Sunday, 25 February 2018 00:00

ኢትዮ-አፍሪካ የካርኒቫል ሳምንት ይካሄዳል

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

  የ“ወይዘሪት ምድረ ቀደምት” የቁንጅና ውድድር ይደረጋል

   የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች እርስ በእርስ ይበልጥ ይተዋወቁበታል የተባለለትና አዲሱ የኢትዮጵያ ቱሪዝም መለያ የሆነውን “ምድረ ቀደምት”ን ለማስተዋወቅ ያለመው “ኢትዮ አፍሪካ ካርኒቫል” በግንቦት ወር የመጀመሪያው ሳምንት ላይ እንደሚካሄድ ተገለፀ፡፡
 የኢትዮጵያ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር፣ አዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮና የኢትዮጵያ ቱሪዝም ድርጅት፣ ከዘጠኙ ክልሎች እንዲሁም ከአይጂ ኢንተርቴይመንትና ከብርሀን ኤቨንት ኦርጋናይዘር ጋር በጋራ በሚያካሂዱት በዚህ ካርኒቫል የ”ምድረ ቀደምት” ሞዴል ሆና በዓለም ብራንዱን የምታስተዋውቅ አምባሳደር ለመምረጥ “የወይዘሪት ምድረ ቀደምት” የቁንጅና ውድድር እንደሚካሄድ ታውቋል፡፡ ክልሎች ለመጨረሻ ዙር ያለፉ አምስት አምስት አሸናፊዎችን ወደ አዲስ አበባ በመላክ የሚያወዳድሩ ሲሆን አሸናፊዋ “ወ/ሪት ምድረ ቀደምት” ሆና እንደምትሾምና ፖስተሯ ተሰርቶ ለአለም እንደምትተዋወቅ፣አዘጋጆቹ ከትላንት በስቲያ ረፋድ ላይ በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ጠቁመዋል፡፡
በዚህ የካርኒቫል ሳምንት “ምድረ ቀደምት አገር ኢትዮጵያ በመወለዴ እኮራለሁ” በሚል መሪ ቃል፣ምድረ ቀደምት ሎጎ የታተመበት ቲ-ሸርት የለበሱ 10 ሺህ ያህል ሰዎች የእግር ጉዞ እንደሚያደርጉም ተገልጿል፡፡ ለሶስት ቀናት የሚቆይ ባዛርና ኤግዚቢሽንም የካርኒቫሉ አንዱ አካል እንደሚሆን የተነገረ ሲሆን በዚህ ባዛር ላይ ብሔር ብሔረሰቦች ምርታቸውን፣ ባህላዊ ምግባቸውን፣ አልባሳትና የንግድ ሥራቸው ለእይታ የሚያበቁበትና ልምድ የሚለዋወጡበት እንደሚሆንም ታውቋል። የመንገድ ላይ ትርኢትን በሚያካትተው በዚህ ካርቪናል፤የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች ዳንሶቻቸውንና ባህላዊ ጭፈራዎቻቸውን ለተመልካች ያቀርባሉ ተብሏል፡፡ በዚህ የጎዳና ላይ ትርኢት ሥራቸውን እንዲያቀርቡ ሌሎች የአፍሪካ አገራትም እንደሚጋበዙ የተገለፀ ሲሆን በስፔይን አገር በየዓመቱ የሚካሄደው “ሮቶቶም” የተባለው የሬጌ ፌስቲቫል ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ፣በምሽቱ በሚያቀርበው የሬጌ ኮንሰርት  ካርኒቫሉ እንደሚዘጋ ለማወቅ ተችሏል፡፡

Read 884 times