ዋጋዋና የመስተንግዶ ገቢዋ
ሲልቪዮ ጋዚንጋ በ95 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩት ከዓመት በፊት ሲሆን፤ የሰሯትን የዓለም ዋንጫ እንደ ልጄ የምቆጥራት የስነ ጥበብ ውጤት ናት ብለው ነበር፡፡ በ1971 እ.ኤ.አ ላይ ዲዛይን አድርገው እንደጨረሷት የዋንጫዋ ዋጋ እስከ 50 ሺህ ዶላር ይገመት ነበር፡፡ ዘንድሮ በወቅታዊው ዋጋ የፊፋ ዓለም ዋንጫ ከ20 ሚሊዮን ዶላር በላይ እንደምታወጣ ተተምኗል። በነገራችን ላይ የዓለም ዋንጫን የሚያህል ታላቅ የስፖርት መድረክ በማዘጋጀት በአማካይ ከ5-9 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘታቸው የዋንጫዋን ውድ ስጦታነት ያመላክታል፡፡
በ2002 እ.ኤ.አ ላይ ጃፓንና ደቡብ ኮሪያ 17ኛውን የዓለም ዋንጫ በማስተናገድ 9 ቢሊዮን ዶላር፣ በ2006 እ.ኤ.አ ላይ ጀርመን 18ኛውን የዓለም ዋንጫ በማስተናገድ 12 ቢሊዮን ዶላር፤ በ2010 እ.ኤ.አ ላይ ደቡብ አፍሪካ 19ኛውን የዓለም ዋንጫ በማስተናገድ 5 ቢሊዮን ዶላር እንዲሁም በ2014 እ.ኤ.አ ብራዚል 20ኛውን የዓለም ዋንጫ በማስተናገድ  እስከ 14 ቢሊዮን ዶላር ገቢ አግኝተዋል፡፡ የዓለም ዋንጫን ለ32 አገራት አዘጋጅቶ ለአሸናፊው የሚሸልም አገር በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ 30 ቢሊየን ዶላር እንዲንቀሳቀስ ያደርጋል፡፡ ዓለም ዋንጫውን በሚያዘጋጅበት 4 ዓመታት ውስጥ ደግሞ እስከ 4 ሚሊየን ለሚደርሱ ዜጎች የስራ ዕድል የሚፈጥር ይሆናል፡፡
የዓለም ዋንጫም ዋጋ እስከ 20 ሚሊዮን ዶላር መተመኑን የሚስተካከል ሌላ የስፖርት ሽልማት የለም። ከእግር ኳሱ ዓለም ውድ ዋጋ ያለው ሽልማት ተብሎ ቢጠቀስ የዓለማችን አንጋፋው የክለቦች ውድድር የሆነው የእንግሊዝ ኤፍኤ ካፕ ነው፡፡ ለ5 የተለያዩ ጊዜያት የተቀረፀው ይሄ የኤፍ ኤ ካፕ ዋንጫ እስከ 420 ሺ ፓውንድ ያወጣል፡፡ የዓለማችን ቁጥር 1 የክለቦች ውድድር የሆነው የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ዋንጫ ከ1992 እ.ኤ.አ አንስቶ ለሻምፒዮኖቹ የሚበረከት ነው፡፡ ምንም እንኳን በቴሌቪዥን ስርጭት መብት፣ በስታድየም ገቢ፣ በስፖንሰርሺፕ የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ሻምፒዮን እስከ 200 ሚሊዮን ዶላር ቢያገኝም ዋንጫው ግን ያን ያህል አያወጣም፡፡ በብር ተለብጦ የተሰራው የእንግሊዝ ፕሮሚር ሊግ ዋንጫ ማልቻለት የተባለ የከበረ ማዕድን መሰረት የሆነለት ነው፡፡ 104 ሴ.ሜትሮች የሚረዝምና 25 ኪ.ግ የሚመዝን ነው፡፡ የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የተለበጠበት ብር በዋጋ ቢተመን ከ10 ሺ ዶላር አይበልጥም፡፡ በ1967 እ.ኤ.አ ላይ የተሰራው የአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ ዋንጫ 71 ሴ.ሜትር የሚረዝምና 7.5 ኪ.ግ ክብደት ያለው ሲሆን፤ በምንም አይነት ዋጋ አልተተመነም፡፡ በአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር ደንብ መሰረት ማንም ቀርፆ የመሸጥ መብት የለውም፡፡  

Read 4736 times
Administrator

Latest from Administrator