Sunday, 25 February 2018 00:00

ጎንደርና ወልቂጤ ከአድማ ወደ መደበኛ እንቅስቃሴ ተመልሰዋል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

    ከአድማ ጋር ተያይዞ በወልቂጤ ወጣቶች ታስረዋል

    የንግድና የትራንስፖርት አድማ ሲካሄድባቸው የሰነበቱት የጉራጌ ዞኗ ዋና ከተማ ወልቂጤና ጎንደር፣ከትናንት በስቲያ ጀምሮ ወደ መደበኛ እንቅስቃሴያቸው የተመለሱ ሲሆን በወልቂጤ ከአድማው ጋር ተያይዞ በርካቶች መታሰራቸውን ምንጮች ጠቁመዋል፡፡
በወልቂጤ በህዝብ ከተነሳው የልማት ጥያቄ ጋር ተያይዞ “ጥያቄያችን አፋጣኝ ምላሽ እያገኘ አይደለም” በሚል የከተማዋ ነዋሪዎች ለ7 ቀናት የንግድ ተአቅቦ አድማ ያደረጉ ሲሆን ከፖሊስ ጋር በተፈጠረ ግጭትም የሰው ህይወት መጥፋቱ ታውቋል፡፡
አድማው በመጀመሪያ ለሶስት ቀናት ብቻ እንዲቆይ የተጠራ ቢሆንም የሰው ህይወት መጥፋቱን ተከትሎ  ለተጨማሪ 4 ቀናት መቀጠሉን  ምንጮች ተናግረዋል፡፡ ከትናንት በስቲያ ሐሙስ የከተማዋ ምንጮች ለአዲስ አድማስ እንደገለፁት፤አብዛኞቹ በአድማ ላይ የሰነበቱ ንግድ ቤቶች አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል፡፡
ለችግሩ እልባት ለመስጠት የሀገር ሽማግሌዎች እርቅ ለማካሄድ ቢሞክሩም ሳይሳካ መቅረቱን የጠቆሙት ምንጮች፤ በዚህ ሂደትም በርካታ ወጣቶች መታሰራቸውን ተናግረዋል፡፡  
በሌላ በኩል በጎንደር ከተማ “የታሰሩ ይፈቱ” በሚል ከሰኞ የካቲት 12 እስከ ረቡዕ የካቲት 14  የንግድና ትራንስፖርት ማቆም አድማ የተደረገ ሲሆን ከተማዋ ከሐሙስ ጀምሮ ወደ መደበኛ እንቅስቃሴዋ መመለሷን ምንጮች ጠቁመዋል፡፡
የወልቂጤ ከተማ የዞኑን አስተዳደሮች በስልክ አግኝተን ለማነጋገር ያደረግነው ጥረት ባይሳካም የደቡብ ክልላዊ መንግስት የህዝብ ግንኙነት ም/ኃላፊ አቶ ሰመንጉስ ሸኑ፣ታስረዋል የተባሉትን በተመለከተ ለቪኦኤ በሰጡት ምላሽ፤ “የታሰሩት ደረቅ ወንጀል ውስጥ ተሳትፈዋል ተብለው የተጠረጠሩ ናቸው፤እየተጣራ  በጉዳዩ የሌሉበት እየተለቀቁ ነው” ብለዋል፡፡

Read 4470 times