Saturday, 28 April 2012 13:04

ሊንድሴይ ሎሃን ኤልዛቤት ቴይለርን ትተውናለች

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

“ሊዝ ኤንድ ዲክ” የሚል ጊዜያው የሥራ ርእስ በተሰጠውና የእውቋን የሆሊውድ ወይዘሮ ኤልዛቤት ቴይለር የህይወት ታሪክ በሚያሳይ ፊልም ሊንድሴይ ሎሃን በመሪ ተዋናይነት እንድትሰራ መመረጧን ሮይተርስ አመለከተ፡፡ የፊልሙ ጭብጥ ኤልዛቤት ቴይለር        “ክሊዮፓትራ” በተባለ ታዋቂ ፊልም ላይ አብሯት ከሰራው የቀድሞ ተዋናይ ሪቻርድ በርተን ጋር የነበራትን የፍቅር ህይወት የሚተርክ ይሆናል፡፡ ሊዝ ቴይለር ከሪቻርድ በርተን ጋር ሁለቴ ተጋብታ መፈታቷ ይታወቃል፡፡

ባለፉት ሦስት ዓመታት በአደንዛዥ ዕፅ ሱሰኝነት፤ በቤተሰብ ችግርና በሌሎች የገንዘብ ኪሳራ እክሎች ስትባክን የቆየችው የ25 ዓመቷ ሊንድሴይ ሎሃን፤ በፊልሙ ላይ ለመስራት ጉጉት እንዳደረባት ሮይተርስ አውስቷል፡፡ “ሊዝ ኤንድ ዲክ” በሰኔ ወር የፊልሙ ቀረፃ እንደሚጀመር ሲታወቅ ሊንድሴይ ሎሃን በተሳካ ትወና የተዳከመ ዝና እና ገቢዋን በማስመለስ ልታገግምበት እንደምትችል ተገምቷል፡፡

ለመጨረሻ ጊዜ ፊልም ከሰራች ሶስት ዓመት ያለፋት ሎሃን፤ ለትወናው በመመረጧ ታላቅ ክብር እንደተሰማት ብትገልፅም አንዳንድ ታዋቂ ሰዎች ለኤልዛቤት ቴይለር ስብእና የማትመጥን ናት በሚል ተቃውሞ እያሰሙ ነው፡፡ በሙያው በቆየችባቸው አስር ዓመታት ከ20 በላይ ፊልሞች የተወነችው ሊንድሴይ ሎሃን፤ በዓለም ዙርያ 708 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ያስገኘች ስትሆን በአንድ ፊልም 39 ሚሊዮን ዶላር አማካይ ገቢ እንዳላት የቦክስኦፊስ ባይ መረጃ ያመለክታል፡፡

 

 

Read 1361 times Last modified on Saturday, 28 April 2012 13:08