Sunday, 25 February 2018 00:00

ለ40/60 ቤቶች አሉሚኒየም አቅርቦት የወጣው ጨረታ ቅሬታ አስነስቷል

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

 “የወጣው መስፈርት አንድን ግለሰብ ታሳቢ ያደረገ ነው”
       “በ4 ወር እንኳን አንድ ድርጅት በምስራቅ አፍሪካ ያሉም ቢተባበሩ ሥራው አያልቅም”

   የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቁጠባ ቤቶች ልማት ኢንተርፕራይዝ ጥር 1 ቀን 2010 ዓ.ም በአዲስ አበባ በሦስት ሳይቶች የሚገኙ 40/60 ቤቶችን የአሉሙኒየም በርና መስኮት ከነመስታወቱና ከነሙሉ ገጠማ ስራው እንዲሰራለት ያወጣው የ1 ቢሊዮን ብር ጨረታ ሠነድ ቅሬታ አስነስቷል፡፡
በጨረታው ሠነድ ላይ የወጣው መስፈርት ለአንድ ድርጅት የወገነ፣ የወቅቱን የምንዛሬ እጥረት ያላገናዘበና በአጠቃላይ ሌሎች ተፎካካሪ ድርጅቶችን ከጨዋታ ውጭ የሚያደርግ ነው ሲሉ  በአልሙኒየም አስመጭነትና ሥራ ላይ የተሰማሩ ድርጅቶች ቅሬታቸውን ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡
ለአንድ ግለሰብ እንዲመች ሆኖ የተሰናዳው የጨረታ ሠነድ እንኳን በ4 ወር በ4 ዓመት በአንድ ድርጅት ተሰርቶ  ሊያልቅ ቀርቶ በምስራቅ አፍሪካ ያሉ በአልሙኒየም ሥራ ላይ የተሰማሩ ድርጅቶች ቢተባበሩ እንኳን ሥራው እንደማያልቅ ቅሬታ አቅራቢዎቹ ጨምረው ገልፀዋል፡፡
ኢንተርፕራይዙ ባወጣው የጨረታ ሠነድ ተጫራች ድርጅቶች የአልሙኒየም ክምችት (ስቶክ) እንዲኖራቸውና ከኢትዮጵያ ደረጃ መዳቢዎች የተሰጠ የብቃት ማረጋገጫ እንዲያቀርቡ መጠየቁን የገለፁት ድርጅቶቹ ባለው የውጭ ምንዛሪ እጥረት ድርጅቶች ቶሎ ቶሎ እቃውን እያስገቡ ማከማቸት እንደማይችሉ፣ አንድ ዕቃ ታዝዞ እስኪገባ የሚፈጀውን ጊዜ ግምት ውስጥ ሳያስገቡ ሠነዱን በዚህ መልኩ ማዘጋጀታቸው አንድን ድርጅት ለመጥቀም ሆን ብሎ የተሰራ ሴራ ነው ሲሉ ያማርራሉ፡፡
ከደረጃ መዳቢዎች የተሰጠ ሠርተፍኬት አቅርቡ መባሉን በተመለከተም፤ “እኛ እቃውን ከውጭ የምናስመጣ እንደመሆናችን ከኢትዮጵያ ደረጃ መዳቢዎች የሚሰጠን ሠርተፍኬት እንደሌለ ይታወቃል” ያሉት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፤ ከውጭ አገር የሚሰጥ ተመጣጣኝ ሠርተፍኬት እንዲያቀርቡ አለመጠየቃቸውም ሆን ተብሎ ተፎካካሪዎችን ከጨዋታ ውጭ ለማድረግ የተሰራ በመሆኑ ሠነዱን ቢገዙም በጨረታው እንደማይሳተፉ ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡
የጨረታው ሠነድ አንድ ድርጅትን ለመጥቀም ታስቦ ለመውጣቱ ምን ማረጋገጫ አላችሁ በሚል ከአዲስ አድማስ ለተነሳው ጥያቄ፣ ቅሬታ አቅራቢዎቹ ሲመልሱ፣  ታሳቢ የተደረገው ድርጅት ከውጭ በሚመጣ አልሙኒየም ተረፈ ምርት ሪሳይክል እያደረገ የሚያመርት በመሆኑ ክምችትም የኢትዮጵያ ደረጃ መዳቢዎች ሠርተፍኬትም እንዳለው ይታወቃል በአጠቃላይ የታዘዘው የአልሙኒየም አይነትና ቀለም ሳይቀር ለዚሁ ድርጅት የታሰበ ነው ብለዋል፡፡
ከዚህ ቀደምም ከአምስት ዓመታት በፊት በክራውንና በሰንጋ ተራ ለተገነቡ ቤቶች ተመሳሳይ የ1 ቢሊዮን ብር ጨረታ ወጥቶ ይሄው ድርጅት ማሸነፉንና እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ያላጠናቀቀው ሥራ እንደነበር ገልፀው፤ ጭራሽ እነዚህን ቤቶች በአራት ወር (በ120 ቀናት) አንድ ድርጅት በጥራትና በፍጥነት ያጠናቅቃል ማለት ዘበት ነው ብለዋል፡፡
የቁጠባ ቤቶች ልማት ኢንተርፕራይዝ በአራት ወር አልሙኒየም በሮች ከነመስታወታቸው ተገጥመው እንዲጠናቀቁለት ጨረታ ያወጣባቸው ሦስት ሳይቶች ሲሆኑ፤ እነዚህም ሳይት አንድ ቦሌ ቡልቡላ የሚገኝ ሲሆን፤ በዚህ ሳይት 15 ባለ 15 ወለል (G+15)  ቤቶች፣ በሳይት ሁለት ቦሌ በሻሌ 22 ባለ 15 (G+15)፣  15 ባለ 13 ወለል (G+13)፣ 21 ባለ 9 ወለል (G+9) ቤቶች፣ በሳይት ሦስት ደግሞ ቦሌ አያት፡- 16 ባለ 15 ወለል (G+15)፣   34 ባለ 13 ወለል (G+13)፣ 10 ባለ 8 ወለል (G+8) ቤቶች ሲሆኑ እነዚህን ብሎኮች በ120 ቀናት የአልሙኒየም በር ከነመስታወቱ ለመግጠም አልሙኒየሙ በካሬ ተባዝቶ፣ ለ120 ቀናት ሲካፈል ድርጅቱ በቀን 3637 ካሬ ሜትር አልሙኒየም መስራት እንዳለበት የገለፁት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፤ ይህ በህልምም በእውንም የማይታሰብ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ አንድ ጠንካራ የሚባል ድርጅት በቀን ከ30 ካ.ሜ በላይ አልሙኒየም ቆርጦ አስተካክሎ፣ መስታወት ገጥሞና ሠርቶ ማጠናቀቅ እንደማይችል የጠቆሙት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፤ ይሄ በቤት ችግር እየተሰቃየ መቶ ፐርሰንት ከፍሎ በጉጉት ለሚጠብቀው ህዝብ ተጨማሪ መዘግየትን እንደሚፈጥር ገልፀው፤ ኢንተርፕራይዙ እነዚህን ሕገ-ወጥ አሰራሮች በጥሞና ተመልክቶ፣ የጨረታ ሠነዱን እንዲያስተካክል ጠይቀዋል፡፡ ምላሽ የማይሰጣቸው ከሆነም መብታቸውን በህግ እንደሚያስከብሩ ቅሬታ አቅራቢዎቹ ገልፀዋል፡፡  
የቁጠባ ቤቶች ልማት ኢንተርፕራይዝ ኃላፊዎች በጉዳዩ ዙሪያ ምላሽ እንዲሰጡን ላለፉት ሁለት ሳምንታት በተደጋጋሚ ቢሮአቸው ብንመላለስም ኃላፊነት ወስዶ ምላሽ የሚሰጥ ባለመገኘቱ የኢንተርፕራይዙን ሀሳብ ማካተት አልቻልንም፡፡

Read 2135 times