Saturday, 17 February 2018 14:22

የጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሣለኝ ስንብት

Written by  መታሰቢያ ካሣዬ
Rate this item
(5 votes)

 ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሣለኝ በመስከረም ወር 2003 ዓ.ም ነበር በ47 ዓመት ዕድሜያቸው በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርነትና በውጪ ጉዳይ ሚኒስትርነት ማዕረግ ወደ ከፍተኛው ሥልጣን የመጡት፡፡ ይህም በገዥው ፓርቲ አመራሮች ዘንድ ተግባራዊ ለማድረግ የታሰበው የመተካካት ስትራቴጂ አንዱ ክፍል ነበር። የአገሪቱ ከፍተኛ ሥልጣን በእጃቸው የነበረው የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ፤ አቶ ኃይለማርያም ደሣለኝን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር አድርገው ወደ ሥልጣን ሲያመጧቸው& በሂደት ሥልጣናቸውን ሙሉ በሙሉ ለተተኪያቸው የማስረከብ ሃሳብ አላቸው የሚሉ ወገኖች ነበሩ፡፡ ነገር ግን እሳቸው ሥልጣናቸውን ለተተኪያቸው አስረክበው ገለል የማለቱ ፍላጐት አልነበራቸውም፡፡
አቶ መለስ ከምርጫ 2002 በኋላ ሥልጣን ላይ መቆየት እንደማይፈልጉ ቢገልፁም፤ ፓርቲያቸው በግድ እንዲቀጥሉ አስገድዷቸዋል በሚል ምክንያት ህይወታቸው እስካለፈበት ጊዜ ድረስ ሥልጣናቸውን እንደያዙ ቆይተዋል፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ ግን ተተኪ የሚሆናቸውን ሰው ሲመርጡና በተለያዩ መንገዶች ሲፈትኑ ኖረዋል፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሣለኝ ሃይማኖተኛነት፣ የፖለቲካና የሥልጣን ምኞት የሌላቸው መሆናቸውና በሥልጣን ላይ ላለው ሥርዓት ያላቸው ታማኝነት  ለሥልጣን እንዲታጩ እንዳደረጋቸውም ይነገራል፡፡
ከቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ ሞት በኋላ የጠቅላይ ሚኒስትርነቱን ሥልጣን የሚረከበው ሰው ማን ይሆን የሚለው አነጋጋሪ ጉዳይ ነበር፡፡ በሕገ-መንግሥቱ መሰረት፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ህይወታቸው ባለፈበት ወቅት ወዲያውኑ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አቶ ኃይለማርያም ደሣለኝ መተካት የነበረባቸው ቢሆንም፤ መንግሥት በጉዳዩ ላይ ጊዜ በመውሰድ ሹመቱን አዘግይቶታል። ይህ ሁኔታም በኅብረተሰቡ ውስጥ የተለያዩ መላ-ምቶች እንዲነሱ ምክንያት ሆኗል፡፡ ከእነዚህ መላ-ምቶች መካከልም በኢህአዴግ ውስጥ የሥልጣን ሽሚያ ተፈጥሯል፣ ሕወሓት አመራሩን ከትግራይ ውጪ ብሔር ላለው ሰው መስጠት አልፈለገም፤ እንዲሁም አቶ ኃይለማርያም ለጠቅላይ ሚኒስትርነት አይመጥኑም በሚል ኢህአዴግ ሌላ ሰው እያፈላለገ ነው የሚሉ ይገኙበታል፡፡
ሆኖም ኃይለማርያም ደሣለኝ መስከረም 6 ቀን 2005 ዓ.ም በተካሄደው የኢህአዴግ ምክር ቤት ስብሰባ ተመርጠው፣ መስከረም 11 ቀን 2005 ዓ.ም በተደረገው አስቸኳይ ስብሰባ ሥልጣናቸው ፀድቆ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆኑ፡፡ ከአቶ መለስ ዜናዊ ህልፈት በኋላ አቶ ኃይለማርያም ደሣለኝ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው የአቶ መለስን ወንበር ሲይዙ በርካቶች፣ “ሠላማዊ የሥልጣን ሽግግር ተካሄደ” ሲሉ ተደምጠዋል፡፡ ነገር ግን ይህ ሠላማዊ የሥልጣን ሽግግር ጽንሰ ሃሳብን በትክክል የሚያንፀባርቅ መሆኑ የሚያጠራጥር ነው፡፡ ያው ገዢው ፓርቲ ነው ወደ ሥልጣን ያመጣቸው። ከሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር ይልቅ መተካካት ቢባል ያስኬዳል የሚሉ ብዙዎች ናቸው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሣለኝ ገና ወደ ሥልጣን እንደመጡ ተልዕኰአቸው የአቶ መለስን ራዕይ መከተልና ማስፈፀም እንደሆነ አስረግጠው ተናግረው ነበር፡፡ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ በነበረው የመጀመሪያ የፓርላማ ውሏቸው “እኔ የተመረጥኩት የመለስን ራዕይ ለማሳካት ነው” ብለዋል፡፡ ይህ አነጋገራቸው በወቅቱ “ከእኔ ምንም አዲስ ነገር አትጠብቁ” “እኔ አቶ መለስን መተካት አልችልም፤ እዚህ ቦታ ላይ የተቀመጥኩት የመለስን ራዕይ ለማስፈፀም ነው” ሲሉ ለአቶ መለስ የወንበራቸው ብቻ ሳይሆን የራዕያቸውም ወራሽ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሣለኝ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ ከአቶ መለስ መስመር ሳይወጡ፣ አቶ መለስ ሳይፈጽሟቸው የቀሩትን ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ተግባራትን የመፈፀም ግዴታ ተጥሎባቸው ቆይቷል፡፡ ብዙ ጅማሮዎችን ትቶ ከዚህ ዓለም በሞት በተለየ መሪ እግር መተካት ለአቶ ኃይለማርያም እጅግ ፈታኝ ነበር፡፡ ለዛውም “የፈለገውን የማድረግ፣ በፈለገው ጉዳይ ላይ ውሣኔ የመስጠት አቅም የለውም” እየተባሉ፡፡
አንዳንድ የፖለቲካ ተንታኞች፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሣለኝን ከቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ጋር ሲያነፃጽሯቸው፤ ሥልጣናቸው የይስሙላ ነው ይሏቸዋል፡፡ አቶ መለስ እውነተኛ ሥልጣን (Real Power) የነበራቸው፣ ብዙ ነገሮችን ማንንም ሳይጠይቁ በራሳቸው ማድረግ የሚችሉ በብዙዎቹ የኢህአዴግ አመራሮች ዘንድ ተደማጭና ተፅዕኖ ፈጣሪ እንደነበሩ ይነገራል። በዚህም የተነሳ የሥልጣናቸው አድራጊ ፈጣሪ ነበሩ። ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ከቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ጋር የሚተካከል ሥልጣን እንዳልነበራቸው የፖለቲካ ተንታኞች ይገልፃሉ፡፡ “የአቶ ኃይለማርያም የፖለቲካ ስብዕና የተገነባው በመለስ መንፈስ ውስጥ ነው የሚሉም ወገኖች አሉ፡፡ አቶ ኃይለማርያም ደሣለኝ የጠቅላይ ሚኒስትርነት ሥልጣኑን ከያዙ በኋላ የተፈፀመው የሁለት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሮች ሹመት፤ የእሳቸው ሥልጣን መሳሳቱን ወይም መቀነሱን አመላካች ነበር፡፡
በአቶ መለስ የሥልጣን ዘመን የፕሬስ ነፃነት ተዳክሟል፣ የሰብአዊ መብቶች ተዘንግተዋል፣ የፀረ-ሽብርተኝነትና የሲቪክ ማኅበራት ሕጐችን የመሳሰሉ ኅብረተሰቡን ያስደነገጡና ያስፈራሩ ሕጐች ተደንግገው ሥራ ላይ ውለዋል፡፡ የኑሮ ውድነቱና የዋጋ ግሽበቱ በየጊዜው እየጨመረና እየተባባሰ ሄዷል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሣለኝ ወደ ሥልጣን ሲመጡ፤ ከእነዚህ ችግሮች ቢያንሱ ለጥቂቶቹ አዳዲስ መፍትሄዎች ያመጣሉ ብሎ ተጠብቆ ነበር፡፡ ነገር ግን አጣዳፊ ችግሮቻችን ተጨባጭ መፍትሄን ሳያገኙ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የወረሱትን ራዕይ በማስጠበቅ ሥራ ላይ እንደተጠመዱ ዓመታት ነጉደዋል የሚሉት የፖለቲካ ተንታኞች፤ ህዝቡ ከእሳቸውና ከሚመሩት መንግስት ብዙ ጠብቆ ምንም አጥቷል ሲሉ ይተቻሉ፡፡ ያለፉት 3 ዓመታት ደግሞ የጠ/ሚኒስትሩን የሥልጣን ዘመን ይበልጥ አዳጋችና ፈታኝ አድርገውባቸዋል፡፡ በህዝብ ተቃውሞና አመፅ የምትናወጠውን አገር መምራት ከባድ ነው። ያም ሆነ ይህ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሣለኝ ለተፈጠረው ሁኔታ የመፍትሄ አካል ለመሆን በማሰብ ስልጣኔን በገዛ ፈቃዴ ለመልቀቅ ወስኛለሁ ብለው በይፋ ነግረውናል፡፡ ሁኔታው ወደየት እንደሚያመራና ቀጣዩ ጠቅላይ ሚኒስትር ማን ሊሆን እንደሚችል በሂደት የምናየው ጉዳይ ይሆናል፡፡   

Read 3723 times