Print this page
Tuesday, 06 March 2018 00:00

በደቡብ ኮርያ፣ በኮከብ ቆጠራና ጥንቆላ፣ 3.7 ቢ. ዶላር ይንቀሳቀሳል

Written by 
Rate this item
(7 votes)

በደቡብ ኮርያ በኮከብ ቆጠራና በጥንቆላ ተግባር ላይ የተሰማሩና የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ እንደሚገኝ ያስነበበው ኒውስዊክ፤ ከአጉል ልማዶቹ ጋር በተያያዘ በየአመቱ የሚንቀሳቀሰው አጠቃላይ ገንዘብ በጥቂት ጊዜያት ውስጥ 3.7 ቢሊዮን ዶላር ይደርሳል ተብሎ እንደሚጠበቅ አመልክቷል፡፡
በደቡብ ኮርያ በየአደባባዩና በየቤቱ ጧት ማታ፣ የኮከብ ቆጠራና የጥንቆላ ተግባር የሚያከናውኑ ሰዎች እየተበራከቱ ነው ያለው ኒውስዊክ፤ የኮርያ ነቢያት ማህበርም በአገሪቱ ከ300 ሺ በላይ ኮከብ ቆጣሪዎችና 150 ሺ ገደማ ጠንቋዮች እንዳሉ መገመቱን ጠቅሷል፡፡ በመጫወቻ ካርዶች የሚከናወኑ የኮከብ ቆጠራና የእለት ዕጣ ፋንታ ትንቢቶች፣ በአገሪቱ ለረጅም አመታት የተለመዱ ድርጊቶች እንደሆኑ ያስታወሰው ዘገባው፤ አሁን አሁን ደግሞ በቴክኖሎጂ የታገዙ የሞባይል አፕሊኬሽን ጥንቆላዎችና ኮከብ ቆጠራዎች እየተበራከቱ መምጣታቸውን ገልጧል፡፡
ሃንዳሶፍት የተሰኘው ታዋቂ የአገሪቱ ሶፍትዌር አምራች ኩባንያ፣ ባለፉት አምስት አመታት ብቻ 13 ያህል የጥንቆላና የዕለት ውሎ ትንበያ ሶፍትዌሮችን አምርቶ በገበያ ላይ ማዋሉን ያስታወሰው ዘገባው፤ ጂኦምሲን የተባለውና ከ2 አመታት በፊት ገበያ ላይ የዋለው ተወዳጅ የውሎ ትንበያ የሞባይል አፕሊኬሽን ሶፍትዌር፣ከ3 ሚሊዮን ጊዜ በላይ ዳውንሎድ መደረጉን አውስቷል፡፡
ኮርያ ኢኮኖሚክ ደይሊ የተባለው የአገሪቱ ጋዜጣ ባለፈው አመት ያወጣው መረጃ በበኩሉ፤የአገሪቱ ዜጎች በማህበር ተደራጅተው ኮከብ በማስቆጠርና በማስጠንቆል፣ ጊዜያቸውንና ገንዘባቸውን በከንቱ በማባከን ላይ እንደሚገኙ ጠቁሞ፣ ኮርያን ኪዩንግሲን ፌዴሬሽንና የጥንቆላ ማህበር የተባሉት ሁለት የአገሪቱ ታዋቂ ማህበራት ብቻ በድምሩ አንድ ሚሊዮን ያህል አባላት እንዳሏቸው አመልክቷል፡፡ በማህበር የታቀፉ አስጠንቋዮች ቁጥር ባለፉት አስር ዓመታት በእጥፍ ማደጉንም ጋዜጣው አክሎ ገልጧል፡፡

Read 7634 times
Administrator

Latest from Administrator