Sunday, 18 February 2018 00:00

የቀሩት ታሳሪዎችም እንዲፈቱ ተጠየቀ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(7 votes)

 አቶ በቀለ ገርባ በአዳማ ስቴዲየም ደማቅ አቀባበል ተደረገላቸው
      የኛ ጥያቄ፣ እውነተኛ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ይፈጠር ነው - ጋዜጠኛ እስክንድር
      የተፈታነው ጥቂቶች ነን፤ የበለጡት እስር ቤት ነው ያሉት - ጋዜጠኛ ውብሸት

    ሰሞኑን ከእስር የተፈቱ ፖለቲከኞችና ጋዜጠኞች እንዲሁም የሀይማኖት መሪዎች፣ የነሱ መፈታት ብቻውን  ትርጉም እንደሌለው በመግለጽ፤በእስር ቤት የቀሩት በሺ የሚቆጠሩ እስረኞችም እንዲፈቱ ጠይቀዋል፡፡ በሌላ በኩል፤ ሰሞኑን ከእስር ለተፈቱት ፖለቲከኞች፤ ደጋፊዎቻቸው ደማቅ የሆነ አቀባበል አድርገውላቸዋል፡፡
ከ6 ዓመት ተኩል እስር በኋላ በይቅርታ የተለቀቀው የ18 ዓመት እስር ፍርደኛው ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ለአዲስ አድማስ በሰጠው አስተያየት፤ ”ከመታሰሬ በፊት በሰላማዊ ትግል ውስጥ ነበርኩ፤ አሁንም በዚሁ መንገድ ትግሌን እቀጥላለሁ” ብሏል።
በ1997 ዓ.ም ከምርጫ ቀውሱ ጋር ተያይዞ፣ ታስሮ ከተፈታ በኋላ፣ የራሱን ፕሬስ ለማቋቋም ያደረገው ጥረት በመንግሥት እንቢታ ሳይሳካ መቅረቱን ያስታወሰው ጋዜጠኛ እስክንድር፤እስከ ታሰረበት ጊዜ ድረስ በዌብሳይቶች ላይ ሃሳቡን ይገልፅ እንደነበር በማውሳት፣ አሁንም በፕሬስና በጋዜጠኝነት ስራው መቀጠል እንደሚፈልግ አስታውቋል፡፡
“በጋዜጠኝነት እቀጥላለሁ፤ በሰብአዊ መብት ተሟጋችነቴም ሆነ ለዴሞክራሲ እውን መሆን በመታገል እቀጥላለሁ፡፡ ፍላጐቴ በጋዜጠኝነት ሙያ ብቻ መሥራት ቢሆንም የአገሪቱ ሁኔታ ይህን የሚፈቅድ ባለመሆኑ፣ ከጋዜጠኝነት ጐን ለጐን፣ በአክቲቪስትነቴ እቀጥላለሁ” ብሏል - ጋዜጠኛው፡፡
ማላዊን፣ ጋናንና ቦትስዋናን በመሳሰሉ ሀገራት ውስጥ እንዳለው ዲሞክራሲያዊ ስርአት በሃገራችን እውን ቢሆን ኖሮ፣ በጋዜጠኝነት እቀጥል ነበር ያለው እስክንድር፤ አሁን ለዲሞክራሲ የሚደረገው ትግል መቀጠል ስላለበት እኔም ትግሌን አጠናክሬ እቀጥላለሁ ብሏል፤ ለአዲስ አድማስ፡፡
“አሁንም ቢሆን በርካታ በእስር ቤት የቀሩ የፖለቲካ እስረኞች አሉ” ያለው ጋዜጠኛው፤ “የፖለቲካ እስረኞች መፈታት ብቻ የህዝብን የዲሞክራሲ ጥያቄ አይመልስም፤ የኛ ጥያቄ እውነተኛ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ይምጣ ነው” ብሏል፡፡ የቀሩትን የፖለቲካ እስረኞች ለማስፈታት ትግሉ መቀጠል እንዳለበት የተናገረው ጋዜጠኛ እስክንድር፤ የፖለቲካ እስረኞችን የፈጠረው ኢ-ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ካልተለወጠ፣ሌሎች የፖለቲካ እስረኞች የማይፈጠሩበት ዋስትና የለም ብሏል፡፡
ሰሞኑን ከእስር የተፈታው ጋዜጠኛ ውብሸት ታዬም የእስክንድርን ሃሳብ ይጋራል፡፡ ከእስር ተፈትቶ፣ አካላዊ ነፃነት ማግኘቱና ከቤተሰቦቹ ጋር መደባለቁ እንደሚያስደስተው የገለጸው ጋዜጠኛ  ውብሸት፤ ነገር ግን በእስር ቤት የቀሩትንና አገሪቱ ያለችበትን ሁኔታ ሲያስብ፣ ሃዘን እንደሚሰማው አልሸሸገም፡፡
“አሁን የወጣነው ጥቂቶች ነን፤የበለጡት በእስር ቤት ነው ያሉት፤አሁንም ቢሆን መፍትሄው የቀሩትን መፍታት ነው” ብሏል - ጋዜጠኛው፡፡
እነ ጀነራል አሳምነው ጽጌን ጨምሮ ሌሎች እስረኞች መፈታት አለባቸው ያለው ጋዜጠኛው፤ እንደተባለው የፖለቲካ ምህዳሩ እንዲሰፋ፣ የተጀመረውን አንድ እርምጃ ገፋ አድርጐ፣ የበለጠ ማስፋት እንደሚያስፈልግ ተናግሯል፡፡ ከመንግሥት ሆደ ሰፊነት  ይጠበቃልም ብሏል - ጋዜጠኛ ውብሸት፡፡
በፖለቲካ ረገድም ተቃዋሚና ገዢው ፓርቲ፣ ግማሽ ግማሽ መንገድ ተቀራርበው፣የአገሪቱን ችግር መፍታት እንደሚገባቸው ጠቁሟል፡፡
እስርና እንግልት ሊኖር እንደሚችል አምኜ ነው ወደ ፖለቲካ ትግል የገባሁት የሚለው ፖለቲከኛው አንዱአለም አራጌ በበኩሉ፤የኢትዮጵያ ህዝብ የደረሰበት ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ደረጃ እንዳስደነቀው ተናግሯል፡፡ “በአሁኑ ሰዓት ህዝቡ ፍርሃትን እያሸነፈ በመምጣቱ ደስተኛ ነኝ” ብሏል፡፡
“በቀጣይ ዘረኝነትን አሸንፎ፣ እጅ ለእጅ ተያይዞ፣ ለልጆቻችን የምትሆን አገር መፍጠር አለብን” በማለት ህልሙን  የገለጸው አንዷለም፤ “የማያልፍ ስርዓት የማይፈርስ አገር ለመፍጠር፣ ሰላማዊ ትግሉን አድርጐ፣ ይቺን አገር ወደ ተሻለ ዘመን ማሸጋገር ያስፈልጋል ብዬ አምናለሁ” ብሏል።
“ህዝቡ በክብር ከእስር ነፃ እንደሚያወጣኝ አስቀድሜ ተናግሬ ነበር፤ ፈጣሪ የፈቀደው ጊዜ አሁን ሆኖ ልወጣ ችያለሁ፤ የኔ ቀን እንደሚመጣ እገምት ነበር” ሲል የተፈታበትን ሁኔታ ተናግሯል - አንዱአለም፡፡
ረቡዕ አመሻሽ ላይ ከእስር ከተለቀቁት መካከል የሙስሊሙ መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባል  ኡስታዝ አህመዲን ጀበል አንዱ ሲሆኑ ቀሪ እስረኞችም እንዲለቀቁ ጠይቀዋል፡፡ የአገሪቱን ፖለቲካዊ ችግሮች በመግባባት መፍትሄ ማፈላለግ ተገቢ እንደሆነም ነው የተናገሩት፡፡  
ማክሰኞ አመሻሽ ከቂሊንጦ ማረሚያ ቤት የተለቀቁት የኦፌኮ ምክትል ሊቀመንበር አቶ በቀለ ገርባና ሌሎች የፓርቲው አመራሮች፤ በመኖሪያ አካባቢያቸው ደጋፊዎቻቸው ደማቅ አቀባበል ያደረጉላቸው ሲሆን እነሱም  ምስጋናቸውን  አቅርበዋል፡፡ አቶ በቀለ ገርባ፤ በአዳማ ስታዲየም፣ የከተማዋን ከንቲባ ጨምሮ በመቶ ሺዎች የሚገመቱ ደጋፊዎች ባደረጉላቸው የአቀባበል ሥነ ስርዓት ላይ፣ ለደጋፊዎቻቸው ባስተላለፉት መልዕክት፤ ”በመካከላችሁ ንፋስ ሳታስገቡ በፖለቲካ ድርጅት ወይም  በሀይማኖት ሳትከፋፈሉ፣ አንድ ሆናችሁ፣ አገራችንን ወደፊት ማራመድ ይኖርብናል፡፡ አሁን የተገኘው ነፃነት ዝም ብሎ የተገኘ አይደለም፤ ከዚህ በኋላ  ተቀባይነት ባለው ሰላማዊ መንገድ ብቻ መታገል ይኖርብናል” ብለዋል፡፡ ኢትዮጵያን በዘር መከፋፈል እንደሌለባቸው፣በሌሎች ብሄረሰቦች ላይ ጉዳት ማድረስ ተገቢ አለመሆኑን፣ ለሰዎች  ፍቅርና መልካምነትን መለገስ እንደሚያስፈልግም  ለደጋፊዎቻቸው መክረዋል - አቶ በቀለ፡፡  

Read 5537 times