Sunday, 25 February 2018 00:00

የጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ዘመን

Written by  ተፈሪ መኮንን
Rate this item
(3 votes)

 የዛሬዋ ኢትዮጵያ ልዩ ችሎታ ያለው፤ አዲስ ጎዳና ለመከተል የማይፈራ መሪ ትፈልጋለች
               
    አንድ ነገር መነሻ እናድርግ፡፡ በሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ሆነ በተተኪያቸው በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ዘመን የምናያት ኢትዮጵያ ገና ያልተደላደለ እና በመሰራት ላይ ያለ ፌደሬሽን የያዘች ሐገር ናት፡፡ በራሱ በፌደሬሽኑ ቅርጽ ወይም ጠቅላይ ሚኒስትር ሆኖ በሚመራው ሰው ልዩ ባህርይ የተነሳ ሳይሆን፤ መዋቅራዊ ለውጥ በሚያስከትሉ በርካታ ጉዳዮች (ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ) ግፊት ሳቢያ የኢትዮጵያ ፌደሬሽን አዳዲስ ክስተቶችን እያስተናገደ የሚገኝ ይመስለኛል፡፡ ኢትየጵያ የጠበቀው ሲላላ፤ የላላው እየጠበቀባት አሁን አዲስ ባህርይ ለመያዝ ጥረት የምታደርግ ሐገር ሆናለች፡፡
በአንዳንድ አካባቢዎች ለውጡ የአህያ ውሃ ጠጪ ዓመል አለው፡፡ በሌላ አካባቢ ‹‹ጭር ሲል አልወድም›› ያሰኘዋል፡፡ የወደፊቷን ኢትዮጵያ ሁኔታ የሚወስኑ ነገሮች በዘጠኙም የፌደሬሽኑ አባል ክልሎች ውስጥ በ‹‹አህያ ውሃ ጠጪ›› ወይም በ‹‹ጭር ሲል አልወድም›› ዓመል እየተከናወኑ ይመስለኛል፡፡ ለጊዜው የኢትዮጵያን የወደፊት ሁኔታ የሚወስኑ አዳዲስ ክስተቶች በጉልህ የሚታዩት በአራት ክልሎች ነው፡፡ ከአራቱም የሦስቱ ሁኔታ የተለየ ነው፡፡ ከሦስቱም የሁለቱ ጠንከር ይላል። ደግሞ ከሁለቱ የአንደኛው የመሪነት ሚና የሚጫወት ይመስላል፡፡ እነዚህ ክልሎች አንድም - ሦስትም (አራትም) ሆነው ኢትዮጵያን ለለውጥ እየገፋፏት ነው። ቀሪዎቹን ለወሬ እንዲመቸን ዝምተኛ እንበላቸው። እነዚህ ዝምተኛ ክልሎች በአዲሱ የኬሚስትሪ ሂደት ድርሻ ያላቸው አይመስሉም፡፡
ይህን የለውጥ ማዕበል የተመለከቱት ጠቅላይ ሚኒስትራችን፤ በፈቃዳቸው የፓርቲ እና የመንግስት ሥልጣናቸውን ለቅቀዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ያበረከተው የሬዴሬሽናችን አባል ክልል፤ ዝምተኛ ካልኳቸው ክልሎች ውስጥ አንዱ ነው፡፡ ሆኖም ለፌደሬሽኑ መሪ ያበረከተው ይህ ክልል፤ አሁን ለምናየው የለውጥ ሂደት ‹‹ገለል በማለት›› ወሳኝ ሚና መጫወቱን አውቃለሁ፡፡ ገለል ማለትን ከዝምታ መቁጠር የሚቻል ይመስለኛል፡፡ እንደ ቡዲስቶች አነጋገር፤ ‹‹አክሽን ኢን ኢን-አክሽን›› ማለት ግን ይቻላል፡፡
ደቡብ ኢትዮጵያ በዝምታ የሚመራ ነው። ለፌደሬሽኑ አባላት በህብረት መኖርን በተግባር እያስተማረ ያለ ክልል ነው፡፡ ራሳቸው የኢህአዴግ ጎምቱ መሪዎች፤ ‹‹የአዲሲቱ ኢትዮጵያ ተምሣሌት›› ሲሉ ይጠሩታል፡፡ ከ50 በላይ ብሔር ብሔረሰቦችን ይዞ፤ የሥራ ቋንቋውን አማርኛ አድርጎ፤ ከልዩነት ውስጥ አንድነት ፈጥሮ በመኖር ምሳሌ ሆኖ፤ በመናገር ሳይሆን በመኖር የመሪነት ወይም የአብነት ሚና የሚጫወት ክልል ነው፡፡ አቶ ኃይለ ማርያም መኖራቸው ብዙ የሚሰማ መሪ አልነበሩም፡፡ ኃላፊነቱን ፍጹም ሳያስቡት በድንገት የተሸከሙ መሪ ናቸው፡፡ ሸክሙ በድንገት ከትከሻቸው ሲወድቅ፤ ለመምራት ሳይሆን ለማስተዳደር ሞከሩ፡፡  
የቻይናው ፈላስፋ ላኦትዙ፤ ‹‹አንድ መሪ መኖሩ በጣም ከተሰማህ፤ ያ ሰው ጥሩ መሪ አይደለም›› ይላል። አቶ ኃይለ ማርያም መኖራቸው ብዙ የሚሰማ መሪ አልነበሩም፡፡ ከአቶ ኃይለ ማርያም ሰብእና በጉልህ የሚታየው ቅንነታቸው ይመስለኛል፡፡ በቁጣቸው መሐል ሳይቀር ርኅሩኅነታቸው ጎልቶ ይታየኛል፡፡ ሐገራቸውን የሚወዱ፤ ከብዙ ስህተቶች የሚጠብቅ ሞራላዊ እሴት ያላቸው፤ ከ‹‹ሰሜናዊ ዘይቤ›› ራቅ ያለ የአመራር ወይም የአስተዳደር ዘይቤ የሚከተሉ ሰው ናቸው፡፡ በቅርብ የሐገራችን ታሪክ  (በንባብ እና በህይወት) ከምናውቃቸው በርካታ ኢትዮጵያውያን መሪዎች የተለየ ሰብእና ያላቸው መሪ ናቸው፡፡
በዋናነት የአቶ መለስን ሞት ተከትሎ በተለያዩ የግንባሩ አባል ድርጅቶች እና መሪዎች መካከል ሊፈጠር ይችል የነበረውን ፉክክርና ገመድ ጉተታ ያስቀረው የህዝቡ ሁኔታ ቢሆንም፤ ከውጭ ሆኜ ሳየው እርሳቸው የመሐል ሰው በመሆን፣ ሁሉንም ወገን ለማረጋጋት የቻሉ ይመስለኛል፡፡
እንደ አቶ መለስ ሊወደዱ ወይም ሊከበሩ የሚችሉ እንጂ የሚፈሩ መሪ አይመስሉኝም፡፡ ይህን ለማረጋገጥ ባለሥልጣናቱ ከአቶ መለስ ጎን ሲቆሙ በገጽታቸው የሚነበበውን ነገር፣ ከአቶ ኃይለ ማርያም ጎን ሲቆሙ ካለው ሁኔታ ጋር በማስተያየት፣ ማንኛውም ሰው መረዳት ይችላል፡፡ አቶ ኃይለ ማርያም ዘና የሚያደርግ ሁኔታ አላቸው፡፡ ‹‹ሰሜነኛ ዘይቤ›› ያልኩት፤ ብዙዎቻችን የምናውቀው (የምንወደው ባይሆን የምናደንቀው) ባህርይ እርሳቸው ያላቸው አልመሰለኝም፡፡ ይህ የዴሞክራሲ ባህል ዕድገቱን ሊያግዝ የሚችል ትልቅ እሴት ሊሆን የሚችል ነበር፡፡ ነገር ግን የክልሎችን ግጭት፣ መፈናቀል እና በአባል በፓርቲዎች መካከል የተነሳውን ሽኩቻ ለማረቅ የሚችል አልሆነም፡፡ እርሳቸውም፤ ‹‹የመፍትሔው አካል ለመሆን ከኃላፊነቴ ተነሳሁ›› ሲሉ የተረዳሁት፤ ‹‹እዚህ በጠቅላይ ሚኒስትር መንበር ተቀምጬ ሁኔታዎች ሲባባሱ ከመመልከት፤ ለምንገኝበት ችግር ተገቢ ምላሽ ሊሰጥ የሚችል መሪ እንዲመጣ ገለል በማለት መፍትሔውን በማዋለድ እገዛ ላድርግ›› ማለታቸውን ነው፡፡ ውሳኔአቸውም ትክክል ይመስለኛል፡፡
በነገራችን ላይ ‹‹ሰሜነኛ ዘይቤ›› የለመደው የኢትዮጵያ ህዝብ፤ የእርሳቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር ሆኖ መሾም ከልብ የተቀበለው ይመስለኛል፡፡ ኃላፊነቴን ለቀቅኩ ሲሉም የደነገጡት ብዙዎች ናቸው፡፡ ብዙዎች ለእርሳቸው መልካም አስተያየት እንዳላቸው የሚመሰክር የተለያዩ አስተያየቶች ሲሰጡ ሰምቻለሁ፡፡
በእኔ አስተያየት የኢትዮጵያ ህዝብ በርካታ ዘመናትን በጦርነት ያሳለፈ በመሆኑ፤ እንዲሁም አካባቢያዊ እና የሐገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታዎች ‹‹በፉከራ እና በሽለላ›› የደመቀ መንፈስ ያለው ወይም ‹‹ኮምጠጥ ያለ›› ያለ  መሪ የሚወድ ይመስለኛል፡፡  ‹‹ኮምጠጥ ያለ›› ያለ  መሪ ደግሞ መኖሩ በብዙ እንዲሰማን የሚያደርግ መሪ ነው። በእኔ አስተያየት አቶ ኃይለ ማርያም እንዲህ ዓይነት መሪ አልነበሩም፡፡ አቶ ኃይለ ማርያም ‹‹መኖራቸው ብዙ የማይሰማ›› የሰላም ዘመን መሪ ናቸው፡፡
በተረፈ፤ አቶ ኃይለ ማርያም ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ሲሾሙ፣ ከየትኛው ብሔር መምጣቸው ለኢትዮጵያ ህዝብ ትርጉም ያለው ሆኖ የታየ አልነበረም። የወላይታ ተወላጅ መሆናቸውን የገለጹት ኢህአዴግ እና አንዳንድ የውጭ የመገናኛ ብዙሃን እና ምሁራን ናቸው። ኢህአዴግ ሲያሾማቸው ‹‹ብሔር- ወላይታ›› ሲል ሰማነው፡፡ አንዳንድ የውጭ ሐገር ምሁራንም፤ ‹‹አቶ ኃይለ ማርያም ከኢትዮጵያ ህዝቦች በቁጥር አነስተኛ ከሆነ ብሔር የመጡ ናቸው፡፡ በሐይማኖትም ቁጥራቸው ከአናሳው ወገን ነው›› ብለው ሲጽፉ አይቻለሁ። ለተቀረው የኢትዮጵያ ህዝብ ግን የሐይማኖታቸው እና የብሔር ምንጫቸው ከቁም ነገር የተቆጠረ አልመሰለኝም፡፡
ነገር ግን እኔ፤ አቶ ኃይለ ማርያም ወደ ሥልጣን በመጡ ጊዜ፤ በብሔር ከወላይታ መሆናቸው እና ከምኒልክ ቤተ መንግስት መግባታቸው ትርጉም ሰጥቶኝ ነበር፡፡ በሐይማኖትም አናሳ ከሚባለው ወገን መሆናቸውን ከቁም ነገር ቆጥሬው ነበር፡፡ አንድ ከወላይታ የተወለደ ሰው፤ የምኒልክ ቤተ መንግስት መግባቱ የታሪክ እርማት ሆኖ ታይቶኝ ነበር፡፡ የምኒልክ እና የወላይታ ህዝብን ጉዳይ እናውቃለን፡፡ አጼ ምኒልክ ወደ ወላይታ ሲገቡ፤ ከብዙ አካባቢዎች የተለየ ተግዳሮት ገጥሟቸው ነበር፡፡ እናም ከዚህ ብሔረሰብ ተወላጅ የሆነ ኢትዮጵያዊ፤ የምኒልክ ቤተ መንግስት ሲገባ ታሪካዊ ክስተት ነው ማለት እንችላለን፡፡
አንዳንዶች የኋላ ታሪክ አይተው፣ ከሐገረ ኢትዮጵያ ጋር ጸብ ይገጥማሉ፡፡ ችግሩ ከኢትዮጵያ ጋር አይደለም። ዴሞክራሲያዊት ያልነበረችው ኢትዮጵያ ከዚህ የተሻለ ባህርይ ሊኖራት አይችልም፡፡ ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ ግን ለሁላችንም ቦታ እንዳላት መረዳት እንችላለን። በመሆኑም ጸቡ ከኢ-ዴሞክራሲያዊነት ጋር እንጂ፤ እኛ የሆነውን ከመሆን በቀር ሌላ መሆን ከማትችለው  ኢትዮጵያ ጋር መጣላት ተገቢ አይደለም፡፡ ዛሬ ከእኛ የተለዩት የኤርትራ ወንድም - እህቶቻችን የተጣሉት ከኢትዮጵያዊነት ጋር ነው፡፡ ጸቡ መሆን ነበረበት፡፡ ከኢ-ዴሞክራሲያዊነት ጋር መጣላት ትተው፤ ከኢትዮጵያዊነት ጋር ተጣሉ፡፡ በመጨረሻም ከኢትዮጵያዊነት ጋር ተጣልተው፤ ፀረ- ዴሞክራሲያዊነትን ታቅፈው ይኖራሉ። ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ ለሁላችምን ትበቃ ነበር፡፡ ለሁላችን የምትሆን ኢትዮጵያ ስንፈጥር፤ አቶ ኃይለ ማርያም ከምኒልክ ቤተ መንግስት ገቡ፡፡ በዛሬይቱ ኢትዮጵያ፤ እንደ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ፤ ከደቡብ ኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ክልል፤ እንደ አቶ መለስ ዜናዊ ከትግራይ፤ እንደ …………… ከአማራ ወይም ከኦሮሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ሊመጣ ይችላል፡፡
ከዚህ አንጻር አቶ ልደቱ አያሌው ሰሞኑን የተናገሩትን አንድ ነገር ለማንሳት እፈልጋለሁ፡፡ ‹‹በኢህአዴግ አደረጃጀት የተነሳ ዛሬ ኢትዮጵያን ሊመራ የሚችል ጠቅላይ ሚኒስትር ሊመጣ የሚችለው ከአራቱ የኢህአዴግ ክልሎች ብቻ ነው›› ሲሉ ተችተዋል፡፡ ‹‹በኢህአዴግ አደረጃጀት የተነሳ፤ ከአፋር፣ ከቤኒሻንጉል -ጉምዝ፣ ከኢትዮጵያ ሶማሌ፣ ከአፋር፣ ሐረሪ ወይም ከጋምቤላ ጠቅላይ ሚኒስትር ለመምረጥ የምንችልበት ሁኔታ አልተፈጠረም›› ሲሉ ህብረ ብሔራዊ ድርጅት አለመሆኑን ተችተዋል፡፡ ትክክል ናቸው፡፡ ኢህአዴግ ግንባር ሆኖ እስከ መቼ? ሆኖም ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ ለሁላችንም መሆን የምትችል ሐገር መሆኗን፤ በኃይለ ማርያም ደሳለኝ ሹመት መረዳት እንችላለን። መፍትሔው እንደ ኤርትራውያን ዜግነት ሳይሆን አገዛዛችንን መቀየር እና ማሻሻል መሆኑን ያስረዳናል፡፡
እዚህ ላይ፤ ሰለሞን ደሬሳ (ነፍሱን ይማረው) እንዳለው፤ ‹‹እኒህ ሦስቱ ክልሎች›› (በተለይ ኦሮሞ፣ ትግራይ እና አማራ) ጠግበዋል ማለት እፈልጋለሁ። ሰለሞን ደሬሳ ከብዙ ዓመታት በኋላ በ1991 ዓ.ም ለመጀመሪያ ወደ ኢትዮጵያ በመጣ ጊዜ ጓደኛዬ ገዛኸኝ ጌታቸው ስለ ብሔር ብሔረሰብ ጉዳይ ጠይቆት፡-
‹‹ስለዚህ ጉዳይ ከውጭ መጥቼ በአንድ ሣምንት ውስጥ ስለ ኢትዮጵያ ኤክስፐርት መሆን አልፈልግም። ግን ካየሁት እና ከምሰማው አንድ የሚታየኝ፤ ትግርኛ የሚናገሩ፤ አማርኛ የሚናገሩ፤ ኦሮምኛ የሚናገሩ ኢትዮጵያውያን እዚህ ያሉት እነሱ ብቻ ሆነው እንደሚናገሩ ይመስላል፡፡ በርካታ ቁጥራቸው ትንሽ የሆኑ ህዝቦች መኖራቸውን የረሳነውና ውይይቱ በኛ መካከል ብቻ የሚካሄድ ይመስላል፡፡ እኔ ይህ ጥጋብ ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም በቁጥር ብዛት እውነት አይቆምም፡፡ እውነቱ ደግሞ ቀላል ነው፤ ኢትዮጵያ ውስጥ የተለያየ ቋንቋ የሚናገሩ ብዙ ህዝቦች አሉ›› ብሎ ነበር፡፡
ሰለሞን ስለ ኢትዮጵያ ታሪክ የሚናገረው ነገር፤ ለመሪዎቻችን እና ለዜጎቹም ብዙ ያስተምረናል፡፡
‹‹የኢትዮጵያ ታሪክ ያየኸው እንደሆነ በአንድ በኩልም ያስገርማል ያሰኛል፡፡ በአንድ በኩል ደግሞ ያሳዝናል፡፡ ሥልጣኗን ተፈራርቀንባታል፡፡ ጎንደርን ኦሮሞች ገብተው ንጉሥ አንግሰው የሚገዙበት ጊዜ ነበር፡፡ አጼ ቴዎድሮስ ከተነሱ በኋላ ግዛቱ ወደ ጎንደር ህዝብ ተመለሰ፡፡ አጼ ዮሐንስ ሲመጡ የትግራይ ዘመን ሆነ፡፡ ምኒልክ ሲመጡ የመሐል ሐገር የአማራው ግዛት ሆነ፡፡ አሁን ደግሞ ሥልጣኑን የያዙት ከውጭ እንደሚታየው ከትግራይ የመጡ ሰዎች ይመስላሉ፡፡ ሁሉም ኃላፊዎች ናቸው፡፡ መፈራረቅ አይቀርም፡፡ ነገ ማን እንደሚመጣ አላውቅም፡፡ ወይ አማራው ይሆናል ወይ ኦሮሞው ይሆናል፡፡ የሚመጣበትን መንገድ ደግሞ ልንገምት አንችልም፡፡ የማያልፈው ይኸ ግንኙነት ነው፡፡ የማያልፈው ደግሞ የእኛ ግንኙነት ትልቅ ሆኖ፤ ከሌላው ዓለም የበለጠ የሚያምር ሆኖ ሳይሆን የመልክዐ ምድር አቀማመጣችን ነው፡፡ በአንድ በኩል ስታስበው ኢትዮጵያ ውስጥ ተቀምጦ እኔ የትግራይ ሰው ነኝ፣ እኔ አማራ ነኝ ብሎ አፍ ሞልቶ መናገሩ አለማወቅ ይመስለኛል፡፡ በሴት አያቶቻችን በራፍ ላይ ማን እንዳለፈ ስንቶቻችንን ነን የምናውቀው፤ የእኔን ጥሩ ኦሮሞነት እግዚአብሔር እና የሴት አያቶቼ ብቻ ናቸው የሚያውቁት፡፡ የሁሉንም እንዲሁ፡፡ ጦር ባለፈ ቁጥር መዋለድ፣ በንግድ መገናኘት፣ ተቸግሮ ከሐገር ወጥቶ ሌላ ቦታ በመኖር ይቀላቀላል፡፡ እኔ እናቴ ወለጋ ነበር የሚኖሩት፡፡ ያደግኩት ጋሼ መሐሪ፣ አባባ ደስታ እያልኩኝ ከትግራይ፣ ከጎጃም፣ ከጎንደር፣ ከሸዋ፣ ከጉራጌ የመጡና እዚያ የሰፈሩትን እየጠራሁ ነው፡፡
‹‹…..የኢትዮጵያ ታሪክ የመጣው ሁሉ አማራ የገዛ እንደሆነ ሌላውን ቁልቁል ይዞ፣ ትግሬ የመጣ እንደሆነ ሌላውን ቁልቁል ይዞ እያልን ይህንን ስንት ሺሕ ዓመት ነው የምንደጋግመው፡፡ ምን ያህል እንለያያለን? ዘር በመቁጠር ደረጃ እኔ ምንም ችግር አይታየኝም፡፡ ምክንያቱም በራስህ ለመኩራት መጀመሪያ በአባትህ እና በእናትህ መኩራት አለብህ፡፡ እሱን እንደ ምግብ በልተኸው ነው የአንተ በራስህ መተማመን የሚመጣው። ለምሣሌ፣ እኔ ከትግራይ ሰው ጋር ተገናኝቼ፤ የማጫውትህ የትግራይን ትልቅነት ነው ቢለኝ በል ቁጭ በልና እንጫወት ነው የምለው፡፡ ከዚህ በላይ ምን ያጫውተኝ? የወለጋውን እንዳያጫውተኝ የእርሱ አይደለም፡፡ ከጎንደር የመጣ ሰው የጎንደርን ትልቅነት ላጫውትህ ሲለኝ ሌላ ምን ያጫውተኝ፡፡ ጎንደር የሄድኩት፤ የዘመዶቼን ትልቅነት ለመስማት አይደለም። የእነሱን ትልቅነት ለማየት እና ለመስማት ነው፡፡ ከዚህ ባለፈ ግን ስንት ኦሮሞ ከብት በነዳበት ሐገር፤ እኔ የጠራሁ አማራ ነኝ ወይ ንጹህ ትግሬ ነኝ ቢለኝ፤ አነጋገሩ ‹‹ለማያውቅሽ ታጠኚ›› ነው። በባህል በኩል፣ በጥበብ በኩል ምንም ዋጋ ያለው አይመስለኝም።››
እንደ ሰለሞን ደሬሳ ያሉ ጥቂት እብዶች ያስፈልጉናል፡፡ እንደ ጅሉ ሞሮን እውነትን የሚናገሩ እብዶች ተቸግረናል፡፡ በተረፈ ዛሬ በኢትዮጵያ ሁኔታዎች ተለዋውጠዋል፡፡ ለውጡን ለመረዳት የፈለገ ሰው፤ ዛሬ ለፌደሬሽኑ አንድነት የሚጨነቁ የሚመስሉት፤ የመሐሎቹ ሳይሆኑ የዳሮቹ መሆናቸውን ይገነዘባል። በሰለሞን ቋንቋ ‹‹ሦስቱ ጥጋበኞች›› እንደ ለመዱት እርስ በእርስ ይጨቃጨቃሉ፡፡ የድቡብ ኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ክልል፣ አፋር፣ ቤኒሻንጉል-ጉምዝ፣ ጋምቤላ እና ሐረሪ የሚሆነውን በዝምታ ይታዘባሉ፡፡ ዛሬ ለአዲሲቱ ኢትዮጵያ አንድነት የሚጨነቁ የሚመስሉት፤ ቀድሞ ደንታ የሌላቸው የሚመስሉት ናቸው፡፡ ቀደም ሲል የመገንጠል ጥያቄ ይሰማባቸው የነበሩ ክልሎች፤ ዛሬ የአንድነትን መፈክር ጎላ አድርገው የሚያሰሙ ሆነዋል፡፡ በተቃራኒው፤ ለብሔር ጉዳዮች ደንታ የሌለው ሆኖ የቆየው ክልል፤ የብሔር አጀንዳን አጥብቆ የያዘ ይመስላል፡፡ የዛሬይቱ ኢትዮጵያ አንዳንዶችን አስደንግጣለች፡፡ የመገንጠል ጥያቄን ያነሱ ‹‹የመንደር ድምጾችን›› አሰምታናለች፡፡ ኢትዮጵያ እጅግ ተለውጣለች፡፡ የተለወጠችው ኢትዮጵያ ልዩ ችሎታ ያለው እና አዲስ ጎዳና ለመከተል የማይፈራ መሪ ትፈልጋለች፡፡

Read 2607 times