Sunday, 25 February 2018 00:00

በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ክልሎች በፀጥታ ጉዳይ ላይ መግለጫ እንዳይሰጡ ተከለከሉ

Written by  መታሰቢያ ካሣዬ
Rate this item
(3 votes)

 - በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ በማናቸውም ጊዜ ብርበራ ይደረጋል
    - ከኮማንድ ፖስቱ ፈቃድ ውጪ ማንኛውንም ሰልፍና የአደባባይ ስብሰባ ማድረግ ተከልክሏል
    - ሰዓት እላፊን ተላልፎ በተገኘ ሰው ላይ እርምጃ ይወስድበታል
    - ፅሁፎችን በሞባይል፣ በፅሁፍና በማህበራዊ ሚዲያዎች መለዋወጥ ተከልክሏል
      
    በአገሪቱ የፀጥታ ጉዳዮች ላይ ከኮማንድ ፖስቱ አውቅና ፈቃድ ውጪ ክልሎች ለህዝብ ይፋ የሚሆን መግለጫ መስጠት እንደማይችሉ ተገለፀ፡፡
መንግስት ሰሞኑን ይፋ ያደረገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መመሪያ እንደሚያመላክተው፤ የአገሪቱን የፀጥታ ጉዳይ የተመለከቱ ጉዳዩች ላይ ኮማንድ ፖስቱ ከሚያወጣውና ከሚሰጠው መግለጫ ውጪ ማንኛውም የክልል አካል ወይም ሃይል ለህዝብ ይፋ የሚሆን መግለጫ መስጠት አይችልም፡፡
አዋጁ በማንኛውም የአገሪቱ ክፍሎች የተከለከሉ ተግባራት በሚል ባወጣው የማስፈፀሚያ መመሪያ ላይ እንደተገለፀው፤ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁንና አዋጁን ለማስፈፀም የወጡ መመሪያዎችን ማደናቀፍ፣ በማጥላላትና በመቃወም ላይ ያተኮሩ መረጃዎችን ማሰራጨት ተከልክሏል፡፡ ማናቸውንም ስለት ነክ ነገሮችና የጦር መሳሪያዎችን ወደ ገበያ፣ የሃይማኖት ተቋማት ወይም ወደ ማናቸውም ህዝብ ወደ ተሰበሰበበት ቦታ ይዞ መግባትም በጥብቃ ተከልክሏል፡፡
ከኮማንድ ፖስቱ ፈቃድ ውጪ ማናቸውንም ሰልፍና የአደባባይ ስብሰባ ማድረግ፣ በትምህርት ተቋማት አድማ ማድረግ፣ የትምህርት ተቋማትን መዝጋት፣ በስፖርት ማዘውተሪያዎች ውስጥ ከስፖርት ተግባራት ውጪ የሆኑ ሁከቶችንና ብጥብጦችን መፍጠር በአዋጁ የተከለከለ ተግባር ነው፡፡
በህዝቦች መካከል ሁከትና ብጥብጥ መፍጠር፣ አድማና ህገወጥ ተግባራት እንዲፈፀሙ ማነሳሳት፣ የቅስቀሳ ፅሁፎችን በተለያዩ መንገዶች ማሰራጨት ማሳተም፣ በምልክት መግለፅ ወይም መልዕክትን በሌላ በማናቸውም መንገዶች ማስተላለፍ፣ ተከልክሏል፡፡ ፈቃድ ሣይኖር ማንኛውንም ህትመት ወደ አገር ውስጥ ማስገባት ወይም ወደ ውጪ አገር መላክ፣ በሞባይል፣ በፅሁፍ በቴሌቭዥን፣ በሬዲዮ፣ በማህበራዊ ሚዲያ ወይም ሌሎች የግንኙነት ዘዴዎች መለዋወጥ የተከለከሉ ተግባራት ናቸው። ባህላዊ፣ ህዝባዊ ፣ ሃይማኖታዊና ብሔራዊ በዓላትን በማንኛውም ሁኔታ ማወክ ፣ ማደናቀፍ ወይም ከበዓሉ ጋር የማይገናኙ ድርጊቶችንና መፈክሮችን በማንኛውም መንገድ ማስተጋባት፣ የበዓሉ ተሣታፊዎች ላይ የሃይል ድርጊት ወይም ዛቻ መፈፀም፣ በህዝቦች መካከል መቃቃርና መጠራጠርን እንዲሁም ስጋትን የሚፈጥሩ ፣ ሁከትና ብጥብጥን የሚያነሣሱ ቅስቀሣዎችን ማድረግ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ተከልክሏል፡፡
በአሸባሪነት ከተፈረጁ ድርጅቶች፣ አመራር አካላትና ጸረ-ሰላም ቡድኖች ጋር ማናቸውንም ግንኙነት ማድረግ፣ የአሸባሪ ድርጅቶችን አላማ ማስፈጸም፣ ጹሁፎችን መያዝ፣ ማስተዋወቅ የትራንስፖርት እንቅስቃሴዎችን ማወክ፣ የመንገድ ሀዲድ መዝጋትና መሰል እንቅስቃሴዎችን ማድረግ፣ ከታሪፍ በላይ ማስከፈል በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከተከለከሉ ተግባራት መካከል የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
አዋጁ በተወሰኑ የአገሪቱ አካባቢዎች እንዳይፈጸሙ ከከለከላቸው ተግባራት መካከል ሁከትና ብጥብጥን በማስነሣት የሚጠረጠሩ ሰዎችን ወይም ቡድኖችን ወደ ተወሰነ አካባቢ እንዲመጡ ማድረግ፣ ወደተዘጋ መንገድ ወይም ወደተከለከለ አካባቢ ኮማንድ ፖስቱ ያስቀመጠውን እገዳ መተላለፍ የሚሉት ይገኙበታል፡፡
ማንኛውም ቤት አከራይ ወይም ድርጅት የተከራዩን ዝርዝር መረጃ በ24 ሰዓት ውስጥ ለፖሊስ አካል የማሣወቅ ግዴታ አለበት፡፡
በአዋጁ የተቀመጡ ክልከላዎችን ተላልፎ የተገኘ ሰው፤ ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ በቁጥጥር ስር ማዋል አዋጁ እስከሚያበቃ ድረስም ኮማንድ ፖስቱ በሚወሰነው ስፍራ እንዲቆይ ማድረግ ይችላል፡፡ ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ በማናቸውም ጊዜ ብርበራ ማድረግ ተብሏል፡፡
በትምህርት ተቋማት ላይ ሁከትና ረብሻ በሚያስነሱ ተማሪዎችና ሠራተኞች ላይ ህጋዊ እርምት መውሰድ፣ አስተዳደራዊ እርምጃ እንዲወሰድ ለተቋማት ትዕዛዝ መስጠት ይችላሉ፡፡
በትምህርት ቤቶች፣ ዩኒቨርሲቲዎች በሌሎች ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ አድማ የሚያደርጉ ሰዎችን ለመያዝና ለማስቆም፣ የህግ አስከባሪ ኃያላት በእነዚህ ተቋማት ውስጥ በመግባት አስፈላጊውን እርምጃ መውሰድ ይችላሉ፡፡ እንዲሁም በሌሎች የግልና የመንግስት ተቋማት ውስጥ አድማ የሚያደርጉ ሰዎች ለመያዝና ሰላምና ፀጥታን ለማረጋገጥ፣ የህግ አስከባሪ አባላት በእነዚህ ተቋማት ውስጥ መግባት አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ  በተቋማቱ ውስጥ መቆየት ይችላሉ፡፡
የሰአት እላፊን በተመለከተ የወጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መመሪያ እንደሚያመለክተው፤ የልማት አውታሮች፣ መሰረት ልማትና የኢንቨስትመንተ ተቋማት፣ በፋብሪካዎች በመሰል የልማት ተቋማት ወይም በመኖሪያ አካባቢ ኮማንድ ፖስቱ በሚወስነው ጊዜ ከተፈቀደለት ሰዓት በስተቀር መንቀሳቀስ ክልክል ነው፡፡ በተከለከሉ ቦታዎች ላይ ሰዓት እላፊውን ተላልፎ የተገኘ ማንኛውም ሰው ላይ እርምጃ እንዲወስድ ታዟል፡፡

Read 2537 times