Sunday, 18 February 2018 00:00

የሁለቱ መስተዳደሮችና የአካባቢ ምርጫ መቼ እንደሚካሄድ አልተወሰነም

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

- ቦርዱ ከፓርቲዎች ጋር መክሮ የሚያሳልፈው ውሳኔ እየተጠበቀ ነው
   - ጽ/ቤቱ አስፈላጊውን ዝግጅት አድርጌአለሁ ብሏል
    
    ዘንድሮ የሚካሄደው የአዲስ አበባ እና ድሬዳዋ መስተዳደሮችና የአካባቢ ምርጫ የጊዜ ሠሌዳ ገና ያልታወቀ ሲሆን ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ  ከፓርቲዎች ጋር መክሮ የሚያሳልፈው ውሳኔ እየተጠበቀ ነው ተብሏል፡፡
የምርጫው የመራዘምም ሆነ ያለመራዘም ጉዳይ ከቦርዱ ውሳኔ በኋላ እንደሚታወቅ የተገለጸ ሲሆን የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ጽ/ቤት በበኩሉ፤ ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ ምርጫውን በዚህ ዓመት ለማካሄድ አስፈላጊውን ዝግጅት ሲያደርግ መቆየቱን፣የጽ/ቤቱ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ተስፋለም አባይ ለአዲስ አድማስ አስታውቀዋል፡፡
“እንደ ጽ/ቤት፤በዚህ ዓመት ይካሄዳል ብለን አስፈላጊውን ዝግጅት አድርገናል፣ የጊዜ ሠሌዳም አውጥተን ለቦርዱ አቅርበናል” ያሉት አቶ ተስፋለም፤ ቦርዱ ደግሞ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ተወያይቶ፣ የጊዜ ሠሌዳውን ይፋ ያደርጋል ብለዋል፡፡
በተለምዶ ይህ መሰሉ ምርጫ በግንቦት ወር የሚካሄድ ቢሆንም እስካሁን ግን ምንም ዓይነት  እንቅስቃሴ አይታይም፡፡ ከዚህ አንጻር በቀሪዎቹ 4 ወራት ጊዜ ውስጥ እንዴት ምርጫ  ማካሄድ ይቻላል ያልናቸው አቶ ተስፋለም፤ “በኛ በኩል አስፈላጊ ቁሳቁሶችን አጠናቀናል፣ የምርጫ አስፈፃሚዎችንም መልምለን አሰልጥነናል” ብለዋል፡፡ በጊዜ ሠሌዳው መራዘምና አለመራዘም ጉዳይም የሚጠበቀው ቦርዱ ከፓርቲዎች ጋር መክሮ የሚያሳልፈው ውሣኔ ነው ብለዋል፤አቶ ተስፋለም፡፡
ሊካሄድ የታቀደው የሁለቱ መስተዳደር የምክር ቤት ምርጫ እንዲሁም የወረዳና የክፍለ ከተማ ም/ቤት ምርጫ ሲሆን የአካባቢ ምርጫ ደግሞ በመላ ሃገሪቱ በሚገኙ ወረዳዎችና ዞኖች የሚካሄድ ይሆናል ብለዋል ፤አቶ ተስፋለም፡፡
የማሟያ ምርጫ ሊካሄድ የሚችለው የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት የተጓደሉ አባላት እንዳሉት ገልጾ፣ እንዲካሄድለት ከጠየቀ መሆኑንም፣ ኃላፊው ለአዲስ አድማስ አስታውቀዋል፡፡

Read 2189 times