Sunday, 04 March 2018 00:00

ፌስታል ሲሸጡ የተገኙ 19 ኬንያውያን ታስረዋል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

በኬንያ ባለፈው ነሐሴ ወር ተግባራዊ የተደረገውንና ፌስታሎችን ጨምሮ ፕላስቲክ ከረጢቶችን መጠቀምን የሚከለክለውን ህግ በመጣስ፣ ፌስታል ሲሸጡ ተገኝተዋል የተባሉ 19 ኬንያውያን፣ባለፈው ሳምንት በፖሊስ ቁጥጥር ስር መዋላቸው ተዘግቧል፡፡
የአገሪቱ ፖሊስና የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ግብረሃይል ኪሲ፣ ኬሮካና ኔማ በተባሉት ከተሞች ባለፈው ቅዳሜና እሁድ ምሽት ላይ ባደረገው ፍተሻ በቁጥጥር ስር የዋሉት 19 ኬንያውያን፣ ከሰሞኑ ፍርድ ቤት ይቀርባሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ የኬንያው ኔሽን ዘግቧል፡፡ አገሪቱ የአካባቢ ብክለትን ለመከላከል በማሰብ ተግባራዊ ያደረገቺውንና  የፕላስቲክ ከረጢቶችን ማምረት፣ መሸጥና መጠቀምን የሚከለክለውን ህግ ጥሰው የተገኙ ዜጎች፤ በ4 ሚሊዮን የኬንያ ሽልንግ ወይም በአራት አመታት እስር እንደሚቀጡ መደንገጉንም ዘገባው አስታውሷል፡፡
ኬንያውያን ከፕላስቲክ ከረጢቶች ይልቅ ወረቀትና ጨርቅን ከመሳሰሉ በቀላሉ የሚበሰብሱና አካባቢን የማይበክሉ ነገሮች የተሰሩ ከረጢቶችንና ቦርሳዎችን እንዲጠቀሙ ጥሪ ያቀረቡት የባለስልጣኑ ተወካይ፤መንግስት የተከለከሉ ከረጢቶችን ሲጠቀሙና ሲሸጡ የሚገኙ ህገወጥ ዜጎችን ቅንጣት ታህል እንደማይታገስና በቁጥጥር ስር አውሎ እንደሚቀጣ አስጠንቅቀዋል፡፡

Read 3170 times