Sunday, 18 February 2018 00:00

“ያ ሌላ ይኼ ሌላ!”

Written by  ሌሊሳ ግርማ
Rate this item
(0 votes)

  “አውድ” የሚለው ቃል በመዝገበ ቃላት ውስጥ የተቀመጠለት ብያኔ ምን እንደሆነ አላውቅም፡፡ የቃሉ ትርጉም አካባቢው ግን ይገባኛል፡፡ መዝገበ ቃላት ራሱ አውድ ነው፡፡ የቃል ትርጉሙ፣ አገባቡ፣ ርቢው የሚዘረዘርበት አውድ ነው፡፡ … ከመዝገበ ቃላቱ ውጭ ባለው የዕለት ተዕለት ህይወታችን፣ በመዝገበ ቃላት ያለውን ቃል ለሌላ ትርጉም ስንገለገልበት ልንገኝ እንችላለን፡፡… የጎዳና ቋንቋና የመዝገበ ቃላቱ አንድ ሊሆን አይችልም፡፡ አውዱ ይለያያል፡፡
አውድ የሚለው ቃል በመዝገበ ቃላት ውስጥ ቢተረጎምም… ቃሉ መልሶ መዝገበ ቃላቱን ይገልፀዋል፡፡ መዝገበ ቃላት አንድ አውድ ነው። “አውድ” የሚለውን ቃል እኔ ወደ እንግሊዝኛ አስጠጋው ብባል “Context” አይደለም የምለው። “Context” በጽሁፉ (Text) ውስጥ ያለ አንድምታን እንጂ “የአውድን” መጠነ ሰፊ ባህሪይ አይገልፅልኝም።
ይልቅስ እኔ አውድን ሰፋ አድርጌ የምረዳው “Controlled” በሚለው ቃል ውስጥ ነው። “የተጠበቀ፣ የተከለለ” የሚለውን ምስል ይሰጠኛል። እንዲያውም አቅሙ የተቆጠበ ማለት ነው፡፡… ለምሳሌ “አውደ ርዕይ” አንዳች ትዕይንት ለተመልካች በተቆጠበ ስፍራ ላይ የሚቀርብበት ነው፡፡ … አውድ… እስካለ “ስፍራም” አብሮ አለ፡፡ የተቆጠበው ነገር የሚቀርብበት ስፍራ ማለት ነው፡፡
ቤተ-መቅደስ አውድ ነው፡፡ አምላኪዎቹ አምላካቸውን (በተለየ ሁኔታ) የሚያገኙበት ስፍራ ነው፡፡ … መኖሪያ ቤት የመኖሪያ አውድ ነው፡፡ ቤተ-መቅደስ የአምልኮ፡፡ … መቆጠብ ወይንም መከለል ሳይኖር … ምድርም ምድር ባልሆነን ነበር፡፡… ሰው የመሆን ፀጋ ለእኔ የሚገለፀው፣ በአውድ ግድግዳ ውስጥ ነው፡፡
የተለያዩ እምነቶች እንደየ አውዳቸው ፈጣሪያቸውን በተቆጠበ ስፍራ ላይ ያገኛሉ፡፡ ለምሳሌ አንዳንድ ሃይማኖትን ከአውዳቸው ወጥተው መላ ሀገሩ ላይ በልበ-ሙሉነት የሚሰብኩበት ሁኔታ ይኖራል፡፡ የቤተ-መቅደሱን ቁጥብነት ወደ ሀገር ደረጃ አድጎ “ኢትዮጵያ የክርስቲያን ደሴት ናት” ብሎ በልበ-ሙሉነት የሚናገር ይኖራል፡፡
የአውዶች ቁጥብነት መጠንከርን ነው እኔ “መቻቻል”፣ “ፍትሐዊነት” ወይንም “የሀሳብ ነፃነት” የሚሉትን ማስተንተኖችን (abstracts) የምገነዘባቸው፡፡
ለምሳሌ “ነፃ ትግል” የሚባል ስፖርት አለ፡፡ ወይንም “ቦክስ ግጥሚያ”፡፡ ሙሉ ሀገር የነፃ ትግል ወይንም የቦክስ ፍልሚያ ሜዳ ሊሆን አይችልም፡፡ የቦክሱ መድረክ ዙሪያ የተዘረጉ ገመዶች፣ በውጭው ዓለምና በፍልሚያው ሜዳ መሀል ቁጥብነት መኖሩን የሚገልፁ ናቸው፡፡ ከዚህ በመለስ… እንፋለማለን የሚሉት የሚቧቀሱበት… ከዚህ በመለስ… እንመለከታለን የሚሉት የሚመለከቱበት ነው፡፡ በቦክሱ መድረክና በተመልካቹ ስፍራ መሀል ልዩነት ቢኖርም፤ በጥቅሉ ግን የአንድ አውድ ቤተሰቦች ሊባሉ ይችላሉ፡፡… ከፍለው ወይንም በቦታው ላይ ተገኝተው ትዕይንቱን የሚመለከቱት አውዱ ስለሚመለከታቸው ነው፡፡
እንደ አቅም ልንመስለው እንችላለን - አውድን። ኤሌክትሮኖች በኒውክለሱ ዙሪያ ይሽከረከራሉ። … ኤሌክትሮን ከአንድ አቅም ወደ ሌላው ይሸጋገራሉ፡፡ የኤሌክትሮኖቹ መጠን ለአቶሙ ማንነቱን ይሰጠዋል፡፡ ወይንም የነበረውን ማንነት ይለውጠዋል፡፡… አውዱ አቶሙ ነው፡፡ ግን አቶሞች አንድ ላይ ተከማችተው የሞሎኪውል ማንነትና አውድም ይፈጥራሉ፡፡
… የተነሳሁበትን ጉዳይ የበለጠ ለማብራራት ስል፣ እኔም ወደሌላ አውድ እንዳልገባ፡፡ … በመሠረቱ ሁሉም አውድ ወደ አንድ ምንነት ይተረጎማል … ብለው በደፍረት ይናገራሉ፤ ሳይንቲስቶቹ። “Unified Field theory” በሚል “ባንዲራ” ሁሉንም የተነጣጠለ አውድ፤ ወደ አንድ ቀላል ፎርሙላ ለመሰብሰብ የጣሩ ነበሩ፡፡
ሌሎች ደግሞ “አውዶች ዝንተዓለም ወደ አንድ ቅልብጭ ያለ ቅንብብ ሊመጡ አይችሉም” የሚሉ የኳንተም (Theory of the Small) ልሒቃን አሉ። በሁለቱ አቅጣጫ የሚመራመሩ ሀሳባዊያንም፤ በሀሳባቸው አውድ መጠን የተቆጠቡ ናቸው፡፡… ምንም እንኳን እንደ መዝገበ ቃላት፣ አንዳንድ ቁጥብ የሚመስሉ አውዶች ሁሉንም ነገር በእጅ አዙር ጠቅልሎ የመመልከቻ መሳሪያ የሚቸሩን ቢመስሉም… መርሳት የሌለብን ዞሮ ዞሮ ሁሉም የአውድ አይነት መሆኑን ነው፡፡
ጾታ አውድ ነው፡፡ “ጾታ” ብሎ ነገር የለም… እንቁላል እና እስፐርም ብቻ ነው ያለው … ወይንም … `X` እና `y` ክሮሞዞም ብቻ ነው ያለው… የጾታ ባህርይ (Gender role) በማኅበረሰብና የባህል ተፅዕኖ መጣ” ብለው ለሚከራከሩትም፣ የሚከራከሩበት ሀሳብ ራሱ አውድ ነው፡፡
ይሄ መጣጥፍ አውድ ነው፡፡ ስለ አውድ ፀሐፊው የተገነዘበበትን በራሱ አገላለፅ ለማስቀመጥ የሚጥርበት አውድ ነው፡፡ ፀሐፊው ስለ አውድ የፃፈውን ለአንባቢያን ለማስነበብ የሚጠቀምበት አውድም አለ፡፡ ጋዜጣ ተብሎ ይጠራል፡፡… ጋዜጠኝነትም አውድ ነው፡፡ የስራው አይነት ከሌሎች የስራ አይነቶች በመለየቱ መጠን፣ ስለ ራሱ ምንነት የሚሰጠው ትርጉም ራሱ አውድ ይፈጥርለታል፡፡
ግን አውዶች በሙሉ ቁጥብ መሆናቸው መዘንጋት የለበትም፡፡ ቁጥብነት ከሌለ የአንዱ አውድ ተለጥጦ የሌላውን ስፍራ ሊወስድ ይችላል። በአንድ ሀገር ላይ ብዙ ህዝቦች በመቻቻል መኖር የሚችሉት አውዶች ቁጥብነታቸው እስከተከበረ ድረስ ነው፡፡ መከበርና ማስከበር እንዲቻል የአውድ ጠባቂ አካል መኖር አለበት፡፡… ሕግ ወይንም ሕገ-መንግስት የሚያስፈልጉት ጠንካራው ቁጥብነቱን ጥሶ ደካማውን አውድ እንዳይሰለቅጥ ነው፡፡… አምባገነንነት ቁጥብነቱን ጥሶ የወጣ አውድ፣ የሚያደርሰው በደል ወይንም ማን አለብኝነት ሊሆን ይችላል፡፡
…አዎን ይሄንን ተግባር ሕግ ብቻ ሊያሳካው አይችልም፡፡ ማኅበረሰብና ባህልም ያስፈለጉት፣ አስተማማኝ የ“ቁጥብነት ጠባቂ” ስለሚያስፈልግ ነው፡፡ ጠባቂነትም ግን አውድ መሆን መቻል አለበት፡፡ በጠባቂነት ስም ወይንም በማስማማት ስም፣ አውዶችን ለመጨፍለቅ ከተንቀሳቀሰ ይሄም ችግር ነው፡፡
ለዚህ ነው መዝገበ ቃላቱም፣ የሕግ ረቂቁም፣ የቋንቋ ሥርዓቱም፣ ትምህርቱም ያስፈለጉት።… መዝገበ ቃላቱ ከሰጠው ትርጉም ውጭ ቃላትን በዘፈቀደ የሚጠቀም ከሆነ የቋንቋ አውዱን አጠፋዋለሁ፡፡… እኔ ባጠፋሁት መንገድ ሌላውም እያዛባ እንዳይከተለኝ የቋንቋው ስርዓት ይከለክላል። ሥርዓቱን ሳላጠፋ ቋንቋው ላይ የምጨምረው እድገት አዎንታዊ ሊባል ይችላል። ቋንቋው ቁጥብነቱን ሳይለቅ (ሌሎች ቋንቋዎች ወደኔ ካልተለወጡ ሞቼ እገኛለሁ ሳይል) ራሱን ማሳደግ ችሏል፡፡
… አንዳንድ ጊዜ ግን ራሱን ችሎ፣ አምባገነን ሳይሆን በማደጉ ሌሎች አውዶችን የሚውጥ ገናና አውድ ይከሰታል፡፡ ይሄንን የዘመን መንፈስን የሚዘውር ተፅዕኖ ፈጣሪ አውድ ልንለው እንችላለን።… በዚህ አቅጣጫ የመጣሪ እድገትን ከመቀበል ውጨ ምንም ማቅማማት አይቻልም።… አልያም በዚህ የዘመን መንፈስ ተውጦ እያለ አልተዋጥኩም… እያለ ከዘመን መንፈስ ጋር እንካ ሰላንቲያ የሚያወራ ህልመኛ ሆኖ መቅረትን ያመጣል፡፡
ሎጂክ አውድ ነው፡፡ በግሪክ ዘመን የተተነተነ የአውድ አይነት ነው፡፡ ሎጂክ የሚለው ቃል logos = word = reason ማለት ነው፡፡ በቃል መልክ የሚቀርብ ንግግርም የሆነ ጽሁፍ ምክንያታዊ እስከሆነ ድረስ በሎጂክ አውድ ስር የሚጠቃለል ነው፡፡ “The Science of the Laws of thought, that is, of the method of reason” ይለዋል ሾፐንሀወር፣ ከአሪስጣጣሊስ ከተዋሰው ሀሳብ ቆንጥሮ፡፡
…እኔ እስካሁን እየፃፍኩ የመጣሁት ጽሁፍ ሎጂክ ነው እያልኩ አይደለም፡፡ ሎጂክ ባይሆንም ግን - (እንደተጠቀሰው) ቃላትን እስከተጠቀምኩ ድረስ ሀሳብን አፍልቄያለሁና… “የምክኒያታዊነትን መንገድ” ባልከተል እንኳን ጽሁፍ እስከሆነ ድረስ አንድ አውድ ውስጥ የሚወድቅ ነው፡፡
አሪስቶትል ሀሳብ በሎጂክ አውድ ካልተጠቀለለ፣ በ“ዲያሌክቲክስ” አውድ ስር በግድ መጠቃለሉ አይቀርም ይላል፡፡… እኔ ስለ አውድ በራሴ አተያይ የገለፅኩበት መንገድ አንድም ሎጂካል ይሆናል-ካልሆነ ደግሞ ዴያሌክቲካዊ ነው፡፡ በእነዚህ ሁለቱ ውስጥ ካልገባ ደግሞ ሦስተኛ አውድ ይፈለግለታል። “Eristic” ሊባል ይችል ይሆናል፡፡ “ኤሪስቲክ” የሚለውን የሀሳብ አይነት አሪስጣጣሊስ ሲተረጉመው፣ የተደረሰበት ድምዳሜ ትክክል የሆነ… ግን መነሻው “ሀሳብ” የተሳሳተ በሚሆንበት ጊዜ ነው ይለናል፡፡
…እኔ በመሠረቱ ስለ አውድ በራሴ ቁጥብ አቅም ለመግለፅ ነው እንጂ የፈለኩት… የአሪስጣጣሊስ አውዶች ውስጥ “ለመቀነፍ” አይደለም መፃፍ የጀመርኩበት ግብ። ሎጂካል፣ ዳያሌክቲካል፣ ሬንሪካል፣ አሪስቲካል ወይንም ሶፊስቲክ ሊሆን ይችላል፡፡ ስህተትም ሆነ ትክክል ማለት ከአንድ አውድ አንፃር የተሰጠው ብያኔ ነው፡፡ ሁሉም ብያኔ ከራሱ አውድ ወጥቶ ዓለምን በራሱ የአመለካከት መነጽር ስር ብቻ ለማጉላት ይጥራል፡፡ ጥረቱ ግን ፍሬያማ የሚሆነው እውነት ሆኖ ፍሬ የሚያፈራ ከሆነ ብቻ ነው፡፡
ሳጠቃልል፡-
አውድ የሚባለው ቃል የነገራትን ምንነት ለመግለጽ ጥሩ ሞዴል መስሎ ታይቶኛል፡፡ በታየኝ መጠን፤ አውድ… ሁሉ ራሱን ዋና አድርጎ ሌሎችን መጠቅለል ቢሻም… አውዶች ግን ሁሌም አሉ፡፡… የሰው የተሞክሮና የእውቀት መጠን የሚለካው በአውዶቹ ብዛት ነው፡፡ … ግን አውድ ስንል “ቁጥብነት” (Controlled) የሚለውን ቃል ፈጽሞ መርሳት የለብንም፡፡
ሳይንቲስቱ በቁጥብ ቤተ ሙከራው፣ በጎዶሎ የአተም ቀኒጠፋ (Sub atomic particles) ላይ ያገኘው ግኝት… በሰፊው ሕዋና በግዙፎቹ የጠፈር አካላችን ላይ አልሰራ ቢለው … መመርመር ያለበት የአስተሳሰብ አውዱን ይመስለኛል፡፡ … የትንሹ ወደ ትልቁ አውድ አንድ እና አንድ ሆኖ አለመገልበጥ፣ የአውዶች ልዩነት ዘላቂና ተፈጥሮአዊ መሆኑንም ገላጭ ሊሆን እንደሚችል የሚያሳስብ ነው፡፡ ከሁለት አቅጣጫ ከማሰብ ወደ ሦስተኛ የሀሳብ አውድ መሸጋገርም የተሻለ ሊሆን ይችላል፡፡… ሦስተኛው ወይንም አራተኛው-አውድ “unique anomaly” ተብሎ እስኪብራራ በቅንፍ ይቀመጣል፡፡
በቤተ-መቅደስ ውስጥ… ከመንፈስ ተአምራትን የሚሰሩ ሰዎች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ደግሞም አሉ፡፡… በቤተ-መቅደስ ውስጥ ሆኜ በፀሎታቸው መንፈስ ውስጥ ሲዘፈቅ እኔም የአውዱ አካል እሆናለሁ፡፡… ግን የምክንያታዊ ወይንም ሎጂካዊ አስተሳሰቤን ይዤ ወደ መንፈሳዊው አውድ ከገባሁ… “እያጭበረበሩ ነው” ብዬ ልንቃቸው ሁሉ እችላለሁ፡፡ ችግሩ አውድን አለማወቅ ነው፡፡ የአውድን ቁጥብነት አለመረዳት ነው።… ሳይንቲስት ከላቦራቶሪው የሚያስብበትን አውድ በቤተ-መቅደስ ውስጥ ይዞ ከመጣ… አንባገነን ሆኗል፡፡ በራሱ አውድ ዓለምና እውነታን መሸምቀቅ ፈልጓል፡፡… ግን ይሄ ለሳይንቲስቱ ብቻ ሳይሆን ለአማኞቹም ይሰራል። በቤተ-መቅደሳቸው የሚሰሩትን ታአምራት… ወደ ህዝብ አደባባይ ወስደው በገበያና በፓርላማ ጉባዔ ላይ ማከናወን ከሆነ ፍላጎታቸው… ቁጥብነታቸውን እንደሳቱና በተቃራኒ አቅጣጫ መንፈሳዊ አንባገነን ለመሆን እየተንቀሳቀሱ እንደሆነ… ሁሌም ባይሆን አንዳንድ ጊዜ ቢታወሳቸው፣ ጭፍን መሆናቸው በማስተዋል ሊለወጥ ይችላል፡፡
ፌስቡክ ላይ የሚጽፍ አንድ ወጣት፣ እኔ ሳወራው ከቆየሁት ሀሳብ ጋር ባልተገናኙ ጉዳዮች ላይ አንድ አባባል ሰሞኑን አስፍሮ ነበር፡፡ እኔም ድንገት አባባሉ ለዚህ አውድ እንደሚመጥን ተሰማኝና ልገለገልበት አሰብኩ፡፡ አባባሉ “ያ ሌላ ይኼ ሌላ” የሚል ነው፡፡
ስለ አውድ ባህርይ ማሰብ ስፈልግና በአውዶች መሀል ያለው እንዳይጣስ … ቁጥብነት እንዳለ መቀጠል እንደሚገባው ለማስረገጥ ስፈልግ፣ “ያ ሌላ ይኼ ሌላ” የሚለውን አባባል ደጋግሜ ማስታወስ ይኖርብኛል፡፡

Read 2062 times