Sunday, 18 February 2018 00:00

“አዲስ ምዕራፍ ለመጀመር የምህረት አዋጅ መታወጅ አለበት”

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(3 votes)

• ላለፉት 40 ዓመታት ያየነው አብዮተኛ ትውልድ፣ ፍላጐቱ ካፒታሊዝም ነው
   • ወጣቱ ክፍል ከኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ጐን ለጐን ነፃነት ይፈልጋል
   • የእስረኞቹ መፈታት ትልቅ ትርጉም ያለው አዎንታዊ እርምጃ ነው
   • መንግሥት ችግር ውስጥ የሚገባው ፖለቲካና ህግን እያምታታ ነው


    ታዋቂው የህግ ባለሙያ አቶ ሞላ ዘገየ፤እስረኞች በይቅርታ፣በምህረትና ክሳቸው ተቋርጦ ይፈታሉ ሲባል ከህግ አንጻር ምን ትርጉም እንዳላቸው ያብራራሉ፤አብዛኞቹ መገናኛ ብዙሃንና የመንግስት ሃላፊዎች እያደበላለቁ እንደሚጠቀሙባቸውም በመግለጽ፡፡ የህግ ባለሙያው፤ አጠቃላይ
የምህረት አዋጅ መታወጅ እንዳለበትም አበክረው ይሞግታሉ፡፡ ያለፈውን የመጠፋፋት ፖለቲካ ቋጭተን፣አዲስ ምዕራፍ ለመክፈት ይሄ የምህረት አዋጅ አስፈላጊ ነው ይላሉ፡፡ እንዴት? ለምን? የሚለውን ከእነ ፋይዳው በዝርዝር ያስረዳሉ፡፡ በወቅታዊ የፖለቲካ ጉዳዮችም ላይ ህግን መሰረት ያደረጉ አስተያየቶችን ሰንዝረዋል፡፡ አቶ ሞላ ዘገየን በቢሮአቸው ያነጋገራቸው የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ፣ ቃለ ምልልሱን

    የታሰሩ ፖለቲከኞችና በአመፅ ተሳትፈዋል የተባሉ ግለሰቦች በይቅርታ፣ በምህረትና ክሳቸው ተቋርጦ ይፈታሉ በተባለው መሰረት እየተፈቱ ይገኛሉ፡፡ ለመሆኑ ይቅርታ፣ ምህረትና ክስ ማቋረጥ ከህግ አንጻር ልዩነታቸው ምንድን ነው?    
ይቅርታና ምህረት በኛ ህግ መሰረት የተለያየ ትርጉም ነው ያላቸው፡፡ ይቅርታ የሚመለከተው ጥፋት ፈፅመዋል ተብለው በህግ የተፈረደባቸውና ፍርዳቸውን የሚጠባበቁ ሰዎችን ነው፡፡ እነዚህ አካላት ጥፋተኝነታቸው ከተረጋገጠ በኋላ ነው ይቅርታ የሚደረግላቸው፡፡ ምህረት ግን በህግ ጥላ ስር ያልዋሉ አካላትን የሚመለከት ነው፡፡ ለምሳሌ፡- ሽፍታ ሰው ገድሎ ጫካ ይገባል፤ ግን በህግ ጥላ ስር አልወደቀም፤ መንግሥት ደግሞ ከዚህ አካል ጋር ሰላም ማውረድ ይፈልግ ይሆናል፡፡ ይሄን ጊዜ  ሽፍታው በህግ ቁጥጥር ስር ሳይውል፣ባለበት ሆኖ “ምህረት አድርጌልሃለሁና ተመለስ” ይለዋል። ምህረት እንዲህ ነው የሚደረገው፡፡ የወንጀል ድርጊት ተፈጽሟል ግን ፈጻሚው በህግ ሥር አልዋለም፡፡ ያንን ሰው ለመመለስ ሲፈለግ ምህረት ይደረጋል፡፡
በይቅርታ ለመፍታት ያለው የህግ ሂደት ምን ይመስላል? የክስ ማቋረጥ ሂደትስ እንዴት ነው የሚፈፀመው?
አንድ ሰው በይቅርታ እንዲፈታ ከፈለገ ማመልከቻ ያቀርባል፤ ቅፅ ይሞላል፡፡ ያንን ተከትሎ ደግሞ ይሄ የይቅርታ ጉዳይ የሚመለከተው በህግ የተቋቋመ አካል አለ፡፡ ይህ አካል የቀረበውን ማመልከቻ ይመረምርና የመጨረሻ ውሳኔ ለሚያሳልፈው አካል፣ የይቅርታ ቦርድ ያቀርባል፡፡ ይህ ቦርድ ይቅርታው ይገባዋል ወይስ አይገባውም የሚለውን ይወስናል፡፡ ይህ የሚመለከተው በህግ የተፈረደበትን ሰው ብቻ ነው፡፡ የክስ ማቋረጥ ጉዳይ ደግሞ ለአቃቤ ሕግ፣ በህግ የተሰጠ ስልጣን ነው፡፡ አቃቤ ህግ በፈለገ ጊዜ ያሻውን ክስ ማቋረጥ ይችላል፡፡ በፍርድ ቤት እንኳን ለምን ክሱን አቋረጥክ ተብሎ ሊጠየቅ አይችልም፤ ሞት የሚያስፈርድ እንኳን ቢሆን አቃቤ ህግ ከፈለገ፣ ክሱን ማቋረጥ ይችላል፡፡ ለምን አቋረጥክ ብሎ የሚያስጠይቀው የህግ አግባብ የለም፡፡
ከይቅርታ ጋር በተያያዘ፣ ከሰሞኑ በእነ ጋዜጠኛ እስክንድር ጉዳይ፣የይቅርታ ሰነድ ላይ ፈርሙ አንፈርምም በሚል ውዝግብ መፈጠሩ ይነገራል፡፡ ይሄ ከህግ አንጻር እንዴት ይታያል?
የፖለቲካ ጉዳዩን ትተነው ከህግ አንፃር ጉዳዩን ስንመለከተው፣ አቶ አንዷለምና ጋዜጠኛ እስክንድር ጥፋተኛ ተብሎ ተፈርዶባቸዋል፡፡ ከተፈረደባቸው ዘንዳ በህግ የተቀመጠውን ሂደት የሚከተሉ ይሆናል ማለት ነው፡፡ ማመልከቻ ይፅፋሉ፤ የሚመለከተው አካልም ማመልከቻቸውን መርምሮ ውሳኔ ያሳልፋል፡፡ ነገር ግን በእነ አቶ አንዷለም ጉዳይ እኔም ከሚዲያዎች እንደተከታተልኩት፣ “የግንቦት 7 አባል ነን ብላችሁ ፈርሙና ይቅርታ ጠይቁ ተብለናል” የሚል ነው፡፡ ይሄ ከሆነ ፈፅሞ በህግም ድጋፍ የለውም፡፡ ስህተት ነው፡፡ መንግሥት ይሄን ብሎ ከሆነ፣ ፍፁም የሆነ የህግ ስህተትና ጥፋት ሰርቷል ማለት ነው፡፡ ለምን ከተባለ፣ እነዚህ ሰዎች የግንቦት 7 አባል ስለሆናችሁ ተብሎ ተፈርዶባቸዋል፡፡ እነሱ ያድርጉትም አያድርጉትም “ጥፋት ፈፅማችኋል” ተብለው አስቀድሞ ተፈርዶባቸዋል ማለት ነው፡፡ በተፈረደባቸው ጉዳይ በድጋሚ ወደ ኋላ ተመልሶ፣ “እንዲህ በልና እፈታሃለሁ” ማለት አይቻልም፡፡ ይሄ ቅድመ ሁኔታ ማስቀመጥ ማለት ነው፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ በወህኒ ቤት ቆይታቸው ያላቸውን ስነምግባርና የመታረም ሁኔታ በተመለከተ ወህኒ ቤቱ የምስክርነት አስተያየት ያቀርባል፡፡ እነዚህ ታይተው ነው ይቅርታው ላይ ውሳኔው ሊሰጥ የሚችለው፡፡ እዚህ አገር ትልቁ ችግር፣ ፖለቲካውና ህጉ መቀላቀሉ ነው፡፡ ጥርት አድርጐ ይቅርታና ምህረትን ለይቶ አለማወቅ፣ ፖለቲካና ህግን ነጣጥሎ አለማየት ነው፣ ሁልጊዜ ችግር የሚያመጣብን፡፡
አቃቤ ህግ ያቋረጠውን ክስ፣ መልሶ ለፍርድ ቤት የማቅረብ ስልጣኑ ምን ድረስ ነው?
አቃቤ ህግ ክሱን በፈለገው ጊዜ መልሶ ሊያንቀሳቅስ ይችላል፡፡ በዚህ ረገድ ድጋሚ ራሱ አይንቀሳቀስም የሚል ዋስትና የለም፡፡ ያንን ክስ ሊቀጥለው ይችላል፡፡ እንዳይቀጥለው ገደብ የሚያበጅ የህግ ድንጋጌ የለም፡፡
በአሁኑ ወቅት በፀረ ሽብር ህጉ የተከሰሱ ፖለቲከኞችና ግለሰቦች በይቅርታና ክሳቸው እየተቋረጠ እየተለቀቁ ነው፡፡ ይሄ የፀረ ሽብር ህጉን ዋጋና ግምት አያሳንሰውም?
የፀረ ሽብር ህጉ ሲጀመር ፖለቲካዊ ፍላጐቶች የተጫኑት ነው፡፡ በአብዛኛው በዚህ ህግ ሲከሰሱ ያየናቸው፣ የፖለቲካ ተቀናቃኝ የሆኑ ሰዎች ናቸው። አክቲቪስቶች፣ ጋዜጠኞች፣ ጦማሪያንና ፖለቲከኞች ሊያውም በሚገባ በህብረተሰቡ ዘንድ የሚታወቁ ናቸው የሚከሰሱት፡፡ እነዚህ ፖለቲከኞችና የለውጥ አቀንቃኞች ደግሞ ታዋቂ በመሆናቸው የህብረተሰቡ አብሪ የለውጥ ሃዋሪያዎች ናቸው፡፡ እስክንድር ነጋ የታወቀ ጋዜጠኛ ነው፡፡ አንዷለም አራጌ፣ በቀለ ገርባ፣ ዶ/ር መረራ ጉዲና የታወቁና ህብረተሰቡ የሚያከብራቸው ፖለቲከኞች ናቸው። እነዚህ ናቸው እንግዲህ ሽብርተኛ ተብለው የታሰሩት፡፡ እኔም ራሴ እንደምታዘበው፣ በርካቶች “ይሄን ተላልፈሃል፣ ያንን ጥሰሃል” እየተባሉ ነው የሚከሰሱት። ይሄን ስንመለከት በርግጥም የፀረ ሽብር ህጉ ዋጋው እንዲያንስ ይሆናል፡፡ እነ ዶ/ር መረራ እነ በቀለ ገርባ --- በዚህ የፀረ ሽብር ህግ ነው የተከሰሱት፡፡ ይሄ የሚያሳየው የፀረ ሽብር ህጉ እንደገና መፈተሽ እንዳለበት ነው፡፡ አሁን የሚደረገው ሁሉ የሽብር ግምትንና የፀረ ሽብር ህግን ዋጋ የሚያሳጣ ነው፡፡ ህጉ እንደገና መታየት አለበት፡፡
ፖለቲከኞች ከእስር መፈታታቸው የአገሪቱን ፖለቲካዊ ሁኔታ ከማሻሻል አንጻር ያለው ፋይዳ እንዴት ይገለጻል?
የእስረኞቹ መፈታት ትልቅ ትርጉም ያለው አዎንታዊ እርምጃ ነው፡፡ ኢህአዴግ የያዝ ለቀቅ ማሻሻያዎችን ትቶ ሁለንተናዊ ለውጥ እንዲመጣ ነው መጣር ያለበት፡፡ ጥያቄውን እያነሳ ያለው ደግሞ ወጣቱ ነው፡፡ በኛ ሀገር ወጣቱ ጠንካራ ሃይል ያለው አካል ነው፡፡ አብዛኛው ወጣት ደግሞ ከተለያዩ የትምህርት ተቋማት ትምህርቱን ጨርሶ የተቀመጠ የደሃ ልጅ ነው፡፡ ይህ ወጣት እድል ቢያገኝ፣ በሀብት የመካከለኛ ገቢ ደረጃ የህብረተሰብ ክፍል መሆን የሚችል ነው፡፡ አሁን እየጠየቀ ያለው ይሄን እድል እንዲያገኝ ነው፡፡ በአብዛኛው ራሱን ለማሸነፍ እየተሰደደ ነው፡፡ አሁን እድል ይሰጠኝ እያለ የሚጠይቀው፣ ከስደት የተረፈው ነው፡፡ እኔም ሰርቼ ልኑር ነው ጥያቄው፡፡ አመፅና ተቃውሞ እያደረገ ያለው ይህ የህብረተሰብ ክፍል፣ ከኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ጐን ለጐን ነፃነት ይፈልጋል፡፡ በነፃነት መናገር፣ በነፃነት መፃፍ፣ በነፃነት መሰብሰብ ይፈልጋል፡፡ ሳይፈራ ሳይሸማቀቅ በሀገሩ መኖር ይፈልጋል፡፡ ካፒታል ይፈጠርልኝ ሲልም የሌለ ነገር አይደለም የሚጠይቀው፡፡ መንግሥት ከተለያዩ ሀገራትና ድርጅቶች የሚያገኛቸው እርዳታዎችና ብድሮች ለኔም ይድረሰኝ ነው ጥያቄው፡፡ ለዚህ መፍትሄው ደግሞ መንግሥት ስርዓቱን ማሻሻል ነው ያለበት፡፡ እያንዳንዱን ሰው ከድህነት ለማላቀቅ የሚያስችል ካፒታል ለመፍጠር፣ አዲስ ስልት መንደፍ ያስፈልጋል፡፡ አብዛኛውን ኢኮኖሚ መንግሥት ነው የያዘው፡፡ ይሄ እንዲለወጥ ነው ህብረተሰቡ በስፋት እየጠየቀ ያለው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ጥቂት ሰው ብቻ ሳይሆን መኖር ያለበት፤ እኔም ህይወት አለኝ መኖር እፈልጋለሁ፤ የምኖርበት እድል ማግኘት አለብኝ ነው ጥያቄው፡፡ ይሄ ላለፉት 40 ዓመታት ያየነው አብዮተኛ ትውልድ፣ ፍላጐቱ ካፒታሊዝም ነው፡፡ አዲሱ ትውልድ፤ ዲሞክራሲ ፍትህ ነፃነት ነው የሚፈልገው፡፡ ይሄን ኢህአዴግ መመለስ ካልቻለ ቢበቃው ጥሩ ነው፡፡
አገሪቱን ከፖለቲካ ቀውስ አዙሪት ለማውጣት መፍትሄው ምን ይመስልዎታል?
ከዚህ ችግር ውስጥ ለመውጣት በኔ በኩል የሚታዩኝ መፍትሄዎች አሉ፡፡ የፖለቲካ ችግርን ለመፍታት ዘግይቷል የሚባል ነገር የለም፡፡ ምንጊዜም ቢሆን የፖለቲካ ችግርን ለመፍታት ጊዜ አለ፡፡ የመጀመሪያው እርምጃ ይሄን ሊፈነዳ ያለን ነገር ማቆም ነው፡፡ የሚቆመው በጠመንጃ አይደለም፡፡ ግድያ በተፈፀመ ቁጥር የባሰ እየከረረ ነው የሚሄደው፡፡ ይሄን በደርግ ጊዜ አይተነዋል። ደርግ “ሽብርተኞች፣ ገንጣዮች፣ አስገንጣዮች” እያለ ሲያወግዝ ሲገድል፣ ሲያስር ከኖረ በኋላ በዙሪያው ተወጥሮ ሲታነቅ፣  አንዴ ለንደን፣ ሌላ ጊዜ ሮም እያለ እየተንከራተተ ሲደራደር አይተናል። ይሄ ልማድ ዛሬም አልተወንም፡፡ መጀመሪያ ጥያቄ አንሺው ይወነጀላል፡፡ ከዚያም ስም ይወጣለታል፡፡ ይሳደዳል። በመጨረሻ ደግሞ የጭንቅ እርምጃዎች ሲወሰዱ እናያለን፡፡ ከዚህ ሁሉ ምስቅልቅል ይልቅ ተረጋግቶ፣ አስፈላጊ እርምጃዎችን መውሰድ ይገባል፡፡ በመጀመሪያ ጋዜጠኞችን፣ አክቲቪስቶችን፣ ፖለቲከኞችን ወዘተ--- ያላንዳች ቅድመ ሁኔታ መፍታት ያስፈልጋል፡፡ ሁለተኛ ከ1960ዎቹ ጀምሮ በተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶች ታቅፈው እርስ በርስ የተጋደሉትና እስካሁን ድረስ በጠላትነት የሚፈላለጉት ሁሉ ኢህአዴግን ጨምሮ ላለፉት የፖለቲካ ድርጊቶቻቸው፣ ይሄ ማለት፡- ለፈፀሙት ግድያና ማሰቃየት፣ ምህረት የሚያደርግ፣ የምህረት አዋጅ መታወጅ ይገባዋል፡፡ ይሄ አስቸኳይ እርምጃ ነው መሆን ያለበት፡፡ ይሄ አዋጅ ደግሞ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፀድቆ መውጣት አለበት፡፡ ኢህአዴግ ጫካ ከገባበት ጊዜ ጀምሮ የመንግሥት ስልጣን ይዞ የፈፀማቸውን ድርጊቶች የሚያስተሰርይለት ይህ የምህረት አዋጅ ነው፡፡ ሌሎች የፖለቲካ ድርጅቶችም በፖለቲካ መነሻነት የፈፀሟቸውን ወንጀሎች የሚያስተሰርይላቸው ይህ የምህረት አዋጅ ነው፡፡ ይህ የምህረት አዋጅ በዓለም የተበተኑ ኢትዮጵያውያንን በሙሉ የሚያጠቃልል መሆን አለበት። ኦነግ፣ ግንቦት 7፣ ኦብነግ፣ ኢህአፓ ወዘተ--- የሚባሉት በሙሉ በዚህ የምህረት አዋጅ መካተት አለባቸው፡፡ ኢህአዴግን ጨምሮ በተለያየ አግባብ የተፈረጁ በሙሉ የምህረት አዋጁ ይመለከታቸዋል፡፡ የሀገሪቱ የመጠፋፋት ዘመን በዚህ አዋጅ መቋጫ አግኝቶ፣ አዲስ ምዕራፍ ነው መከፈት ያለበት፡፡ ከዚያ በኋላ ደግሞ በውጭ ሀገር የሚገኙ ሊቃውንቶቻችን አዋቂዎቻችን በሙሉ ወደ ሀገራቸው እንዲገቡ ጥሪ ማቅረብ ነው የሚያስፈልገው። በአጭር ጊዜ ውስጥ ይህቺን አገር ሊለውጡ የሚችሉ የትየለሌ ምሁራን በውጭ አገር አሉ፡፡ እነዚህ ምሁራን አብዛኞቹ በ1960ዎቹ የመጠፋፋት ፖለቲካ ውስጥ የተሳተፉ ናቸው፡፡ ይህ የምህረት አዋጅ ቢታወጅ ወደ ሀገራቸው ለመመለስ ሁነኛ ዋስትና ይሰጣቸዋል፡፡
 በዚህ መንገድ ያለፈውን ምዕራፍ በመዝጋት አዲስ ምዕራፍ መጀመር ያስፈልጋል፡፡ ኢህአዴግም ነገ ከስልጣኔ ብወርድ ምን እሆናለሁ ብሎ አይጨነቅም። አሁን በስልጣን ላይ ያለው ስጋት፣ ከወረድኩ በኋላ ምን እሆናለሁ የሚለው ጭንቀት ነው፡፡ ነገር ግን ይህ አዋጅ ይሄን ስጋት ይቀርፍለታል። አሁንም ቢሆን ለዚች ሀገር ሰላም የምንመኝ ሰዎች፣ ለኢህአዴግ ዋስትና መስጠት አለብን፡፡ ከአንዱ የመጠፋፋት ምዕራፍ ወደ ሌላ ምዕራፍ ከምንሄድ፣ ለምን አዲስ መፅሐፍ አንፅፍም? ያንን ተከታታይ ምዕራፍ እንዝጋና አዲስ መፅሐፍ እንፃፍ። አሁን ያለንበት ሁኔታ ደግሞ ለዚህ ጥሩ አጋጣሚ ነው። የፖለቲካ ምህዳር ማስፋት ሲባልም እዚህ አገር ውስጥ ላሉት የፖለቲካ ድርጅቶች ብቻ አይደለም። በመላው ዓለም በስጋት ሀገራቸውን እንደናፈቁ፣ ምጡቅ አእምሮአቸውን ይዘው የተቀመጡ ስደተኛ ወገኖቻችን፣ የሚመጡበትን ሁኔታ ማመቻቸት አለብን፡፡ እነዚህ ወገኖቻችን ከፈለጉ መጥተው የፖለቲካ ድርጅት ይክፈቱ፣ ከፈለጉ ነጋዴ ይሁኑ፣ ከፈለጉ ደግሞ የሲቪል ተቋማትን ይክፈቱ፡፡ ይሄ ነው መሆን ያለበት፡፡ ከዚህ በኋላ ሀገሪቱ የተወሰነ የፖለቲካ ቡድን በጠቅላይነት ይዟት፣ እንዳሻው የሚያደርግበት ሁኔታ ማብቃት አለበት፡፡ ለዚህ ደግሞ ይሄ የምህረት አዋጅ ያስፈልጋል። ይሄ ከተደረገ በኋላ ታዋቂ ሰዎችን፣ ምሁራንን፣ የሀገር ሽማግሌዎችን ያካተተ፣ ሁሉን አቀፍ የሆነ ብሔራዊ የእርቅ ጉባኤ መደረግ አለበት፡፡ መንግሥት እነዚህንና  ሌሎች እርምጃዎችን ባስቸኳይ ከተገበረ፣ የዚች አገር ትንሳኤ እውን የማይሆንበት ምክንያት አይኖርም፡፡ ይህን የማስጀመር ስራ፣ የምህረት አዋጅን ከማርቀቅ መጀመር አለበት፡፡
በአሁኑ ወቅት በመላ ሀገሪቱ የመንግሥት ህግን የማስከበር አቅም ምን ደረጃ ላይ ነው ያለው?
ይሄ መንግሥት ብዙ ጊዜ ችግር ውስጥ የሚገባው ፖለቲካና ህግን እያምታታ ነው፡፡ ለምሳሌ ሰሞኑን የተካሄደው የስራ ማቆም አድማን ብንመለከተው፣ የስራ ማቆም አድማ ማድረግ፣ ህገ መንግሥታዊ ዋስትና ያገኘ መብት ነው፡፡ ይሄን ለማድረግ የመንግሥት ፈቃድ አያስፈልግም። በሌላ በኩል ደግሞ የስራ ማቆም አድማ አደርጋለሁ ተብሎ በሂደቱ መሳተፍ የማይፈልገውን ህብረተሰብ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አኗኗር የሚያውክ ድርጊት መፈፀም ህግን መጣስ ነው፡፡ መንገድ ላይ ድንጋይ እየደረደሩ፣ መኪና አያልፍም ማለት ለዲሞክራሲ መብት መታገል ማለት አይደለም። የሌላውን ሰላማዊ ሰው መብት መድፈር ፈፅሞ የዲሞክራሲ ትግል አይደለም፡፡ ለዚህ ነው ህገ ወጥ ድርጊትና ፖለቲካዊ እርምጃዎች መለየት አለባቸው የሚባለው፡፡ ይሄን መንግሥትም ህብረተሰቡም ያምታታዋል፡፡ የሌላውን መብት የሚነካ እንቅስቃሴ ማድረግ ለዲሞክራሲ መታገል ማለት አይደለም። መንግሥት ደግሞ ህግና ሥርዓትን ማስከበር አለበት፡፡ ካላስከበረ እንደ ሀገር ዋስትና የለንም ማለት ነው፡፡ ይሄ መንግሥት የህግ ችግር የለበትም። ችግሩ የማስፈፀም ነው፡፡ የህግ የበላይነት መከበር አለበት። አድማ የሚያደርጉ፤ በንግግር በፅሁፍ፣ በዲስኩር የሚቃወሙ ደግሞ የማይቃወሙትንም መብት ማክበር አለባቸው፡፡ ዲሞክራሲ ማለት ይሄ ነው፡፡ ዲሞክራሲ ማለት ልዩነትን ማክበር ማለት ነው። ይሄንን ለውጥ ፈላጊዎች ከወዲሁ ልንለማመደው ይገባል። ይሄን ንቅናቄ የሚመሩ ሰዎች፣ ንቅናቄያቸው በሌላው ህብረተሰብ ተቀባይነት እንዲያገኝላቸው በዚህ አግባብ ቢጓዙ ውጤት ያመጣል፡፡
ህዝብ ከሚያነሳቸው ጥያቄዎች አንዱ፣ የሰው ህይወት ያጠፉ ለህግ ይቅረቡ የሚል ይገኝበታል፡፡ መንግሥት በበኩሉ፤ እንዲህ ያሉ አካላትን አጣርቶ፣ ለህግ እንደሚያቀርብ በየጊዜው በይፋ ቃል ይገባል።  ይሄ ምን ያህል ተፈጻሚ ይሆናል ብለው ያምናሉ?
የፖለቲካ ችግርን ወይም አስተዳደራዊ ችግርን በጠመንጃ መፍታት አይቻልም፡፡ ለፖለቲካ ችግር ፖለቲካዊ መፍትሄ ነው መቀመጥ ያለበት። እንግዲህ በዳዮችን ለህግ ለማቅረብ በመጀመሪያ ጥልቅ ማጣራትና ምርመራ መደረግ አለበት፡፡ አንድ ችግር ሲፈጠር የፀጥታ ሃይሉ ሄዶ የፈፀመው ድርጊት፣ ከተሰጠው ሃላፊነትና ተልዕኮ ውጪ ነው፣ አይደለም የሚለው ይጠናል፡፡ በሌላ በኩል፤ ሰራዊቱ የተሰጠው ግዳጅ ምንድን ነው? በምን አግባብ ነው የተሰጠው? አብዛኛው ወታደራዊ ትዕዛዝ በቃል ነው የሚሰጠው፡፡ ነገር ግን የትዕዛዝ አሰጣጡ በገለልተኛ አካላት አሁንም መጣራት አለበት፡፡ ይሄ አጣሪ አካል የሚያቀርበው ሪፖርት ነው፣ የህግ ሂደቱን ቀጣይነት የሚወስነው፡፡ የዚህ አጣሪ አካል ክትትልም በህግ አፈፃፀሙ ላይ ወሳኝ ድርሻ አለው ማለት ነው፡፡
በግድያ ተሳትፈዋል ተብለው የሚጠረጠሩ የፀጥታ አካላት፣ ጉዳያቸው የት ነው የሚታየው?
ሀገሪቱ ወታደራዊ ፍርድ ቤት አላት፡፡ እንደዚህ አይነት ጉዳዮች እዚያ ነው ሊቀርቡ የሚችሉት፡፡
እንደሚከተለው አጠናቅሮታል፡፡ እነሆ፡-

Read 2052 times