Sunday, 25 February 2018 00:00

“ዮሐንስ ራዕይ የዓለም መጨረሻ” መፅሐፍ ይመረቃል

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(1 Vote)

 በዲያቆን ዳንኤል ክብረት የተዘጋጀው “ዮሐንስ ራዕይ የዓለም መጨረሻ” የተሰኘ መፅሐፍ የፊታችን ማክሰኞ ከቀኑ 11፡00 ጀምሮ በብሔራዊ ቴአትር አዳራሽ እንደሚመረቅ የምርቃት ሥነ ስርዓቱ አዘጋጅ ምስክር ጌታነው ሚዲያና ፕሮሞሽን አስታወቀ፡፡
በምርቃቱ ላይ መጋቢ ሀዲስ እሸቱ አለማየሁ መፅሐፉን ከሃይማኖት አንፃር የሚዳስሱት ሲሆን ረ/ፕሮፌሰር አበባው አያሌው ከታሪክ አንፃር፣ ሃያሲ ቴዎድሮስ አጥላው ከስነ ፅሁፍ አንፃር፣ ሰለሞን ተሾመ ደግሞ ከፎክሎር አንፃር እንደሚዳስሱት የጠቆመው ጋዜጠኛ ምስክር ጌታነው፤ መጋቤ ስብሃት አለሙ አጋ፣ የበገና ድርደራ እንደሚያቀርቡ ገልጿል፡፡ የሲሳይ የባህል መሳሪያ ት/ቤት መምህራንና ተማሪዎችም የዋሽንት የበገና፣ የመሰንቆና የመለከት ትርኢት ያቀርባሉ ብሏል፡፡
አርቲስት አለማየሁ ታደሰ፣ ይገረም ደጀኔና ደሳለኝ ሀይሉ ደግሞ ከዲያቆን ዳንኤል መፅሐፍት የተመረጡ ወጎችን እንደሚተርኩና ታዋቂ ገጣሚያን ግጥሞቻቸውን እንደሚያቀርቡም ለማወቅ ተችሏል፡፡

Read 3849 times