Sunday, 25 February 2018 00:00

በየዓመቱ 2.6 ሚ. ህጻናት አንድ ወር ሳይሞላቸው ይሞታሉ ተባለ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

ኢንፌክሽን፣ የወሊድ ችግሮችና ካለወቅቱ መወለድን ጨምሮ በተለያዩ ምክንያቶች በአለማችን በየአመቱ 2.6 ሚሊዮን ያህል ህጻናት በተወለዱ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ እንደሚሞቱ የተባበሩት መንግስታት የህጻናት መርጃ ድርጅት ዩኒሴፍ አስታውቋል፡፡
በፈረንጆች 2016 በአለማችን አገራት የተከሰቱ መሰል የህጻናት ሞት ክስተቶችን በማጥናት የአገራቱን የችግሩ ተጠቂነት ደረጃ ባለፈው ማክሰኞ ይፋ ባደረገው ሪፖርት ያወጣው ድርጅቱ፤ በከፋ ደረጃ ላይ በመገኘት ቀዳሚ በሆነቺው ፓኪስታን በአመቱ ከተወለዱ ህጻናት በአማካይ ከ22ቱ አንዱ ዕድሜው አንድ ወር ሳይሞላው መሞቱን አመልክቷል፡፡
ከጃፓን በመቀጠል በርካታ ህጻናት በተወለዱ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ የሚሞቱባቸው የአለማችን አገራት ተብለው በሪፖርቱ የተጠቀሱት ማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክና አፍጋኒስታን ሲሆኑ ሶማሊያ፣ ሌሴቶ፣ ጊኒቢሳኦ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ኮትዲቯር፣ ማሊና ቻድ በቅደም ተከተላቸው እስከ አስረኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል፡፡
ከአለማችን አገራት ለመሰል ችግር በመጋለጥ የመጨረሻውን ደረጃ በያዘቺው ጃፓን፣ በአመቱ ከተወለዱ እያንዳንዳቸው 1ሺህ 111 ጨቅላዎች በአማካይ አንዱ ብቻ ለህልፈተ ህይወት መዳረጉን ያስታወሰው ሪፖርቱ፤ ከጃፓን በመቀጠል አይስላንድና ሲንጋፖር ዝቅተኛ የህጻናት ሞት ያለባቸው የአለማችን አገራት እንደሆኑ ጠቁሟል፡፡
በቀዳሚዋ ፓኪስታንና በመጨረሻዋ ጃፓን መካከል ያለውን የችግሩ ተጠቂነት ደረጃ ያነጻጸረው ሪፖርቱ፤ በፓኪስታን የሚወለድ አንድ ህጻን በጃፓን ከሚወለድ ሌላ ህጻናት ጋር ሲነጻጸር የአንድ ወር እድሜውን ሳይሞላ ለህልፈተ ህይወት የመዳረግ እድሉ በ50 እጥፍ ያህል የጨመረ እንደሆነ አብራርቷል፡፡

Read 3097 times