Sunday, 18 February 2018 00:00

በሰሞኑ አድማና ተቃውሞ፣ የ9 ሰዎች ህይወት ጠፍቷል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(3 votes)

 በወልቂጤ ግጭት 3 ሰዎች ሞተዋል

    ከሰሞኑ በአዲስ አበባ ዙሪያ እንዲሁም በኦሮሚያ ክልል ከተሞች ከተደረገው አድማና ተቃውሞ ጋር በተገናኘ የዘጠኝ ሰዎች ህይወት ማለፉን የክልሉ የመንግሥት ኮሚኒኬሽን ፅ/ቤት ምክትል ኃላፊ ወ/ሮ ኡሚ አባጀማል የገለጹ  ሲሆን አብዛኞች ከተሞች ከሐሙስ ጀምሮ ወደ መረጋጋት መመለሳቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡ በተመሳሳይ በወልቂጤ፣ በተቃዋሚዎችና በጸጥታ ሃይሎች መካከል በተፈጠረ ግጭት፣ የ3 ዜጎች ህይወት መቀጠፉን ምንጮች ጠቁመዋል፡፡  
በኦሮሚያ ለሁለት ቀናት በተካሄደው አድማና ተቃውሞ፡- በሆለታ፣ በጅማ፣ በሀሮማያ፣ በዝዋይ፣ በዱግዳ ወረዳዎች የንግድ ተቋማትና የትራንስፖርት አገልግሎት ሙሉ በሙሉ ተቋርጦ የነበረ ሲሆን  በርካታ ንብረቶች መውደማቸውም ተጠቁሟል፡፡
በቀጣይ አስፈላጊው ማጣራት ተደርጐ የሰው ነፍስ ያጠፉ፣ ለፍርድ እንደሚቀርቡ የተናገሩት የኮሙኒኬሽን ኃላፊዋ፤ በአድማ ሰበብ መንገድ በመዘጋጋት፣ በአገሪቱ የንግድ እንቅስቃሴ ላይ የሚደረግ መስተጓጐልም በመንግሥታቸው ተቀባይነት እንደማይኖረው አስረድተዋል፡፡
በተለይ በጅማ ከተማ የተደረገው አድማና ተቃውሞ ጠንካራ እንደነበር የጠቆሙት ምንጮች፤ በከተማው የሚገኝ አንድ ህንጻ መቃጠሉንና ተቃዋሚዎች ከፀጥታ አካላት ጋር መጋጨታቸውን አመልክተዋል፡፡ ለሦስት ቀናት ሊቀጥል እንደሚችል ተፈርቶ የነበረው አድማና ተቃውሞ፣ ባለፈው ረቡዕ በእነ አቶ በቀለ ገርባ ከወህኒ መለቀቅ የተነሳ ከእስር የተፈቱትን ወደ መቀበል ሥነ ሥርዓት መለወጡን ለማወቅ ተችሏል፡፡ ወጣቶች  ከአዲስ አበባ ውጪ በሆኑት ቡራዩና ዱከም፣ ደብረዘይትና አዳማ፣ ከእስር ለተፈቱት አቶ በቀለ ገርባና የኦፌኮ አመራሮች፣ የደስታ መግለጫ ሰልፎችና የአቀባበል ሥነ ስርዓት ትዕይንቶች ሲያደርጉ መዋላቸውን ምንጮች ለአዲስ አድማስ ጠቁመዋል፡፡
በሌላ በኩል ማክሰኞ፣ ረቡዕና ሐሙስ በአማራ ክልል፣ በደብረ ማርቆስ፣ ገብረ ጉራቻና ደብረብርሃን አካባቢ ተመሳሳይ አድማና ተቃውሞ መደረጉን  ምንጮች ተናግረዋል፡፡ ከአድማው ቀደም ብሎ ቅዳሜ የካቲት 3 ቀን 2010 ዓ.ም በሃርጌሳ፣ ከሶማሌ ክልል የተፈናቀሉ ዜጐች በተጠለሉበት ካምፕ በተፈጠረ ግጭት የ4 ሰዎች ህይወት መጥፋቱ አይዘነጋም፡፡
በሌላ በኩል፣ ከትናንት በስቲያ በወልቂጤ ዩኒቨርስቲ የተነሳው ተቃውሞ፣ ወደ ከተማው ተሸጋግሮ፣ ከፀጥታ ኃይሎች ጋር በተፈጠረው ግጭት፣ የሦስት ሰዎች ህይወት ጠፍቷል፡፡ ምንጮች ለአዲስ አድማስ እንደገለፁት፤ በከተማው በተቀሰቀሰው ተቃውሞ፣ የመንግስት ተቋማትና ተሽከርካሪዎች ላይ ጥቃት ተፈፅሟል። ተቃውሞው የልማት ጥያቄያችን ምላሽ አላገኘም በሚል መቀስቀሱን የጠቆሙ ነዋሪዎች፤ ባለፈው ረቡዕና ሐሙስ መንገዶች በመዘጋታቸው፣ የተሽከርካሪዎች ጉዞ መስተጓጎሉንና የንግድ እንቅስቃሴ መቆሙን ተናግረዋል፡፡
ከሁለት ሳምንት በፊት በወልቂጤ ከ10 ሺ የማያንሱ የከተማዋ ነዋሪዎች ለተቃውሞ አደባባይ መውጣታቸውን መዘገባችን የሚታወስ ሲሆን በርከት ያሉ የልማት ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙላቸው መጠየቃቸው አይዘነጋም፡፡ የዞኑ አስተዳደር፣ ነዋሪዎቹ ያቀረቡትን የልማት ጥያቄዎች በተመለከተ ለአዲስ አድማስ በሰጡት ማብራሪያ፣ ጥያቄዎቹ በሙሉ ትክክልና  ተገቢነት ያላቸው እንደሆኑ ጠቁመው፣ ፈጣን ምላሽ ለመስጠት ጥረት እንደሚደረግ መናገራቸው ይታወሳል፡፡

Read 4395 times