Print this page
Sunday, 25 February 2018 00:00

መንቃት እንዴት ያለ ነው?

Written by  ያዕቆብ ብርሃኑ (singofbird@gmail.com)
Rate this item
(1 Vote)

    ሰዓሊና ገጣሚ ዳንኤል ታዬ “ቅዠት” በተሰኘ መፅሐፉ “ዝንብ ምግቧን ስትፈጭ በጨጓራዋ ውስጥ የምትፈጥረው ድምፅ ሳይቀር ይረብሸኛል” ይላል። አዎ ፅሞናን አጥብቆ ለሚመኝ ሰው የትንኝ ድምፅ እንኳን ስሜትን ያናጥባል። ዳሩ እኛ የምንኖረው ለ24 ሰዓታት በሙሉ አቅሟ በምትጮህ ከተማ መሃል ነው።
ሲመሽ ዘወትር ግርርር ይለኛል። በአዲስ አበባ አንድ የከፍታ ጥግ አድፍጬ ጀንበሯን ለመሰናበት እቀመጣለሁ። የደስታ የሚመስል ግን ደግሞ የሚያባባ ስሜት አቅሌን እስክስት ይቆጣጠረኛል።  እንዲህ ሲሆን የፀጋዬን “መሸ ደሞ አምባ ልውጣ” “ወንድ ብቻውን ነው የሚያለቅሰው” ውብ ግጥሞች ለውስጤ እየሰባበርኩ እዘምራለሁ።
“መሸ ደሞ አምባ ልውጣ
አምባ ወጥቼ እኩለሌት ስለት ገብቼ በስሟ
ከርሞ ሰይጣን በሷ አስቶኝ ልገላገል ከሕመሟ
ጠበሏ አፋፍ በጨረቃ ደጋግሜ ማሕሌት ቆሜ
ሆዴ ቃትቶ ባርባር ብሎ እርቃኔን ከእሷ ታድሜ
ደጀ ሰላሟን በአራት እግር ተንበርክኬ ተሳልሜ
በስጋዬ የሚነደውን በጸሎት ላቤ አጣጥሜ
 እፎይ ብዬ አመስግኜ ውዳሴዋን ደጋግሜ…
ገና ከደጅዋ እልፍ ሳልል ደሞ ይምጣ የቁም ሕልሜ?
 ሌት በጥምቀቷ የነጣው ነጋ ደፈረሰ ደሜ፡፡
ለእሷ እንጂ ለኔ አልያዘልኝም አዬ የስለት አታምጣ!
በውጣውረድ በጠበል ባሳር ወዜ ቢገረጣ
ልክፍቷ እንደሁ አልለቀቀኝ መሸ ደሞ አምባ ልውጣ!
*  *  *  
 ‹‹…መሽቶ ረፍዶ ጀምበር ጠልቆ
 በእንቅልፍ ጥላ ሲከበብ፣ በዝምታ ሲዋጥ አገር
ፍጡር ሁሉ ተስለምልሞ ብቸኝነት ብቻ ሲቀር…
የኋላ ኋላ ማታ
ምድር አገሩ በእፎይታ
ዓይኑን በእንቅልፍ ሲያስፈታ
ሁሉ በእረፍት ዓለም ርቆ ብቸኝነት ብቻ ሲቀርብ
ያኔ ነው ወንድ ዓይኑ የሚረጥብ
የብቻ እምባ ወዙ እሚነጥብ፡፡…››
ሁልጊዜ በጉርምስና እድሜ ወደ ዓለም እንደተጠራ ዓይነት እንግድነት ይሰማኛል። መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተረፈ ኤርሚያስ ምዕራፍ 9 ላይ ይህንን ስሜቴን የሚጋራ አንድ የሚገርም ታሪክ አንብቤያለሁ፡፡ በእስራኤል ህዝቦች ላይ መከራ ከብዶ በመጣ ጊዜ ነብዩ ኤርሚያስ ከሞት ያዳነውን ኢትዮጵያዊውን አቤሜሌክን የበለስ ፍሬ ቀጥፎ ያመጣ ዘንድ ወደ ማሳዎች ላከው። አቤሜሌክ እንደታዘዘው የበለሱን ፍሬዎች ቀጥፎ በሙዳዩ አጠራቀመ፡፡ ችፍርግ ያለች አንዲት የበለስ ዛፍ አግኝቶ ጥቂት ያንቀላፋ ዘንድ አሸለበ። እናም 66 ዘመናት እስቲፈራረቁ፣ ነብዩ ኤርሚያስና ባሮክ እንዲሁም እስራኤላውያን በባርነት ወደ ባቢሎን እስቲጋዙ፣ እየሩሳሌም እንዳልነበረች ሆና እስክትወድም ጥልቅ እንቅልፍን ተኛ፡፡
ከእንቅልፉ ሲነቃ የቀጠፋቸው የበለስ ፍፌዎች ትኩስ (fresh) ነበሩ፡፡ ወደ ከተማ ሲገባ ግን ብዙ ነገሮች ተቀያየሩበት፡፡ አንዳችም የሚያውቀው ነገር አጣ፡፡ በእጅጉም ደነገጠ፡፡ በተራራማው መንገድ ሲጓዝ አንድ አዛውንት አግኝቶ፤ ‹‹እባክህ እንቅልፍ ውስጥ ነበርኩና ብዙ ነገሮች ተቀይሮብኝ ተቸግሬያለሁ፡፡ ነብዩ ኤርሚያስና ባሮክ ወዴት ናቸው?›› ሲል ጠየቃቸው፡፡
አዛውንቱም፤ ‹‹አንተ የዚህ አገር ሰው አይደለህምን? 66 ዓመታት ቆይተህ እንዴት ይህንን ጥያቄ ትጠይቃለህ? ኤርሚያስና እስራኤላውያን በምርኮ ወደ ባቢሎን ከተጓዙ እነሆ 66 ዓመታት ተቆጥረዋል›› አሉት፡፡
‹‹ይህ እንዴት ይሆናል? የያዘኳቸው የበለስ ፈሬዎች እንኳን ትኩስ ናቸው››
‹‹እግዚአብሔር የእስራዓልን ጥፋት እንዳታይ ጥልቅ እንቅልፍ ጣለብህ እንጂ ወደ ማሳዎች ተመልከት፤ ወቅቱ እንኳን የበለስ አይደለም›› ብለው አስረዱት፡፡
ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጭ ያሉ ታሪካዊ ጥናቶች እንደሚያሳዩት፤ አቤሜሌክ የተቀየሩ መገበያያ ሳንቲሞችን ሳይቀር ይዞ ተገኝቷል፡፡ ምናልባት የአቤሜልክ ግር የመሰኘት ሂደት አውዱ መንፈሳዊነት ስለሚጫነው ሊለይ ይችላል፡፡ ሆኖም እኔም በእያንዳንዱ ዕለት የሚሰማኝ እንግዳነት ልክ እንደ አቤሜሌክ ነው። አፄ ቴዎድሮስ ወይም ሌላ የመካከለኛው ዘመን ሰው በጎልማሳነት ዕድሜ እንደገና አሁን ቢጠራ የሚሰማው ዓይነት፡፡ በየዕለቱ ግር የሚሉኝ የማውቃቸው የነበሩና የሚቀየሩብኝ፣ የማይገቡኝ፣ የሚያደነጋግሩኝ ነገሮች እልፍ አዕላፋት ናቸው፡፡
እንዲያም ቢሆን በየዕለቱ ግራ ጥምዝ ከሚሽከረከረው ወለፈንዲ ኑሮአችን ጋር በግድ እየተጎተትኩ አለሁ፡፡ ግን ይሄ ግር መሰኘት መንቃት የሚሉት መተተኛ ሂደት አንዱ መገለጫ ይሆን? አዎ እንዲያ መሆን አለበት፡፡ ማወቅ ማለት እኮ መንቃት ነው ...እንጂ አንድ ወጥ ቅርፅና ደርዝ ይዞ፣ ሳይሸራረፍና ሳይለወጥ ዘመናትን የሚሻገር እውቀት እንደሁ የለም፡፡ መንቃትማ ማወቅ ነው ወዳጄ… ለመሆኑ ግር ይልሃል? ብዙ ነገሮች አልገቡህ እያሉ ትቸገራለህ? የዚህ ዓለም ግልብና ስግብግብ የኑሮ ዘይቤ አልጥምህ ብሎሃል? የማፈንገጥ የራስህን መንገድ የመምረጥ ዓይነት ባህሪ ይሰማሃል? … መልስህ አዎ ከሆነ ነቅተሃል ማለት ነው፡፡ አንዴ ከነቁ ወዲያ መሳከር መበርገግ፣ መሳከር መበርገግ እንጂ መልሶ መተኛት ስለሌለ ቻለው፡፡ በተለይ የኪነት ግርድፍ ጥሪ የተጫነባት ነፍስ ተሸካሚ ከሆንክ፣ መንቃትን ልትሽት ግድ ይልሃል፡፡ ምክንያቱም ከዘመን ያልተጣላ፣ ከትውልድ ያልተኳረፈ ከያኒ መንጠራወዙ ረብ አይወጣውማ! ይህ ካልሆነ ግን ጥልቅ እንቅልፍ ውስጥ መሆንህን እወቀው፡፡ ዳሩ ከዘመንና ትውልድ እንዲሁም ከራስህ ያጋጭሃል እንጂ መንቃት ምን ያደርግልሃል? ይልቅ ዝም ብለህ እንቅልፍህን ለጥጥ፡፡
እኔና ጥላዬ ግን ግር በሚለውና ብዙ ሰው ባልሄደበት የሕይወት አሳቻ መንገድ መሄዱን መርጠናል፡፡ ለመሆኑ እስከ ዓለም ጥግ በባዶ እግሬ ብጓዝ፣ የእኔን እውነት የእኔን ያህል የሚረዳልኝ አንድ ሰው እንኳን ሊኖር ይችላልን? በፍፁም! እንኳንም ግን እንዲያ ሆነ፡፡ ሰዎች በእኔ የነፍስ ውጥንቅጥ ውስጥ የሚካሄደውን የማያባራ ፍልሚያ ምንነት ቢረዱ፣ ማንም እንደመሰለው፣ ወደመሰለው የሚገፋው ብጣሽ ወረቀት ወይም ብናኝ ሆንኩ ማለት አይደለምን? ይሄው ነው ብቸኛ መጽናኛዬ…
ይህ የብይትውርና ስሜት ለእኔ ብቻ የተተወ የብቻ መፍገምገም ነውን? በበኩሌ አይመስለኝም፡፡ አልበርት ካሙ ከሔርማን ሔሰ እኩል የማደንቀው የሃሳብ ሰው ነው፡፡ “The Stranger በሚል ርዕስ ፍልስፍናዊ አመለካከቶቹን በልብወለድ መልክ ባቀረበበት መጽሐፉ ላይ፣ በዋናው ገፀባህሪ አንደበት እንዲህ ይላል፡- ‹‹በአንድ ቦታና ጊዜ ያለው ሕይወት ምርጥ የመሆኑን ያህል በሌላ ቦታ ያለውም ሕይወት እንዲሁ ምርጥ ነው፡፡ …እኔ በዘመኔ ይህንን አድርጌያለሁ፡፡ ያንን አላደረግሁም። ይህን ፈጽሜያለሁ፣ ያንን አልፈፀምኩም፡፡ ይህንን አሸንፌያለሁ፣ ያንን አላሸነፍኩም፡፡ እዚህ ቦታ ሄጃለሁ፣ እዚያ ግን አልሄድኩም፡፡ እና ምን ይጠበስ?››
አስቡት እስቲ … እኔ ገርጂ ጊዮርጊስ የመቃብር ቦታ ላይ ቆሜ፣ ሞተው እንኳን እረፍት ያጡ ሰብዓዊያንን እያሰብኩ ስብሰለሰል፣ እዚያ አሜሪካ በውሃዋ ማማ ሚያሚ በጀልባ የሚፈነጥዘው የማላውቀው የማያውቀኝ ወዳጄ፣ ከእኔ የተለየ ስሜት እየተሰማው ስለመሆኑ እርግጠኛ መሆን አልችልም፡፡ እንደኔ ሰው በመሆን የተጣለበትን ሃዘን እያባበለ ቢሆንስ? የእርሱ የቅብጠት፣ የመዘባነን፣ የቅንጦት የኑሮ ዘይቤ በሕይወት ለዛው ከእኔ የሽሽት፣ የመፍገምገም፣ የመሳከር ኑሮ መብለጡን አላውቅም፡፡
አንድ ኢትዮጵያዊ የገበሬ ልጅ በብዙ ዓይነት እንግልትና ባህላዊ እውቀት ተሞርዶ እንደሚያድግ ሁሉ የህንዱም እንደዚያው ነው፡፡ በዚህ መካከል ያለው ልዩነት ምንድን ነው? ምንም… ዋናው ነገር ኢትዮጵያ ተወለድክ ወይም ጃፓን አይደለም፡፡ ዋናው ነገር ሕይወትን በንቃት መኖሩ ነው፡፡ ሆኖም ወዳጄ መንቃት እንዲሁ ስለፈለጉ ብቻ የሚገቡበት ክፍት በር ከመሰለህ ተሳስተሃል፡፡ መንቃት ሂደት ነው፡፡ ብዙ ዋጋ የሚጠይቅ የፍለጋ ሂደት!! …አይገርምም አንዲት ዘለላ የሕይወት እውቀት ለመማር የዘመናት ጥበቃና ስቃይ ያስፈልግሃል፡፡ ለዚያውም ከዚያ ወዲያ ይሄው እውቀትህ ምንም ላይጠቅምህ መሆኑ ያበግናል፡፡ ሆኖም ሕይወትን በንቃት መኖር እንዲሁ ቀላል አይምሰልህ። ከመንፈሳዊነት፣ ከየዋህነት ሕይወትን መመልከቻ ጽንፍ ወጥተህ፣ ሕይወትን በሌጣው ስትመለከት ምን እንደሚገጥምህ ኦስካር ዋይልድ ይንገርህ፡-
‹‹After the first glass you see things as you wish they were. After the second you see them as they are not. finally you see things as they really are and that is the most horrible thing in the world.››
ለማንኛውም አሁን እየመሸ ነው። ቢያንስ ይህን መጣጥፍ በምጽፍበት ቅፅበት እየመሸ ነበር... በበኩሌ ሕይወት የምልዑነት ከፍታ የምታገኝበት ነጥብ ይሄ ምሽትና ምርጥ ሙዚቃ የተገናኙበት ነጥብ ይመስለኛል። ምሽት ልብ ብለው ሲያስተውሉት፣ ከጥልቅ ሃዘን ጋር እየታገለ፣ ፈገግ ያለን ሰው ፊት ይመስላል። የሁለትዮሽ መስመር ጠርዝ ስለሆነ ይሆን? የብርሃንና የጨለማ... ምርጥ ሙዚቃ ይህን የፅሞና አፍታ ልክ የለሽ የመንፈስ ከፍታ ይሠጠዋል። ምሽት... የጊዜ ግንጥል ጌጥ... የድብልቅልቅ ስሜቶች ነፀብራቅ... እጅ ላይ የሚሟሟ የቅፅበት ውበት... ከዝንታለም የተሸረፈ የጊዜ ሽርፍራፊ አፍታ...ፍዝ የሕይወት ሰሌዳ፣ ልብ ላይ መንጭቶ፣ ዓይን ላይ የሚቀልጥ የቅጽበት የውበት ድግምት… በእነዚህ ስብርባሪ መረዳቶች የምትዳኝ ሕይወት ግን ምን ዓይነት ናት? ሽሽት የበዛባት? ስክነት የሌለባት? ...

Read 1971 times