Sunday, 18 February 2018 00:00

“እውነተኛ፣ ትክክለኛና ቅጥ ያለው ሃሳብ ይዣለሁ” ብሎ የሚናገር የጠፋበት ዘመን!

Written by  ዮሃንስ ሰ.
Rate this item
(5 votes)

   • ውጤቱስ? እንኳንና ፓርቲንና መ ንግስትን መምራት ይቅርና፣… በ እግርኳስ ፌ ደሬሽንም መተራመስ!
   • የቀጣዩ ጠቅላይ ሚኒስትር ቀዳሚ ትኩረት ሊሆኑ የሚገቡ 3 ዋና ዋና ጉዳዮች!
   • አሁን፣… “የሃሳብ ብዝሃነት፣ ውይይት፣ የሃሳብ ፍጭት”… ራሳቸውን የቻሉ ግቦች ሆነዋል!
   • “ግጭት፣ መጥፎም ጥሩም አይደለም። ኒዩትራል ነው” የሚል የተሳከረ ስብከት በቲቪ የምንጋትበት ዘመን!
     
    “ጠቃሚ አላማ ወይም ፖሊሲ ይዣለሁ”፣… አልያም “ተገቢ ዘዴ፣ አቅጣጫ፣ መርህ ወይም ስትራቴጂ፣… ይዣለሁ” የሚልና… 1፣2፣3… ብሎ ለመዘርዘርና ለማስረዳት የሚሞክር ሰው እየጠፋ ነው።
ለምሳሌ እንደድሮ፣… “ሦስት ዋና ዋና አላማዎች… 1. ሰላም፣ 2. ልማት፣ 3.ዲሞክራሲ…” ብሎ፣ እጥር ምጥን ያለ ሃሳብ የሚናገር ወይም ሃሳቡን ለማብራራት የሚሞክር ሰው አንሰማም። ሃሳቡ፣… ትክክል አልያም ስህተት መሆኑን ለመለየት፣… ጎደሎ ይሁን ሙሉ ፈትሾ ለማወቅ፣… ለመወያየትም ሆነ ለመከራከርም ጭምርኮ፣… ቢያንስ ቢያንስ ቅጥ የያዘ፣ መያዣና መጨበጫ ያለው ሃሳብ ያስፈልጋል። ዛሬ ዛሬ ይሄ እንኳ እየጠፋ ነው።
“አላማዎችን የሚያሳኩና አገሪቱ ካለችበት ደረጃ ጋር ተጣጥመው የተቃኙ ሦስት ተገቢ መርሆችና አቅጣጫዎች ይዣለሁ… 1.የሕግ የበላይነት፣ 2.ነፃ ገበያ፣ 3.የግል ነፃነት፣…” የሚል አይነት ሃሳብ፣ ወይም ሌላ የተሻለ ሃሳብ የማቅረብ፣ የመዘርዘርና የማስረዳት ሙከራም ጠፍቷል።
ዋና ዋና ነገሮችን አንጥሮ የማሳየት፣… ከተያያዥ ቅርንጫፍ ዝርዝሮች ጋር እያገናዘቡ፣ ሃሳቦችን ስርዓት ማስያዝ፣… እየቀረ ነው። “ያኛው መርህ ትክክል ነው፣ ይሄኛው ስህተት ነው” ለማለትና ለይቶ ለማወቅኮ፣… መጀመሪያ፣… ሃሳቦቹን ወይም መርሆቹን መልክ አስይዞ የሚያቀርብ ሰው ያስፈልጋል። አለበለዚያ ምን ላይ መወያየት ይቻላል?
ዋና ዋና አላማዎችን በግልጽ ካላወቀና በቅጡ ካላቀረበ፣… ከዝርዝር ቅርንጫፎቹ ጋር እያገናዘበ፣ እንዲሁም ከአጭርና ከረዥም ጊዜ ግቦቹ ጋር እያቀናጀ ሃሳቦቹን በስርዓት ካላቀረበ፣… ራሳቸው የፓርቲው መሪዎች ወይም ራሳቸው የመንግስት ሃላፊዎችስ፣ ምን ለማሳካት እንደሚፈልጉ እንዴት ያውቃሉ? እንዴትስ ይግባባሉ? እልፍ ጉዳይ ላይ፣ ወደ እልፍ ቦታ እየሄዱ፣ እልፍ ውሳኔና ትዕዛዝ እለት በእለት በአካል ተገኝቶ መስጠት አይቻል ነገር!
ዋና ዋና አላማዎቹንና መርሆቹን፣ ዋና ዋና የተግባር መንገዶቹንና እቅዶቹን፣… ቅልብጭ ባለሁኔታ አንጥሮና አጥርቶ፣ ሃሳቦቹን በትክክል ካላወቀ፣… በቃ አለቀለት። እልፍአእላፍ ዝርዝር እቅዶች፣ እልፍአእላፍ ሕጎች፣ ሚሊዮን ውሳኔዎች እየተፈለፈሉ፣ እርስበርስ እየተጣረዙና አንዱ ሌላውን እያፈረሰ፣ መያዣ መጨበጫ ጠፍቶ፣ በአቅመቢስነት ከመሳከርና ከመቃወስ ሊያመልጥ አይችልም።
ሺ ሃላፊዎችና ባለስልጣናት፣ ሚሊዮን አባላትና ሰራተኞች ያሉት ፓርቲ ወይም መንግስት ይቅርና፣… ከ10 ሰው በላይ የሌላት ትንሽዬ የቢዝነስ ድርጅት አልያም አንድ ቤተሰብ እንኳ፣… ያለ ዋና ዋና ሃሳቦች፣… ብዙም በጤና መራመድ አይችልም። የቢዝነስ ድርጅት፣… ቢያንስ ቢያንስ ምርትንና ትርፋማነትን የማሳደግ ዋና አላማ ይኖረዋል። ማሳደግ ባይችል እንኳ የእስከዛሬዋን ላለማጣትና ላለመክሰር ያልማል። በዚህ ዋና አላማ ላይ በመመስረትም ነው፣ የየእለቱ ውሳኔና ስራዎቹ፣ የወር እና የአመት እቅዶቹ… ሁሉም ነገሮቹ ትርጉም የሚኖራቸው። ጠቃሚና ጎጂነታቸውንም መመዘን የሚቻለው። አለበለዚያ ሚዛንና መለኪያ፣… ከነጭራሹ መግባቢያ ይጠፋል።
ሺ ሃላፊዎችና ሚሊዮን ሰራተኞች የያዘ ከሆነማ፣… ነጥረውና ጠርተው በግልፅ የሚታወቁ፣… 1፣2፣3 ተብለው የሚዘረዘሩ አላማዎችን፣… መርሆችን እየዘነጋ፣… እንዴት እንዴት ብሎ፣ ስርዓት ባለው መንገድ መግባባትና ስራን መምራት ይችላል? ድብልቅልቁ ነው የሚወጣው።
እንዴ፣… ትክክለኛ ሃሳቦችን ለይቶ ለማወቅ፣ ለማስረዳትና ለማብራረት መሞከርን እየተወ፣… “የሃሳብ ብዝሃነት”ን እንደ ግብ የሚቆጥር አስተማሪም ሆነ ፀሃፊ፣ ገዢ ፓርቲም ሆነ ተቃዋሚ ፓርቲ፣ መንግስትም ሆነ ማህበር፣… መጨረሻው ትርምስ ነው።
ዛሬም ሆነ ለዘለቄታው፣ ፈፅሞ ቸል ሊላቸው የማይገቡ ጉዳዮችን እንዴት ማወቅ ይችላል? ፈፅሞ አይችልም።
መንግስት፣… ህግን እና ሰላምን ቸል እስከማለት ድረስ የሚሄደው ለምን ሆነና!
በየትኛውም ክልል የሚገኝ አብዛኛው ነዋሪ፣ ህግ አክባሪና ጨዋ ሰው፣… ማለትም እጅግ የሚበዛውን ህግ አክባሪና ጨዋ ሰው (ሕዝብን)፣… ለጉዳት እንደማጋለጥ ነው። አብዛኛው ሰላማዊ ሰው፣ የትርምስና የስርዓት አልበኝነት ሰላባ እንዲሆን የመፍቀድ ያህል ነው።
ዋናው ነገር፣ “ሰላምና ህግ፣… የሕዝቡ ጥያቄ ነው?” የሚል ጉዳይ እንዳልሆነ እስከመዘንጋት መድረስ ምን ይባላል? “መንግስት ያስፈልጋል ወይም አያስፈልግም የሚለው ጥያቄ፣… የሕዝብ ጥያቄ ነው ወይ?” እያልን የመቶ ሚሊዮን ሰዎች ኑሮ ላይ እንደመቀለድ ነው።
አዎ። ሰላምን መጠበቅና ህግን ማክበር ማለት፣… ህግ አስከባሪዎች እንዳሻቸው ህግ እንዲጥሱ መፍቀድ ማለት አይደለም። አልያም ህግ አስከባሪዎች ስራቸውን እንዲዘነጉ ማድረግም አይደለም። ይህንን መርሳትና ቸል እስከማለት የተደረሰውና ነገሮች የተደበላለቁት፣… ዋና ዋና ሃሳቦችን በቅጡ ካለማወቅ፣ አልያም ለዋና ዋና ሃሳቦች ቀዳሚና ቋሚ ትኩረት ካለመስጠት ነው። የእለት ተእለት ስራን ለመምራትና ለመመዘን፣ የረዥም ጊዜ እቅድን ለማዘጋጀትና ተግባራዊ ለማድረግ፣ የየጊዜውንም ውጤት ለመለካት፣… ዋና ዋና ሃሳቦችን (ዋና ዋና አላማዎችንና ዋና ዋና መርሆችን) በቅጡ ማወቅ፣ ከዚያም መተንተንና ማብራራት፣ አገናዝቦም ማስረዳት ያስፈልጋል።
ይህም ብቻ አይደለም።… ከእለት እለት ስራ ጀምሮ፣… መጪውን ረዥም የታሪክ ዘመን አማትሮ እስከማየትም መዝለቅ አለበት። በየትኛውም አገር፣ በየትኛውም ዘመን፣ ከመቶ ዓመት በኋላ ቢሆን እንኳ እውን እየሆነ የሚመጣ፣ ምርጥ ራዕይ ይዣለሁ ብሎ የሚዘረዝር፣… ለምሳሌ፣… 1. እያንዳንዱ ሰው በተግባሩና በባህርይው የሚመዘንበት ስልጡን የመከባበር ባህል… 2. እያንዳንዱ ሰው በጥረት ኑሮን ለማሻሻል የሚስችል ስልጡን የብልፅግና ኢኮኖሚ፣ 3. እያንዳንዱ ሰው በእውቀት ራሱን መምራት የሚችልበት ስልጡን የነፃነት ፖለቲካ፣… እንዲህ ወይም ይበልጥ አጥርቶና አንጥሮ ራዕዩን ለማስረዳ የሚሞክር ፓርቲ፣ አመራር፣ ምሁር ወይም የመንግስት መሪ… እየጠፋ መምጣቱስ አይታያችሁም?
ይሄ ሁሉ ፋሽኑ እያለፈበት፣… በእልፍ አእላፍ ቅንጥብጣቢ ሃሳቦችና ስሜቶች እየተነዱ መወራጨት፣ መሳከር፣ መናቆር፣ መጋጨት፣ መላተም… መውጪያ የሌለው ትርምስ ውስጥ መዘፈቅ እየበዛ ነው።
“ሰላምን መጠበቅና ህግን ማስከበር” የተሰኘው ዋነኛ የመንግስት ስራ እንኳ፣ እንዴት እስከመረሳት ደረሰ? በቴሌቪዥን በይፋ፣… “ግጭት መኖሩ ችግር አይደለም” የሚል ረዥም የምሁር ዝባዝንኬ ስንጋትኮ ነው የከረምነው። “ግጭት ጥሩም መጥፎም አይደለም። ግጭትን እንደ እድል የመጠቀምና ያለመጠቀም ጉዳይ ነው።”… እንዲህ አይነት የተሳከረ ሃሳብ የተበራከተበት ዘመን ላይ፣ ብዙ ኑሯችን ቢሳከር ይገርማል?
ህግ የሚባል ነገር የሌለ ይመስል፣ “የግጭት አፈታት” የተሰኘ ፈሊጥ በቦታው ከተተካ፣ እንዴት ጤና ይኖራል? ዛሬማ “የግጭት አፈታት” የሚለው አባባልም እየቀረ ነው። “የግጭት አስተዳደር”… በማለት 100 ሚሊዮን ሰዎችን፣ የግጭትና የስርዓት አልበኝነት ሰለባ እንዲሆኑ ማጋለጥ!
ሰላምን መጠበቅና ህግን ማስከበር… ቀዳሚው የመንግስት ስራና ሃላፊነት እንደሆነ መዘንጋት፣ መዘዙ በመቶ ሚሊዮን ህግ አክባሪና ጨዋ ሰዎች ላይ ነው።
ሁለተኛው ቀዳሚ ትኩረት - ኢኮኖሚ ነው - ማለትም የሰዎች ኑሮ።
በጥረታቸው ኑሯቸውን የማሻሻል የእያንዳንዱ አላማ፣… ትልቁና አቻ የሌለው አላማ ነው። ይህንን አላማና የስራ ጥረታቸውን፣ የስራ ፍሬያቸውንና ኑሯቸውን ማክበር፣ ከማንኛውም አደናቃፊ ተግባር መቆጠብ፣… በተለይም የስራ እድል የሚፈጥሩ ሰዎችንና ኢንቨስትመንትን ከማዳከም፣… ሃብትን በከንቱ የሚያባክኑ የፌደራልም ሆነ የክልል መንግስታዊ ፕሮጀክቶችን ከመፈልፈል መቆጠብ፣… ቢያንስ ቢያንስ የፕሮጀክቶቹ ግንባታ ላይ ሃብት እንዳይባክን በኮንትራት በግል ኩባንያዎች ማከናወን፣… ከመቶ ዓመት በኋላ የሰሜን ወይም የደቡብ ዋልታ በረዶ በስንት ቶን ይቀንሳል ይቀልጣል በሚል ጨዋታ ኢንዱስትሪን የማዳከም ቀልድ እንዲቀር መወሰን፣… 100 ሚሊዮን ሰው፣… በመንግስት ድጎማና ምፅዋት ጥገኛ ሆኖ የሚኖር እንዳልሆነ መገንዘብ ያስፈልጋል።
በኢኮኖሚ ላይ፣… በሰው ኑሮ ላይ፣ ቅንጣል ቀልድና ጨዋታ እንዳይኖር ማድረግ፣… ሁለተኛው ቀዳሚ ትኩረት ነው። እንዴ? ድህነት ዋና ጠላታችን ነው የሚለው አባባል እንኳ ተረሳኮ።
ሦስተኛው ቀዳሚ ትኩረት - ለዛሬም ለዘለቄታውም፣ ንፁህ ነገር መስራት ነው - በሰበብ አስባቡ እያመካኙ፣… ከጊዜው ነው እያሉ፣…. ለነገ መዘዝ ከሚያመጡ ነገሮች፣… “ከጭፍን ፕሮፓጋንዳ” የፀዳ፣ “ከእውቀት አልባ መረን የሃሳብ ብዝሃነት”… የራቀ፣ ለእውነት፣ ለአእምሮና ለእውቀት ክብር የሚሰጥ ጉዞ መጀመር ያስፈልጋል። 1 ሲደመር 1 ሁለት የመሆኑ ጉዳይ ላይ የሃሳብ ብዝሃነትና ውይይት ያስፈልጋል ወደሚል ቧልትና ጨዋታ ውስጥ መግባት ምን ማለት ነው? ይሄ የተጋነነ ምሳሌ ከመሰላችሁ፣ የዘመናችንን ችግር ገና በውል አላያችሁትም። ትምህርት እና እውቀት እየተራራቁ፣ እየተጠፋፉ እንደሆኑ አልታዘባችሁም ማለት ነው።
“የዩኒቨርስቲ ትምህርት”… ተብሎ ሲወራ፣… “እውቀት፣ ክህሎትና ብቃት” የተሰኙት ነገሮች እየደበዘዙ፣… “ዩኒቨርስቲ ማለት፣… የሃሳብ ፍጭት፣ የክርክርና የሰላማዊ ትግል አውድማ” እንደሆነ ሲነገር፣… “ምን?!” ብሎ የሚጠይቅ እንኳ የለም። እንደ ኖርማል ነው የሚቆጠረው። በመቶ ሺ የሚቆጠሩ ወጣቶች ከዩኒቨርስቲ ተመርቀው ሲወጡ፣ በየትኛው እውቀት፣ ክህሎትና ብቃት ኑሯቸውን እንደሚመሩ ማሰብ ቀረ? በእውቀት፣ በክህሎትና በብቃት ኑሮን ለማሻሻል ከመትጋት የላቀ፣ “ሰላማዊ ትግልስ” አለ?
ጭራሽ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ሳይቀር፣… የልጆች “በምናባዊ ፈጠራ” የሚወያዩበትና ስሜታቸውን የሚገልጹበት ጨዋታ እንደሆነ ያለሃፍረት የሚነገርበትና ይህም እንደአዋቂነት የሚቆጠርበት የተቃወሰ ዘመን ላይ ደርሰናል።
እና ደግሞ፣ ይሄ ሁሉ በተግባር ጉዳት የማያደርስ ጊዜያዊ ስካርና ባዶ ወሬ የሚመስላቸው አሉ - በዝምታ የሚያዩ።
በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሕፃናት፣ በፍጥነትና በጉጉት መሰረታዊ እውቀትንና ክህሎትን የሚጨብጡበት ውድ ጨቅላ እድሜያቸው ሲባክንና፣… አንዲት ቃል ማንበብም ሆነ መፃፍ የማይችሉ የ3ኛ እና የ4ኛ ክፍል ሚሊዮን ተማሪዎችን የማየት መዘዝ አይመጣም ብለው ነው? ወይስ መዘዙ ከተፈጠረ በኋላም ቢሆን፣ ውድቀቱን ባለበሌለ ሰበብና እልፍ ማመከኛ ወዲህና ወዲያ ማላከክ ይቻላል ብለው ነው? ግን፣ ውድቀትን በሌላ ላይ ማላከክ፣ ውድቀቱን አይሰርዘውም። መች ቆም ብለው፣ የተሳከረ ሃሳባቸውን ለማስተካከል ይሞክራሉ? የትምህርት ዋና አላማ፣ “እውቀትንና ክህሎትንና ብቃትን ማዳበር ነው” ወደሚል ከስካር የራቀ ጤናማ ሃሳብ ለመመለስ አይሞክሩም።
ለጊዜው ብቻ ነው እያሉ፣… በድጎማ፣ በምፅዋትና በገንዘብ ሕትመት፣… ለነገ የኢኮኖሚ ቀውስን ከመፈልፈል ይልቅ፣ በጥረት ኑሮን የማሻሻል አላማን መደገፍ፣ ስራን መውደድና ስኬትን ማድነቅ የባህላችን አካል እንዲሆን የስልጣኔ እርምጃ መጀመር አለብን።
በተደጋጋሚ እንደታየው፣… በዘርም ይሁን በሃይማኖት፣ ጭፍን የመቧደን ቅስቀሳ፣… ውሎ አድሮ፣… እጅጉ “መጥፎ” ለሆኑ ሰዎች የሚመችና አብዛኛውን ጨዋ ሰው የጥፋት ሰለባ የሚያደርግ መሆኑ… ፈፅሞ አከራካራ አይደለም። እናም፣ እያንዳንዱ ሰው በተግባሩና በባህርይው የሚመዘንበትን ስልጡን የመከባበር ባህልን መገንባት መጀመር አለብን።

Read 2009 times