Sunday, 18 February 2018 00:00

ኦፌኮ ለኦህዴድ የድርድር ጥያቄ አቀረበ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(3 votes)

      “ከ26ሺ በላይ የፖለቲካ እስረኞች በኦሮሚያ አሉ”
                የኦፌኮ አብይ አጀንዳዎች

       • የምርጫ ሥርዓት
       • የምርጫ ቦርድ አደረጃጀት
       • በኦሮሚያ ጽ/ቤቶች መክፈት
       • የፖለቲካ እስረኞች አፈታት

    ከእስር በተፈቱት ዶ/ር መረራ ጉዲና ሊቀመንበርነትና በተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበሩ አቶ በቀለ ገርባ የሚመራው የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ)፤ ኦሮሚያን እያስተዳደረ ለሚገኘው ኦህዴድ፣ በክልሉና ሌሎች ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ለመደራደር ጥያቄ አቀረበ፡፡
ኦፌኮ ለኦህዴድ ሰሞኑን በጽሁፍ ባቀረበው የእንወያይና እንደራደር ጥያቄው፤ አራት ወሣኝ ሃገራዊ ጉዳዮችን ለድርድር መምረጡን ም/ሊቀመንበሩ አቶ ገብሩ ገ/ማርያም ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡
ለድርድር የተመረጡት አጀንዳዎች፡- የምርጫ ስርዓትና አፈፃፀም፣ የምርጫ ቦርድ አደረጃጀት፣ የፖለቲካ እስረኞች አፈታትና በክልሉ የሚገኙ የኦፌኮ ጽ/ቤቶችን የተመለከተ መሆኑን አቶ ገብሩ አስረድተዋል፡፡
ፓርቲያቸው በሃገሪቱ ሠላማዊ የመንግስት ለውጥ ለማምጣት ምርጫ ወሳኝ ነው ብሎ ያምናል ያሉት አቶ ገብሩ፤ ሁሉም የሂደቱ ተሳታፊዎች የሚተማመኑበት የምርጫ ሥርዓትና የምርጫ ቦርድ ሊቋቋም እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ ለዚህም የሃገሪቱ የምርጫ ሥርዓትና የአስፈፃሚው አካል አደረጃጀት፣ ስር ነቀል ለውጥ ያስፈልገዋል ብለዋል - አቶ ገብሩ። ኦህዴድ ጉዳዩን በኢህአዴግ አባል ድርጅቶች እንዳያሳስብ እንፈልጋለን ያሉት አቶ ገብሩ፤ በዚሁ ጉዳይ ከኢህአዴግ ጋር ለመደራደርም፣ ኦፌኮ አባል በሆነበት በመድረክ በኩል ጥያቄ ማቅረባቸውን አስታውቀዋል፡፡
መንግስት ዋነኛ የፖለቲካ አመራሮችን መፍታቱን ፓርቲያቸው በአዎንታዊነት እንደሚቀበለው የገለፁት አቶ ገብሩ፤ ይሁን እንጂ አሁንም በኦሮሚያ ክልል ብቻ ከ26 ሺህ በላይ በፖለቲካ ጉዳይ የታሰሩ አሉ፤ እነሱ እንዲፈቱ ለመደራደር እንፈልጋለን ብለዋል፡፡
በሌላ በኩል፤ ኦህዴድ በቅርቡ የእስረኞችን ሁኔታ አስመልክቶ በሰጠው መግለጫ፤ አዲሱ የድርጅቱ አመራር ወደ ስልጣን ከመጣ ወዲህ ብቻ ከ30 ሺህ በላይ እስረኞችን መፍታቱን አስታውቋል።
ሌላው ኦፌኮ ለድርድር የመረጠው አጀንዳ፣ በክልሉ የተለያዩ ዞኖችና ወረዳዎች፣ ቅርንጫፍ ቢሮዎችን ለመክፈት የሚያስችለውን ሁኔታ የማመቻቸት ጉዳይ ነው፡፡ እስከ ዛሬ ቢሮዎችን ለመክፈት ከወረዳና ዞን ካድሬዎች ወከባና ጫና ያጋጥመን ነበር ያሉት አቶ ገብሩ፤ በዚህም የተነሳ በክልሉ የፓርቲ ስራ ለመስራት አዳጋች ሆኖ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡
በዚህ ድርድር ይህን እንቅፋት በማስወገድ፣ በክልሉ የተለያዩ ዞኖችና ወረዳዎች ተጨማሪ ጽ/ቤቶች ለመክፈት የሚያስችል ውጤት ማምጣት እንፈልጋለን ብለዋል - አቶ ገብሩ፡፡ በምርጫ ቅስቀሳ ጉዳይም ከዚህ በፊት ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን መነሻ በማድረግ፣ ውይይትና ድርድር ለማካሄድ ለኦህዴድ ጥያቄ አቅርቧል - ኦፌኮ፡፡ ፓርቲያቸው ከዚህ በፊት ለኦህዴድ ተመሳሳይ ጥያቄ አቅርቦ እንደነበር ያስታወሱት አቶ ገብሩ፤ በወቅቱ ምላሽ ባያገኝም፤ ኦህዴድ ራሱ በቅርቡ ለፖለቲካ ድርጅቶች የአብረን እንስራ ጥሪ ማቅረቡ፣ በድጋሚ ድርድሩን ለመጠየቅ እንዳነሳሳው ገልጸዋል፡፡

Read 7386 times