Print this page
Saturday, 17 February 2018 15:00

7ኛው የሃዋሳ የግማሽ ማራቶንና ሌሎች ተያያዥ ሁኔታዎች

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(1 Vote)

  • ለአትሌቶች በአገር ውስጥ የውድድር እድል የምንፈጥርበት፤ የስፖርት ቱሪዝምን የምናጠናክርበት ነው፡፡ - አቶ ኤርሚያ አየለ የታላቁ
    ሩጫ በኢትዮጵያ ዋና ስራ አስኪያጅ
   • ውድድሩን በንፁህ ከተማ ማስተናገዳችሁ ይደነቃል፡፡ - የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት ኃይሌ ገብረስላሴ
   • የሃዋሳን ሐይቅ የሚያካልለው የመሮጫ ጎዳናና የከተማዋ ነፋሻ አየርና ንፁህ ጎዳናዎች አስደስተውኛል፡፡ እንግሊዛዊው ቶማስ ቦንድ
   • ግማሽ ማራቶኑን ለማሳደግ ስፖንሰርሺፕ ያስፈልጋል፤ የመሮጫ ጎዳናው ልኬት ዓለም አቀፍ ደረጃውን ጠብቆ በየዓመቱ ይካሄዳል፤        ባህርዳር፣ አዳማና ድሬዳዋ ግማሽ ማራቶን ማዘጋጀት ይችላሉ፡፡ - የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የኤቨንትና ኦፕሬሽን ስራ አስኪያጅ     የሆነው ዳግም ተሾመ

    ባለፈው ሳምንት 7ኛው የሃዋሳ የግማሽ ማራቶን በታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ አዘጋጅነት በሃዋሳ ከተማ ተካሂዶ ነበር፡፡ ውድድሩ ዓለም አቀፍ ደረጃውን በማሟላት እያደገ እንዲቀጥል፤ ከዓለማችን ምርጥ ግማሽ ማራቶኖች ተርታ እንዲሰለፍ፤ በርካታ አገራትን የሚወከሉ አትሌቶች በብዛት እንዲሳተፉበት እና ለምርጥና ታላላቅ አትሌቶች ጥሩ የተሳትፎ ክፍያ እና ማራኪ የሽልማት ገንዘብ በማቅረብ እንዲጠናከር ግን የባለድርሻ አካላት ትኩረት ያስፈልገዋል፡፡
ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የግማሽ ማራቶኑን ለ5 ዓመታት ካካሄደ በኋላ በ2007 እና በ2008 ዓ.ም ላይ አቋርጦት የነበረ ሲሆን ባለፈው አመት የሃዋሳ ከተማ መስተዳድር ባቀረበው ልዩ ጥያቄ መሰረት መልሶ ከጀመረው በኋላ  ዘንድሮ በልዩ ትኩረት እንዲቀጥል አድርጓል፡፡ የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ኤርሚያስ አየለ እንደተናገረው ውድድሩ ለአትሌቶች በአገር ውስጥ የውድድር እድል መፍጠር የሚቻልበትና የስፖርት ቱሪዝሙን የሚያጠናክር ነው፡፡ ዘንድሮ የግማሽ ማራቶኑ አብይ ስፖንሰር ከሆነው ታል ጋርመንት እና ሌሎች የታላቁ ሩጫ አጋሮች ጋር በእነዚህ አቅጣጫዎች በቅርበት እየሰራን እንቀጥላለንም ብሏል፡፡  ታል ጋርመንት በሃዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ከሚንቀሳቀሱ ግዙፍ ኩባንያዎች አንዱና በጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪው ከ70 ዓመታት በላይ ልምድ ያለው ኩባንያ ሲሆን፤ የግማሽ ማራቶኑን በአብይ ስፖንሰርነት ለመደገፍ የ3 ዓመት ውል ፈፅሟል፡፡ የሃዋሳ መስተዳድር፤ አርኪ ውሃ፤ አይዋፕ እና ሃይሌ ሪዞርት ሌሎች የውድድሩ አጋሮች  ነበሩ፡፡ የሃዋሳ ከተማ መስተዳር ውድድሩን በንፁህ ከተማ ለማስተናገድ መቻሉን ያደነቀው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳት ኃይሌ ገብረስላሴ፤ በ7ኛው የሃዋሳ ግማሽ ማራቶን  ‹‹የሃዋሳን ሐይቅ እንጠብቅ›› በሚል መርህ 50 ድርጅቶችን በማስተባበር መካሄዱን በመጥቀስ የከተማዋን ቱሪዝም በማነቃቃት በምንጫወተው ሚና የከተማው መስተዳድር፤ ነዋሪዎች፤ ተሳታፊዎች ለሚያደርጉት ድጋፍ አመሰግናለሁ ብሏል። በሃዋሳ የግማሽ ማራቶን ውድድር ላይ ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚኖሩ የውጭ ዜጎች በተጨማሪ ከዩጋንዳ፤ ከአሜሪካ፤ ከተባበሩት አረብ ኢምሬትስ፤ ከእስራኤል፤ ከጃፓን፤ ከፈረንሳይና ከአውስትራሊያ ተሳታፊዎች መምጣታቸው ለከተማዋ  ልዩ ድምቀት የፈጠረ ነበር። ከአትሌቶች ውጭ ስፖርተኞችን ባሳተፈው ውድድር ላይ  ለመጀመርያ ጊዜ የሮጠውና በ3ኛ ደረጃ አጠናቆ የነሐስ ሜዳልያ የተጎናፀፈው እንግሊዛዊው ቶማስ ቦንድ በተሳፎው በጣም መደሰቱን ይናገራል። ለስፖርት አድማስ በሰጠው አስተያየት፤ ግማሽ ማራቶኑ የሃዋሳን ሐይቅ የሚያካልለው የመሮጫ ጎዳና፤ የከተማዋ ነፋሻ አየርና ንፁህ ጎዳናዎች እንዳደሰቱት ተናግሯል። በምስራቅ አፍሪካ በኬንያ፤ ታዛኒያና ኡጋንዳ ላይ በተካሄዱ የግማሽ ማራቶን በመሮጥ ካለው ልምድ በመነሳትም  ቶማስ ቦንድ ሲናገር፤ የሃዋሳ ግማሽ ማራቶን በተሳታፊዎቹ ብዛት ከፍተኛ እድገት የሚያሳበት አቅም መኖሩን መስክሯል፡፡
በ7ኛው የሃዋሳ የግማሽ ማራቶንና በ7 ኪሜትር የውድድር መደቦች ላይ በአጠቃላይ ከ3ሺ በላይ ስፖርተኞችን ተሳታፊዎች ነበሩ፡፡ በዋና የግማሽ ማራቶን ውድድር  ከ120 በላይ አትሌቶች ተሳትፈው በወንዶች ምድብ  የኦሮሚያ ማርሚያ ቤቶች የስፖርት ክለብ አትሌት የሆነው ሲሳይ ያለው በ1፡03.12 ሲያሸንፍ፤ በሴቶች ምድብ ደግሞ በግል የተወዳደረችው ጌጤ አለማየሁ በ1፡19.34 ጊዜ አሸንፋለች፡፡ በህዝብ አሳታፊው የ7 ኪሜ የጎዳና ላይ ሩጫው በክልሉ የሚገኙ 100 አትሌቶች የተሳተፉ ሲሆን በወንዶች የኤሌክትሪክ ክለብ አትሌት ቢራ ሰቦቃ ሲያሸንፍ፤ በሴቶች ምድብ ደግሞ ሰዓዳ ከድር ከቤተል ክለብ ድል ቀንቷታል፡፡  
የሃዋሳን ግማሽ ማራቶንን ለማሳደግ
የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የኤቨንትና ኦፕሬሽን ስራ አስኪያጅ የሆነው ዳግም ተሾመ  በዚህ ሃላፊነቱ የውድድሩን አጠቃላይ ሂደት ከእቅድ አንስቶ እስከ አፈፃፀም ይከታተላል፡፡ የውድድሩ መነሻና መድረሻን ለአትሌቶች እና ለተሳታፊ ስፖርተኞች እንዲመች ያዘጋጃል፤ የእንግዶች የተመልካቾችና የፀጥታና ጥበቃ ሃይሎችን በየተመደበላቸው ስፍራዎች ላይ መገኘታቸውን ይቆጣጠራል፡፡ የውድድሩን አዘጋጆች ቡድን በማስተባበር ይንቀሳቀሳል፡፡ ዳግም ተሾመ ለስፖርት አድማስ እንደሚናገረው የኢቨንት እና የኦፕሬሽን  ባለሙያ ዋና ስራው የተዘጋጀውን ውድድር ዓለም አቀፍ ደረጃና  ስኬታማነት ማረጋገጥ ነው፡፡ ለሃዋሳው የግማሽ ማራቶንና ለሌሎች የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ውድድሮች ከሚደረጉ ዝግጅቶች አንዱና ዋንኛው የመሮጫ ጎዳና ልኬት መሆኑን ለስፖርት አድማስ ሲያስረዳ፤_ ውድድሮች በትክክል ተለክተውና በሚመለከተው አካል በተረጋገገጠ የመሮጫ ጎዳና ላይ እንዲካሄዱ ማድረግ ወሳኝ በመሆኑ በዚህ ሙያ ላይ ተጨማሪ ትኩረት ሰጥቼ እየሰራሁበት ነው ይላል፡፡ የመሮጫ ጎዳናን የልኬት እና አጠቃላይ የውድድር ዝግጅትና የኦፕሬሽን ስራ በብቃት ለማከናወን ሲልም በብራይተን ማራቶን እንዲሁም በአሜሪካ ግማሽ ማራቶንና ማራቶን አጣምሮ በሚያካሂዱ ዓለም አቀፍ የጎዳና ላይ ሩጫዎች ላይ በበጎ ፈቃድ አገልጋይነት ከአዘጋጆቹ ጋር ለመስራት ችሏል፡፡ በተለይ ግን ከዓመት በፊት በህንድ ባንግሎር በተካሄደ የግማሽ ማራቶን ቅድመ ዝግጅት ላይ የዓለም አቀፉ የጎዳና ላይ ሩጫዎች ማህበር AIMS የልኬት ባለሙያ በሆነው ታዋቂው እንግሊዛዊው ሂው ጆንስ ስለመሮጫ ጎዳና አለካካክ የወሰደው ስልጠና የሚጠቀስ ይሆናል።  እንግሊዛዊው ሂው ጆንስ የቀድሞ ማራቶን ሯጭ ሲሆን፤ በጎዳና ላይ ሩጫዎች የመሮጫ ጎዳና ልኬት ዙርያ ከሚሰሩ ጥቂት ዓለም  አቀፍ ባለሙያዎች አንዱ ነው፡፡ በኢትዮጵያ በዚህ ሙያ በመስራት ከፍተኛ ልምድ ያለው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን ባለሙያ የሆነው አቶ ተሾመ በቀለ ሲሆን የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ዋና ስራ አስኪያጅ ኤርሚያ አየለ በዚህ ሙያ የሰለጠነ ነው፡፡
የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የኤቨንትና ኦፕሬሽን ስራ አስኪያጅ የሆነው ዳግም ተሾመ እንደሚያስረዳው የመሮጫ ጎዳና ላይ ልኬት ብዙዎች እንደሚገምቱት በመኪና ተዟዙሮ ኪሎሜትሮችን በመቁጠር የሚወሰን አይደለም፤ ልኬቱ ዓለም አቀፍ ፈቃድ እና የሙያ ብቃት ባለው ባለሙያ የሚሰራ፤ የጎዳናው ልኬትም በብስክሌት የፊት ጎማ ላይ ታስሮ በስንት ሽክርክሪት? ስንት ኪሎሜትር እንደሚሸፍን? በሚቆጥር ‹‹ጆንስ ካውንተር›› ከዚያም በተለያዩ ቀመሮችና ስሌቶች ተረጋግጦ የሚወሰን ነው፡፡ በልኬት ሙያው ላይ የሚሰራ ባለሙያ እንደ ሯጭ እያሰበ፤ ሯጩ ሊሮጥበት የሚችለውን ሂደት እየገመተ መንገዱን ይለካል የሚለው ዳግም ስራው ሲጠናቀቅ ውጤቱ ከመሮጫው ጎዳና ካርታ ጋር ወደ የዓለም አቀፉ የጎዳና ላይ ሩጫዎች ማህበር ተልኮ ሲፀድቅ ብቻ ውድድሩን ለማካሄድ ይቻላል ብሏል፡፡ የጎዳና ላይ ሩጫዎች የመሮጫ ጎዳናዎች ልኬት በተለያዩ ምክንያቶች በየዓመቱ መካሄድ ያለበት ሲሆን፤ የዓለም አቀፉ የጎዳና ላይ ሩጫዎች ማህበር AIMS ከመላው ዓለም የሚደርሱትን ሪፖርቶች በመስፈርቶቹ በመለካትና በባለሙያዎቹ በደንብ መርምሮ ከተመለከተ በኋላ ውድድሮቹን እንዲያካሂዱ ማረጋገጫ ይሰጣል፡፡ የመሮጫ ጎዳናዎች  በየዓመቱ በአግባቡና በትክክለኛ ባለሙያ ተለክተው የሚረጋገጡ መሆናቸው በዓለም አቀፉ የጎዳና ላይ ሩጫዎች ማህበር እውቅና ያገኙ እንዲሆኑና የሪከርድ ሰዓቶችን ለማስያዝ እና ለማስመዝገብ የሚጠቅም ይሆናል፡፡ የየውድድሮቹ የተሳትፎና የውጤት መረጃዎች በየትኛውም የዓለም ክፍል እንዲታወቁ ያስችላል፡፡ ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የዓለም አቀፉ የጎዳና ላይ ሩጫዎች ማህበር AIMS አባል እንደመሆኑ በየዓመቱ የሚያካሂዳቸውን ውድድሮች ልኬት በማስፈፀም እያረጋገጠ ይሰራል የሚለው ዳግም ተሾመ፤ የ10 ኪሜ የጎዳና ላይ ሩጫ፤ የሃዋሳ ግማሽ ማራቶንና ቅድሚያ ለሴቶች የ5 ኪሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ ልኬት የሚሰራባቸው ዋና ውድድሮች ቢሆኑም አትሌቶችን በምናሳትፍባቸው ሁሉም ውድድሮች ዓለም አቀፍ ሰርተፍኬቶችን እንቀበላለን ብሏል፡፡
ዳግም ተሾመ ለስፖርት አድማስ በሰጠው አስተያየት የሃዋሳውን ግማሽ ማራቶንና ሌሎች የግማሽ ማራቶንና የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድሮችን ለማሳደግ በዋናነት የሚያስፈልገው የስፖንሰሮች ድጋፍ ሲሆን በውድድሮቹ አጠቃላይ ሂደት ገንዘብ በበቂ ሁኔታ መኖሩ ዓለም አቀፍ  ደረጃን ለመጠበቅ የሚያስችሉ ብዙ ነገሮችን መጨመር ያስችላል፡፡ ስለዚህም በታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የሚዘጋጀው የግማሽ ማራቶን እና የፌደሬሽኑ ውድድሮች በቂ ስፖንሰሮች ሲኖሯቸው በውድድሮች ላይ ዘመናዊ የዶፒንግ ምርመራ ለመትከል፤ ለአትሌቶች የተሳትፎ ክፍያ በመክፈል ተሳትፏቸውን ለማነቃቃት፤ ዳጎስ ያሉ የገንዘብ ሽልማቶችን በማቅረብ ትልልቅ አትሌቶችን ለመሳብ እንዲሁም በመሮጫ ጎዳናዎች ላይ ለተወዳዳሪዎች በቂ የውሃ እና የኤነርጂ መጠጦች ለማቅረብም ያግዛል፡፡ ለተወዳዳሪዎች የሰዓት መቆጣጠርያ ቺፕ ለመግጠም፤ ሰዓት ተሸክሞ ተወዳዳሪዎችን የሚመራ ልዩና ዘመናዊ መኪና ለመመደብ የሚቻልም ይሆናል፡፡ እነዚህን ዓለም አቀፍ የውድድር መስተንግዶ ደረጃዎች በሟሟላት የግማሽ ማራቶን ውድድሮችን በኢትዮጵያ በተሻለ አቅም ማሳደግ እና ማስፋፋት ይቻላል፤ የውጭ አገር ተሳታፊዎችን ብዛት መጨመር ይቻላል፡፡ በስፖርት ቱሪዝም ከፍተኛ ስኬት የሚገኝበትም ይሆናል ብሏል ዳግም ተሾመ። ከስፖንሰሮች ድጋፍ መጠናከር ባሻገር በተሟላ የብቃ ደረጃ ቀደም ብሎ መዘጋጀት፤ የፀጥታና የጥበቃ ስራዎችን በተቀናጀ ሁኔታ ማከናወን፤ የመሮጫ ጎዳናዎች ለውድድር ተዘግተው ለአገልግሎት ክፍት የሚሆኑበትን እቅድ በመዘርጋት እንዲሁም የመሮጫ ጎዳና ላይ ምልክቶችን በብዛት በመስቀል መስራት የግማሽ ማራቶን ውድድሮችን የሚያሳድጉ አሰራሮች ናቸው፡፡
የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የኤቨንትና ኦፕሬሽን ስራ አስኪያጅ የሆነው ዳግም ተሾመ ለስፖርት አድማስ እንደጠቆመው ከሃዋሳ ባሻገር የግማሽ ማራቶንን ማስተናገድ ከሚችሉ የኢትዮጵያ ከተሞች መካከከል ባህርዳ፤ አዳማ እና ድሬዳዋ ዋናዎቹ መሆናቸውን ጠቅሶ ምናልባትም ውድድሩን ለማስፋፋት በእነዚህ ከተሞች ውድድሮችን ማዘጋጀት ያስፈልጋል ብሏል። በተለይ ከሃዋሳ ቀጥሎ በባህርዳ የግማሽ ማራቶን የሚካሄድበት እድል ሰፊ መሆኑን ሲገልፅም፤ ባህርዳር ለጥ ባለና ቀጥተኛ ጎዳናዋ   እንዲሁም በጣና ሃይቅ ዙርያ መሮጥ የሚቻል መሆኑ ተመራጭ ያደርጋታል ሲልም ተናግሯል።
ስለ ግማሽ ማራቶን
ግማሽ ማራቶን ባለፉት 10 ዓመታት በከፍተኛ እድገት ላይ ከሚገኙ የአትሌቲክስ ውድድሮች አንዱ ሲሆን ካለፉት 15 ዓመታት ወዲህ ደግሞ በዓለም ዙርያ ተዘዋውረው የሚወዳደሩ አትሌቶችና የተሳትፎ ብዛት ጨምሯል፡፡የግማሽ ማራቶን ሙሉ ርቀት 21.0975 ኪሜትር ሲሆን 21ኬ, 21.1ኬ ወይም 13.1 ማይሎች ሌሎች የውድድሩ ስያሜዎች ናቸው፡፡ ውድድሩ እንደ ማራቶን ፈታኝ ቢሆንም የልምምድ ጫና እና ዝግጅቱ በተሻለ የሚቀል በመሆኑ ከፕሮፌሽናል አትሌቶች ባሻገር በየትኛውም እድሜ ደረጃ ያሉ ስፖርተኞችን የሚማርክም ነው፡፡
የግማሽ ማራቶን ውድድሮች በሚካሄዱበት ውብ የተፈጥሮ ሁኔታ፤ በታዋቂነታቸውና በአዝናኝነታቸው፤ በተሳታፊዎች ብዛት እና ድምቀት በመወዳደርያ ጎዳናቸው አመቺነት ምርጥ መሆናቸው ይለካል፡፡በአሜሪካ ከ500 በላይ የግማሽ ማራቶን ውድድሮች የሚካሄዱ ሲሆን  የኒውዮርክ፤ የዩጂን፤ የሪችሞንድ፤ የባልቲሞር፤ የአትላንታ እና የቺካጎ ግማሽ ማራቶኖች ዋናዎቹ ተጠቃሾች ናቸው፡፡ ፓሪስና ላ ቻምፒዮንሴ በፈረንሳይ፤ ቫንኮቨር በካናዳ፤ ፖላር ናይት በኖርዌይ፤ ቤርሙዳ በቤርሙዳ፤ ኪሊማንጃሮ በታንዛኒያ፤ ኢየሩሳሌም በእስራኤል፤ ታሂቲ ሙዌራ  በሙዌራ ደሴት፤ ግሬት ዎል በቻይና የሚከናወኑ እውቅ የግማሽ ማራቶን ውድድሮች ናቸው፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ደረጃ ካላቸው የግማሽ ማራቶኖች መካከል ከ54000 በላይ ተሳታፊዎች ያሉት ግሬት ኖርዝ ራን ይጠቀሳል፡፡ በእንግሊዝ ኒውካስትል በየዓመቱ የሚካሄደው ‹ግሬት ኖርዝ ራን› ላይ የዓለማችን ምርጥ የረጅም ርቀት ሯጮች ከባድ ትንቅንቅ የሚያደርጉበት ሆኖ ይታወቃል፡፡ የዓለማችን ግዙፍ ማራቶን ሆኖ ለመጀመርያ ጊዜ የተመዘገበው በ2014 እኤአ በስዊድን የተካሄደው ጎቴቦርግስቫርቬት ግማሽ ማራቶን ሲሆን 64288 ተሳትፈውበት 47491 ጨርሰዋል፡፡
የዓለም ግማሽ ማራቶን ሪከርዶችና ፈጣን ሰዓቶች
የዓለም ግማሽ ማራቶን ሪከርዶችና የምንግዜም ፈጣን ሰዓቶች  ዝርዝር ላይ በሁለቱም ፆታዎች የኬንያውያን የበላይነት የሚስተዋል ቢሆንም፤ በወንዶች የኤርትራ እንዲሁም በሴቶች የኢትዮጵያ አትሌቶች የቅርብ ተፎካካሪዎች ናቸው፡፡  በአሁኑ ወቅት የዓለም ግማሽ ማራቶን ሪከርድ በወንዶች ምድብ  በኤርትራዊው ዘረሰናይ ታደሰ 58:23 በሆነ ጊዜ  በ2010 እኤአ በሊዝበን ግማሽ ማራቶን ፖርቱጋል ላይ እንዲሁም በሴቶች ደግሞ በኬንያዊቷ ጆይሲሊን ጄፕኮሴጌ በ1:04:51 በሆነ ጊዜ 2017 እኤአ በፕራግ ግማሽ ማራቶን ቼክ ሪፖብ. ላይ የተመዘገቡ ናቸው፡፡
የኢትዮጵያ የግማሽ ማራቶን ሪከርዶች በወንዶች ምድብ አፀደ ፀጋዬ በ2012 እኤአ ላይ በቼክ ፕራግ በ58፡47 ያስመዘገበው ሲሆን በዓለም የግማሽ ማራቶን የፈጣን ሰዓቶች ደረጃ ላይ 7ኛ ነው፡፡ በሴቶች ደግሞ ለሪከርድ ፈቃድ በሌለው የመሮጫ ጎዳና መሰረት ደፋር ፈጣኑን ሰዓት በ2013 በኒውካስትል በ66፡09 ብታስመዘግብም የኢትዮጵያ ሪከርድ ሆኖ የሚመዘገበው ወርቅነሽ ድጋፌ በ2014 እኤአ በቼክ ፕራግ ያስመዘገበችው 66፡14 የሆነ ጊዜ ሲሆን በምንግዜም ፈጣን ሰዓቶች ደረጃ 21ኛ ላይ ተቀምጧል፡፡
በግማሽ ማራቶን የምንግዜም ፈጣን ሰዓቶች የደረጃ ዝርዝር በሁለቱም ፆታዎች የኬንያ አትሌቶች ፈጣን ሰዓቶች እና የውጤት የበላይነት ቢኖርም የቅርብ ተፎካካሪዎች በተለይ የኢትዮጵያ እንዲሁም ጥቂት የኤርትራ አትሌቶች ናቸው፡፡ የአውሮፓ እና የሰሜን አፍሪካ አትሌቶች በጠንካራ ተሳትፏቸው የሚጠቀሱም ናቸው፡፡ በወንዶች የግማሽ ማራቶን የምንግዜም ፈጣን ሰዓቶች ደረጃ ላይ ከ1 እስከ 10ኛ ደረጃ ያሉት የኬንያ አትሌቶች ናቸው፡፡  ይሁንና በፈጣን ሰዓት መሪው የዓለም ሪከርድ የያዘው ዘረሰናይ ታደሰን ሲሆን የሚፎካከሩት ኬንያውያንና ለባህሬን ዜግነቱን ቀይሮ የሚወዳደር ሌላው ኬንያዊ ቢሆንም በ2012 እኤአ ላይ በፕራግ 58፡47 ሰዓትን ያስመዘገበው አፀዱ ፀጋዬ በ7ኛ ደረጃ ተቀምጧል፡፡ በወንዶች ምድብ ከ1 ሰዓት በታች ግማሽ ማራቶንን በመጨረስ ከሚጠቀሱ 21 አትሌቶች 18 ኬንያውያን ሲሆን ኢትዮጵያውያን 2 እንዲሁም አንድ እንግሊዛዊናቸው፡፡ በ2014 እኤአ አምስት፤ በ2015 እኤአ 2 የኢትዮጵያ አትሌቶች ከአንድ ሰዓት በታች ግማሽ ማራቶንን  ገብተዋል፡፡ በሴቶች ምድብ  ከ68 ደቂቃዎች በታች የሚገቡ 13 ኬንያውያን ሲመዘገቡ 5 ደግሞ የኢትዮጵያ ናቸው፡፡
የግማሽ ማራቶኖችና
የጎዳና ላይ ሩጫዎች ደረጃ አሰጣጥ
ዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌደሬሽኖች ማህበር ለጎዳና ላይ ሩጫዎች የወርቅ፤ ብርና የነሐስ ሜዳልያዎችን መስጠት የጀመረው ከ2008 እኤአ ወዲህ ሲሆን፤ በየዓመቱ ባወጣቸው መስፈርቶች መሰረት ደረጃዎቹን በዓለም ዙርያ ለሚያመለክቱ የውድድር አዘጋጆች ይሰጣል፡፡ ሁሉም ደረጃዎች ከ5 አገራ ምርጥ አትሌቶች ተሳፎ፤ የመሮጫ ጎዳናው በኤይምስ ተለክቶ የተረጋገገጠ፤ ለተሳታፊዎች የኤሌክትሮኒክ ሰዓት አያያ የሚተገበርበት፤ የዶፒንግ ምርመራ የሚካሄድበት፤ (AIMS) የዓለም አቀፍ ማራቶኖችና የጎዳና ላይ ሩጫዎች ማህበር በማራቶኖች ሊግ የሚካሄዱትን 6 ትልልቅ ማራቶኖች ግንባር ቀደም ደረጃ ይሰጣቸዋል፡፡ የወርቅ ደረጃ ላይ የታላቸውን 10 የጎዳና ሩጫዎች ግበማስመዝገብ ጃፓን ግንባር ቀደም ስትሆን እያንዳንዳቸው እኩል 5 የጎዳና ላይ ሩጫዎች በወርቅ ደረጃ በማስመዝገብ አሜሪካ እና ቼክ ሪፖብሊክ ይጠቀሳሉ፡፡ በአፍሪካ አህጉር የአይኤኤኤፍ የጎዳና ላይ ሩጫ ደረጃ የተሰጣቸው 3 የጎዳና ላይ ሩጫዎች ናቸው፡፡
የዓለም ግማሽ ማራቶን ሻምፒዮና እና ኢትዮጵያ
ግማሽ ማራቶን በኦሎምፒክ እና በዓለም አተሌቲክ ሻምፒዮና ላይ የሚካተት የውድድር መደብ ባሆንም የዓለም የግማሽ ማራቶን ሻምፒዮና በሚል ስያሜ በ1992 እኤአ ተመስርቶ በየዓመቱ በአይኤኤፍ እየተዘጋጀ ለ13 ዓመታት እስከ 2005 እኤአ ተካሂዷል፡፡ በ2006  እኤአ ላይ በዴብራካን ሃንጋሪ የግማሽ ማራቶን ውድድሩ በ20 ኪሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ ተቀይሮ የዓለም የጎዳና ላይ ሩጫ በሚል ስያሜ እስከ 2008 እኤአ ተካሄደ፡፡ ከዚያ ከ2010 እኤአ ላይ የዓለም ግማሽ ማራቶን ሻምፒዮን የሚል ስያሜውን መልሶ በየሁለት ዓመቱ በአይኤኤኤፍ የሚካሄድ ሆኗል፡፡ የዓለም ግማሽ ማራቶን በ2010 እኤአ  በበርሚንጋም እንግሊዝ፤ በ2010 በናኒንግ ቻይና፤ በ2012 እኤአ በካቫቲና ቡልጋያ፤ በ2014 እኤአ በኮፐንሃገን ዴንማርክ እንዲሁም በ2016 እኤአ በካርዲፍ እንግሊዝ ተደርጓል፡፡በዓለም የግማሽ ማራቶን ሻምፒዮና ላይ በሁለቱም ፆታዎች የኬንያ አትሌቶች ያስመዘገቡት ውጤት ከፍትኛ ነው፡፡ በወንዶች ምድብ ኬንያ 12 የወርቅ ሜዳልያዎች ስትሰበስብ፤ ሌላ ከፍተኛ ውጤት የተመዘገበው በኤርትራዊው ዘረሰናይ ታደሰ የተሰበሰቡት 5 የወርቅ ሜዳልያዎች ናቸው፡፡ ከኢትዮጵያ ብቸኛን የወርቅ ሜዳልያ ድል ያስመዘገበው ኃይሌ ገብረስላሴ በ2001 እኤአ በብሪስቶል እንግሊዝ በተደረገበት ወቅት ሲሆን የኢትዮጵያን ሌላ ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገበው በ1991 እና በ2000 እኤአ ሁለት የነሐስ ሜዳልያዎችን እንዲሁም በ2001 እኤ የብር ሜዳልያ የተጎናፀፈው ተስፋዬ ጅፋር ነው፡፡ በ2012 እኤአ ላይ ደሬሳ ጨምሳ የብር እንዲሁም በ2014 እኤአ ጉዬ አዶላ የነሐስ ሜዳልያዎችን አግኝተዋል። በሴቶች ምድብ ደግሞ ከ1997 እኤአ ጀምሮ ኬንያ  የወርቅ ሜዳልያዎችን በማመዝገብ ግንባር ቀደም ናት፡፡ ለኢትዮጵያ ሁለት የወርቅ ሜዳልያዎችን ያገኙት በ2002 እኤአ ብርሃኔ አደሬ እና በ2012 እኤአ መሰረት ሃይሉ ናቸው፡፡ ብርሃኔ ከወርቅ ሜዳልያዋ ባሻገር በ2000 እኤአ የነሐስ እንዲሁም በ2003 እኤአ የብር ሜዳልያዎችን ስታመዘግብ፤ በ2008 እኤአ አሰለፈች መርጊያ የብር፤ በ2009 እኤአ አበሩ ከበደ የነሐስ፤ በ2006 እኤአ ድሬ ቱኔ የብር እንዲሁምበ2012 እኤአ ፈይሴ ታደሰ የብር  ሜዳልያዎችን በዓለም ግማሽ ማራቶን ሻምፒዮናው አግኝተዋል፡፡
23ኛው የዓለም ግማሽ ማራቶን ሻምፒዮና በቫሌንሽያ
በ2018 እኤአ ላይ 23ኛውን የዓለም ግማሽ ማራቶን ሻምፒዮና ከወር  በኋላ የምታስተናግደው የስፔኗ ቫሌንሺያ ከተማ ስትሆን ከዓለማችን ምርጥ የግማሽ ማራቶን አትሌቶች ባሻገር ከ15 በላይ ስፖርተኞችን የሚያሳትፍ ይሆናል፡፡ በ2020 እኤአ ደግሞ 24ኛውን የዓለም የግማሽ ማራቶን ሻምፒዮና የፖላንዷ ጊዲያና ከተማ እንድታዘጋጀው ተመርጣለች፡፡ በዚሁ ሻምፒዮና ላይ የሚካፈለውን የኢትዮጵያ ቡድን ለመምረጥ ከወር በፊት ከአዲስ አበባ 10 ኪሜትር ርቃ በምትገኘው ለገጣፎ ለ11ኛ ጊዜ የግማሽ ማራቶን ውድድር እንደማጣርያ ተካሂዶ ነበር፡፡ አትሌት ጌታነህ ሞላ በወንዶች ምድብ እንዲሁም ዘይነባ ይመር በሴቶች አሸናፊዎች ነበሩ። በዚሁ የግማሽ ማራቶን ከ1 እስከ 6ኛ ደረጃ ያገኙት አትሌቶች በቫሌንሻ 23ኛው የዓለም ግማሽ ማራቶን ኢትዮጵያን በመወከል የሚሳተፉ ሲሆን ያገኙት ደረጃ እና ያመዘገቡት ሰዓት ከዚህ በታች የቀረበው ነው፡፡
በወንዶች
ጌታሁን ሞላ 1:01:25
ቤተአሰፋ ጌታሁን 1:01:33
ዳዊት ፍቃዱ 1:01:44
ጂክሳ ታደሰ 1:02:13
አይቶልኝ ካሰው 1:02:17
አሰፋ ተፈራ 1:02:39

በሴቶች
ዘይነባ ይመር 1:10:24
መሰረት በለጠ 1:10:35
በቀለች ጉደታ 1:11:19
ዝናሽ መኮንን 1:11:27
የሺ ካላዩ 1:11:32
እታፈራሁ ወዳጆ 1:11:39

Read 4387 times