Sunday, 25 February 2018 00:00

“ምቀኞች አያስቀምጡህም!”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(6 votes)

  እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ከጥቂት ጊዜያት በፊት የሆነ ነው፡፡ ልጅቷ ደከም ካለ ቤተሰብ የመጣች ነች… እና ታገባለች፡፡ የአጋጣሚ ሆኖ ባለቤቷ ደግሞ ደህና አቅም ያለው ነው፡፡ ትንሽ ቆይቶ ጤናዋ ላይ መጠነኛ ችግር ይደርስባታል፡፡ “ይኸው!” ተባለ፡፡ “ይኸው ምቀኞች አንድ ነገር አድርገውባት ነው ተባለ፡፡ የጤና ችግሯ ግን ቀደም ያለና ከትዳር በፊት ሁሉ የነበረ ነው። የምር ግን…ኮሚኩ ነገር ምን መሰላችሁ፣ በእሷና በባሏ በኩል አቅምን በተመለከተ ያለው ልዩነት በጣም ሰፊ ስለነበረ “ልታገባ ነው” ሲባል የእሷ ቤተሰብ ነበር “ሰውየው ላይ የሆነ ነገር አድርገውበት ነው” ሲባል የነበረው፡፡
ስሙኝማ….እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…ይሄ ሰው ላይ ‘የሆነ ነገር ማስደረግ፣  ማስቋጠር’ ምናምን የሚባሉት ወሬዎች በጣም አልበዙባችሁም! ሰዋችን እኰ ሌላ ሥራ የሌለው ነው የሚመስለው፡፡ አለ አይደል…መስከረም ላይ ቺስታ ተሁኖ፣ ሚያዝያ ላይ የአራት ሚሊዮን ብር መኪና የሚነዳበት ‘ካልኩሌሽኑ’ ይሄ ነው ይላሉ ሰዎች፡፡
እናላችሁ… የምቀኞችን ነገር በመፍራት ደህና ነገር እንኳን ቢገጥመን ይሄን ያህል ልባችን የማይሞላ ሰዎች አለን፡፡
“ስማ፣ ሎተሪ ቢደርስህ ምን ታደርግበታለህ!”
“ኧረ አይድረሰኝ! ድህነቴ ይሻላኛል፡፡”
“ለምን?”
“ምን ነካህ…ምቀኛውን አልችለውም፡፡ እንኳ ሎተሪ ደርሶኝ እንዲሁም አላስቀምጥ ብለውኛል፡፡”
እናላችሁ… መሶባችን ባዶ ሆኖ፣ ኪሳችን ሸረሪት አድርቶበት እንኳን ምቀኛ እንፈራለን፡፡ ድህነታችንንም የሚመቀኝብን እንዳለ እንፈራለን፡፡ ወዛ ብለን አደባባይ መውጣትን እንፈራለን፡፡
“አንቺ እንዲህ ድምቅ ብሎ መልበስ ምንድነው?”
“ቢያምርብኝ ምን አለበት!”
“ሰው ዓይን ትገቢያለሻ! ዘንድሮ ሰዉ ሁሉ ሌላው ላይ ከማፍጠጥ ውጭ ሌላ ምን ያውቃል! ነግሬሻለሁ፣ ቅርጥፍ አድርገው ነው የሚበሉሽ፡፡”
እናላችሁ… የምቀኛ ዓይን ስለምንፈራ ብዙም እንዲያምርብን አይፈለግም፡፡ የምቀኛ ዓይን ስለምንፈራ ብዙም እንድንታይ አይፈለግም፡፡
መንገድ ላይ የሆነ የአእምሮ በሽተኛ ታያላችሁ። እናማ… አለባበሱ ደህና የሚባል አይነት ይሆንና ምናልባትም አውሎ የሚያገባ ኑሮ እንደነበረው ያስታውቃል፡፡ በነገራችን ላይ… አሁን፣ አሁን ቀደም እንዳለው ጊዜ ብጭቅጫቂ ልብስ እንደሚለብሱት ሳይሆን ጥሩ የሚለብሱ የአእምሮ ችግር ያለባቸው ሰዎች አልበዙባችሁም! እናላችሁ…እንደዛ አይነት ሰው ስታዩ…
“አይ ጊዜ፣ አሁን ይሄን የመሰለ ሰው ምን ሆኖ ነው?” ብላችሁ ትጠይቃላችሁ፡፡
“ምን ያልሆነው ነገር አለ፡ አይ አበሻ! አይ አበሻ!”
“አልገባኝም፡፡”
“ምቀኞች ናቸው አሉ፤ እንጋብዝህ ብለው መጠጥ ውስጥ የሆነ ነገር ከተቱበት፡፡”
“አትለኝም! በዚህ ደረጃ የሚጠሉት ደመኞች ነበሩት እንዴ?”
“ወይ ደመኛ! የገዛ ጓደኞቹ ናቸው፡፡”
“ጓደኞቹ! ምን አደረገን ብለው ነው?”
“ምን ያደርጋቸዋል! ለምን ከእኛ ተሻለ ብለው ነዋ፡ የሚገርምህ እኮ አምስት ነው ሰባት ሚሊዮን ብር የሚያወጣ ቤት ከገዛ ወርም አልሆነው፡፡ አገር ያለን መሰለህ እንዴ!”
ታዲያላችሁ… ስለ እንደዚህ አይነት ሰዎች አሥር አይነት ታሪክ ቢወራ፣ የዘጠኙ ዋናው ታሪክ ‘ምቀኝነት’ ይሆናል፡፡
የሆነ ሰው ጥሩ የሚባል መጽሐፍ ይጽፋል እንበል፡፡
“አንተ፣ ሰውየው እንዴት አይነት አሪፍ መጽሐፍ ነው የጻፈው መሰለህ! እኔ እኮ ይሄን ያህል የስነጽሁፍ ሰው አይመስለኝም ነበር፡፡”
“አሁን እሱ መጽሐፍ ነው! ጉድ እኮ ነው…ዘንድሮ ማንም እየተነሳ ጸሃፊ ነኝ ይላል፡፡”
“እና ምን ልትል ነው? እኔ በበኩሌ በጣም ነው የወደድኩት፡፡”
“ለነገሩማ እንዴት እንደጻፈው የማናውቅ መሰለህ፡፡”
“እንዴት እንደጻፈው ስትል…”
“ገልብጦ ነዋ!”
“ከምንድነው የሚገለብጠው?”
“ከእንግሊዝኛ መጽሐፍ ነዋ! እሱ፣ አይደለም መጽሐፍ፣ ማመልከቻ መጻፍ አይችልም፡፡”
እናላችሁ…እንዲህ አይነት አስቸጋሪ ነገሮች አሉ…አለ አይደል…ከእውነተኛ ትችት ይልቅ የምቁነት የሚመስሉ፡፡ ችግሩ ምን መሰላችሁ…እኛም እንዲህ አይነት ነገር ስንሰማ ገፋ ብለን አንጠይቅም። “ከእንግሊዝኛ መጽሐፍ ገልብጦ ነው” ሲባል፣ ከየትኛው እንግሊዝኛ መጽሐፍ?” ብሎ መጠየቅ አልፈጠረብንም፡፡ “ማስረጃ አምጣና አሳምነኝ” የሚል ሙግት የለም፡፡ እንደውም እኛ ቀጥሎ ለምናገኘው ሰው፣ “ስማ ሰውዬዋ እኮ መጽሐፍ ጻፍኩ ያለችው ከእንግሊዘኛ መጽሐፍ ገልበጣ ነው አሉ” እናላለን፡፡ የምናገኘውም መልስ “እኔም እኮ ጠርጥሬ ነበር” አይነት ይሆናል፡፡
“ስማ… እነ እንትና እኮ ቤት ገዙ”
“እውነት! ኮንዶሚኒየም ነው የገዙት?”
“የምን ኮንዶሚኒየም፤ ምን የመሰለ ቪላ ነው የገዙት፡፡”
“አዬ፣ አለቀላቸው በለኛ!”
“እንዴት ነው የሚያልቅላቸው! ቪላ ቤት ገዙ ነው እኮ ያልኩህ!”
“እኮ፣ ምን አለ በለኝ፣ ምቀኛ አያስቀምጣቸውም።”
እናላችሁ…የምቀኝነት ነገር የህይወታችን ትልቅ አካል ሆኗል፡፡
እናማ…ዘመኑ የግድ “እዚህ ነኝ” ማለት የሚያስፈልግበት ነው፡፡ ጮክ ብሎ “ኧረ እዩኝ” ማለት ያስፈልግ ይሆናል፡፡ ግን ደግሞ እንደዛ እንዳናደርግ…ፍርሀት ይገድበናል፡፡
“እኔ ነግሬያለሁ፣ ኋላ ምቀኞች ዓይን እንዳትገቢ!”
“ታዲያ ሥራዬን ካላስተዋወቅሁ እንዴት አድርጌ ነው የምሠራው፡፡”
“ግዴለሽም አልኩሽ፣ ላንቺ ያለው እንጀራ ደጃፍሽ ድረስ ይመጣልሻል፡፡”
እናላችሁ…የምቀኝነት ነገር የህይወታችን ትልቅ አካል ሆኗል፡፡
ታዲያላችሁ…አስተያየት ስንሰጥ ምቀኝነት እንዳይመስልብን የግድ ቃላቶችን መምረጥ አለብን። ለምሳሌ እሷዬዋ አምሮባት ከሆነ…አለ አይደል… “ዛሬ በጣም ነው ያማረብሽ፣” ማለት ይበቃል። አለበለዛ “ቀሚስሽ ትንሽ ረዘም ብትል ኖሮ”፣ “ደረትሽ ላይ እንዲህ ግልጥ ባይል ኖሮ” አይነት ተጨማሪ አስተያየት በበጎ ላይታይ ይችላል፡፡
“ምቀኛ! ሰው ሲያምርበት ዓይኗ የሚቀላ ምቀኛ!”
እናላችሁ…ሁሉንም አስተያየት ከምቀኝነት ጋር የማያያዝ ነገር…አለ አይደል…ብዙዎቻችን ዘንድ ያለ ነገር ነው፡፡
“አንተ እንዴት ነው እንዲህ ያማረብህ! የኳታር ቢሊየነር ልትመስል ምንም አልቀረህ እኮ!” አይነት አስተያየት እንደ ምቀኝነት ሊቆጠር ይችላላ፡፡ ልክ ነዋ…ካልጠፋ ምሳሌ የኳታር ቢሊየነር ማለትን ምን አመጣው! “የኳታር ቢሊየነር ማለቱ እኮ በእሱ ቤት አሽሙር መናገሩ ነው፡፡ ድሮም አውቀዋለሁ እኮ…የለየለት ምቀኛ! ሰው ሸሚዝ ሲለውጥ እንኳን ደስ አይለውም፡፡”
ሰውየው እኮ አስተያየት የሰጠው ከአንጀቱ ሊሆን ይችላል!
“ሰውየው፤ ጭራሽ የባንክ ደብተርህን ሸሚዝ ኪስህ ፊት ለፊት እያሳየህ ነው የምትሄደው?”
“ምን አለበት፣ ወስደው አያወጡበት!”
“ሰዉ ከፍቷል፣ ደግሞ ገንዘብ አለው ብለው አንድ ነገር ቢያደርጉህስ!”
እናላችሁ…ምቀኛ ስለምንፈራ ብዙ መሥራት ያሉብንን ነገሮች ከመተግበር ወደ ኋላ እንላለን፡፡
እናማ…አለ አይደል…ብዙ ንግግሮቻችንን ከምቀኝነት ጋር ስለምናያይዛቸው፣ በንጹህ ልቦና የተሰጡ አስተያየቶችን እንኳን የምንተረጉማቸው በበጎ አይደለም፡፡
አሀ…አይደለም ግለሰብን አገሮችን ሁሉ በምቀኝነት እንኮንናለን፡፡ “ፈረንጆች የማይወዱን ስለሚመቀኙብን ነው፣” እንል የለ!
ከቤት አልወጣ ብላ ያስቸገረች ዝምብ እንኳን አትታመንም፡፡
“የዘንድሮን ዝምብ ማን ያምናል…ምቀኛ ልኳት ይሆናል፡፡”
እናማ…ከምቀኞች፣ ከመመቀኛኘትና “ምቀኞች አያስቀምጡህም!” ከሚል ፍራቻ ይሰውረንማ!
ደህና ሰንበቱልኝማ!

Read 3379 times